የወሎው ንጉሥ የልጅ እያሱ አባት ንጉስ ሚካኤል የልጃቸውን ከሥልጣን መውረድ አዋጅ ተቃውመው በጦር ኃይል ለማክሸፍ ሠራዊታቸውን ይዘው ወደ አዲስ አበባ ይዘምታሉ፡፡ በአንጻሩ ይህን ጦር የሚገጥመው በአልጋ ወራሹ ራስ ተፈሪ መኮንን መሪነት እና በጦር ሚኒስቴሩ በፊታውራሪ ኃብተ ጊዮርጊስ አበጋዝነት የተመራው ሠራዊት ከአዲስ አበባ ተነስቶ ወደ ሰሜን አቅጣጫ ይዘምታል፡፡ ሁለቱ ኃይሎች በሰሜን ሸዋ ሰገሌ ጠራ ሜዳ ወረዳ ላይ ጦርነት ይገጥማሉ፡፡ ከ፭ ሰዐት ውጊያ በኋላም የወሎ ሠራዊት ድል ይሆናል፤ ንጉሡም ይማረካሉ። ይህ ጦርነት የሰገሌ ጦርነት በመባል ይታወቃል፡፡ ይህ የሆነው በዚህ ሳምንት ጥቅምት 17 ቀን 1909 አም ነው፡፡ ይህንንም የዛሬው የሳምንቱ በታሪኩ አምድ ርእሰ ጉዳያችን አድርገን ቀርበናል፡፡
ዳግማዊ ምኒልክ ከአድዋ ድል በኋላ የቆዩበት አስር ዓመት (ከ1888 እስከ 1898 ) የሰላምና የመረጋጋት ወቅት እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ንጉሡ ታመው አልጋ ላይ ሳሉ የሥልጣን ሽኩቻ እንዳያገረሽ በማሰብ መላ ዘየዱ፡፡
በወቅቱ በጎረቤት አገራት የቅኝ ግዛት ይዘው የነበሩት እንግሊዝ፣ ፈረንሳይና ጣሊያን በለንደን የሦስትዮሽ ውል ተፈራርመው « እርስዎ ድንገት ቢያርፉ አገር እንዳትበጠበጥ ሦስታችን መንግሥታት የበላይ ጠባቂ ሆነን አገር ለማረጋጋት…» የሚል ይዘት ያለው ደብዳቤ ለምኒልክ ይልካሉ፡፡
ንጉሡም አገሪቱን ለጅቦች አሳልፎ ላለመስጠት ለሦስቱ አገራት ቅኝ ገዥዎች በማያሻማ መልክ ግልፅ ያለ መልዕክት አስተላለፉ፡፡ « እኔ ብሞት ኢትዮጵያ በአልጋ ወራሼ አማካይነት ትቀጥላለች ፤የተረጋጋ ሥርዓትም እናቆማለንና አታስቡ » ካሉ በኋላ እርምጃዎች ወሰዱ፡፡
በወቅቱ ንጉሥ ምኒልክ ሲሞቱ በይፋ ያልተገለጸበት ምክንያትም የአገር ውስጥ የሥልጣን ሽኩቻ ይቀሰቀሳል፤በጎረቤት አገሮች ያሉ ያደፈጡት ቅኝ ገዥዎች አደጋ እንዳይደቅኑ በመስጋት ሊሆን እንደሚችል ሰነዶች ያስረዳሉ፡፡
በወቅቱ በ1900 በሀገሪቱ የመጀመሪያውን የሚኒስትሮች ምክር ቤት አቋቋሙ፡፡ ከወሎው ኢማም መሀመድ አሊ ( ራስ ሚካኤል ) የተወለደው የልጅ ልጃቸው ልጅ ኢያሱ / እናቱ የዳግማዊ አጼ ምኒልክ ልጅ ናት/ አልጋ ወራሻቸው መሆኑን አወጁ፡፡
ልጅ እያሱ ገና ልጅ ስለነበሩም የሸዋው ራስ ተሰማ ናደውን የልጅ ኢያሱ ሞግዚት አድርገው ሰየሙ፡፡ ራስ ተሰማ ሲሞቱ ሌላ ሞግዚት ለመሰየም እየተከናወነ ባለው ተግባር በመኳንንቱ ዘንድ እኔ እሆን እኔ እሆን የሚል ነገር ተከሰተ፤ ሁኔታው ያላማራቸው ልጅ እያሱ በሸዋ ሞግዚት አያስፈልገኝም ወደሚል ድምዳሜ ደረሱ፡፡ ከ1904 ጀምሮ ማስተዳደር ጀመሩ ፡፡ ይህ የሆነው አጼ ምኒልክ ታመው በነበሩበት ወቅት ነው፡፡
ልጅ ኢያሱ በአጭር የሥልጣን ዘመናቸው አብዛኛውን ጊዜያቸውን በጉብኝት ያሳልፉ ነበር፡፡ በጠረፍ አካባቢዎች የሚያደርጉት ጉብኝት በመኳንንቱ ዘንድ አልተወደደም፤ አሉባልታ ይነዛባቸው ጀመር። በአንደኛው የዓለም ጦርነት ከእንግሊዝ ፈረንሳይና ጣሊያን በተፃራሪ ደረጃ ለነበሩት ጀርመንና ቱርክ ድጋፋቸውን አሳይተዋል በሚልም በሌሎቹ ነጮች ዘንድ ጥርስ ተነከሰባቸው፤ በአገር ውስጥም አድማ ተጠነሰሰባቸው፡፡
ልጅ ኢያሱ በሐረር ሳሉ የአዲስ አበባው የእንግሊዝ ኤምባሲ ሸዋዎችና የግብጹ ጳጳስ አቡነ ማትያስ በቅንጅት ባቀነባበሩት መፈንቅለ መንግሥት የመስቀል በዓል ቀን (በ1909) ከሥልጣን ተነሱ ሲሉ ታዬ ቦጋለ መራራ እውነት በሚል የፃፉት የኢትዮጵያ ታሪክ መጽሐፍ አስፍረዋል፡፡
የልጅ እያሱ ከአልጋ መነሳት በአባታቸው ንጉስ ሚካኤል ዘንድ ሲሰማ ንጉስ ሚካኤል ሸዋዎችን ፈጥነው በመውጋት አልጋውን ለማስመለስ ይወስናሉ። ንጉሥ ሚካኤል ፈጣን እርምጃ ለመውሰድም የተቻኮሉበት ምክንያት የልጃቸው የወይዘሮ ስኂን እና የወዳጆቻቸው መልዕክት ነው፡፡ በቂ ወታደር አዲስ አበባ ስለሌለ ከየቦታው ሠራዊት እስኪሰበስቡ ገስግሰው ቢመጡ አዲስ አበባን በቀላሉ መያዝ ይችላሉ። የሚል እንደነበር ምስጋናው ታደሰ (ዶ/ር) «ሚካኤል ንጉሠ ወሎ ወትግሬ »መጽሐፍ ያስረዳል፡፡ በወቅቱ ድፍን ወሎ ለክተት ሠራዊት ጥሪው ምላሽ ሰጠ፡፡ ይህንንም በግጥም በወቅቱ እንዲህ ገልጸውት ነበረ፡-
አባ ሻንቆ ማሜ በሉ ገፋገፋ
ፍየል ይፈለጋል እንኳን ልጅ ሲጠፋ
መቅደላ አፋፉ ላይ ያሽካካል ፈረሱ
የዘጠኝ ንጉሥ ልጅ አስረኛው እሱ
እንኳን ሴቶችና ወንዶች ቢነግሡ
አልጋውን አይለቅም አባ ጤና ኢያሱ
ታዬ ቦጋለ መራራ እውነት በሚል መጻፋቸው ንጉሥ ሚካኤል የልጃቸውን ሥልጣን ለማስከበር ከትግራይ ወሎ ጎንደር እና ጎጃም የተውጣጣ 80ሺ ጦር ይዘው ክተት አወጁ ይላሉ፡፡ ምስጋናው ታደሰ (ዶ/ር) ግን «ሚካኤል ንጉሠ ወሎ ወትግሬ» በሚለው መጽሐፋቸው ንጉሡ በልጃቸው ላይ በተፈጸመው ደባ እጅግ ተናደውና ቸኩለው ስለነበር ከጦራቸው ከሲሶ (1/3) ባነሰ ማለትም ከ80ሺ እስከ 100ሺ ከሚደርስ ሠራዊት ለውጊያው ይዘው የወጡት ጦር ከሰላሳ ሺ የማይበልጥ ነበር ይላሉ፡፡
በወቅቱ የንጉሥ ሚካኤል ጦር ወደ ሸዋ መዝመቱ እንደተሰማ የሸዋ መሳፍንት ንጉሱ እንዲመለሱ መስከረም 24 ቀን 1909 ደብዳቤ ፅፈው ነበር። ከቅድመ አክሱም እስከ ኢህአዴግ መባቻ በሚል የተጻፈው መጽሐፍ ደግሞ ለሰገሌ ጦርነት በአዲስ አበባ የታየው የመንግሥት ጦር ከንጉሥ ሚካኤል በእጥፍ ይልቅ ነበር ይላል፡፡ ከዚህም በውጊያው ከሁለቱም ወገን ከ90ሺ በላይ ጦር ተሳታፊ እንደነበር መረዳት ይቻላል፡፡
የወሎ ጦር ገስግሶ በደብረብርሃንና በአንኮበር መካከል ከሚገኘው ቶራ መስክ ደረሰ፡፡ በሁለቱም ኃይሎች ጥቅምት 7 ቀን 1909 ዓ.ም ውጊያ ተካሄደ። በጦርነቱም በዚህ የመጀመሪያ ውጊያ የንጉሥ ሚካኤል ጦር አሸነፈ፡፡ የወሎ ጦር ቶራ መስክ ላይ የተቀዳጀው ድል አዲስ አበባ ላይ በስልክ በተሰማ ጊዜ ጦሩ ወዲያው አዲስ አበባ የሚገባ ስለመሰለው የከተማው ህዝብ ተደናገጠ፡፡ ጦርነቱ ለሥልጣን የተደረገ ፖለቲካዊ ዓላማ ቢሆንም፣ ሃይማኖት ለበስ ፕሮፓጋንዳ ተነዛበት፡፡
የጦር ሚኒስትሩ ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴ የሸዋ ሠራዊት ከያለበት እስኪሰበሰብ ድረስ ለንጉስ ሚካኤል የማዘናጊያ ደብዳቤ ጻፉ ፡፡ እንደኔና እርስዎ ያሉ ሁለት ጀግና ወታደሮች መጠላላት የለብንም ፡፡እኔ የመኮንን ልጅ (ራስ ተፈሪን) ሴራና ክህደቱን የሚደግፉትን መኳኳንት መስያለሁ ፡፡ ለዚህ ምክንያት ሠራዊቱን በእጄ ለማድረግና በእርስዎ ፈረሰኞች ረዳትነት በእነሱ ላይ ለመነሳት በማሰብ ነው፡፡ ብዛት ያለው መሣሪያ አዲስ አበባ ደርሷል፡፡ መሣሪያውም ከሥልጣን ነጣቂው እጅ እንዳይወድቅ በማሰብ እኔ ዘንድ እንዲመጣ አድርጌያለሁ፡፡ … ለጥቂት ቀናት ፈረሶችዎንና ሰዎችዎን ያሳርፉ የሚል መልእክት ያስተላልፋሉ ፡፡
በጥቅምት 10 ቀን 1909 ዓ.ም በፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴ የተጻፈው ይህ ደብዳቤ ለንጉሥ ሚካኤል ታማኝ መሆናቸውንና በጋራ እንዘምትባቸዋለን የሚል ይዘት ያለው ማዘናጊያ ነበር።
በዚሁ ደብዳቤ ምክንያት ንጉሥ ሚካኤል ሰገሌ ላይ አስር ቀናት ቁጭ ብለው ጠበቁ፡፡ ባላንጣዎቻቸው ከያሉበት እስኪሰባሰቡ ጠበቁ ማለት ነው፡፡ ንጉሥ ሚካኤል ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ይመጣል ብለው ሲጠባበቁ የአልጋ ወራሽ ተፈሪን መድረስና የጦሩን መበራከት ሰሙ፤ የተላከባቸው ደብዳቤ የማታለል መሆኑን ተረዱ፡፡
ልዑል ራስ እምሩ ኃይለሥላሴ «ካየሁት ከማስታውሰው» በሚል የሰገሌ ጦርነት ተሳታፊ ሆነው በጻፉት መፅሐፋቸው እና ሌሎች የጠቀስናቸው ደራሲዎች ንጉሥ ሚካኤል ባገኙት ድል ሳይዝናኑና በፊታውራሪው ደብዳቤ ሳይዘናጉ በድላቸው ቢገሰግሱ ኖሮ የሰገሌ ውጊያ ሳያጋጥማቸው አዲስ አበባን በፍጥነት ይቆጣጠሩ፣ በልጃቸው ላይ የተካሄደውን የአልጋ ግልበጣ ያከሽፉ እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡
ንጉሥ ሚካኤል ቶራ መስክ ላይ የሸዋን ጦር ድል ነስተው ወደ አዲስ አበባ ገሰገሱ፡፡ ይሁንና ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴ (አባ መላ) የሸዋንና የሰለጠነውን የማዕከላዊ ኃይል በማደራጀት በወሰዱት የአፀፋ እርምጃ ሸኖ አካባቢ በተካሄደ የሰገሌ ጦርነት 16 ሺ ሰው ከሁለቱም አልቆ ድሉ ወደ ሸዋ አመዘነ፡፡ ልጅ ኢያሱም ወደ አዲስ አበባ ለመመለስ ባደረጉት ጥረት መኤሶ ላይ ጭሮ አካባቢ (አሰበ ተፈሪ) ተሸንፈው ወደ ትግራይ አፈገፈጉ፡፡ በአፋር ዞረው 6ሺጦር ይዘው ቢመጡ ንጉሡ መያዛቸውን ልጅ ኢያሱ ተረዱ፡፡
እስከ ዕኩለ ቀን ድረስ በተካሄደው የሰገሌ ጦርነት የወሎ ሠራዊት የአባ ሻንቆ አሽከር እያለ ጥይት እየተኮሰ ጎራዴውን እየመዘዘ በድፍረት ወደ ሸዋ ጦር ቀረበ፡፡ የሸዋ ወታደር በደረቱ ተኝቶ ይታኮስ ነበር፡ ፡ የወሎ ሠራዊት ተጋድሞ የሚያየው የሸዋ ወታደር በጥይት የወደቀ መስሎት ትጥቁን ለመግፈፍ ሲጠጋ በእሩምታ እንደ ቅጠል አረገፈው ሲሉ ምስጋናው ታደሰ (ዶ/ር ) በመጽሐፋቸው ያስረዳሉ፡፡ በጦርነቱ ተፈሪ ጥቅምት 17 ቀን ድልን ተቀዳጁ፡፡
የሰገሌ ጦርነት (በነገራችን ላይ ሰገሌ ቃሉ ኦሮምኛ ነው፤ ድምጽ ማለት ነው፡፡ ኩን ሰገሌ ኢትዮጵያቲ የሚለውን የአፋን ኦሮሞ የኢትዮጵያ ሬዲዮ ድምጽ ያስታውሷል፡፡) ያ ወቅት የኢትዮጵያ መንግሥት ሥልጣን መንታ መንገድ ላይ የቆመበት ታሪካዊ ክስተት ነበር፡፡ ኢትዮጵያ በኢያሱ ወይስ በተፈሪ መስመር ትሄድ ይሆን የሚለውን ጥያቄ የመለሰ የፖለቲካ ሥልጣኑንም ዕጣ ፋንታ የወሰነ ጦርነት ነው፡፡በኢትዮጵያ ከተካሄዱት የእርስ በርስ ጦርነቶች ሁሉ በተሳተፈው የሰው ኃይል ብዛት ትልቁ የሰገሌ ጦርነት ነው ሲል ሚካኤል ንጉሠ ወሎ ወትግሬ በሚል የተጻፈው መጽሐፍ ይጠቅሳል፡፡
የሰገሌ ኰረማሽ በአማራ ክልል፣ በሰሜን ሸዋ ላይ የምትገኝ ወረዳ ናት። ከአዲስ አበባ በምሥራቅ በኩል ሰማንያ አምስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ ሥፍራ ስትሆን፣ በ ‘ስምጥ ሸለቆ’ (Rift Valley) ምሥራቃዊ ፍንጭ አናት ላይ ገዥ ይዞታ ያላት ለመከላከል የተመቸች ቦታ በመሆኗ የተመሠረተች ጥንታዊ ምሽግ ናት።
አዲስ በተመሠረተው የንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ እና የራስ ተፈሪ መኮንን መንግሥት ላይ ጦርነት አውጀው በጥቅምት ወር ከወሎ የዘመቱትን የልጅ እያሱ አባት ንጉሥ ሚካኤልን ሊከላከል የተሰለፈው የፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ሠራዊት ጥቃቱን ያደራጀው እዚሁ ኮረማሽ ላይ ሲሆን፤ ኋላም ዓርብ ጥቅምት 17 ቀን 1909 ራስ ተፈሪና ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ሰገሌ ሜዳ ላይ ንጉሥ ሚካኤልን ድል ያደረጉት ከዚሁ ደጀን ቦታ ነው።
መስከረም 17 ቀን 1909 ዓ.ም ልጅ ኢያሱ ከስልጣን ሲወርዱ በሐረር ነበሩ፤ መኳንንቱና ሕዝቡ መክሮና ዘክሮ በምርጫ ዘውዲቱን ግርማዊት ንግሥተ ነገሥት፤ ራስ ተፈሪ መኮንንን አልጋ ወራሽ እና ባለሙሉ ሥልጣን እንደራሴ እንዲሆኑ ወሰነ (ማለትም ርእሰ መንግሥትና ርእሰ ብሔር ሆነው)መስከረም 21 ቀን “ግርማዊት ዘውዲቱ፣ ንግሥተ ነገሥት ዘኢትዮጵያ” ተብለው ነገሡ።
በጥቅምት የሰገሌ ጦርነት ከተደረገ በኋላ የዘውድ በዓሉ የካቲት 4ቀን 1909 ዓ.ም በትልቁ ደብር በመናገሻ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ተደረገ፣ ለዘውዱ በዓል በኢትዮጵያ አዋሳኝ ያሉት የእንግሊዝ ሱዳንና የእንግሊዝ ሱማሌ ገዥዎች፤ የፈረንሳይ ሱማሌ ገዥ እና በኢትዮጵያም ታላላቅ ራሶች እንዲሁም የየአውራጃው ገዥዎች ተገኝተዋል፡፡
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 21 ቀን 2014 ዓ.ም