በቅርቡ ሽሮ ሜዳ ከወንድሜ ልጅ ጋር ሆነን ለዘመድ ልጆች ደብተር ለመግዛት በየሱቆች ዞር ዞር እያልን ነበር። እኔ በየሱቁ እየገባሁ ደብተር እያገላበጥኩ ስመለከት ብዙ ጊዜ ወስደኩ፤ እሱም የሒሳብ መምህር ስለሆነ ለምዶበት ነው መሰለኝ ደብተር በትኩረት ያያል። እሱ ደብተሮቹን ገዝቶ መጣና የደብተሮችን ሽፋን እያየን እኛ ስንማር ከነበሩት ጋር ማነጻጸር ውስጥ ገባን።
የዋጋው ውድነት ውስጥ አልገባንም፤ የገበያ ሁኔታ ያስከተለው ነውና ለመውቀስም አያመችም። እኛን ያነጋገረን የደብተሮቹ ሽፋን ትምህርታዊ መረጃዎችን አለመያዙ ነው። ምናልባት በዚህ ዘመን የሚመረቱት ደብተሮች ሁሉ ላይሆኑ ይችላሉ፤ ዳሩ ግን እኛ ካየናቸው ቢያንስ ከአራት በላይ ሱቆች የበፊቱን ዓይነት ሽፋን ያለው ደብተር ማግኘት አልቻልንም። የፊቱ ዓይነት የደብተር ሽፋን በጣም አልፎ አልፎ ከሆነ የሚገኝ ልክ አይደለም ።
ሰሞኑ ትምህርት የተጀመርበት ነውና እስኪ በዚሁ እግረ መንገድ ስለደብተር ጀርባም እናውራ ብዬ ይህን ጉዳይ ማንሳቴ። ተማሪነቴን ሳስታውሰው፤ መምህሩ ስለጠቃሚ ነገር (ሁሉም ጠቃሚ ቢሆንም የተለየ ያልኩትን) ሲናገር መሃል ላይ ካለው ዋናው ገጽ ይልቅ ከጀርባ ባለው ገጽ ላይ ነበር የምጽፈው። እንዲያውም ፈተና ላይ እንኳን የሚመጡት ከጀርባ የጻፍኳቸው ናቸው።
ቀደም የተማርኩባቸውን ደብተሮች እያገለባጥኩ ሳይ አሁን ካሉት ደብተሮች ጋር ብዙ ልዩነት አየሁባቸው። ያለው ልዩነት ሁኔታውን እንድታዘብ አድርጎኛል። እንዳይገርማችሁ ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ የተማርኩበት ደብተሬ አሁን ድረስ አለ።
ደብተር በዋናነት የሚመረተው ተማሪን ታሳቢ አድርጎ ነው። ስለዚህ በደብተሩ ሽፋን ላይ የሚሰፍሩ ነገሮች ለተማሩ ትልቅ ፋይዳ አላቸው። ለምሳሌ ቀደም ሲል በነበሩ ደብተሮች ላይ ከፊት ለፊት ባለው ሽፋን በ2009 ዓ.ም በሞት ያጣናቸው የተረት አባት አባባ ተስፋዬ ምስል ይደረግበት ነበር። አባባ ተስፋዬ ልጆች ሁሉ ሊያውቋቸው የሚገባ አባት ናቸው። ልጆችን በተረት እያስተማሩ አንጸው ያሳደጉ። እንደ እርሳቸው ዓይነት ታላላቅ ሰዎች ያስፈልጉናል።
የሚገርመው ግን በዚያው ዓመት አካባቢ ቃና ቴሌቪዥን ገና አዲስ በነበረበት በቃና ቲቪ ላይ የሚታወቁት ዛራና ቻንዲራን የደብተር ሽፋን ላይ ማድረግ ተጀምሮ እንደነበር ሰምቻለሁ። የድራማውን ተወዳጅነት ማድነቅ ይቻል ይሆናል፤ ዳሩ ግን ኢትዮጵያ ውስጥ የደብተር ሽፋን የሚሆን ታዋቂ ሰው ጠፍቶ ነው የውጭ ዝነኞች የምናደርግ? በእርግጥ በፊትም የውጭ ተጫዋቾች ፎቶ ያለበት ደብተር ነበር።
የታዋቂ ሰዎችን ፎቶ እንተወውና ወደ ሳይንሳዊ መረጃዎች እንሂድ። በመማሪያ በደብተር ላይ ሳይንስን የሚያስተምር ምልክት መኖር አለበት። እኔ በደብተር የፊት ሽፋን ላይ የአበባ ምስል ሲደረግ አስታውሳለሁ። በእዚህም ላይ የአበባ ክፍሎች ቁልጭ ብለው ይታያሉ። ተማሪዎች ደግሞ የተክሎችን አረባብ የሚማሩት በአበባ ክፍሎች ነው። ስለዚህ የአበባ ምስል / የተለያዩ ክፍሎቹን በሚያስረዳ መልኩ/ በቀላሉ ሁሌም በሚያዩት በደብተራቸው ላይ ሊኖር ይገባል።
በደብተሮች ላይ በዋናነት ወደታዘብኩት ነገር ስሄድ ደግሞ በደብተሩ ሽፋን ላይ ያሉ መረጃዎችን ማጣቴ አሳሰበኝ። ተማሪዎች የሚማሩባቸውን ብዙ ደብተሮች አየሁ። በደብተሩ ሽፋን ላይ ምንም ዓይነት መረጃ የለም። ልሙጥ ነው። ለዚያውም በጣም ስስ የሆነና በቀላሉ የሚቀደድ። እርግጥ ነው ዋጋቸው ውድ የሆነ መለበድ እንዳያስፈልጋቸው ተደርገው የሚዘጋጁ ደብተሮች አሉ። አብዛኛው ማህበረሰብ የሚገዛቸው ደብተሮች ግን ሽፋናቸው ስስና መናኛ ነው።
የስስነቱ ነገር ዋና ትኩረቴ ባይሆንም እንኳን በተማሪ ደብተር ላይ ያሉ ሳይንሳዊ መረጃዎች ለምን ቀሩ? ምናልባት ዋናው ጉዳይ የሚጻፍባቸው መሆናቸው ሊመስለን ይችል ይሆናል፤ በደብተሩ ላይ ያሉ መረጃዎች ተራ ነገር መስለው ይታዩንም ይሆናል፤ ግን ተራ አይደሉም። እዚያ ላይ የሚወጡ መረጃዎች ታስቦባቸው የተዘጋጁና ጠቃሚዎች ናቸው።
መረጃዎቹ በተለይ ሒሳባዊ ለሆኑ ትምህርቶች በጣም ወሳኝ ናቸው። ብዙ ጊዜ የመለኪያ አሃዶች ያስፈልጋሉ። የክብደት፣ የርዝመት፣ የፈሳሽ፣ የጊዜ መለኪያዎች ከደብተር ጀርባ መገኘት ተማሪዎች መረጃዎቹን በቀላሉ ሁሌም እንዲያገኙዋቸው ያስችላል። ከአንዱ የመለኪያ አሃድ ወደ አንዱ ለመቀየር መረጃዎቹን የግድ መታወቅ ያስፈልጋል። ለምሳሌ ከኪሎሜትር ወደ ሜትር ወይም ከሜትር ወደ ኪሎ ሜትር መቀየር የሚያስፈልገው ቀመር ይኖራል። ይህን ለማወቅ አንድ ኪሎ ሜትር ስንት ሜትር እንደሆነ ማወቅ አለባቸው። ቀላል ምሳሌ ነው ያነሳሁት። በደብተር ጀርባ ላይ ከባድ ስሌት የሚጠይቁ ክፍልፋዮችም ስለሚቀመጡ በቀላሉ ለማወቅ ያግዛል።
በኬሚስትሪ ትምህርት ላይ አንድ የንጥረ ነገሮች ሰንጠረዥ አለ። ሰንጠረዡ በእያንዳንዱ ዓምድ ላይ የየራሳቸው ባህሪ ያላቸው ንጥረ ነገሮችን ይይዛል። በዚህ ውስጥ የንጥረ ነገሮች ክብደት፣ የስማቸው ውክል፣ አቶማዊ ቁጥራቸው መታወቅ አለበት። ይህን የያዘ ሰንጠረዥ በቀላሉ ደብተር ላይ መገኘት አለበት። መረጃው በመማሪያ መጽሐፍ ላይ ቢኖርም ደብተር ደግሞ ከመጽሐፍ ይቀላል፤ ሁልጊዜም ከተማሪው እጅ ላይ ይገኛል።
ከደብተር ጀርባ ላይ ያሉ መረጃዎች ሒሳባዊ ቀመሮች ብቻ አይደሉም። የባዮሎጂ(ስነ ሕይወት) ትምህርትን የሚያሳዩም አሉ። ለምሳሌ የደም ዝውውር ሥርዓትን ለማሳየት፤ የደም ቧንቧዎችን ስም፣ የልብ ክፍሎችን ስም፣ ሳንባን የያዘ ምስል ከደብተር ሽፋን ላይ እንደነበር አስታውሳለሁ። ተማሪዎች የእያንዳንዱን የአካል ክፍል ከነስማቸው በቀላሉ ደብተር ላይ ሲያገኙት ለማስታወስ ያግዛቸዋል።
ለመሆኑ ግን እነዚህን ነገሮች በደብተር ሽፋን ላይ ማድረግ ምኑ አስቸግሮ ይሆን የተተዉት? የደብተሩ ስስ መሆን ምናልባትም ያው የቅሸባ ጣጣ ያስከተለው ይሆናል። ምናልባት ግን የማላውቅው ሆኖ እንጂ እነዚያን ሳይንሳዊ መረጃዎች ለማስቀመጥ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ ሆኖም ይሆናል። መቼም የደብተሩ አምራች ከዕውቀት ገንዘብ ይበልጥበታል። ግን ገዢዎች ለምን ይህን ይገዛሉ? ታዲያ ያልተመረተውን ከየት ያመጡታል? ዋናው ጥያቄ ይህ ነው!
ጉዳዩን ለወላጅም ይሁን ለአምራቹ እንዲሁም ለሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ልተወውና በራሴ ትዝታ ነው የምሰናበታችሁ።
ያቺን ባለ 16 ቅጠል ደብተር ታውቋታላችሁ አይደል? የዛሬ ዋጋዋን ባላውቅም ‹‹የ50 ሳንቲም ደብተር›› እያልን ነበር የምንጠራት። ዛሬ እኮ 20 ብር ሆና ይሆናል (ሲጀመር አለች እንዴ ግን?) ይቺን ደብተር የማስታውሳት በተለይም ከ4ኛ ክፍል በታች ነው። ደብተሯም የአንድ የትምህርት ዓይነት ብቻ ሳይሆን ሁሉም ይጻፍባት ነበር። ለማባዛት የሂሳብ ስሌት ግልግል ነበረች። ከጀርባ በኩል ከ1 እስከ 12 ያሉ ቁጥሮች ብዜትን ይዛለች። ሲጀመር ያኔ ራሴ ማባዛት ሁሉ እችል ነበር። ዛሬ ግን ሻይ ጠጥቼ እንኳን ለማስላት ስልኬን ነው የማወጣው።
ግን አንድ ነገር ማለት እፈልጋለሁ። ያንን የብዜት ሰንጠረዥ ከደብተር ያፋቱበት ግን ለምን ይሆን? ምክንያታቸው ምንም ይሁን ምን ተቀባይነት የለውም። የሰንጠረዡ መኖር ለተማሪው የሚጨምረው እንጂ የሚያጎድለው የለም።
ምናልባት ዘመኑ የቴክኖሎጂ ነውና ተማሪዎች እነዚያን መረጃዎች በቀላሉ ከስልካቸው ላይ ያገኙ ይሆናል። ዳሩ ግን ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በታች ያሉ ተማሪዎች ስማርት ስልክ ከሚጠቀሙ በወረቀት ቢጠቀሙ የተሻለ ይሆናል። በዚያ ላይ ምን ያህል ወላጅ ለልጆቹ ስማርት ስልክ መግዛት ይችላል? በሌላ በኩል ከቴክሎኖጂ ጋር እንዲተዋወቁ ቢያግዝም፣ በልጅነቻቸው ሊያቦዝናቸውም ይችላል። በደብተር እስከተማሩ ድረስ ሳይንሳዊ መረጃዎች ቢኖሩ የተሻለ ነው።
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 6/2014