በዛሬው ማረፊያ / የአዲስ ዘመን ዱሮ አምዳችን አዲስ ዘመን ጋዜጣ በ1950 እና 60ዎቹ ለንባብ ካበቃቸው ዘገባዎች መካከል እናንተም ብታነቧቸው መልካም ናቸው ያልናቸውን ይዘን ቀርበናል። ዘና እያረጉ መረጃ የሚሰጡም ናቸው። ዘገባዎቹ ጋዜጣው ዱሮ ይዟቸው ይወጣ የነበረ ዘገባዎች ምን ያህል በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ያተኩሩ አንደነበሩም ያመለክታሉ። መልካም ንባብ።
1 ሺ 340 ዓመቴ ነው የሚሉ ሰው ተገኙ
1 ሺ 340 ዓመት ዕድሜ ያለው ሰው በሕይወት ይኖራል ብለን ባንምንም ወሬው እንዳያመልጠን ከአዲስ አበባ ወደ አባኮራን ሰፈር ሄድን። ከሼሁ ቤት ደረስን። እንግዳ መጣ ሲባሉ ከአጣና አልጋቸው ላይ ተነሱ። የሱሪያቸውን ጥብጣብ ሸምቅቀው ታጠቁ። ጋቢያቸውን አደገደጉ፤ ቁልፍ የበዛበትን ካቦርታቸውን ደረቡ። ደህና የቆመጥ ምርኩዛቸውን ይዘው ወደ ውጭ ወጡ።
ሼሁ በሰፈራቸው የተከበሩ ናቸው። በተናገሩ ቁጥር የሰፈሩ ሰው ‹‹መጀን የአላህ ታምር›› ይላሉ። ዙሪያችንን የከበቡን ሕጻናት ሼሁን እንደ አንድ ታምር ይመለከቷቸዋል። ሼሁ አይናቸውን አውኳቸዋል እንጂ በምንም ያልደከሙ ናቸው። ሲስቁ እንዳየነው የሼሁ የታች ጥርሶች ከመብለዛቸው በስተቀር ገና የሚያገለግሉ ናቸው።
ከሼሁ ጋር ጭውውት ጀመርን። ‹‹ትክክል ዘንድሮ 1ሺ 340 ዓመት ሞላኝ›› አሉን። ስማቸው ሼህ ሙሳ ኪን ሐጂ መሆኑንና አባታቸው ዓረብ፣ እናታቸው የጅማ ሰው መሆናቸውን ነገሩን። ሼህ የተባለውን ማዕረግ መቼ እንዳገኙት ብንጠይቃቸው ገና በልጅነቴ ስወለድ ነው አሉን። ሼሁ እንደሚሉትና የሰፈሩ ሰውም አምኖ እንደተቀበለው በ617 ዓ.ም ነው።
‹‹በ 1 ሺ 340 ዓመት ዕድሜዬ ኢትዮጵያን የገዟትን ነገሥታትና መሳፍንት አውቃለሁ›› አሉን። ስለግራኝ መሐመድስ ያውቃሉ አልናቸው። ‹‹አዎን አውቀዋለሁ ፤ ብዙ ጊዜ እንገናኝ ነበር። ቀይ ግምጃ የመሰለ ሰው ነው ፤ ፈረሱ የሚበላው የወይራ ግንድ ነበር።
አጼ ቴዎድሮስንስ ያውቋቸዋል አልናቸው። ‹‹ቴዎድሮስ አንዴ ወደ እኛ መጣና በከፋና በጅማ መሐል አለፈ›› አሉን።
የተወለዱ ጊዜ ገንዘብ ነበር ስንላቸው ‹‹በጨው እንገበያይ ነበር። እኔ ግን ስወለድ ጀምሮ ጫት እየበላሁ ነው ያደግሁት›› አሉን። በእድሜዎ ስንት ሚስት አግብተዋል ብንላቸው ‹‹ሁለት ብቻ›› አሉ። ሚስቶችዎም እንደርስዎ ባለዕድሜ ነበሩ አልናቸው። አይደሉም አሉን። ሁለት ልጆች ወልደው እንደነበርና ሁለቱም በምኒልክ ጊዜ መሞታቸውን ነገሩን።
ሸሁ ላቀረብንላቸው ጥያቄ ሁሉ የሰጡን መልሶች ትክክል አይደሉም። የሰፈሩ ሰው ግን ሸሁ በእርግጥ 1 ሺ 340 ዓመት ዕድሜ አላቸው ብሎ ያምናል።
መጋቢት 23 ቀን 1957 ዓ.ም
መኪና ሰርቀው ሲንሸራሸሩ ተገለበጡ የተባሉት
ዘበኞች ተያዙ
ደበሌ ፣ ዲነግዴና ግርማ የተባሉ የመስከረም ቡና ቤት ዘበኞች ቁጥር 2384 ቮልስ ዋገን መኪና ከቆመችበት በአምሳያ ቁልፍ ከፍተው ሲንሸራሸሩ መኪናዋ ባልታወቀ ምክንያት በመገልበጧ መያዛቸውን የአምስተኛ የወንጀል ምርመራ ሹም ሻምበል እሸቱ ተሰማ ገለጹ።
ንብረትነቷ የሜታ ቢራ ፋብሪካ የሆነችው የዚህች መኪና ነጂ ከቡና ቤቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ ለማሳደር በሩን ዘግተው ከሄዱ በኋላ ከላይ የተጠቀሱት ዘበኞች በአምሳያ ቁልፍ አስነስተው እመት ጸሐይ ተስፋሁንና ወይዘሮ ዘነበች ሰይድ የተባሉትን ሴቶች አሳፍረው በደብረዘይት መንገድ ሲያመሩ በቅሎ ሰፈር ከተባለው ስፍራ ሲደርሱ መኪናዋ ባልታወቀ ምክንያት በመገልበጧ በሁለቱ ሴቶች ላይ ጉዳት መድረሱን ሻምበሉ አስረድተዋል።
ቮልስዋገን መኪናዋ በግጭቱ ምክንያት ከአገልግሎት ውጭ ስትሆን ጉዳዩ በምርመራ ላይ መሆኑንና ለስድስተኛ ፍርድ ቤት ጊዜያዊ ቀጠሮ መጠየቁን የአምስተኛ ፖሊስ ጣቢያ የምርመራ ክፍል ሹም ገልጸዋል።
ሐሙስ ታኅሳስ 22 ቀን 1963 ዓ.ም
የሕግ ሚስት እፈልጋለሁ
ስራዬ ሁለገብ ደሞዜ 420 ብር (መነሻ)። የአዲስ ሥራና የገንዘብ ምንጭ ዘዴኛና መቶ በመቶ ጤናማ ነኝ። የትዳር ጓደኛዬ ለምትሆነው ፍቅር ፣ አክብሮት፣ እምነት፣ ጨዋነት፣ ትህትናና ደስታን አብሮ ለመካፈል መቶ በመቶ ዝግጁ ነኝ። ብቸኝነት ሰለቸኝ።
ዕድሜዬ 35 ነው። ሁልጊዜ ብቸኛ ነኝ። አግብቼ አላውቅም። ልጅ የለኝም።ተጣጥሮ አዳሪ ነኝ። የመጠጥ አመል የለኝም። ሲጋራ አጤሳለሁ። ለዳንስ ለሲኒማ ለልዩ ልዩ ደስታና ጨዋታ አልሰንፍም። ሥራዬን አከብራለሁ። ከተቀጠርኩ ሁለት ዓመት ተኩል ቢሆነኝም በህመምም ሆነ በፍቃድ ከሥራ ቀርቼ አላውቅም። ወደሥራ ቀድሞ ከመግባት በስተቀር አንዲት ደቂቃ አሳልፌ አላውቅም። ውጪ ማምሸት አልወድም።
ትምህርቴ ሶስት የውጭ አገር ቋንቋ ነው። በሁለቱ እሰራበታለሁ። ቁመቴ አንድ ሜትር ከ 66 ሳ.ሜ ፣ ክብደቴ 65 ኪሎ ፣ ቀለሜ ጠይም ፣ በአካሄዴና በንግግሬ ፈጣንና አልፎ አልፎ ቀልደኛ ነኝ። ሁልጊዜ ሳቅና ጨዋታ እወዳለሁ። ኩርፊያ ፣ ኩራትና ትዕቢት አልወድም።
ስለዚህ እውነተኛ ዕድሜዋ ከ24 እስከ 32 ዓመት የሆነች ጨዋ ፣ ባለሙያ ፣ ቆንጆ (በተለይ ጥርስና እግር) ፣ ቁመቷ ከአንድ ሜትር ከ65 እስከ 70፣ ቀይ ወይም የጠይም ቆንጆ ፣ ቤተሰቧ የታወቀ ፣ ሙሉ ጤናማ የሆነች (ሥራና ሀብት ቢኖራት ባይኖራት የራሷ ጉዳይ ነው። እኔ ግድ የለኝም። ካላትም አይንን ጨፍኖ ፤ ጆሮን ደፍኖ መቀበል ነው።)፣ ኩርፊያ የማታውቅ ፤ የትምህርት ደረጃዋ የራሷ ፈንታ ነው ፤ ሃይማኖትና ዘር ግድ የለኝም። እኔን ማግባት የምትፈልግ ኢማ. ፍ.አ.ኃ.ማ ፖስታ ሳ.ቁ- 3201 አዲስ አበባ ብላ ትጻፍልኝ።
ታህሳስ 3 ቀን 1963 ዓ.ም
ማስታወቂያ በሾርኒ
ታህሳስ 3 ቀን 1963 ዓ.ም ቅዳሜ በወጣው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ትዳር ፈላጊው ደመወዙን መግለጹ የወር ገቢው ከ420 ብር በታች የሆነ አባወራ ሚስት ጋዜጣውን ካየች እንዳትሸፍት ያሰጋል። እንደዚህ ያለው ራስን ማዋደጃ ያልተከፈለበት የእጅ አዙር ማስታወቂያ በጋዜጣ ሲጠየቅ የመጀመሪያ ጊዜ ባይሆንም እየበዛ መሄዱ አስፈላጊነት የለውም። ሴቶቻችንን በማስታወቂያ ጠርቶ በማወዳደር ትዳርን ችርቻሮ ማድረግን እቃወማለሁ።
ማንም ሰው ባህሪው አካባቢውንና እድሩን ከመሰለና ከተግባባ አዛውንቱ፣ ጓደኞቹና ሌሎች ወዳጆቹ ሚስት በማምጣት ይረዱታል። ‹‹ወላድ በድባብ ትሂድና ኧረ ምን ጠፍቶ?›› የሚለው አያጣም። ከአካባቢው ካልተግባባና ካልተቀላቀለ ግን የጠባይ ጉድለት አለበትና ለትዳርም አይሆንም። የሾርኒው ማስታወቂያ ሚስት ቢያስገኝለትም በማይግባባ ፀባዩ መፋታቱ ስለማይቀር አዲስ ዘመን ጋዜጣ ባመጣለት ሚስት ምክንያት ‹‹አማጭ ረማጭ›› ሊባልብን ነው።
ያን ጊዜ በአዋጅ ማስታወቂያ ያገባው እንደገና በማስታወቂያ አፋቱኝ ቢል አያስደንቅም። ምናልባትም አዲስ ዘመን ያን ጊዜ በማስታወቂያ አምዱ ላይ አስፍሮ ክፍያ ይጠይቀው ይሆናል።
ታህሳስ 8 ቀን 1963 ዓ.ም
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 16/2014