ፋሽን በፋሽንነቱ ተለምዶ ይዘወተር ዘንድ መነሻ የሆኑ ትልልቅ ምክንያች አሉት። አንድ ፋሽን መቼና የት ተፈጠረ? እንዴትስ ተስፋፋ የሚሉትን ጥያቄዎች ስንመረምር በዋናነት ከምናገኛቸው መሰረታዊ ጉዳዮች መካከል ፋሽኑ የተፈጠረበት ዘመን ማህበረሰብ አስተሳሰብ፣ ባህል፣ ቴክኖሎጂ፣ የማህበረሰቡ ወይም ቡድኑ ምርጫና የአየር ሁኔታ የሚሉት ዋንኞቹ ነው።
ወቅትን እየጠበቁ ሽክ ማለት፤ እንደ አየሩ ጠባይ ለብሶ ማጌጥና መዘነጥ ዛሬ ላይ እጅጉን ተለምዷል። የክረምት ወቅትን ደረብረብ አድርገን ብርዱን የተከላከልንበት ወፍራም ገበር ያለውን ሙቀትን የሚጠብቅ ልብስ ክረምቱ አልፎ የፀደይ ወቅት ብቅ ሲል መቀየር ያስፈልገን ይሆናል። ሙቀትን የሚቋቋም ለብሰንም የሚያዘንጠን ቀለል ያለ ልብስ ከቁም ሳጥናችን አውጥተን፣ አልያም ደግሞ ከልብስ መሸጫዎች የሚሆነንን መርጠን ገዝተን እንለብሳለን። ወቅቱ መሸጋገሪያ ነውና ለቀጣዩ በጋ ወቅት የሚዘወተሩ አልባሳት ማየት ወደድን።
በተለይም ቦታ፣ ጊዜና የአየር ሁኔታ መለዋወጫ ወቅት ለፋሽን አልባሳት ዕውን መሆን ወሳኝ ቅድመ ሁኔታዎች ናቸው። የመጀመሪያው በምን አይነት ቦታ ላይ ይለበሳል የሚለው ሲሆን ዘወትር፣ የበዓል ቀን አልያም ሁነቶች መሰረት ሲያደርግ በምን አይነት ጊዜና ወቅት የሚለው ደግሞ ቀን፣ ማታ፣ ፀደይ፣ በጋ ክረምት የመሳሰሉት እንደ አየር ንብረቱና ወቅቱ የሚለበሱትን ልንጠቅስ እንችላለን። ፋሽንም እነዚህ መሰረት አድርጎ የማህበረሰቡ ባህልና እምነት ወይም ልማድ መሰረት ባደረገ መልኩ ይዘወተራል።
እንደ ዘርፉ ባለሙያዎች አስተያየት ማህበረሰብ በፋሽንነት ተላምዶ የሚያዘወትረውና በተደጋጋሚ የሚለብሰው ከላይ የተጠቀሱትን ቅድመ ሁኔታዎች መሰረት ያደረገ ነው።
ዲዛይነር ፅጌረዳ የደሴ ወርቅ ከሰባት ዓመት በላይ በፋሽን ዲዛይኒግ ሙያ ስትሰራ ቆይታለች። ባለሙያዋ ከአየር ንብረት ጋር የሚሄድ ሲለብሱት እና ሲያጌጡበት ከሰውነት ቅርፅና የአለባበስ ምርጫ ጋር የሚሄድ ፋሽን መከተል የሰዎች ተለምዷዊ ተግባር እየሆነ መምጣቱን ታስረዳለች። ማህበረሰባችን ለፋሽን ያለው ምልከታ እያደገ መሆኑን የምታስረዳው ዲዛይነር ጽጌረዳ፣ አቅሙ በፈቀደ መልኩ ወቅቱን እና የአየር ንብረቱን ያገናዘበ አልባሳት በተለይም በከተሜው ዘንድ ተለምዷል ነው የምትለው።
ከወቅቱ የአየር ንብረት ጋር ከመስማማቱም ባሻገር በብዙዎች ተመርጦ የሚለበስና የሚዘወተር አለባባስ ፋሽን ሆኖ በወቅቱ ገኖ እንዲወጣ የሚደርገው ግን አልባሳቱን በሚለብሰው ግለሰብ ይወሰናል። ልብሱ በጥሩ ዲዛይነር ተሰርቶ ከለባሹ ጋር በትክክል ከተሳካ ወይም ከገጠመ ልብሱ በሌሎች እንዲወደድና በብዙዎች እንዲለበስ ምክንያት እንደሚሆን ባለሙያዋ ታስረዳለች።
በበጋ ወቅት በአብዛኛው ቀለል ያሉ፣ ሙቀትን ሊቋቋሙ የሚችሉ፣ በቀለማቸው ፈካ ያሉና ከሰውነት አቋምና ቅርፅ ጋር የሚስተካከሉ አልባሳት በብዙዎች ይዘወተራሉ። ወንዶች ሙቀትን ከሚቋቋሙ ጨርቆች የተሰሩ ሱሪዎች፣ ካናቴራና ሸሚዝ መልበስና “ፍላት” ጫማ ሲያዘወትሩ በሴቶች ደግሞ ቀለል ያሉ ቀሚሶች ሱሪዎችና ቦዲዎች ይዘወተራል።
በእርግጥ እንደ ሰው ፍላጎትና የአለባበስ ምርጫ ቢለያይም ወቅቱን ባገናዘበ መልኩ ለመዋብ ሁሉም የበኩሉን ጥረት ያደርጋል። ከወቅቱ ጋር የሚሄዱ አልባሳት መልበስ አንድም በምርጫ ሲሆን ሌላኛው ጉዳይ ደግሞ ተፈጥሮ በራስዋ ታስገድዳለች። የሞቀው ሙቀቱን ሊከላከልለት የሚችል ልብስ የበረደው ደግ ሰውነቱ በብርድ እንዳይጎዳና ስሜቱ እንዳይረበሽ የሚያስችለውን ልብስ ለመልበስ ይዳዳል። ያለፈው ክረምት ላይ የነበረው አለባበስ ተቀይሮ በዚህ በበጋ ወቅት ቀለል ያሉ ልብሶች የሚዘወተርበት ዋንኛ ምክንያትም የአየር ሁኔታ ለውጡ የሚያመጣው ተፅዕኖ ነው።
የልብስ ነጋዴው የደንበኞችን ፍላጎት ያማከለና ወቅቱን የጠበቀ ልብስ ለተጠቃሚዎች ማቅረብም የወቅቱ ትኩረታቸው ሆኗል። በመዲናችን በተለያዩ አካባቢዎች ባሉ የተዘጋጁ ልብሶች መሸጫ ሱቆች ውስጥ ለወቅቱ የሚሆኑ አልባሳት ማየት እየተለመደ መጥቷል። ለሽያጭ የተዘጋጁ ልብሶች በየመስቀያዎቻቸው ለደንበኞች ምርጫ ምቹ እንዲሆኑ በግልፅ ተደርድረዋል።
እንደ ማህበረሰብ ፋሽንን ከመከተል ባለፈ ወቅቱን ያገናዘበ ከአየር ንብረቱ ጋር የሚስማሙ አልባሳትን እናዘወትር ይሆን? ለዚህ ምላሽ ለማግኘት ይረዳን ዘንድ የፋሽን ዲዛይን ባለሙያዎችና ተጠቃሚዎችን አነጋግረናል። ክረምት ላይ ይለበሱ የነበሩ አልባሳት በዚህ ፀደይ ወቅት ለመቀየር የአየር ንብረቱ ማስገደዱ አይቀርም። ሜክሲኮ አካባቢ ደብረ ወርቅ ህንፃ ጎን በተርታ ተሰልፈው የተዘጋጀ ልብስ ለደንበኞቻቸው የሚያቀርቡ ሱቆች ጉራ ብለናል።
ካሳሁን ግርማ በሱቁ ውስጥ ደንበኞች ሲያስተናግድ አግኝተን ፋታ ሲያገኝ አወራነው። በደንበኞቹ በአብዛኛው የወቅቱን የአየር ፀባይ ያማከሉ ልብሶች እንደሚታዘዝና እሱም ከጅምላ አከፋፋዮች ልብሶችን ሲያዝ በደንበኞቹ ፍላጎት መሆኑን ይናገራል። በዚህ በደንበኞቹ በአብዛኛው የሚመረጡ ልብሶችም ሸሚዞች፣ ካናቴራና ቀለል ያሉና ሙቀትን የሚቋቋሙ ጃኬቶች እንደሆኑ ይናገራል። ዋጋቸውም ቢሆን ተፈላጊነታቸው የመጨመሩን ያህል በፊት ከነበረው መጠነኛ ለውጥ እንዳላቸው ያስረዳል።
መሰለ ኤልያስና ጓደኛው ሳምሶን ገብረህይወት ልብስ ሲገዙ አግኝቼ አወራኋቸው። ለመጪው የበጋ ወቅት የሚሆኑ ልብሶች ለመግዛት ከጓደኛው ጋር እዚያ እንደተገኙ የገለፀልኝ መሰለ፤ ክረምት ላይ ይለብሳቸው የነበሩ ጃኬቶች አሁን ላይ ሙቀቱ ወደመጀመሩ ስለሆነ በሌሎች ቀለል ያሉ አልባሳት መቀየር እንደፈለገ ይናገራል። አቅሙ ባገናዘበ መልኩ ወቅታዊ የሆኑ አልባሳት መልበስ እንደሚያዘወትር ይገልጻል።
በእርግጥ ማህበረሰባችን በተለያየ ጊዜ የራሱን አስተሳሰብና ባህላዊ ገጽታ የሚያንፀባርቁ አልባሳት ፋሽን አድርጎ ሲከተል ይታያል። ወጣት ሳምሶን የመግዛት አቅም ካልወሰነው በቀር፤ ወቅታዊና ከአየር ንብረቱ ጋር የሚሄድ ለሰውነት ምቹ የሆነ ልብስ የመልበስ ፍላጎት እንዳለው ይገልፃል።
ዲዛይነር ፅጌረዳ ወቅቱን የጠበቁ አልባሳት በማህበረሰባችን ዘንድ እየተለመዱ መምጣታቸውን ትናገራለች። የማህበረሰቡ የመግዛት አቅም በአልባሳቱና ፋሽን መከተሉ ላይ የራሱ የሆነ ተፅዕኖ እንደሚፈጥር የእሷም እምነት ነው። ፋሽንና ወቅታዊ የአለባበስ ልምዶች አሁን ላይ እየተለመዱ እንደሆነ ጠቅሳ ይህም ማህበረሰቡ የፋሽን ተከታይ እየሆነ መምጣቱ እንደሚያላክትም ትገልፃለች። ለዚህም ዘርፉ ያለውን ዕድገትና ለውጥ በማሳያነት ትጠቅሳለች። ለእዚህም እስዋና ባልደረቦቿ ከደንበኞቻቸው የሚታዘዙትን ወቅታዊ አልባሳትና በየሁነቱ የሚመለከቱት አለባበስ በማሳያነት ታነሳለች።
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 1/2014