የፋሽን ኢንዱስትሪው ትኩረት ተሰጥቶ ከተሰራበት ለአገር ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የሚያበረክተው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው።አገራዊ ገቢን በከፍተኛ ሁኔታ ከማሳደግ ባለፈ፤ ከሌሎች ዘርፎች በተሻለ የሰው ሀይል የሚያሳትፍና የስራ አጥነት ችግርን ለመቅረፍ የሚያስችልም ነው።የኢንዱስትሪውን ጠቀሜታ የተረዱት አገራት የፋሽን ኢንዱስትሪውን ሰፊ ገበያ በማጥናት በሰጡት ከፍተኛ ትኩረት በዓመት በቢሊዮን ዶላሮችን ያፍሳሉ።
እንደ አሮፓውያን አቆጣጠር በ2016 በተሰራ አንድ ጥናት፤ ያደጉት ሀገራት ከአልባሳት ፋሽን ብቻ (ሌሎች የፋሽን ዘርፎች ሳያካትት) በዓመት ያገኙት ገቢ ከአንድ ነጥብ 26 ትሪሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ መሆኑ ተመልክቷል።ይህ የአንድ አመት ገቢ ብቻ ነው፡፡
በዘርፉ የካበተ ልምድ ካላቸው አገራት መካከል ከፊት ሆነው አለምን በኢንዱስሪው እየመሩ ያሉት አገራት ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ኔዘርላንድ፣ እንግሊዝና ስፔን በቅደም ተከተል ይጠቀሳሉ።ታዲያ ይህ ለእድገትና ለለውጥ ትልቅ አስተዋፅኦ ያለው ዘርፍ የእኛን አገር ተሞክሮና ልምድ ስንመለከት ብዙ የሚቀረው ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
በፋሽን ኢንዱስትሪው አገራዊ ምርትን ከማስተዋወቅና ጥራታቸውን ጠብቆ በገበያው ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ከማስቻል አኳያ ሊሰራና ህዝቡም ለአገራዊ ምርትና የመጠቀም ልምዱ ሊያሳድግ እንደሚገባም ይመክራሉ።
ወጣት ዚነት መሀመድ የፋሽን ዲዛይነርና የራስዋ የልብስ ስፌትና ዲዛይን ትምህርት ቤት ባለቤት ናት።ዚኒት ስለኢትዮጵያ የፋሽን ዘርፍ እድገትና ስላሉበት ችግሮች ስትገልጽ ኢትዮጵያ ውስጥ ዘርፉ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ትገልጻለች፡፡
እንደ ዚነት ገለጻ፤ የኢትዮጵያ የፋሽን ዘርፍ ከጊዜ ወደ ጊዜ ለውጥ እያሳየና እያደገ ቢሆንም ከሌሎች አገራትና በዘርፉ በስፋት ከሚሰሩት ጋር ሲወዳደር እጅጉን ዝቅተኛ ደረጃ ይገኛል።በሀገራችን ለፋሽን ዘርፉ ዕድገት ገቺ ምክንያቶች ናቸው በሚል ሁለት ዋና ዋና ነጥቦችን ትጠቅሳለች ።የመጀመሪያው በሙያው የሰለጠነና ብቁ ባለሙያ በተፈለገው መጠን አለመኖር ሲሆን ሁለተኛው ባሉት ባለሙያዎችም የሚሰሩ አገራዊ ምርቶች በዘርፉ ውስጥ ከሌለው አገር ጋር ሲወዳደሩ የተሻሉ ቢሆኑም እንኳን በህዝብ ዘንድ በአገር ውስጥ ምርት አለማመን ችግር ይታያል ስትል ታብራራለች፡፡
ገበያው ላይ ያሉ የአገር ውስጥ ምርቶች ለህብረተሰቡ በስፋትና ከውጪው በተሻለ ዲዛይን ቢቀርቡ እንኳ የህብረተሰቡ የመጀመሪያ ምርጫ የተሰራበትን አገር አይቶ የውጪውን መምረጥ መሆኑን ከልምድዋ በመነሳት ታስረዳለች።ይህ የምርት ጥራት ከአገር ውስጥ ምርት ይልቅ የውጪ አገር ምርት ይሻላል ብሎ የማመን የተሳሳተ ልምድ ውጤት መሆኑን ታስገነዝባለች።
እንደ ባለሙያዋ ገለጻ፤ ህዘቡ በአገር ውስጥ ምርት ላይ ያለው አመለካከት ሊለወጥ ይገባል።በአገር ውስጥ ምርት መገልገል እና ምርጫ ማድረግ ጠቀሜታው ለራስም ለአገርም ትልቅ ለውጥ ለሚያመጣው ለፋሽን ዘርፉ ዕድገትም ወሳኝ መሆኑ ሊረዳ ይገባል።ይህን ማድረግ ከተቻለ በተለይ በአልባሳት ዘርፍ ያለውን በውጪ ምርቶች ላይ የማመን ችግር በቀላሉ መቅረፍ ይቻላል።
ለዘርፉ ዕድገት ውስንነት ሌላኛው ምክንያት አድርጋ የምትጠቅሰው በዘርፉ የሰለጠነ በቂ የሰው ሀይል አለመኖርን ነው።ይህን ችግር ለመቅረፍ ትምህርት ቤቶች በስፋት ሊኖሩና ባለሙያዎችም ወቅቱ የሚጠይቀውን የሙያው ክህሎት እና እውቀት ሊላበሱ ይገባል።
ኢትዮጵያ ብዙ ህዝብ የሚኖርባትና ለውጪ ሀገራት የተለያዩ የፋሽን ኢንዱስትሪ ግብዓቶችን ማቅረብ የምትችል አገር መሆንዋን ገልፃ፤ ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረት አነስተኛ መሆንና የሰለጠነ የሰው ሀይል አለመኖሩ የዘርፉ ትልቅ ተግዳሮት መሆኑን ትገልፃለች፡፡
በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በርካታ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች በተለያዩ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ እንደ መቋቋማቸው በአልባሳትና በአዳዲስ ዲዛይን ለውጪ ገበያ በማቅረቡ ስራ ላይ ትኩረት ሰጥቶ ቢሰራና ዲዛይነሮችም እዚህ ላይ ትኩረት አድርገው ቢሰሩ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚቻል በመፍትሄነት ታቀርባለች።
ዲዛይነር ፅጌረዳ የደሴወርቅ በዲዛይነር ዚነት የቀረበው በውጪ ምርቶች የማመን የማህበረሰቡ እምነትና ልማድ ላይ ብትስማማም፣ የባለሙያዎች ብቁ አለመሆንና ቁጥራቸው ማነስ ላይ ግን አትስማማም።ይልቁንም እንደእሷ በዲዛይኒግ ትምህርት ቤት በቂ እውቀት ጨብጠው ወጥተው በዘርፉ የስራ ዕድል ባለማግኘት ሌላ ስራ ላይ የተሰማሩ ጓደኞች እንዳሏት በማሳያነት ታነሳለች፡፡
እንደ ዲዛይነር ፅጌረዳ የዘርፉ ዕድገት ዋንኛው ችግር ማህበረሰቡ በአገር ውስጥ ዲዛይነሮች አለማመንና በአገር ውስጥ ምርት የመገልገል ልምድ አለመኖር ነው።ማህበረሰቡ አገራዊ ምርቶችን በተለይ አልባሳት ላይ እምነት ሊያድርበትና በአገር ውስጥ ምርት የመጠቀም ባህሉን ሊያሳድግ ይገባል።በማትም ሀሳብዋን ታጋራለች።ሙያተኛውም ቢሆን በዘር የተማረውን ትምህርት ጥቅም ላይ ለማዋልና ማህበረሰቡን የሚያሳምን ምርጥ ምርጥ ዲዛይኖችን በመስራትና የራሱን ፈጠራ በመጠቀም ዘርፉን ሊያሳድግና ለአገርም የሚጠቅም ስራ ሊሰራ ይገባል በማለት ምክረ ሀሳብዋን ትገልፃለች።
በፋሽን ኢንዱስሪው በተለይ በአልባሳት ዘርፍ ያለውን ሰፊ ገበያ ለመጠቀምና አገራዊ ምርትን ከፍ ለማድረግ ብሎም የውጪ ምንዛሬን ግኝትን ለማሳደግ በሙያው በቂና የሰለጠነ ሀይል ከማፍራት ባሻገር ህብረተሰቡ የሀገር ውስጥ ምርት እንዲጠቀም በማበረታታቱ ላይ ሰፊ ስራ መስራት ይጠበቃል።በእርግጥ ከዘርፉ አዲስነት አንፃር በአገር ውስጥ ያሉ የዘርፉ ባለሙያዎች ቁጥር ማነስና ባለሙያዎቹ ዘንድ አልፎ አልፎ የሚታየው የክህሎት ችግርም እንደ ምክንያት ሊነሳ ይችላል።
በፋሽን ዘርፍ ርቀው የሄዱ አገራት አገራዊ ገቢን በማየት ብቻ ለዘርፉ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ባለሙያዎቹ ያሳስባሉ።በአለም ገበያ የፋሽን ኢንዱስትሪውን መቀላቀልና አገራዊ ምርትን ማሳደግ ከተቻለ ገቢን ከማሳደግ ባለፈ የስራ አጥ ቁጥርን በመቀነስ አዎንታዊ ሚናው የጎላ ነው።ይህ በአገር ደረጃ የረዘመ ታሪክ የሌለውና ኢንዱስትሪ በሚባል ደረጃ ገና ያላቆመው የፋሽን ዘርፍ፣ ገና በጅምር ላይ ያለ እንደመሆኑ ከሚያስገኘው ፋይዳ አንፃር ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል የሚለው የዝግጅት ክፍላችን መልዕክት ነው።አበቃሁ፤ ቸር ይግጠመን፡፡
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 8 ቀን 2014 ዓ.ም