አሮጌውን 2013 ዓ.ም ሸኝተን 2014 ዓ.ም ከተቀበልን አንድ ወር ከአስር ቀናት ተቆጥሯል። በአሮጌው 2013 ዓ.ም በሀገር ውስጥ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ያጋጠመው ጦርነት፣ ዓለም አቀፍ ስጋት የሆነው ኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝ ከወትሮው በተለየ ሁኔታ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ምስቅልቅሎሽ ተፈራርቀውበታል።
‹‹አፍንጫ ሲነካ አይን ያለቅሳል›› እንዲሉ ለኢኮኖሚው መነቃቃት አንዱ የሆነው ፖለቲካ ባለመረጋጋቱ ኢኮኖሚው ሲታመም ከራርሟል። የፖለቲካ አለመረጋጋት በኢኮኖሚው ላይ ያሳረፈው ጫናም በተጨባጭ ታይቷል። ላለፉት በርካታ ዓመታት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የምርት እጥረትና የሸቀጦች ዋጋ መናር አጋጥሟል። መንግስትም ነገሩን በቸልታ ባያየውም ለኢኮኖሚው መረጋጋት ዘላቂ መፍትሄ አልተገኘም። በመሆኑም ማህበረሰቡ ከኑሮ ጫና ሊላቀቅ አልቻለም። መስከረምና ጥቅምት ወራቶች ደግሞ የተለዩ ወቆቶች ናቸው።
የበዓላት መደራረብ፣ ትምህርት የሚጀመርበት ወቅት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የገንዘብ ወጪ ከፍ ስለሚል የአብዛኛው ሰው ኢኮኖሚ ይዳከማል። ዝቅተኛ ገቢ ላለውና ኑሮው ከእጅ ወደአፍ ለሆነ ማህበረሰብ ደግሞ እጅጉን ከባድ እንደሆነ መገመት አያዳግትም። አሁን የሚታየው የገበያ ተለዋዋጭነት ደግሞ ነገሩን የከፋ አድርጎታል። ብዙዎች እንደሚሉት በእያንዳንዱ የአገልግሎት አቅርቦት ላይ የሚስተዋለው የዋጋ ጭማሪና ፍጥነት ከገቢ ጋር የሚመጣጠን አይደለም። በዚህ ወቅት በስፋት እየተነሳ ያለው ደግሞ የትምህርት ቁሳቁስ አቅርቦትና ወጋ መናር ጉዳይ ነው። አብዛኞቹ ትምህርት ቤቶች የጀመሩት በዚህ የጥቅምት ወር በመሆኑ የትምህርት ቁሳቁስ ግዥው ወይም ገበያ ገና በመካሄድ ላይ ነው።
በአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ማርታ አበራ ገበያው እንዳማረራቸው ነው የገለጹልን። እርሳቸው ለአንድ ልጅ የትምህርት ቁሳቁስ ለማሟላት እንዲህ ከተቸገሩ ሁለትና ከዚያ በላይ የሚያስተምሩ ወላጆች በጭንቀት ውስጥ ሊሆኑ እንደሚችሉ ነው የተናገሩት። እርሳቸው እንዳሉት በዘንድሮ ዓመት በትምህርት ቁሳቁስ ላይ የታየው የዋጋ ንረት ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በእጥፍ ጨምሯል። የላጲስ፣ የመቅረጫ የደብተር፣ የቦርሳ፣ የምሳ ዕቃና ሌሎችም አስፈላጊ ግብአቶች ዋጋቸው በእጥፍ ጨምሯል።
ለአብነትም እንደገለጹት ባለፈው ዓመት 400 ብር የገዙት ቦርሳ አሁን ላይ 700 መቶ ብር፣ 230 ብር የገዙት የምሳ ዕቃ መያዣ ቦርሳ ዘንድሮ 500 ብር ሆኖ ነው ያገኙት። ደብተር እጅግ በጣም ከመወደዱ በተጨማሪ በቂ አቅርቦትም የለም። ባለፈው ዓመት በአማካኝ 18 ብር ሂሳብ የገዙት ደብተር ዘንድሮ ከእጥፍ በላይ ጨምሮ በአሁን ወቅት አንድ ደብተር በ41 ብር ሂሳብ አካባቢ ማለት ነው አንድ ደርዘን በ500 ብር ነው የገዙት። በቂ የደብተር አቅርቦት አለመኖሩ ሰዎች በአንድ ስፍራ ላይ እንዲሰበሰቡ ከማድረጉ በተጨማሪ ገንዘብ ይዞ ለመግዛት የማይቻልበት ደረጃ ተደርሷል። የትምህርት ቤት የደንብ ልብስ (ዩኒፎርም) እንዲሁ የዋጋ ጭማሪ አሳይቷል። ከላይ የሚለበሰው ሹራብ ብቻ ይሸጥ ከነበረበት 250 ብር በአሁኑ ጊዜ እስከ 400 ብር በመሸጥ ላይ ይገኛል።
እርሳቸውን ጨምሮ አብዛኛው ሸማች ቀድሞ የመግዛት ልምድ የሌለውና በዕለቱ የመጣደፍ ሁኔታ እንደሚስተዋል ያነሱት ወይዘሮ ማርታ፤ ዘንድሮ ሁሉም ነገር የጨመረና የትምህርት ቁሳቁስም እንዲሁ የቱንም ያህል ቢወደድ እና ብዙ ለውጥ ባይኖረውም ቀድሞ መግዛትና መዘጋጀት ይገባ እንደነበርና አሁን ያለውን መጨናነቅ መቅረፍ ይቻል እንደነበር ያስረዳሉ።
ለሁሉም ነገር ቀድሞ መዘጋጀት ተመራጭ መሆኑ እየታወቀ ሁሉም ሰው ጫፍ ሲደርስ ለመግዛት ይወጣል። በዚህ ጊዜ ግርግሩን መጠቀም የሚፈልግ ነጋዴ ዕቃው ቢኖረውም የለም አልገባልንም በማለት በተጋነነ ዋጋ ሸጦ መጠቀም ይፈልጋል። ከዚህ በተጨማሪም አንድ የደብተር አይነት የተሻለ ሽፋን አለው ጠንካራ ነው ከተባለ ሁሉም ሰው ያንኑ አይነት ይፈልጋል። ትምህርት ቤቶችም እንዲህ አይነት ደብተር አቅርቡ ብለው ትዕዛዝ ያስተላልፋሉ ይህም አንዱ ችግር ነው።
ከዚህ በተጨማሪም ትምህርት ቤቶች ለተማሪዎች የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን በተለይም ጀማሪ ተማሪዎች በአይነትም ሆነ በመጠን በርካታ ነገሮችን እንዲያቀርቡ ያስገድዳሉ። የሚጠይቁት አቅርቦት ከመጠን ያለፈ በመሆኑ ተገቢነት የሌለው ነው። አንዳንድ ትምህርት ቤቶች በዓመቱ መጨረሻ የተረፈውን ቁሳቁስ በታማኝነት የሚመልሱ ሲሆን አንዳንዶቹ ግን አይመልሱም።
ምንም እንኳን ትምህርት ቤቶች የሚጠይቁት ግብዓት ከትምህርት ቤት ትምህርት ቤት ቢለያይም በአብዛኛው ከመጠን ያለፈ ቁሳቁሶችን የሚጠይቁ እንደሆነ ነው ወይዘሮ ማርታ ያነሱት። በዘንድሮ ዓመት እንኳን እርሳቸው ለአንድ ትምህርት ሶስት ደብተር የተጠየቁ ሲሆን በትንሹ ለሶስት ትምህርት ዘጠኝ ደብተር መግዛት ይገደዳሉ ማለት ነው። ይህ ማለት ደግሞ ወላጆች ወደ ትምህርት ቤት የሚልኳቸው ልጆች መጠን በጨመረ ቁጥር የሚኖረው ጫና ቀላል ግምት የሚሰጠው አይሆንም።
ታዲያ ይህ የደብተር ቁጥር ዋና ዋና ለሚባሉት የትምህርት አይነቶች ማለትም አማርኛ፣ ሒሳብ፣ እንግሊዝኛ እና አካባቢ ሳይንስ ትምህርቶች ነው። አብዛኞቹ የግል ትምህርት ቤቶች ለእነዚህ የትምህርት አይነቶች ሁለትና ሶስት ደብተር ከመጠየቃቸው በተጨማሪ የእጅ ጽሁፍ መማሪያ፣ ስኩሪ፣ የሥዕል ደብተርና ወዘተ…ይጠይቃሉ። ይህ በመሆኑም የዘንድሮ ዓመት የትምህርት ቁሳቁስ ወጪ በወላጆች ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደረ ይገኛል። በመሆኑም ልጅ ማስተማር ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በ2014 ዓ.ም የትምህርት ዘመን እጅግ ፈታኝ እንደሆነ አንስተዋል።
ስሜ አይገለጽ ያሉት እና ሁለት ልጆቻቸውን በመንግስት ትምህርት ቤት እንደሚያስተምሩ የገለጹት ሌላኛዋ ወላጅም እንዲሁ የትምህርት ቁሳቁሱ ከመወደዱ መጥፋቱን ይናገራሉ። እርሳቸው እንደሚሉት መንግስት ለተማሪዎች ዩኒፎርም እና የትምህርት ቁሳቁስ ከማቅረብ ጀምሮ ምገባ መጀመሩ እጅግ በጣም ጥሩና ለአብዛኛው ማህበረሰብ እፎይታን የሰጠ እርምጃ እንደሆነ ተናግረዋል። አያይዘውም ልጆቻቸው በሚማሩበት ትምህርት ቤት ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ዩኒፎርም እና የትምህርት ቁሳቁስ ለተማሪዎች አልቀረበም። በመሆኑም እርሳቸው ጥቅምት አንድ ቀን 2014 ለተጀመረው ትምህርት ደብተርን ጨምሮ አጠቃላይ የመማሪያ ቁሳቁስ ገዝተው ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት ልከዋል። ዩኒፎርምም እንዲሁ ያልቀረበ በመሆኑ ነባር ተማሪዎች ያለፈውን ዓመት ዩኒፎርም ለብሰው ወደ ትምህርት ቤት እየሄዱ እንደሆነና አዳዲስ ተማሪዎች ግን ከዩኒፎርም ውጭ በሆነ ልብስ ወደ ትምህርት ቤት መሄዳቸውን ታዝበዋል።
ይሁን እንጂ አሁን ባለው የኑሮ ውድነት ላይ የተማሪዎች አጠቃላይ ወጪ ቢጨመር የቱን ያህል ከባድ እንደሚሆን በማንሳት መንግስት ምገባን ጨምሮ የትምህርት ቁሳቁስ ማሟላቱ ለማህበረሰቡ ትልቅ እፎይታን ሰጥቷል። ይህም ገበያውን በተወሰነ መንገድ ከማረጋጋቱ በበለጠ ማህበረሰቡ ያለበትን ኢኮኖሚያዊ ጫና በማቃለል በኩል ትልቅ ድርሻ አለው ብለዋል።
አራት ኪሎ አካባቢ በሚገኘው ጀነራል የጽህፈት መሳሪያ ያገኘናቸው ወይዘሮ ሙሉ ብርሃን በዘንድሮ ዓመት የትምህርት ቁሳቁስ በከፍተኛ መጠን እጥረት ያጋጠመና እንደልብ የማይገኝ መሆኑን አንስተው ዕቃው ሲገኝም ከፍተኛ ዋጋ ጨምሮ የመጣ መሆኑን ይናገራሉ። ለአብነትም ባለፈው ዓመት 25 ብር ይሸጥ የነበረው ባለ 50 ሉክ ደብተር በአሁን ወቅት ከ35 እስከ 45 ብር እየተሸጠ ነው። እያንዳንዱ እቃ እንደ አገባቡ የሚለያይ በመሆኑ ዋጋውም ይለያያል።
በተለይም በአሁን ወቅት የትምህርት መጀመሪያ ሳምንት በመሆኑ የትምህርት ቁሳቁሶች ከመወደዳቸውም በላይ እንደልብ መገኘት እንዳልቻሉ የገለጹት ወይዘሮ ሙሉ፤ አስመጪዎች አልገባም የለም እንደሚሉ እና ቢኖርም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ማሳየቱን ነው የጠቆሙት።
ከዋጋ መናር ባለፈ ለትምህርት ቁሳቁሶቹ እጥረት ወላጆች ቀደም ብለው ባለመግዛታቸው ነው ወይስ ሌላ ምክንያት ይኖር ይሆን ብለን ላነሳነው ጥያቄ ወይዘሮዋ ሲመልሱ፤ ‹‹ዘንድሮ ከትምህርት መጀመሪያ ጊዜም ቀደም ብለው የገዙ ወላጆችም ቢሆኑ በከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ነው የገዙት። እኛም ዋጋ ጨምረን የገዛን በመሆኑ ጨምረን ለመሸጥ ተገደናል። ምናልባት አሁን ላይ ፍላጎቱ ሲጨምር እጥረቱን አባብሶት ከሆነ እንጂ የዋጋው መናር ቀደም ብሎ የጀመረ ነው›› ብለዋል።
ይሁንና አሁን እየታየ ያለው አጠቃላይ የገበያ ሁኔታና የኑሮ ውድነት ሀገሪቱ አሁን ያለችበት ሁኔታ ምክንያት እንደሆነ ጠቅሰው በቀጣይ ሀገሪቷ ወደ ሰላሟ ተመልሳ ስትረጋጋ ሁሉም ነገር የሚስተካከል ስለመሆኑ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
በ2014 የትምህርት ዘመን መንግስት የሚያቀርበው የትምህርት ቁሳቁስ አቅርቦትና ስርጭት ምን ይመስላል? ስንል ላነሳነው ጥያቄ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተማሪዎች ምገባ ኤጀንሲ ምክትል ዳይሬክተር ወይዘሪት ዘለቃሽ ባህሩ ሲመልሱ፤ ኤጀንሲው ወጣት ተማሪዎች በምግብ እና በትምህርት ቁሳቁስ እጥረት ምክንያት ከትምህርት ገበታ ውጭ እንዳይሆኑ እየሰራ ነው።
በዘንድሮ በጀት ዓመት ስድስት መቶ ሃያ ሺ የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለሚማሩ ተማሪዎች ትምህርት ከመጀመሩ አስቀድሞ የደንብ ልብስ ተዘጋጅቷል። በዚህም አብዛኛው የደንብ ልብስ በየትምህርት ቤቶቹ ተደራሽ እየሆነ ይገኛል። በተወሰነ መጠን ተደራሽ ያልሆነባቸው ትምህርት ቤቶች እንዳሉ ይታወቃል። ይህም እያንዳንዱ የተማሪ ደንብ ልብስ አቅራቢ ወይንም ጋርመንት የደንብ ልብሱን እኩል ሊያቀርብ ባለመቻሉ ነው። ይሁንና በአሁን ወቅት አብዛኛው የማጠቃለል ሥራ ብቻ የቀረ በመሆኑ በቀጣይ ሳምንት ሙሉ ለሙሉ የማሰራጨት ሥራ ይሰራል።
ኤጀንሲው ለመንግስት ትምህርት ቤቶች ከሚያሰራጫቸው ግብዓቶች መካከል ደብተር ሌላኛው ግብዓት ነው። ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት ከመግባታቸው አስቀድሞ ትምህርት ለማስጀመር የሚሆን ከአንድ ነጥብ አራት ሚሊዮን በላይ ደብተር ማሰራጨት ተችሏል። በአሁን ወቅት ደግሞ አቅራቢዎች በግልጽ ጨረታ ተወዳድረው አራት ሚሊዮን የሚደርስ ደብተር ለማስገባት በዝግጅት ላይ ናቸው።
ሌላው ከቅድመ መደበኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ላሉ ተማሪዎች ኤጀንሲው ጫማ ያቀርባል። ይህም ሙሉ ለሙሉ መጠናቀቅ ባይችልም ከአቅራቢዎች ጋር ያለው ሂደት ተጠናቅቆ በስርጭት ላይ ይገኛል። በተያያዘም የሴቶች የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ የሚቀርብ ሲሆን ይህም ከተለያዩ ረጂ ድርጅቶች ተሰብስቦ የሚሰራጭ ይሆናል። በአሁን ወቅትም በቂ ነው ባይባልም ኤጀንሲው በእጁ ላይ ያለውን ለትምህርት ቤቶቹ ተደራሽ እያደረገ ይገኛል ያሉት ዳይሬክተሯ፤ በዘንድሮ የትምህርት ዘመን የትምህርት ቁሳቁስ በተለይም ደብተር ውድ መሆኑ አንስተው በተለይም ጨረታ ተወዳድረው ያለፉ ተጫራች አስመጪዎች ደብተሩን ገና እያስገቡ ነው። በመሆኑም ወላጆች ላልተገባ ወጪ እንዳይዳረጉና ችግር እንዳይገጥም በማሰብ ከዚህ በፊት ከተማ አስተዳደሩ ከተለያዩ በጎ አድራጊ ድርጅቶች ሰብስቦ ያስቀመጠውን አንድ ነጥብ አራት ሚሊዮን ደብተር በውሳኔ እንዲሰራጭ መደረጉን ተናግረዋል። በቀጣይም ቀሪዎቹ ተደራሽ ይሆናሉ ብለዋል።
መንግስት ትምህርት ቁሳቁሶችን በወቅቱ ማቅረብ ካልተቻለና የግል ትምህርት ቤት ተማሪም የመንግስት ትምህርት ቤት ተማሪም ፍላጎቱ እኩል ከሆነ ጫና ይፈጥራል። ያሉት ዳይሬክተሯ፤ በተለይም በዘንድሮ ዓመት የነበረውን የደብተር መወደድ ከግምት ውስጥ በማስገባት ከግዢ አስቀድሞ ቀድሞ የተከማቸውን ደብተር በውሳኔ መጠቀም እንደቻሉና ይህም ገበያው ላይ ያለውን ጫና በመጠኑ ያቃለለ መሆኑን ተናግረዋል። በግዢ ሂደት ላይ ያለውም በሳምንት ጊዜ ውስጥ ተጠናቅቆ ሙሉ ለሙሉ ተደራሽ እንደሚሆን አስረድተዋል።
ፍሬህይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 10/2014