የጥቅምት ብርድ እትት እያረገኝ ወደ ቤቴ አቀናሁ:: ጥቅምት ቅልጥም የሚበላበት ትክክለኛው ጊዜ እንደሆነ የገባኝ ሦስት ያህል ልብስ ደራርቤ እትት ማለቴን ሳይ ነበር:: የኢትዮጵያ ህዝብ ግን ጥበበኛ ነው:: መስከረምን ለተስፋና ለአደይ አበባ ሰጥቶ ጥቅምትን በአጥንት መሰየሙ የሚደንቅ ነው:: ዘፋኙስ ብትሉ ‹በጥቅምት አንድ አጥንት ሲል ማቀንቀኑ ይሄን ተመልክቶ አይደል::
ጥቅምት የውርጭ ብቻ ሳይሆን የውበት መገለጫም እንደሆነ የገባኝ ዘግይቶ ነው:: ሳይደግስ አይጣላም የሚለው አባባል ለጥቅምት ወር ጥሩ መፈክር ይወጠዋል ስል አሰብኩ:: የነዋይ ደበበ ሙዚቃ ፊቴ ላይ ድቅን አለ፤ ‹የጥቅምት አበባ…
የጥቅምት አበባ…
የጥቅምት አበባ ነሽ አሉ…አወድሽው አካሌን በሙሉ:: እንደዛሬ ቅኔ ነጋሪ ሙዚቃ ሰምቼ አላውቅም:: ሙዚቃ አድማጭ አለመሆኔ ቆጨኝ:: ንዋይ ደበበ ሴትነትን ከወቅት ጋር፣ ውበትን ከአበባ ጋር ያዛመደበት መንገድ ለመንገዴ ሃሳብ ሆኖኝ ብዙ አዘገምኩ:: ሳላውቀው ዘፈኑ ውስጥ ነፍስ ዘራሁ…::
የሐምሌና የነሐሴን ጠል የጠጣች ጽጌሬዳ፣ የመስከረምን ተስፋ የለበሰች፣ ጥቅምት ላይ ያበበች አንዲት ጽጌሬዳ በምናቤ ተጸነሰች:: ፊቴ ላይ የሆነ ነገር ተሳለ፤ የርብቃ ውበት ድቅን አለ:: ያለጥርጥር ይሄ ሙዚቃ ለእሷ ነው ስል አሰብኩ.፤ ለርብቃ::
ርብቃ የተከራየሁበት ግቢ ተከራይታ ትኖራለች:: እንደ ቤተመንግሥት የሰፋ ቤት ለብቻዋ ይዛ የምትኖር ሴት…ይሄን የሚያክል ሰፊ ቤት ለብቻዋ ምን ያደርግላታል እያልኩ በማያገባኝ እየገባሁ አስባለሁ:: አንድም ቀን ግን ጠይቄአት አላውቅም:: ታስደንቀኛለች…በሴትነቷ ውስጥ ለሰው ልጅ ሁሉ የሚበቃ እውነት አለ::
እውነት ቢሏችሁ እውነት አይምሰላችሁ፤ በየትኛውም የሴት ልጅ ነፍስ ውስጥ የሌለ ገናና እውነት ነው::…ይቺን ሴት ማፍቀር ሲያንሰኝ ነው:: ፈጣሪ ድንቅ አድርገህ የፈጠርካትን አንድ ሴት ጥራ ቢባል ርብቃን እንደሚጠራ ጥርጥር የለኝም::
ረጅም ናት፤ እንደ ሰንደቅ:: በጠይም ፊቷ ላይ ለዘላለም የሚታወሱ አይንና ከንፈር ታድላለች:: ጉንጮቿ እንደ ላመ የተልባ ብናኝ ለስላሳ ናቸው ቢባል አይገልጻቸውም:: ለመላዕክትነት ታስባ ሰው የሆነች ይመስለኛል::
ስታወራ ድንቅ ሴትነት አላት:: የምትዘምር ትመስላለች:: ስለማፈቅራት ይሆን አላውቅም ቅዱስ ያሬድ የመጀመሪያውን ዜማ ሲፈጥር ከእሷ ሳቅ ውስጥ የኮረጀ ይመስለኛል:: ስትስቅ ነፍሴ ትስቃለች:: ስትስቅ በዘላለም ውስጥ እበቅላለሁ:: ስትስቅ እንደ እስቅያስ በዕድሜዬ ላይ ዓመታትን እጨምራለሁ:: ደሞ ጨዋነቷ…ሴት ልጅ በዛ ልክ ጨዋ ስትሆን አይቼ አላውቅም:: ለሁለት ዓመት አፍቅሬአታለሁ::
ከአዲስ ዓመት እቅዴ አንዱ ፍቅሬን ለእሷ መግለጽ ነው:: መስከረም ሳይጠባ ነፍሴን ከነፍሷ ጋር በአንድ የመቋጠር ትልቅ ዓላማ ይዣለሁ::
የጥቅምት ውርጭ እላዬ ላይ እየተወራጨብኝ የሰፈሬን መንገድ አጋመስኩት:: በልቤ ርብቃ አለች፤ በስጋዬ ደግሞ የጥቅምት ውርጭ:: ነፍሴ እትት እያለች ወደ ፊት ተራመድኩ:: በህይወቴ ውስጥ የርብቃን መኖር ሳስብ ሙሉ የሆንኩ ያህል ይሰማኛል::
ገና እንደማፈቅራት አልነገርኳትም፣ ነገር ግን በማፍቀሬ ብቻ ዓለም ላይ ደስተኛውን ሰው የሆንኩ ያህል ይሰማኛል:: ብዙ ሰዎች አፍቅረው ሲሳካላቸው ብቻ የሚስቁ ናቸው:: እኔ ግን ባልተሳካ ፍቅር ውስጥም ደስታ አለ ባይ ነኝ:: ፍቅር ሞት የሌለበት ዓለም ነው:: ፍቅር ነፍስን በደስታ ማስጨነቅ ነው:: እኔ አሁን በዚህ እውነት ውስጥ ነኝ::
ሰፈር ደረሰ:: የውጪውን በር ከፍቶ ሊገባ ሲል በር ላይ ‹የሚከራይ ቤት አለ› የሚል ጽሑፍ ተንጠልጥሎ ተመለከተ:: ነገሩ ሁሉ ግራ ገባው:: ግቢው ውስጥ ሦስት ክፍል ነው ያለው፤ ሦስቱም ተከራቷል:: ግራ ተጋባ፤ ምናልባት ኩሽናውን አድሰው ማከራየት ፈልገው ይሆናል ሲል አሰበ:: ኩሽናው ደግሞ አልታደሰም፤ የማያውቀው ሌላ ክፍል ያለ ይመስል ግቢውን በሃሳቡ ዞረው::
ከሦስቱ ክፍል ውጪ ሌላ ክፍል አላገኘም:: በቃ ኩሽናውን ይሆናል ሲል…በዚህኛው ሃሳቡ እርግጠኛ በመሆን ወደ ውስጥ ገባ::
ወደ ውስጥ ሲገባ ግቢው ጭር ብሏል:: ርብቃ ክፍል ጠፍቶ የማያውቀው የሙዚቃ ድምፅ እንኳን አይሰማም:: ከሙዚቃው እኩል የሚሞዝቀው ለስላሳ ድምጽዋም የለም:: ግራ እንደ ተጋባ ወደ ክፍሉ ሄደ:: ክፍሉ ደርሶ ዓይኖቹን ወደ ርብቃ ክፍል ሲወረውር በሩ ተከፍቶ ኦና ቤት ተቀበለው:: ልቡ መምታት አቆመ…:: በደመነፍስ ወደ ርብቃ ክፍል ተራመደ፤ ቤቱ ባዶ ነው:: ርብቃ የለችም:: ዕንባው ጠብ ጠብ አለ::
በቆመበት የአመሻሽ ብርዳም አየር ዠልጦት ሄደ:: ምን እያሰበ ነበር? አያውቀውም፤ ፍቅር ደስታ ብቻ ነው ብሎ ነበር፤ ብዙ ሰዎች አፍቅረው ሲሳካላቸው ብቻ የሚስቁ ናቸው ብሎ ነበር፤ ራሱን ምን ይበለው?
ግራ ተጋብቶ በቆመበት አንድ ድምፅ ከኋላው ተሰማው፤ የሚዘምር የሚመስል ድምፅ:: ሞቶ ነበር፤ በጥቅምት ሰማይ ስር ራሱን ጥሎ ነበር፤ ያን ቅጽበት ሲያስታውሰው ለዘለዐለም ይገርመዋል:: ፈጣሪ በደመና ድምጹን ያሰማው ነው የሚመስለው::
ርብቃ ነበረች፤ ‹‹ሳልሰናበትህ አልሄድም ብዬ ነው ተመልሼ የመጣሁት::›› ስትለው ከኋላው ሰማት:: እንደ ወትሮው በሚሞዝቅ ሙዚቃዊ ድምጹዋ:: በዚያ ሰዓት ምን ሆኖ እንደነበርና ምን እያሰበ እንደሆነ ብታውቅለት ብቻ ይበቃው ነበር::
ከውብ አለባበስና ከውብ ጠረኗ ጋር ፊቱ ስትቆም ለዘላለም ደግሞና ደጋግሞ እንዲያፈቅራት ሆኖ ነበር:: ከውብ መልኳና ከውብ ተፈጥሮዋ ጋር አጠገቡ ሲያገኛት እያሰባት ሊኖር ለራሱ እየማለ ነበር:: በመልካም ምግባርና በመልካም ሴትነት ጎኑ ስትቆም መቼም እንደማይረሳት እያመነ ነበር::
ብዙ የሚጠይቃት አለ፤ ከየት ጀምሮ እንደሚጨርስ አያውቀውም:: ግን ያስባል፤ ዛሬም ነገም፤ ለሚመጣውም:: ስለ እሷ፣ ስለ ፍቅሯና ውበቷ…ስለ ቅን ምግባሯና ጨዋነቷ::
ደጉ የጥቅምት ውርጭ ያለቅጥ እየጋለበ በእውን የራቀውን ሴትነቷን ከወንድነቱ ጋር ቀላቀለው:: ነፍሱን ከነፍሷ በአንድ ጻፋት::
‹ብርድ ነው ወደ ቤት እንግባ? ከአፉ የወጣ የመጀመሪያም የመጨረሻም ቃል ነበር::ወደ ቤት ሲገቡ ፈጣሪ ምን ያህል እንደሚወደው እያሰበ ነበር::
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ጥቅምት 12/2014