የአዲስ አበባ ጎዳኖች ከቀን ወደ ቀን እጃቸው ምጽዋትን ለመጠየቅ በሚዘረጉ ሰዎች እየተሞላ ነው። ከህጻን እስከ አዛውንት በጎዳና ላይ ሆነው “አንድ ዳቦ መግዢያ” የሚሉ በርክተዋል። ህጻናትን ታቅፎ በህጻናቱ ልግስናን መጠየቅም የተለመደ ስልት ከሆነ ሰነባበተ። ልባቸውን ስለ መልካም ነገር አትግተው ችግሩን ለመቅረፍ የሚተጉ በጣት የሚቆጠሩ ሆነው ቢሰሙንም የተሳሳትን ልንሆን አንችልም። በችግራችን ምክንያት ኑሯቸውን ያደላደሉትም እንዲሁ ከሰፈራችን በቅርብ እርቀት ላይ ይገኛሉ።
ከሀገራችን ወጣ ስንል ብዙ የኢትዮጵያውያንን ኑሮ በመደገፍ የሚታወቁ ሃገራትን እናገኛለን። የአሜሪካ መንግሥት ከቀዳሚዎች መካከል የሚጠቀስ ሲሆን አውሮፓውያን የሚከተሉት ናቸው። የልግሥና ተግባር ከግለሰብ እስከ መንግሥታት የራሱ ባህሪ እንዳለው እንረዳለን።
ልግስና ከልግስና ልብ ውስጥ ሲሆን ተጽእኖ ፈጣሪነቱ ታላቅ ነው። ከእዚያ መለስ ሰጥቶ በመቀበል ስሌት ውስጥ ሲሆን ይረክሳል። የረከሰ ልግስና! ልግስና ምንም ካለመፈለግ ልብና በፖለቲካ ስሌት ውስጥ ሆኖ ሲተገበር አመታት ተቆጠሩ። የአሜሪካ የተራድኦ ድርጅት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ማስፈጸሚያ ሆኖ መዋቀሩ ልግስናንና ፖለቲካን አብሮ አቆራኝቶ ሲታሰብ ግምት ውስጥ የሚገባው የተቸገረን ሰው ችግር ብቻ ሳይሆን የለጋሹን ከልግስና ያለፈ ፍላጎትም እንደሆነ በብዙ አሳየን።
የዛሬው መግቢያ ታሪካችን በአንድ ታዳጊ ልብ ውስጥ ስለ ልግስና የተቀጣጠለን ልብ ያስተዋውቀናል። መነሻው ያለንበትን ወቅታዊ ሁኔታ ያደርጋል።
ታዳጊው ብላቴና ትምህርት ሲከፈት ለጓደኞቹ የጻፈውን ጽሁፍ ሊያነብላቸው ቆመ። መምህሩ የብላቴናውን ጽሁፍ ሲሰማ “በትዝብት አርጩሜ ሁላችንም የሚሸነቁጥ” ሲል ለራሱ ተናገረ። ብላቴናው የስድስተኛ ክፍል ተማሪ ነው። የሚሰማውን ነገር በጽሁፍ ከትቦ በዙሪያ ላሉ ሰዎች በማንበብ ሃሴት የማድረግ ልማድ ያለው። ዘንድሮ ትምህርት ቤት በተከፈተበት የመጀመሪያው ሳምንት ውስጥ አስተማሪውን አስፈቅዶ ለተማሪዎቹ ያቀረበላቸው ጽሁፍ “ለጋሾች ወዴት አሉ?” ይላል። በጥያቄ የተሞላው የታዳጊው ጽሁፍ ህሊና ላለው ሁሉ ጥያቄን የሚያጭር ነው።
ከክረምቱ ቀናት መካከል በአንዱ ቀን ታዳጊው ከቤተሰቡ ጋር የሚኖርበት መኖሪያ ጊቢ ተንኳኳ። እንደ ወትሮው ሮጦ ሄዶ በሩን ከፈተው። በሩን ሲከፍት አለባበሳቸው ከቀዬው ለየት ያለ አንድ አባት ከበራቸው ቆመዋል። ደንግጦ ወደ ቤት ተመልሶ በር ላይ ስለቆሙት ሰው ለእናቱ ተናገረ። እናቱ የልጃቸውን መልእክት ሰምተው ወደ በሩ ወጡ፤ ከበር የቆሙትን አባት ሊያነጋግሩ። በሰላምታ ልውውጥ ንግግር ተጀመረ። ከበር የቆሙት ሰው ሀገሪቱ ውስጥ ባለው አለመረጋጋት ተሰደው መምጣታቸውን አስረዱ። ያሳለፉትን አስቸጋሪ ጊዜ ከሚተናነቃቸው እንባ ጋር ሆነው ተናገሩ፤ እንዴት ያሉ ብርቱ አርሶ አደር የነበሩ መሆናቸው እየታወሳቸው ለምጽዋት ሰው ደጅ ዛሬ ላይ መገኘታቸው እየረበሻቸው።
በሽማግሌው ንግግር ውስጥ የመውለጃ ጊዜዋ እየተቃረበ ያለች ሚስታቸውን እና ልጃቸውን ለመመገብ እየዞሩ እየለመኑ መሆናቸውን አስረዱ። የስደት ጉዞውን ከጀመሩ በኋላ በመንገድ የሞተችባቸውን ልጃቸውንም ታሪክ ሲያስረዱ ሲታገላቸው የነበረው እምባ ያለከልካይ ፊታቸውን ሸፈነው። ብርቱው አርሶ አደር ዛሬ ተመጽዋጭ ሆኖ ከማያውቀው ቤተሰብ በር ላይ እንዲህ ቆሟል። የብላቴናው እናትም እምባቸውን መቆጣጠር አቃታቸው። ብላቴናው የእናቱንና ከበራቸው የቆሙትን አባት ሁኔታ እየተመለከተ “ለጋሾች ወዴት አሉ?” እያለ ራሱን ይጠይቃል። ለጥያቄው ምላሽ ውስጥ የራሱን ኃላፊነትም እየፈለገ።
ሽማግሌው ወደ ቤትገብተው ቤትያፈራውን እንዲመገቡ ተጋበዙ። ምላሻቸው እምቢታ ሆነ። “የሚባለውን በፌስታል አድርጉልኝና ከሚስቴና ከልጄ ጋር እበላለሁ እንጂ እኔ ለብቻዬ እንዴት ችዬ ልበላ” አሉ። የብላቴናው እናት ሃሳባቸውን ተቀብለው ቤት ያፈራውን ቆጣጥረው ሸኟቸው። ሽኝቱ ግን በአካል እንጂ ከውስጥ አልነበረም። የሰሙት ታሪክ እናትንም ሆነ ልጅን ውስጥ ተቆጣጥሯል።
ብላቴናው በመንገድ ላይ የሞተችውን የሽማግሌውን ልጅ፣ አሁን በሆድ ውስጥ ያለውን ጽንስና የዚህን ቤተሰብ አሁናዊ የሆነ ቀጣይ እጣ ፈንታ እያሰበ “ለጋሾች ወዴት አሉ?” እያለ ጠየቀ። ለጋሾችን ከባህር ማዶ ብቻ የመጠበቁ አተያይ ስህተት ሆኖም ተሰማው። ለጋሾቹ ሁሉ ኢትዮጵያውያን መሆን አለባቸው ሲል ለራሱ መለስ ሰጠ። ራሱንም ከለጋሾቹ ዝርዝር ውስጥ ጨመረ። በቀን ሦስቴ የሚበላ ሁለቴ እንዲበላ በማድረግ ሁሉም ሰው በልግሥና ህይወት ውስጥ መኖር የሚችልበትን ልብ ቢኖረው ችግሩ ምን ያህል በቀለለ ሲል አሰበ።
ማምሻውን ቤተሰቡ በሞላ ሲሰበሰብ ብላቴናው አንድ ሃሳብ አቀረበ። በቀን ሁለቴ እየበላን አንዴ የምንበላውን ለዚህ ቤተሰብ ለምን አንሰጥም? አለ። ደግሞም ከቤታችን ውስጥ አንድ ክፍል ቤት ለምን አንለቅላቸውም? ሲል ጥያቄ አቀረበ። ቤተሰቡም የብላቴናውን ሃሳብ ተቀብሎ ምቾቱን ሰውቶ እንዲህ ባለ ወቅት ለአንድ ቤተሰብ በመገኘት የሚጠበቅበትን ለመወጣት ቃል ገባ። ቃላቸውንም ተገበሩት። ነፍሰ ጡሯም እናት ወለደች። አንድ ቀን ነገሮች ሲረጋጉ ወደ ሃገራቸው እስኪ መለሱ ይህ ቤተሰብ የእነርሱ ለጋሽ ሆኖ ራሱን አቀረበ።
ብላቴናው የጻፈው ጽሁፍ ለክፍል ተማሪዎቹ ሲነበብ ከተማሪዎቹ መካከል ተፈናቅሎ የመጣ ተማሪ ታሪኩን ሲሰማ በእምባ ታጅቦ ንባቡን ያደምጣል። እንደ ሀገር ያለንበት ሁኔታ ይህ ነው። እንዲህ ባለ ወቅት ለጋሽነትን ለባለሙያ ለጋሾች ሰጥቶ ከመቀመጥ ሁላችንም የምንነሳበት ወቅት አሁን የሆነበት ወቅት። ለጋሾች ወዴት አሉ? የሚለውን ጥያቄ ለእያንዳንዱ ግለሰብ፤ ለእያንዳንዱ ቤተሰብ፤ ለእያንዳንዱ ቤተክርስቲያን እንዲሁም ሌሎች የእምነት ተቋማት በታላቅ ትህትና እናቅርብ። ሰው እየፈረሰ ነው፤ ድንጋይን በድንጋይ ላይ ደራርበን የሰራነውን ልማት ሊጠቀምበት የሚገባው ግለሰቡ እየፈረሰ ነው! በልግሥና ልብ ልንቆምበት የሚገባ ወቅት።
ለጋስ ሆይ ተነስ!
በልግስናቸው ሚሊዮን ሆነ ቢሊዮንን ከነኩት እንደ አንድሪው ካርኔጂ፣ ጄ ፒ ሞርጋን እና አንድሪው ሜሎን የመሳሰሉ ቀደምት ሚሊዬነር ላጋሾች ወይንም እንደ አሁኖቹ እነ ቢል ጌትስ እና ጆአን ክሮክ አይነት ሰዎችን ለወቅታዊ ሁኔታችን ከመጠበቅ ወደራሳችን እንመልከት የሚል ጥሪ።
ለጋስነትን በትኩረት ወደራሳችን በማቅረብ የምንችለውን በማድረግ መርህ ለመትጋት ጥቂት ነጥቦችን እናንሳ።
1. ከምንም ነገር በፊት ሰው ይቀድማል እንበል፣
“የአንድ መሪ መለኪያው እርሱን የሚያገለግሉ ሰዎች ብዛት ሳይሆን እርሱ የሚያገለግላቸው ሰዎች ብዛት ነው። ” ይላሉ ጆን ማእከስዌል። የልግስና ሕይወትን ለማዳበር ቀዳሚው እውነት ሰውን የምናይበት መነጽር ነው። ሁሉም ነገር ስለሰው ልጆች መሆኑን ስንረዳ ልግስና ትርጉም ይኖረዋል። ከፖለቲካም፤ ከባህል፤ ከሃይማኖት ወዘተ ልዩነቶች በፊት ሰውን በሰውነቱ በመመልከት አጠገቡ መቆም አስፈላጊ ነው። የብላቴናው ቤተሰብ ያስጠጋቸው ስደተኞች ምናልባት በእምነትም ሆነ በብሔር ሆነ በሌላ መንገድ የማይገናኙ ናቸው። ነገርግን ሰዎች ናቸው! ልግስና ሌሎችን በሰውነት ሚዛን ቆጥሮ ማስቀደምን ይጠይቃል።
2. ስለ ገንዘብ ያለንን አተያይ መፈተሽ፣
ገንዘብ ለምን ያስፈልገናል ወይንም የገንዘብ ዓላማው ምንድን ነው ብለን መጠየቅ አስፈላጊ ነው። ገንዘብም ሆነ በሌላ መንገድ የሚገለጽ ሃብትለሰው ልጆች መጠቀሚያ ነው። ዛሬ እንጠቀመው ነገ ዞሮ ዞሮ መጠቀሚያ ነው። ዛሬ ገንዘብ እኛ ጋር ሆኖ ነገርግን ገንዘብ የሌላቸው ሰዎችን ስናገኝ እንዴት ልንረዳቸው እንደምንችል ማሰብ አለብን።
አንድ ሰው ስለ ገንዘብ ሲናገር ገንዘብንም በየትኛውም ምእራፍ በቀላሉ ማሸነፍ የምትችለው እንዳልሆነ ማሳያዎች አሉ ይላል። ለምሳሌ ትኩረትህ ገንዘብን መስራት ሲሆን የቁስ ተከታይ ትሆናለህ። ገንዘብ ለመስራት ጥረት አድርገህ ሳይሳካልህ ቢገኝ የከሰርክ ሰው ሆነህ ራስህን ትቆጥራለህ። ብዙ ገንዘብ ሰርተህ ነገርግን አንተ ጋር ይዘህ ብታቆየው ንፉግ ትሆናለህ። ገንዘብን ሰርተህ እንዳሻህ ስታወጣው አባካኝ ትሆናለህ። ገንዘብን ለመስራትም ሆነ ሃብት ለማፍራት ፍላጎቱ ከሌለህ እንዲሁ አንድን ነገር ለማሳካት መነሳሳት የሌለህ ሰው ሆነህ ራስህን ታያለህ። ባለብዙ ሃብት ሆነህ ብትሞት እንደ ሞኝ ነህ።
ምክንያቱም ያልተጠቀምክበት ሃብት ሰብሳቢ ስለነበርክ። ብቸኛው የገንዘብን ፈተና ማሸነፍ የምትችልበት እድል አጥብቀህ አለመያዝ እናም በምታምንበት ነገር ላይ ለጋስ መሆን ነው። ኢ.ስቴንሊይ ጆንስ የተባለ ግለሰብ “ገንዘብ ጥሩ አገልጋይ ነው ነገር ግን መጥፎ አለቃ ነው። ” በማለት ገልጾታል። ይህ ሰው ሲቀጥል “ገንዘብ ከበላይ ከሆነ አንተ ከበታች ነህ ማለት ነው በሌላ አገላለጽ አንተ የገንዘብ ባሪያ ሆነህ። ” ሲል ገንዘብ ባሪያው ሊያደርገን የሚችልበትን መንገድ ገልጾታል።
ራእይ ይዞ አንዳች የሚጠቀም ነገር ለማድረግ እየሰራ ያለ የምታውቀው ሰው አለ? እንግዲያውስ ለእዚህ ሰው በመለገስ ገንዘብህ በስራ ላይ እንዲውል በማድረግ ገንዘብ መጠቀሚያ መሆኑን አሳይ።
3. መስጠትን መለማመድ፣
ራሳችንን ያስለመድናቸው ብዙ ነገሮች አሉ። ትርጉም ከሚሰጡ ራስን ማስለመድ ውስጥ አንዱ ነው። ስለ ሰው መልካም አመለካከት ኖሮን እንዲሁም ስለ ገንዘብ ያለን የተስተካከለ አተያይም ሆኖ ነገርግን መስጠት በቀላሉ የምንችለው ላይሆን ይችላል። መስጠትን ራስን በማስለመድ ውስጥ የምንደርስበት መሆኑን መረዳት ይገባል። በ1889 እ.አ. ኢንዱስትራሊስቱ ሚሊዬነር አንድሪው ካርነጊ Gospel of Wealth የተሰኘ መጽሐፍ ጽፎ ነበር።
በእዚህ መጽሐፍ ውስጥ የአንድ ባለሃብት ዘመን በሁለት ክፍለ-ጊዜ ውስጥ የተዋቀረ እንደሆነ ጸሃፊው ይገልጻል። የመጀመሪው ክፍለ-ጊዜ ሃብት የምትሰበስብበት ሲሆን ሁለተኛው ክፍለ ጊዜ የምትበትንበት ነው ይላል። የልግስናን አስተሳሰብ የምታሰፋበት ብቸኛው መንገድ መስጠትን ባለህ ጊዜ፣ ትኩረት፣ ገንዘብ እና ሌሎችም ሃብቶች ላይ በተጨባጭ መግለጽ ስትጀምር ነው። ስለሆነም መስጠትን ልምድ ማድረግ ይገባል።
4. የሃብት አምሮትን መቆጣጠር መቻል
የሃብት አምሮትን ያህል የምድራችን መላ እንቅስቃሴ ቅኝት የሰጠ አምሮት ስለመኖሩ እጠራጠራለሁ። ሰው ፈጣሪን ለመምሰል ያለው አምሮት በላይ የሃብት አምሮት ከፍተኛውን ስፍራ የያዘም ይመስላል። አምሮት ለተግባር እንቅስቃሴ የሚያነሳሳ በመሆኑ ለአንድ ሰው አምሮት አስፈላጊው ነገር ነው። የሃብት አምሮት በራሱ ችግር የለውም። ኤርሊ ዊልሰን የተባሉ ሰው በሚከተሉት ሦስት ምድቦች ሰዎችን ይከፍሏቸዋል እነርሱም “ያላቸው፣ የሌላቸው እና ዋጋ ሳይከፍሉ ያላቸውን ነገር ያገኙ” በማለት። በርካታ ሰዎች ሃብት ለማፍራት ባለመሻት የሃብት አምሮት ባሪያ ሆነዋል።
ደራሲ ሪቻርድ ፎስተር የተባሉ ሰው ደግሞ “በባህላችን የንብረት ባለቤት መሆን ሁለንተናችንን የሚቆጣጠር ጉዳይ ሆኗል። የንብረት ባለቤት ስንሆን ንብረቱን እንደምንቆጣጠረው ይሰማናል። የምንቆጣጠረው ሲሆን የበለጠ እርካታ እንደሚሰጠን ይሰማናል። ” ይላሉ። ልብህን ልትመራ የምትፈልግ ከሆነ፣ የሃብት አምሮት ልብህን እንዳይቆጣጠር አድርግ። የሃብት አምሮት ችግር ባይኖርበትም ህይወትን ሃብት ከማሰባሰብ አንጻር ብቻ በመቃኘት መመላለስ የለጋስነት ህይወት እንዳይኖረን ያደርጋል። በመነሻችን ላይ ያነሳነው ታሪክ ውስጥ የተጠቀሰው ለጋሱ ቤተሰብ አንድ ክፍል ቤት በሚለቅበት ጊዜ ምቾቱን አሳልፎ በመስጠት ወይንም ቤቱን አከራይቶ የሚያገኘውን ሃብት በማጣት ነው።
5. ያለንን ነገር መመልከት መቻል፣
የሃብት አምሮት መላ ህይወታችንን ሲቆጣጠረው ያለንን ሳይሆን የሌለንን እያየን በብዙ ስንባክን ዘመናችንን እንጨርሳለን። ዛሬ ምን አለን? ባለን ነገር የመጠቀም እንዲሁም ሌሎችን ለመጥቀም የምንሄድበት እርቀትስ?
ባለው ነገር የማይረካ ሰው ለጋስ መሆን እጅግ ይቸግረዋል። ልግስና ከውስጥ ግፊት የሚወጣ እንጂ ባለን ነገር ብዛት የሚመጣ አይደለም። ሚሊዬነር ጆን ዲ. ሮክፌለር እንዲህ አለ “በሚሊዮን የሚቆጠር ሃብት ማፍራት ብችልም ደስታን ይዞልኝ ሊመጣ ግን አልቻለም። ” በትንሽ ነገር ላይ የለጋስነት ህይወት ከሌለህ ብዙ ሲኖርህም የመኖር እድሉ አነስተኛ ነው። በትንሹ ለጋሽ መሆን ካልቻልክ፣ ባለጸጋ በሆንክ ጊዜ በቅጽበት መቀየር አትችልም። ስለሆነም ዛሬ ያለንን ነገር በመመልከት ባለን ነገር የመርካትን ልማድ እናዳብር።
እስኪ በአንተ ባለቤትነት ያሉ ነገሮችን ቁጠራቸው። ካሉህ ነገሮች መካከል ትርጉም የምትሰጠውን አንድ ነገር አንሳና ብትሰጠው የበለጠ ሊጠቀም ለሚችልበት ሰው ስጠው። ይህንን ማድረግህን ቀጥል። በሂደቱ ያለህን ማወቅና ለምን ማዋል እንዳለብህ እየለመድክ ትሄዳለህ።
መሪዎች በልግሥና ልብ ውስጥከመሪው በኩል የሚደረግ ልግስና ከሌሎች በርካታ ስራዎቹ ጎልቶ የሚሰማ ነው። ተከታዮችን ለማንቀሳቀስ እድል የሚሰጥ ነው። በማህበራዊ ሚዲያ ብዙ ተከታይ ያላቸው እውነተኛ ለጋስ ቢሆኑና ሌሎችንም ቢያስተባብሩ ምን ያህል አዎንታዊ ተጽእኖ ሊፈጥሩ እንደሚችሉ ምሳሌ የሚሆኑ ጥረቶችን ተመልክተናል።
እውነተኛ ለጋስነት አልፎ አልፎ የሚሆን ነገር ሳይሆን የቀንተቀን የህይወት ዘይቤ መገለጫ ነው። ልግስናው ከልብ የሚመጣ ከሆነ በመሪው መላ ህይወቱ ማለትም በጊዜው፣ በችሎታው እንዲሁም ባለው ሃብት ላይ ሁሉ የሚገለጽ ነው። ውጤታማ መሪዎች ለራሳቸው የሚሰበስቡ ሳይሆኑ ለሌሎች ለማካፈል የሚሰብስቡ ናቸው። የልግስናን ህይወትን በመሪነት ህይወት ውስጥ ኮትኩቶ ማሳደግ የሚገባው ለእዚህ ነው።
የአመራር ህይወትህ ወደ አንድ ትርጉም ያለው ደረጃ ባደገ ቁጥር ለሰዎች ልትሰጣቸው የምትችለው ውድ ነገር ጊዜህ ነው። ወደ ህይወትህ ልታቀርበው የምትፈልግ ሰው ፈልግ። ይህ ሰው የተሻለ መሪ እንዲሆን ጊዜህንም ሆነ ገንዘብህን ለግሰው። ጊዜን በመስጠት ውስጥ አንድ መሪ ሊሰጥ የሚችለውን በመስጠት ወደ ሌላም ድጋፍ በመተላለፍ የአመራር ህይወትህ ልግስናን የሚያበረታታ እንዲሆን ማድረግ ትችላለህ።
ጆን ማእክስዌል ስለ ልግስና ሲጽፉ ያነሱትን አንድ ታሪክ በማንሳት እናጠናቅቅታዋቂው ፈረንሳዊ ደራሲ ዶሚኒክ ላፔሪ ለሚጽፈው አዲስ መጽሐፍ ጥናት ለማድረግ ወደ ህንድ ጉዞ ያደርጋል። በእዚህ ጉዞ ለመጽሐፉ የሚያስፈልገውን ጥናት ቢያደርግም በልቡ የሚቃጠል አንዳች ሸክም ግን ከተመለከተው ነገር የተነሳ ይዞ ተመለሰ።
በድህነትና ጉስቁልና ያሉ ሰዎችን በተመለከተ ጊዜ ለእኒህ ሰዎች ሊደረግ ስለሚገባው ልገሳ ማውጠንጠን ጀመረ። እነርሱን ለመርዳትም የተግባር እርምጃ ጀመረ። ይህ ጉዞ የህይወቱን መስመር ስለቀየረው መደበኛ ጊዜ ውስጥ ከጽሑፍ ስራው በተጨማሪ ለልግስና የሚውል ሃብት ማሰባሰብ እና ልግስናውን ማድረግ የሚሉ ጉዳዮችን ጨመረ። የእዚህ ደራሲ የቢዝነስ ካርዱም የህንዳዊ ገጣሚን አባባል የያዘ ነው፤ አባባሉም እንዲህ ይላል ያልተሰጠ ነገር በሙሉ የጠፋ ነው።
አንተስ በእጅህ ላይ በማቆየትህ የተነሳ እያጠፋኸው ያለው ነገር ምንድን ነው? ዛሬ ሀገራችን ኢትዮጵያ ካለችበት ሁኔታ አንጻር በእጃችን ያለ እየጠፋ ያለውን ነገር ተመልክተን የልግሥናን አብዮት እንቀስቅስ። በመስጠት ውስጥ አብረን መዳን።
ነገሮች በተወሰኑ የሀገሪቱ መሪዎች ላይ ብቻ የምንተወው አይደለም። በጋራ ሁላችንም እጅ ለእጅ ተያይዘን የምንወጣው እንጂ። በድጋሚ በመስጠት ውስጥ አብረን እንዳን!
በአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 6/2014