ኪነ ጥበብ በየዘመኑ የተለያየ ባህሪ ይላበሳል። ለዚህም ነው የሥነ ጽሑፍ ሰዎች ‹‹የዚህ ዘመንና የዚያ ዘመን ኪነ ጥበብ›› የሚሉት። በየመዘኑ የተለያየ ባህሪ እንዲኖረው ከሚያደርጉት ምክንያቶች መካከልም ኪነጥበቡ የተገኘበት ዘመን ወቅታዊና አስተዳደራዊ ሥርዓት ባህሪ ይጠቀሳሉ።
ለምሳሌ አስተዳደራዊ ሥርዓቱን ብንመለከት በንጉሳዊው እና ወታደራዊው ዘመን መንግስትን በግልጽ መተቸት አይቻልም ነበር፤ ይህም ከመንግስታቱ ባህሪ የመነጨ ነው። በዚህም ምክንያት ከያኒያኑ ሃሳባቸውን የሚገልጹት ቅኔ ለበስ በማድረግ ነበር።
በደርግ ጊዜ ይወጡ የነበሩ ዘፈኖች የአገር ፍቅርን ለመግለጽ በሴት ፍቅረኛ በመመሰል ነበር ይባላል፤ በዚያ ውስጥ ቅኔ ይኖረዋል። የተወዳጇን ሴት እናትና አባቶች በባለሥልጣናቱ በመመሰል ‹‹አስቸገሩኝ›› የሚለው መልዕክት ይተላለፋል።
በነገራችን ላይ እንዲህ አይነት አፈና ራሱ መንግስትን ነው የሚጎዳው፤ አፈና ሲበዛ ህዝቡም ትርጉም ፍለጋ ይሄዳል፤ በትክክል ለሴት ፍቅረኛ የተዘፈነን ለመንግስት የተዘፈነ አስመስለው ሊተረጉሙት ይችላሉ። መንግስትም ያንን በመፍራት ሥራው ሁሉ ዘፈን ማስተርጎም ሊሆን ነው። ሌላ አንድ ምሳሌ አይተን ወደ ዛሬው ሃሳብ እንግባ።
ነፍሳቸውን ይማረውና የማስታወቂያ ባለሙያው ጋሽ ውብሸት ወርቃለማሁ በአንድ ቃለ መጠይቅ ላይ ሲናገሩ እንደሰማሁት፤ ጋሽ ውብሸት በደርግ ጊዜ ታስረው ነበር፤ የታሰሩትም በሰሩት አንድ ማስታወቂያ መንግስት እንደፈለገው ተርጉሞት ነው። ማስታወቂያው የበረሮና ፀረ ተባይ ማስታወቂያ ሲሆን ፤በረሮ አታመልጭም ዘንድሮ ቢንቢ ከእንግዲህ የት ትገቢ
በሚሉ ስንኞች የቀረበ ነበር። ይህን የሰማው የወቅቱ መንግስት ጫና በዝቶበት ስለነበር ‹‹እኔን ለመንካት ነው›› ብሎ ተረጎመው፤ እንግዲህ በወቅቱ ማስታወቂያው መንግስትን ለመንካት ታስቦ ይሰራ አይሰራ እነርሱ ናቸው የሚያውቁት! እንደ ማስታወቂያ ግን አስቂኝ የሆነ ገላጭ ማስታወቂያ ነው። መንግስትን ለመንካት ባይሆን እንኳን የሚገለጸው በዚህ መንገድ ነው።
ለመሆኑ አሁን ያለንበት ወቅትስ በኪነ ጥበብ ስራዎች እንዴት እየተገለጸ ነው? ይህን ጥያቄ ለመመለስ ከመሞከሬ በፊት በመጀመሪያ አንድ የራሴን አስተውሎት ልግለጽ።
ኢህአዴግ ሲገባ የነበረውን ክስተት ስለማላውቀው ምንም አልልም። ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በኋላ ከአካባቢዬ ራቅ ብዬ በዩኒቨርሲቲ ቆይታየም በሥራ አጋጣሚም ባስተዋልኩት ግን ወጣቶች ስለአገር ጉዳይ አለማውራታቸውና አለመሳተፋቸው የጋዜጦችና መጽሔቶች ሁሉ መነጋገሪያ ነበር።
ይህ የወጣቶች የአገር ስሜት ማጣት የኪነ ጥበብ ዘርፉን የውደሳ ሳይሆን የወቀሳ፣ የእሮሮና የለቅሶ አድርጎታል። በኪነ ጥበብ መድረኮች ላይ የሚቀርቡት ሁሉ የመንግስትን አፋኝነትና የአገሪቱን መጎሳቆል የሚገልጹ ናቸው። በወቅቱ የነበሩ ወጣቶች ግጥም ማለት መንግስትን መውቀስ ማለት ብቻ ሊመስላቸው እስኪችል ደረስ ብሎ መውሰድ ይቻላል።
ከ2010ሩ ሀገራዊ ለውጥ ወዲህ ደግሞ ነገሮች ተቀይረዋል፤ ወጣቶች በአጠቃላይ ዜጎች ስለአገራቸው በግልጽ እየተናገሩ ናቸው። የፖለቲካ ኢኮኖሚው ሥርዓት ሲቀየር የኪነ ጥበቡ ይዘትና አቀራረብ እየተቀየረ እንደሚመጣ ከዚህ መረዳት ይቻላል።
ከዚያ በፊት በፖለቲካዊና መንግስታዊ መድረኮች የማይታወቁት ድምጻውያን ብቅ ብለው መሳተፍ ጀመረዋል። የኪነ ጥበብ ሥራዎች መንግስትን ከመውቀስ ወጥተው የሚያወድሱ ሆኑ። የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ከመሸማቀቅ ወጥተው ቤተመንግስትን ጨምሮ በየአደባባዩ ስራዎቻቸውን የሚያቀርቡበት ሁኔታ እየተፈጠረ መጥቷል። ይህም ሀገራዊ ወቅታዊ ሁኔታው የፈቀደው ነው።
አዎ፤ ከታሪክ እንደምንረዳውም ሀገራዊ ወቅታዊ ሁኔታ የኪነጥበቡን ሚና ይፈልጋል። የሀገር ሉአላዊነት በውጭ ወራሪዎች በተደፈረበት ወቅት፣ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግንባታ በተጀመረበት አካባቢ የወጡ የኪነጥበብ ስራዎችም ይህንኑ አቅንቅነዋል። የሀገር ሉአላዊነት ሲደፈር ወረራን ለመቀልበስ ህዝቡ እንዲነሳ ያደረጉ ዜማዎች እየተዘጋጁ ህዝብን አነሳስተዋል። ለእዚህም ዛሬም ድረስ የሚደመጡትን የእነ ጥላሁን ገሰሰ ፣ ማህሙድ አህመድ እና የሌሎች አርቲስቶችን ዜማዎች ይጠቀሳሉ።
በደርግ ወቅት የ77ቱን ድርቅ ተከትሎ ዓለም ህዝብን ከረሃብ ለመታደግ ላከናወነው ተግባር ምስጋና ለማቅረብ ‹‹ህዝብ ለሀዝብ›› በሚባለው የኪነጥበብ ቡድን ሳይጠቀስ የሚታለፍ አይደለም። የኪነጥበብ ባለሙያዎቹ ብቻ ሳይሆኑ ዜጎችም ዛሬም ድረስ በዚህ ቡድን ይቀርቡ የነበሩ የኪነጥበብ ስራዎችን በአድናቆት ሲገልጻቸው ይሰማል።
የሀገር ሉዓላዊነት በተደፈረበት በአሁኑ ወቅት ደግሞ ህዝቡ ለህልውና ዘመቻው እንዲነሳ፣ እንዲደግፍ ወጣቶች መከላከያን እንዲቀላቀሉ፣ ለማድረግ የሚያስችሉ ስራዎች በኪነጥበብ ዘርፉ ሲከናወኑ እያየን እያዳመጥን ነው። ኪነጥበቡ የጀግኖች አባቶችን ፣ የመከላከያ ሰራዊቱንና ሌሎች የጸጥታ ሃይሎች የጀግንነት ውሎ በማወደስ የሀገር ፍቅር ስሜት ይበልጥ እንዲቀጣጠል እያደረገ ነው።
የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች የህልውና ዘመቻው የህዝቡን የእያንዳንዱን ሙያተኛ ተሳትፎ እንደሚፈልግ በመረዳት ወዲያውኑ ነበር በሙያው የሀገር ህልውናን ለማስጠበቅ የተነሱት።
በዚህም መሰረት ባለሙያው ተሰባስቦ መክሮና ዘክሮ በቀደሙት የዘርፉ ስራዎች ብቻ ሳይሆን አዳዲስ ስራዎችን በማውጣት ጭምር ለሀገሩ ዘብ እንደሚቆም አረጋግጦ ነው ወደ ስራ የገባው።
እጃቸው ባሉት ዘፈኖችም ወዲያውኑ በትያትር ቤቶች፣ በተለያዩ አዳራሾች፣ የውትድርና ማሰልጠኛ ተቋማትና ጦር ግንባር ጭምር በመገኘት በኪነጥበብ ስራው ህዝብን ሰራዊቱን አነሳስቷል። ስለሀገር ፍቅር ፣ ስለጀግኖች ኢትዮጵያውያን ገድል በማቀንቀን የሰራዊቱ የጀግንነት ውሎ እንዲሰምር እየሰሩ ናቸው።
ባሉት ዜማዎች ብቻ ሳይወሰኑ ታዋቂ አርቲስቶች የተሳተፉበት አዲስ የሙዚቃ አልበምም አውጥተዋል። በብዙ ታዋቂ ከያኒያን ተዘጋጅቶ ለአዲስ ዓመት የተለቀቀው ‹‹ስለኢትዮጵያ›› የተሰኘው ይህ አልበም በሁለት ክፍል 28 ዘፈኖችን ይዟል።
የዜማ እና ሌሎች ቅንብራዊ ጉዳዮችን መስማት የሚቻለው በብሮድካስት መገናኛ ብዙኃን ነው። በህትመት (ጋዜጣ) ማሳየት የሚቻለው ግጥሙን ብቻ ነውና የተወሰኑትን መግቢያ ግጥሞች እዚህ እንጠቅሳለን።
በዚህ አልበም አርቲስት አለማየሁ እሸቴ፣ ፀጋዬ እሸቱ፣ ግርማ ተፈራ፣ ዘቢባ ግርማ እና ኪያ ካሳሁን እየተቀባበሉ ባቀረቡት ዘፈን ኢትዮጵያን እንድትወድቅ መመኘት ከንቱ ምኞች መሆኑን አስገንዝበዋል። እስቲ ግጥሙን እንመልከት።
ሲያምራቸው ይቀራል እንደ ጎመዧት
እንድትወድቅ ሲመኟት ስታድግ እያዩዋት
ለሚያውቃት ተልቃ ለማያውቃት ብታንስ
ልጆቿ ልብ ላይ ተነቅሶ የእሷ ስም
እኔ እያለሁላት ኢትዮጵያ አትፈርስም
እኔ እያለሁላት ኢትዮጵያ አትፈርስም
እኛ እያለንላት ኢትዮጵያ አትፈርስም (በጋራ)።
በደም ላቆሟት ለውርስ እርስቴ
ያውም ለኢትዮጵያ ለአንዲቷ እናቴ
ፈርሳ ምን ልሆን አጥቼ ህልሜን
በአገሬ ስም ላይ አኑሬ ስሜን
ኢትዮጵያ ናት ሀገሬ ቤቴ ትዳሬ
አትምጡብኝ በስሟ በስም በክብሬ
የሚያፈርሳት ይፈርሳል ነካሽ እጇ
ግን ኢትዮጵያ አትፈርስም እያለ ልጇ።
……. በማለት አገራዊ ስሜት የተንፀባረቀበት ውብ ዜማ በህብረት አዚመዋል።
በዚህ ዘፈን ውስጥ ያሉ ድምጻውያን በሥራዎቻቸው አንቱ የተባሉና ዘመን ተሻጋሪ ሥራዎችን የሰሩ ናቸው። አገሪቱ ካለችበት ወቅታዊ ውጥረት አንጻር ስለዚህኛው ሙዚቃ የውይይት መድረክ ተዘጋጅቶም ሆነ ከጋዜጦችና መጽሔቶች በባለሙያዎች ምንም ሲባል አልሰማንም። ነገር ግን ጠንካራ መልእክት የተላለፈበት ዘፈን ነው። ይህ ብቻም ሳይሆን የእነዚህ ድምጻውያን ሥራ መሆኑ በራሱ መልዕክቱ ይበልጥ ተደራሽ እንዲሆን አድርጎታል።
በ ‹‹ስለኢትዮጵያ›› የዘፈን አልበም ውስጥ የተሳተፉ ድምጻውያን ብዙ ናቸው። አልበሙ በአዲስ ዓመት ዋዜማ ጳጉሜን 5 ቀን 2013 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ነው የተመረቀው። በተለያዩ የብሄር ብሄረሰቦች ቋንቋዎች የተሰራ ነው። ይህ መሆኑ ሀገራዊውን ወቅታዊ መልእክት ለሁሉም ተደራሽ ለማድረግ ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል።
በአልበሙ ዙሪያ ከአልበሙ ዘፈኖች አብዛኞቹን ያቀናበረውን ካሙዙ ካሳን አነጋግሬው ነበር። ካሙዙ በወቅቱ እንደተናገረው፤ ለ2014 ዓ.ም አዲስ ዓመት ስጦታ ‹‹ስለኢትዮጵያ›› እና በኦሮምኛ ‹‹ቢያ ኮ›› የተሰኙት አልበሞች፤ የኢትዮጵያን ሰላምና አንድነት የማስጠበቅ አስፈላጊነት ወቅታዊ አጀንዳ መሆኑን ለማስገንዘብ የተዘጋጁ ናቸው።
አልበሞቹ ስለኢትዮጵያ ትልቅነት፣ ስለኢትዮጵያ ሰላምና አንድነት የሚያቀነቅኑ ናቸው። አልበሞቹ 28 ዘፈኖቹን የያዙ ሲሆን፤ ዘፈኖቹ በአማርኛ፣ በኦሮምኛ፣ በትግርኛ በወላይትኛ፣ በጉራጊኛ እና በሌሎች ብሄሮች የተዘፈኑ ናቸው።
‹‹አብዛኞቹን ሙዚቃዎች ያቀናበርኳቸው እኔ ነኝ›› ያለው ካሙዙ፤ አቤል ጳውሎስ፣ ጊልዶ ካሳ፣ ሚኪ ኃይሉ፣ አበጋዝ ክብረወርቅ እና ሌሎች አቀናባሪዎች እንደተሳተፉበት ተናግሯል። ከድምጻውያን መካከል ተሳትፎ ያደረጉትም፤ በቅርቡ ህይወቱ ያለፈው አለማየሁ እሸቴ፣ ፀጋዬ እሸቱ፣ ንዋይ ደበበ፣ አብነት አጎናፍር፣ ብሩክታዊት ጌታሁን (ቤቲ ጂ)፣ ስለሺ ደምሴ (ጋሼ አበራ ሞላ)፣አቡሽ ዘለቀ፣ አቤል ሙሉጌታ፣ አስጌ ዴንዳሾ እና ሌሎችም ናቸው።
አለማየሁ እሸቴ፣ ፀጋዬ እሸቱ፣ ግርማ ተፈራ፣ ዘቢባ ግርማ እና ኪያ ካሳሁን እየተቀባበሉ በጋራ የዘፈኑት ከፍ ሲል የጠቀስነው ‹‹እኛ እያለን›› የሚለው ነው። በጋራ ከተቀነቀኑት ዘፈኖች በተጨማሪ ደግሞ አቤል ሙሉጌታ እና አብነት አጎናፍር ለየብቻ የዘፈኑት አለ። ‹‹ሰንደቋን ብሎ›› የተሰኘው የአቤል ሙሉጌታ ዘፈን ግጥሙ የሚከተለው ነው።
ወጣ ሰንደቋን ብሎ
ደጀን ህዝብ አስከትሎ
ያልፋል ልክ እንደ ጥንቱ
ሳይሆን ፈሪ ለእናቱ
….. እያለ ይቀጥላል ።
ይህ ግጥም ኢትዮጵያ ዳር ድንበሯን የሚጠብቁ ጀግኖች ሞልተዋታል። ሀገሪቱ በወሬ አትፈርስም የሚል መልእከት የተላለፈበት ነው። ህልውናዋን የሚያስጠብቁ ጀግኖች በብዛት እንዳላትም ያመለክታል። የፈለገውን ያህል ልዩነት ቢኖራቸው በሀገር ጉዳይ አንድ መሆናቸውን ያስገነዝባል። ህልውናዋን የሚፈታተን ከመጣ ሆ ብለው የሚነሱ ልጆች ያላት እናት ሀገር ስለመሆኗ መልእክት ያስተላልፋል።
ግጥሙ በዜማ ለዚያውም በታዋቂ ድምጻውያን ዜማ ሲቀርብ የሚኖረው አቅም ምን ያህል ጠንካራ ሊሆን አንደሚችል መገመት ደግሞ አይከብድም።
ወደ አብነት አጎናፍር ሥራ ከመሄዳችን በፊት አንድ የአብነትን ገጠመኝ ልንገራችሁ። በሸገር ኤፍ ኤም 102.1 ‹‹የቅዳሜ ጨዋታ›› የተሰኘው ፕሮግራም ላይ ቀርቦ ከመዓዛ ብሩ ጋር ሲያወራ የሰማሁት ነው። ገጠመኝ ‹‹ለካ አያውቁንም›› ለሚለው ዘፈኑ መነሻ ሃሳብ ነበር።
አብነትና ሌሎች ጓደኞቹ ውጭ አገር (አገሪቷን ዘነጋኋት) ፖሊሶች ያስሯቸዋል። ፖሊሶቹ ‹‹ከየት አገር ናችሁ›› ብለው ሲጠይቋቸው እነ አብነት ‹‹ከኢትዮጵያ›› ይላሉ፤ ፖሊሶቹ ኢትዮጵያን ሊያውቋት አልቻሉም። እነ አብነት የኢትዮጵያን ታሪካዊ ቅርሶች ቢጠቅሱ፣ እነ አበበ ቢቂላንና ሃይሌ ገብረሥላሴን ቢጠቅሱ ፖሊሶቹ ሊያውቋት አልቻሉም። አብነት በዚያ ክስተት ተቆጭቶም ‹‹ለካ አያውቁንም›› የሚለውን ዘፈን ዘፈነ።
አብነት በአገራችን ባለው አሁናዊ ሁኔታ ደግሞ ‹‹አለን አለን›› የሚለውን ዘፈን አቅርቦልናል።
አለሁ እኔም ወታደር ነኝ
ባለኝ ሙሉ አቅሜ
አለሁ እኔም ለኢትዮጵያ በተጠንቀቅ ቆሜ
በዕውቀት በሀብት በደሜ
ለእናት አገር እማማ
ለሰንደቅ ዓላማ
ይከፈላል ሁሉም ነገር በአንቺ ለመጣማ
አለን አለን ልጆችሽ
አለን እኛም ለኢትዮጵያ ወታደር ነን
ታላቅ እንደነበርሽ ታላቅ ሆነሽ ሳናይ
አንተኛም ልጆችሽ ለባዕድ አገር ሸንጋይ።….
በግጥሙ ከገለጻቸው መካከል ሀገሪቱ የገጠማትን ፈተና እንደምታልፈው፣ ትንሳኤዋም መቅረቡን አመልክቷል። ልጆቿ ሀገራቸውን በሚያስፈልገው ሁሉ ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸውንም ጠቅሶ፣ ታላቅ ሆና ለዘላለሙ እንደምትኖር ለባእዳንና ተላላኪያቸው የሚንበረከክ እንደማይኖር አስገንዝቦበታል።
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 4/2014