ጎበዝ ዘንድሮ የሚሰማው ሁሉ አጃይብ ያሰኛል፡፡ የዓለምን ሰላምና ጸጥታ ላስጠብቅ ተፈጥሪያለሁ የሚለው ተቋም የኢትዮጵያን ጸጥታና ሰላም ፈፅሞ የሚፈልገው አልመሰለም፡፡ ተቋሙ ለኢትዮጵያ ሰላም ያልቆመ ስለመሆኑ በርካታ መረጃዎችን መጥቀስ ቢቻልም፣ በቅርቡ የሆነው ደግሞ ዓላማው ግልጽ መሆኑን በሚገባ ያመለክታል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት የሀገሪቱን ሉዓላዊነት በሚፃረር መልኩ በህገ ወጥ ስራ ተሰማርተው በተገኙ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተቋማት ሰባት ሃላፊዎች ላይ የወሰደውን እርምጃ ተከትሎ ምክር ቤቱ በቅርቡ ስብሰባ የተቀመጠበት ሁኔታም ይህንኑ ያመለክታል፡፡
ሽብርተኛው ትህነግ በመቶዎች የሚቆጠሩ እና ከዚያም በላይ ዜጎችን በተለያዩ አካባቢዎች ላይ በተደጋጋሚ በግፍ መጨፍጨፉን እየሰማ በቂ መረጃ እያለውም / እንኳን እሱ ስንትና ስንት ጆሮና አይን ያለው ሌላውም ይህ መረጃ ፈጥኖ ይደርሰዋል/ አንድ ቀን እንኳን ድርጊቱን በተገቢው መጠንና ልክ ሲገልጽና ሲያወግዝ አልታየም፤ አልተሰማም፡፡
ከዚህ ይልቅ ኢትዮጵያ ከአሸባሪው ቡድን ጋር ተገቢ ያልሆነ ግንኙነት እንደነበራቸው በማስታወቅና በማሳሰብ አልማር በማለታቸው ከአገሬ ይውጡልኝ ባለቻቸው የድርጅቱ የተለያዩ ተቋማት ሃላፊዎች ላይ መንግስት እርምጃ ለምን ወሰደ ብሎ እየከሰሰ ነው፡፡ ምን አድርገው ነው? ሳይል ፍርደ ገምድልነቱን በሚያሳይ መልኩ ኢትዮጵያ የወሰደችው እርምጃ ልክ አይደለም ብሎናል፡፡
በተለይ የድርጅቱ ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ኢትዮጵያን ካላመስኩ፣ ሀገሪቱን ካላፈረስኩ እያለ ከውጭ ባዕዳን ሃይሎች ጋር በማበር ጦርነት የከፈተው ህወሓት በዜጎች ላይ ግፍ የተሞላበት ጭፍጨፋ ሲፈጸም ከድርጊትህ ተቆጠብ የሚል ጠንከር ያለ ውግዘት ሳያሰሙ ሰራተኞቼ እንዲባረሩ መወሰኑ አስደንግጦኛል ብለዋል።
ከዚህም ከዜጎች እልቂትና ከአገራችን ህልውና መደፈር ይልቅ የእሳቸው ህገ ወጥ ሰራተኞች ሥርዓት ያዙ መባል እንደሚያስደነግጣቸው ተረድተናል፡፡
ተቋሙ እያከናወናቸው የሚገኙ ተግባሮችን ቆም ብሎ የተመለከተ ምን እየሰራ ነው ብሎ እንዲጠይቅ ያደርገዋል፡፡ ዓላማውን እየፈጸመ ነው ወይስ የሌሎች ዓላማ ማስፈጸሚያ እየሆነ ነው? የሚል ጥያቄ እንዲያነሳ ያደርገዋል፡፡
እኛ ሃያላን ነን ለዓለም ሰላም እንሰራለን እያሉ በዓለም ላይ የሚያሴሩትን ፣ ሀገር የሚያፈርሱትን፣ አፍርሰው ሲያበቁም በስህተት ነው የተደረገው የሚሉትን መንግስታት አንድም ቀን ልክ አይደላችሁም፤ ታረሙ የማይለው ይህ ተቋም፣ በዓለም ሊፈታቸው የሚገቡ በርካታ ችግሮች እያሉ ኢትዮጵያ እየፈታቻቸው ባሉ ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ እየገባ ለመፈትፈት ደጋግሞ ስብሰባ መጥራቱ ተገቢ አይደለም፤ ያስገርማልም፡፡
አሁን ማን ይሙት ከድርጅቱ ሰራተኞች መባረርና ትህነግ እርዳታ የሚያጓጉዙ የዓለም ምግብ ፕሮግራም በመቶዎች የሚቆጠሩ ከባድ ተሽከርካሪዎችን ወደ ትግራይ አላስገባም ብሎ ለቀናት ሲያግት ምን እርምጃ ወሰደ? ተስከርካሪዎቹ ከትግራይ ተመልሰው እርዳታ እንዳይጭኑ አግቶ ሲያቆይ ምን እርምጃ ወሰደ? ነዳጃቸውን ሙጥጥ አርጎ ጨርሶ ሲገትራቸው ምን እርምጃ ወሰደ? ለአፍታም መቆም የማይገባቸው እርዳታ የሚያደርሱ ተሽከርካሪዎችን ላልተገባ ተግባር ሲጠቀም ፣ ስራቸውን ሲያስተጓጉል ስሙን አንዳንድ መገናኛ ብዙሃን ሲጠቁሙ መቼ ለእርምጃ ተነሳ?
አስሬ ስብሰባ የሚያስጠራው ጉዳይ ይህ ነበር። ማንን ታሸንፋለህ ቢሉት ሚስቴን እንዳለው ሞኝ አሸባሪውን መጠየቅ ሲገባው አሸባሪውን አላላውስ በማለት የምእራባውያኑ ዓላማ እንዳይሳካ እያደረገ ያለውን የኢትዮጵያ መንግስት እየከሰሰ ነው፡፡
ለዓለም ሰላም መጠበቅ በእውነት የቆሙት ወዳጅ ሀገራት ባይኖሩ ኖሮ የድርጅቱ የምእራባውያን መጨዋቻመሆን በሀገራችን ላይ ብዙ ፈተናዎችን ያስከትል ነበር፡፡ ስብሰባ ስንቴ እንደተጠራ ስንቴ ያለስምምነት እንደተበተነ ሲታሰብ የእነዚህ ወዳጅ ሀገሮች ሚና ከፍተኛ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡ በወዳጅ አገራት በኩል ተቋሙ መሳሳቱ በደንብ እየተነገረውና በማይመለከተው ጉዳይ ውስጥ እየገባ መሆኑም እየተገለጸለት ይገኛል፡፡
የኢትዮጵያ ወዳጅ አገራት በተመድ እየተነሱ ያሉ ጉዳዮች ፈጽሞ በምክር ቤቱ ሊነሱ የማይገባቸው መሆናቸውን እየገለጹ ናቸው፤ የተቋሙ እንዳልሆኑም ጭምር እየጠቆሙ ይገኛሉ፤ ተቋሙ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚፃረሩ ተግባሮችን እየተመለከተና በውስጥ ጉዳይዋ ጣልቃ እየገባ ስለመሆኑም እየተናገሩ ናቸው። እነሱም እያሳሰቡ የኢትዮጵያ መንግስትም ማብራሪያ እየተሰጠ ባለበት ሁኔታ ድርጅቱ ስብሰባ በተደጋጋሚ መቀመጥ አልሰለቸው ብሏል፡፡ ማን ያውቃል ዛሬም በሆነ ጉዳይ ሊሰበስብን ይችላል፤ እሱ ምን ተዳው፤ ምእራባውያኑ አጀንዳ ይስጡት እንጂ፡፡
ምእራባውያኑ እንደ ልብ ሲዘውሩት አይባንንም። ተራ በተራ ኢትዮጵያን አጀንዳ እያደረጉ ስብሰባ ሲያስጠሩት ከመታዘዝ ውጪ በእዚህና መሰል ጉዳዮች በተደጋጋሚ ስብሰባ ጠርተን ያለውጤት ተበትነናል፤ አሁንም አልጠራም ማለት ሲገባው በኢትዮጵያ ላይ ያልተገባ ክስ በተሰነዘረ ቁጥር መሰብሰቡን የእለት ተእለት ስራው አርጎታል፡፡ በርካታ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች በሞሉበት ዓለም በኢትዮጵያ ጉዳይ በአጭር ጊዜ ውስጥ አስሬ መሰብሰቡም ይህንኑ ያመለክታል፡፡
ድርጅቱ ጸጥታችንን በሚያመጣልን መልኩ የእኛን ጉዳይ አለማየቱ ያስገርማል፡፡ በኢትዮጵያ ጉዳይ ኑ እንምከር እያለ በተደጋጋሚ የሚሰበሰብባቸው ርዕሰ ጉዳዮች ለእውነትና ፍትህ የቆሙ የተቋሙ አባል አገራት “ምክር ቤቱ ምን ነካው እስከማለት ደርሰዋል፡፡ ድርጊቱን መላልሶ ለተመለከተው በእርግጥም ደግሞ ደጋግሞ ያስገርማል፡፡ ጸጥታ አደፍራሹን ማውገዝ፣ ፀጥታን የሚያሰፍን መፍትሄ ማቅረብ ካልቻለ ምንአለበት ጸጥ ቢል፡፡
በጸጥታው ምክር ቤት ውስጥ ከዚህ በፊት እንወያይበት ተብሎ የቀረበው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ጉዳይ ነበር፡፡ የልማት ጉዳይ ፤ ምክር ቤቱን ፈጽሞ የማይመለከት አጀንዳ፡፡ የኢትዮጵያ የመልማት ውጥን እንጂ አንዳችም አካባቢያዊ ስጋት ሊፈጥር የማይችል ጉዳይ ነው፡፡ ምክር ቤቱ ከተቋቋመበት ዓላማ ውጪ ለመጀመሪያ ጊዜ ሊያየው የቀረበው ጉዳይ ይህ ነበር፡፡
ከዚህ በፊት በተቋሙ አሰራርና ሃላፊነት መሰረት ተደርጎ በማያውቅ ሁኔታ በምክር ቤቱ አጀንዳ ሆነው የቀረቡት ኢትዮጵያን የሚመለከቱ ጉዳዮች ዓለምአቀፉ ተቋም መሳሳቱንና ተገቢ ያልሆነ አካሄድ እየተከተለ መሆኑን በግልጽ የሚያሳዩ ናቸው፡፡ መልማታችሁ የጸጥታ መደፍረስ ያስከትላል ብሎ ሰብስቦ ጉዳዩ በአንተ የሚታይ አይደለም የተባለው ይህ ተቋም፣ ዛሬም ሉዓዊነትን በተመለከቱ የውስጥ ጉዳዮቻችን ላይ እኔ ልወስንላችሁ እያለ ይገኛል፡፡
በእርግጥ ለዓለም እውነተኛ ፍትህና ዘላቂ ሰላም ምዕራባውያንን ሳይሆን ዓለምን ብሎ የሚሰራ እውነትን ብሎ ለሰው ልጆች ፍትህና ለእውነተኛ ነፃነት የሚሰራ ዓለምአቀፍ ተቋም ለዓለማችን ያስፈልጋል ፡፡ እርግጥ ነው ለዓለም ፍትህ መከበር፣ ለሰው ልጆች እኩልነትና ነፃነት መጠበቅ፣ ዓለምአቀፍ ተቋማት ሊኖሩ ይገባል፡፡ ያኔ የእውነት ሰላም በምድራችን ላይ ይሰፍናና ትክክለኛ ፍትህም ይነግሳል፡፡
ከዚህ ውጪ ግን የዓለም ዳኛ ነኝ ያለ ተቋም ዳኝነቱ በተግባር ካልታየ በየትኛው የእውነት ሚዛን ሊሰፈር ይችላል? ግጭትን የሚያባብሱ፣ በአገራት ሉዓላዊነት ላይ ጣልቃ በመግባት ያልተገባ ስራ የሚያከናውኑና ከሚጠበቅባቸው ስራና ሃላፊነት ውጪ ስውር ተልዕኮ የሚፈጽሙ፣ አንዱን ሀገር ጎድተው ምዕራባውያንን የሚጠቅሙ ዓለምአቀፍ ተቋማትን እንዴት ለዓለም የቆሙ ልንላቸውስ እንችላለን? ጸጥታችንን ያልወደደው የጸጥታው ምክር ቤትም ብዙ አነጋገረን፡፡ አበቃሁ፤ ቸር ያሰማን፡፡
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 3/2014