በዚህ የቴክኖሎጂ ዘመን በተለያዩ የዓለም ጫፎች የተከሰቱ ክስተቶችን በበይነ መረብ አማካኝነት እናገኛለን። በሀገራችንም እንደዚያው እየሆነ ነው፡፡ የዚህን ዘመን ብቻ ሳይሆን የቀደሙትን ዘመናት ስራዎች በቴክኖሎጂው ተደራሽ ማድረግ የተጀመረም ይመስለኛል፡፡
በሀገራችን ቀደምት ጽሁፎችን በበይነ መረብ ማግኘት የሚቻል አይመስለኝም፡፡ የዱሮ አዲስ ዘመን ዘገባዎችን በየነ መረብ ገና አልደረሰባቸውም፡፡ በይነ መረብ ባልነበረበት ዘመን የነበሩ የአዲስ ዘመን ዘገባዎችን የምናገኘው ወደ አብያተ መጻህፍት ሄደን በማገላበጥ ነው፡፡
የድሮ አዲስ ዘመን ጋዜጣን ማንበብ ራሱን የቻለ ትምህርት ቤት በሉት፡፡ የድሮ አዲስ ዘመን ጋዜጣን ስናነብ በዘመኑ የነበሩ ሁነቶችን፣ ህግና ደንቦችን ብቻ ሳይሆን አንዳንድ አጋጣሚዎችንም እናገኛለን፡፡ እነዚያ አጋጣሚዎች ዛሬ ላይ ሆነን ከሚያጋጥሙ ነገሮች ጋር ሲገጣጠሙ ደግሞ ፈገግታን ይፈጥራሉ፡፡
በቅርቡ አሸባሪው የህወሓት ቡድን በአማራና አፋር ክልሎች በከፈተው ጦርነት መንደር ውስጥ እየገቡ ሊጥ ይሰርቁ እንደነበር ተዘግቧል፡፡ በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ፎቶ ሾፕ እየተሰራ የህወሓት አዛውንት ከፍተኛ አመራሮች ሊጥ ሲሰርቁ የሚያሳዩ ቀልዶች በስፋት ሲዘዋወሩ ነበር፡፡
እሁድ መጋቢት 26 ቀን 1963 ዓ.ም የወጣ አዲስ ዘመን ጋዜጣ የ75 ዓመት አዛውንት ሊጥ ሰርቀው መታሰራቸውን ይነግረናል፡፡ ዜናው የሚከተለው ነው፡፡
የ75 ዓመት ሰው ሊጥ ሰርቆ ታሰረ
አሥር ጊዜ የሌብነት ወንጀል ፈጽሞ የዘጠኝ ዓመት ተኩል ቅጣት ከተቀበለ በኋላ የተቦካ ሊጥ ከነባሊው ሰርቋል በመባል የተከሰሰው ሰው የፈጸመው ወንጀል በህግ ማስረጃ ስለተረጋገጠበት በአንድ ዓመት ከስድስት ወር እስራት እንዲቀጣ የከፍተኛ ፍርድ ቤት ሁለተኛ ወንጀል
ችሎት ባለፈው ዓርብ ፈረደ፡፡
አቶ ንጋቱ ፋንታ የተባለው ተከሳሽ የሚኖረው በአዲስ አበባ ከተማ የካ ሚካኤል አካባቢ ሲሆን ሌብነትን የዘወትር ሙያው በማድረግ የሰውን ቤት በሌሊት እየሰበረ ልዩ ልዩ የቤት ዕቃዎችን በተደጋጋሚ ጊዜ ሰርቆ እንደነበር ፍርድ ቤት በቀረበለት ማስረጃ መሰረት ለማረጋገጥ መቻሉን ገልጿል፡፡
የ75 ዓመቱ ሽማግሌ የተቦካውን ሊጥ ከነባሊው በሰረቀበት ዕለት ሁለት የቡና ስኒ እና አንድ የስፌት አገልግልም ጨምሮ መውሰዱን ራሱ ለፍርድ ቤቱ በሰጠው ቃል አረጋግጧል፡፡
ተከሳሹ በየጊዜው በፍርድ ቤት የተወሰነበትን ቅጣት ተራምዶ የተደጋገመ ወንጀል መፈጸሙን ፍርድ ቤቱ ጠቅሶ ከገለጸ በኋላ የተከሳሹ ዕድሜ የገፋ ስለሆነ ቅጣቱን አሻሽሎለት በአንድ ዓመት ተኩል ቅጣት እንድቀጣ ወስኗል፡፡
እንዲሁም ከተከሳሹ ጋር የወንጀል ግብረ አበር ሆኗል በመባል የተከሰሰው ደበበ ጫላ ከዚህ ቀደም የሌባ ተቀባይ መሆኑ ቢረጋገጥም በአሁኑ ጊዜ የፈጸመው ወንጀል ከዚሁ ጋር ተመሳሳይነት ያለው በመሆኑ በአንድ ዓመት እስራት እንዲቀጣ ተፈርዶበታል፡፡
በየዘመናቱ አንዳንድ ጊዜ አስገራሚ ነገሮች ይከሰታሉ። እነዚህ አስገራሚ ነገሮች ተሰንደው ሲቀመጡ ከዘመናት በኋላም አስገራሚነታቸው አይለቅም፡፡ ለምሳሌ መጋቢት 11 ቀን 1963 ዓ.ም የወጣው አዲስ ዘመን ጋዜጣ አንዲት አህያ በወንጀል ይፈለግ የነበረውን ግለሰብ ቦምብ አፈንድታ መግደሏ ነው፡፡ አስገራሚ የሚያደርገው አህያ ቦምብ ማፈንዳቷ ሳይሆን የተገደለው ሰውዬ ሰው በመግደል ወንጀል ይፈለግ የነበረ መሆኑን ነው፡፡ ዜናው የሚከተለው ነው፡፡
አህያ ወንጀለኛ በቦምብ ገደለች
ሰው በመግደል ወንጀል ለሁለት ዓመታት ያህል ተደብቆ ይኖር ነበር የተባለው ዑመር ሱሪ የጫናት አህያ ረግጣው በኪሱ ደብቆት የነበረው የእጅ ቦምብ በመፈንዳቱ ምክንያት እርሱም አህያውም ወዲያውኑ ሞተው መገኘታቸውን የሸዋ ጠቅላይ ግዛት ፖሊስ የማስታወቂያ ክፍል ትናንት ገለጠ፡፡
ማስታወቂያ ክፍሉ በሰጠው መግለጫ ላይ እንዳስረዳው ዑመር ሱሪ ለይፋትና ጥሙጋ አውራጃ ደቄ ራህመዶ ወረዳ ግዛት ውስጥ ሀምሌ 18 ቀን 1961 ዓ.ም ሐዊ እንድሪስ የተባሉትን ሴት በጥይት ገድሎ ተደብቆ ይኖር ነበር፡፡ ነገር ግን የካቲት 27 ቀን 1963 ዓ.ም በአንዲት አህያ እህል ጭኖ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ሲሄድ ጭነቱን ሊያስተካክል ሲል በአህያዋ እርግጫ ከኪሱ ያለው ቦምብ ተመቶ በመፈንዳቱ ከአህያዋ ጋር ሞተው ተገኝተዋል፡፡
ቀደም ሲል እንዳልኩት ዛሬ ዘመኑ የቴክኖሎጂ ነው፡፡ ከአንዱ የዓለም ጫፍ የተከሰተ ነገር ወዲያውኑ ከሌላኛው የዓለም ጫፍ ይሰማል፡፡ ያኔ ግን የሚሰማው በሬዲዮ ወይም በቴሌቭዥን ብቻ ነበር፡፡ ከጋዜጣ አንፃር ፈጣን የሚባሉት እነርሱ ናቸው፡፡
አዲስ ዘመን ዓለም አቀፍ አስገራሚ ነገሮችንም ይሰንድ ነበር፡፡ በብሮድካስት ሚዲያ የሚነገር አስገራሚ ነገር ከዓመታት በኋላ ለሌላው ሰው ተደራሽ አይሆንም፡፡ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ግን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍትን ጨምሮ በተለያዩ ትልልቅ ሰዎች እጅና በተቋማት ቤተ መጻሕፍት ውስጥ ይገኛል፡፡
በዘመኑ ይዟቸው ከወጣቸው አስገራሚ ነገሮችም የዘመኑን ሁኔታ እንረዳለን፡፡ ታህሳስ 16 ቀን 1957 ዓ.ም ሮይተርስን ዋቢ አድርጎ ይዞት የወጣው ዜና በዘመኑ ነጮች ለጥቁር የነበራቸውን አመለካከት ያሳየናል፡፡
በፍቅር ደብዳቤ 350 ብር ተቀጣ
ለአንዲት ነጭ ልጃገረድ የፍቅር ደብዳቤ የጻፈ አንድ
አፍሪካዊ የሙዚቃ መሪ የልጃገረዲቱን መብት ተዳፍረሃል ተብሎ በቀረበበት ክስ መሰረት ሦስት መቶ ሃምሳ ብር ተቀጥቷል፡፡
ናታሊ ማሎይ የተባለው ይህ የ28 ዓመት ዕድሜ ያለው የሙዚቃ መሪ ገንዘብ ባስቀመጠበት በአንድ የደቡብ አፍሪካ ባንክ ውስጥ ለምትሰራ የ23 ዓመት ዕድሜ ላላት ነጭ ልጃገረድ የጻፈው ደብዳቤ ተገኝቶበታል፡፡ ስሟ ያልተገለጠው ይቺ ልጃገረድ ፍርድ ቤቱ ከዚህ በፊት ባደረገው ችሎት ላይ አፍሪካዊው ናታሊ ናሎይ ብዙ ደብዳቤዎች እያከታተለ የጻፈላት መሆኑን ገልጻለች፡፡
ናታሊ ማሎይ ለልጃገረዲቱ ከጻፋቸው ደብዳቤዎች ውስጥ አንዱ ‹‹በሰውነቴ ውስጥ የፍቅር እሳት አቀጣጥለሽብኛል፤ በሙሉ ልብ አፈቅርሻለሁ፡፡ በነፍሴም በሥጋዬም ያንችው በመሆኔ እንደፈለግሽው ልታደርጊኝ ትችያለሽ›› የሚሉ ቃላት ተገኝተውበታል፡፡
አዲስ ዘመን ሁሉንም ለታሪክ አስቀምጧል፡፡ ከላይ ካየነው ዜና በተቃራኒው ደግሞ የጥቁር ኩራትና የነፃነት አስጀማሪ የሆነችው ኢትዮጵያ ለእንግሊዝ ያደረገችውን እርዳታ ይነግረናል፡፡ መስከረም 23 ቀን 1940 ዓ.ም የወጣው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ዕርዳታው ሲላክ አብሮ የተላከውን ደብዳቤ እንደሚከተለው አስነብቦ ነበር፡፡
ለሎርድ ሜዮርክ ናሽናል ዲስትሬስ ፈንድ ለንደን
ምንም እንኳን እኛም ራሳችን በህዝባችን ላይ ያለአግባብ በግፍ የደረሰበትን ጉዳት በማቃለል ሥራችን ላይ ብንሆንም ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቀው ሃይለኛና ጨካኝ በሆነው ክረምት ሁልጊዜ በምናስባት በለምለሟ ውብ በሆነችው አገርዎ ላይ ለደረሰው ጥፋት መጠነኛ የገንዘብ እርዳታ መጠየቅዎን ስለሰማን የገንዘቡ ቁጥር ምንም ከፍ ያለ ሳይሆን የኛንና የህዝባችንን እርዳታ ለመግለጽ ያህል አንድ ሺህ ፓውንድ በለጋሲዮናችን በኩል ልከንልዎታል፡፡
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 9/2014