በዘመን አመጣሽ አልባሳት የተዋበ፣ ከልብሱ፣ ከጫማው አሊያም ከመዋቢያ ዕቃዎቹ ታዋቂ መለያ (ብራንድ) ያለው፤ ስለ ሰውነት አቋሙ የሚጨነቅና ሁሌም መዘነጥን የሚያዘወትር ሰው በልማድ ‹‹ፋሽን ተከታይ ነው›› ይባላል። ከወቅቱ ጋር መራመድ ሁኔታዎችን መምሰልና ጊዜ ያለፈባቸውን ትቶ ከአዳዲሶቹ ጎን መሰለፍ ፋሽን መከተል የሚመስለንም ጥቂቶች አይደለንም።
የዘርፉ ባለሙያዎች ግን ፋሽን ራስን የመግለጫ መንገድ ስለመሆኑ ነው የሚጠቁሙት። ጊዜን፣ ቦታን እና ሁኔታን ቁልጭ አድርጎ እንደሚያሳይም ይተነትናሉ። ፋሽን በሚል የወል ስም ውስጥም ደግሞ ልብስና ጫማ፣ የጸጉር አያያዝ ስልት፣ የውበት መጠበቂያዎች፣ የሰው ልጅ መጠቀሚያ የሆኑ ቁሳቁስ አለፍ ሲል ደግሞ የሰውነት አቋምንም ያካትታሉ።
ለማሳያነት ልብስን ብንመለከት መነሻው የሰውን ልጅ ገላ መሸፈን እንዲሁም ከብርድና መሰል ነገሮች መጠበቅ ይሁን እንጂ፤ ከጊዜ በኋላ ግን የማንነት መገለጫ ወደመሆን ተሸጋግሯል። አንድን ህዝብ ከሌላኛው ለመለየትም አልባሳቱን መመልከት ብቻ በቂ ስለመሆኑም አሻሚ አይደለም። አሁን አሁን ደግሞ የሰው ልጆች እጅግ ከሚያተኩሩባቸውና በዕለት ተዕለት ህይወታቸው ሰፊውን ቦታ ከሚሰጧቸው ጉዳዮች መካከል ቀዳሚው ሆኗል።
ያለንበት ዘመን በተለይ የኢንተርኔት እና የመገናኛ ብዙኃን እንደመሆኑ ሰዎች ለፋሽን ይበልጥ ትኩረት እንዲሰጡና ስለሚለብሱት፣ ስለሚጫሙት፣ ስለሚይዙት እንዲሁም ስለሚጠቀሙባቸው ቁሳቁስ ምንነት፣ ጥራት፣ የተሰራበት ጊዜና ቁስ፣… እንዲያስቡ እያረጋቸው ነው።
ሰዎች ከሰውነት አቋማቸው እና ከአኗኗራቸው ጋር የሚዛመድ፣ ከሥራቸውና ከአዋዋላቸው ጋር የሚሄድ፣ ጊዜውንና ሁኔታዎችን ያገናዘበ፣ ያሉበትን የኢኮኖሚ ሁኔታ የሚያሳይ … ፋሽን መከተልንም ይመርጣሉ።
ይህንን ፍላጎት ለሟሟላትም በፋሽን ኢንዱስትሪ የተሰማሩ ተቋማትና ድርጅቶች ሳይታክቱ አዳዲስ ዲዛይኖችን መፍጠርና ማዘጋጀት ላይ አትኩሮታቸውን ማድረጋቸው የግድ ይላል። በመላው ዓለም እጅግ በርካታ የሆኑ ዲዛይነሮችም በየዕለቱ ሊባል በሚችል ደረጃ አዳዲስ ዲዛይኖችን ለገበያው ያበረክታሉ። የገበያው ፍላጎት እጅግ ከፍተኛ በመሆኑ የተነሳ ከግዙፎቹ አንስቶ አስከ አነስተኛ ኢንዱስትሪዎች ድረስ የተጠቃሚዎቻቸውን ፍላጎትንና ሁኔታን ባማከለ መልኩ ተመራጭና ተወዳዳሪ ዕቃ ለማቅረብ ይፎካከራሉ።
በዚህ ሂደትም የፋሽን ኢንዱስትሪው በመላው ዓለም እጅግ ከፍተኛ መጠን ያለው ሀብት የሚፈስበት መሆን ችሏል። ተፋላጊነቱ ዘርፉ ከከፍተኛ የኢኮኖሚ አንቀሳቃሾች መካከል ተጠቃሽ እንዲሆን አስችሎታል።
አሜሪካ፣ ቻይና እና ጃፓን ደግሞ በዘርፉ ቀዳሚ ተሳትፎ ያላቸው ሃገራት ሲሆኑ፤ የፓስፊክ ሃገራትም ተሳትፏቸው በማደግ ላይ እንደሚገኝ ነው መረጃዎች የሚያመላክቱት። ኢንዱስትሪው በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ያለው ተቀባይነትና ቦታ ከፍተኛ ልዩነት ያለው ቢሆንም በአንድም ሆነ በሌላ ግን አሻራውን ማሳረፉ አልቀረም። ይኸውም በፋሽን ኢንዱስትሪ የተሰማሩ ድርጅቶች ፋብሪካዎቻቸውን በማደግ ላይ በሚገኙ ሃገራት በመትከል፤ ከራሳቸው አልፈው ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሰው ኃይል ቀጥረው በመስራትና ገቢ በማስገኘት ረገድ ተጠቃሚ ማድረጋቸው ነው።
ኢንዱስትሪው ከ20ኛው ክፍለ ዘመን ወዲህ የቴክኖሎጂ እድገትን ተከትሎ የዳበረ ቢሆንም፣ በተለይ የአልባሳት ገበያው በአጭር ጊዜ ውስጥ ረጅም ርቀት ሊጓዝ ችሏል። በማሳያነትም ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት 2020 ብቻ በፋሽን ገበያው አንድ ነጥብ46 ትሪሊየን ዶላር ማንቀሳቀሱን ፋሽን ዩናይትድ የተሰኘው ድረገጽ ይጠቁማል። ይህ ቁጥር እአአ እስከ 2025 ድረስም ወደ ሦስት ትሪሊየን ዶላር ይደርሳል ተብሎም ይጠበቃል። ይህም ሁለት ከመቶ የሚሆነውን የዓለም አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት/ ጂዲፒ/ የሚሸፍን ነው።
አሀዞቹ በገበያው አማካይ ዋጋ መሰረት ሲተነተኑም የቅንጦት ዕቃዎች ገበያ 339ነጥብ4 ቢሊየን ዶላር ሲይዝ፤ የወንዶች አልባሳት 402 ቢሊየን እንዲሁም የሴት አልባሳት 621 ቢሊየን ዶላር ተንቀሳቅሶበታል። የሙሽራ ልብስ 57 ቢሊየን፣ የህጻናት ልብሶች 186 ቢሊየን እንዲሁም የስፖርት መጫሚያዎች 90ነጥብ4 ቢሊየን ዶላር መንቀሳቀሱንም መረጃው ያመላክታል። በዚህ ኢንዱስትሪ ከታዋቂዎቹ የአልባሳት ድርጅቶች ባለፈ በየጊዜው አዳዲስና በመጠንም አነስተኛ የሆኑ የጨርቃጨርቅ ድርጅቶች ኢንዱስትሪውን ይቀላቀላሉ።
ከፋሽን ኩባንያዎች መካከል የፈረንሳዩ Louis Vuitton Moët Hennessy (LVMH) የተሰኘው የቅንጦት ዕቃዎች አምራች በኢንዱስትሪው ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል። ይህ ድርጅት ከምርቶቹ ሽያጭ እአአ 2017 ብቻ 42ነጥብ6 ቢሊዮን ዩሮ ትርፍ አግኝቶ ነበር።
ቀጣዩን ደረጃ የያዘው ደግሞ የስፖርት አልባሳትና ትጥቅ አምራቹ ናይኪ ነው፤ ኩባንያው ከ2017 ገቢው 34ነጥብ4 ቢሊየን ዩሮ ገቢ አገኝቷል። ምርቶቹ በመላው ዓለም ተደራሽ የሆነው ይህ ድርጅት በአሜሪካ ገበያ ከፍተኛ ተፈላጊነት አለው። ከገቢው 64 ከመቶውን የሚያገኘውም ከዚህችው ሀገር ነው። የተቀረው 19 ከመቶ የገበያ ድርሻው ምዕራብ አውሮፓ ነው።
አብዛኛው የናይኪ ገቢ / ዘጠና በመቶው/ የሚገኘው ከኒኬ ብራንድ ነው። ከኩባንያው ብራዶች ጥሩ ሽያጭ የሚያስገኘው የጫማ ምርት ነው። ይህም ገቢ በመቶኛ ሲሰላ 63 ከመቶ ነው።
ዛራ፣ ፑል ኤንድ ቤር እና ስትራዲቫሪየስ የተሰኙ መለያዎችን የጠቀለለው የስፔኑ ግዙፍ የአልባሳት ማምረቻ ኩባንያ ‹‹ፋስት-ፋሽን›› ሶስተኛውን ስፍራ ሲይዝ ፣የ2017 ትርፉ 25ነጥብ34 ቢሊየን ዩሮ ነበር።
በርካቶች አዳዲስና ጊዜውን የሚመስሉ ፋሽኖችን ለመመልከት አውሮፓን ይመርጣሉ። ፈረንሳይና ጣሊያንን የመሳሰሉ ሃገራት ደግሞ የፋሽን እንዲሁም የታዋቂ መለያ ምርቶች ማዕከል ሊባሉ የሚችሉ ስፍራዎች ናቸው።
ስታቲስታ የተሰኘው ድረገጽ በመረጃው እንዳሰፈረው ከሆነ ያለፈውን ዓመት (እአአ 2020) የአውሮፓ የፋሽን ኢንዱስትሪ ቀዳሚውን ስፍራ የያዘችው ጀርመን ናት፤ አመቱ በአማካይ 63ነጥብ17 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር የተንቀሳቀሰበት ዓመት ነበር። 39 ከመቶ የሚሆነውን ገበያ በመያዝም የሴቶች አልባሳት ሰፊውን ድርሻ ይይዛል። ቻይና፣ ባንግላዴሽ፣ ህንድ እና ካምቦዲያ ደግሞ ወደ አውሮፓ ገበያ ልብሶችን በብዛት አምርተው በመላክ ገቢ የሚያገኙ ሃገራት ናቸው።
ይህ የምዕራባዊያን ተጽዕኖ ካለባቸው መካከል አህጉረ አፍሪካ ቀዳሚዋ ስትሆን፣ አነስተኛ መጠን ካለው ተጠቃሚነት ባለፈ በኢንዱስትሪው ያላት ተሳትፎ እዚህ ግባ የማይባል ነው። ከአጠቃላይ የዓለም ፋሽን ኢንዱስትሪ የአፍሪካ ድርሻ 1ነጥብ 5 ትሪሊየን ዶላር ብቻ ነው። ከዚህም ውስጥ ጫማ ደግሞ 31 ቢሊየን ዶላር ሚና ነበረው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ‹‹በአፍሪካ የተመረተ›› የሚሉ አልባሳትና መጫሚያዎች ገበያውን በመቀላቀል ላይ መሆናቸውን መረጃዎች ያመላክታሉ።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 15/2014