አዲስ አበባ አብነት አካባቢ ነው ተወልዳ ያደገችው። መጀመሪያ ፈለገ ህይወት በተባለው ትምህርት ቤት ቀጥሎም ባልቻ አባነፍሶና ሽመልሽ ሀብቴ በሚባሉ ትምህርት ቤቶች ከልጅነት ጀምሮ የቀለም ትምህርት የተከታተለችባቸውና ውቡ የልጅነት ጊዜዋን ያሳለፈችባቸው ትምህርት ቤቶች ናቸው። ልጅ ሆና ጨዋታና ሳቅ ያለበት መዋያዋ ሙዚቃና የኪነጥበብ ጉዳዮች የሚዘወተሩበት ስፍራ ነበር።
ጠንካራና ታታሪ እናቷን የንግድ ስራ ማገዝ ደግሞ ከትምህርትና ከምትወደው ጨዋታ ውጪ ስትሆን መገኛዋ ነበር። ስራ ላይ ሆና ሙዚቃ ከሰማች የሚያስቆማት ማንም አልነበረም። ጥልቅ የሆነው የሙዚቃ ፍቅርዋን ባገኘችው አጋጣሚ ሁሉ ለመወጣት ስትሞክርና ስታዜም መታየቷ የተለመደ ነበር። መድረክ ላይ ተዋንያን ስታይና የትወና ብቃታቸውን ስትመለከት ተዋናይ የመሆን ፍላጎት ውስጧ ያድርባታል።
አባቷ ምንአለ ሸዋ ብለው ይጠርዋት ነበር። በኋላ ላይ በቤተሰብና በአካባቢዋ ይዘወተር የነበረው ስሟ ጎልቶ ወጥቶ ምንአሉሽ በሚለው ታወቀች፤ ድምፃዊት ምናሉሽ ረታ። በዛሬው የዝነኞች ገፅ አምዳችን ከዚህች ታዋቂና ዝነኛ ድምፃዊት ጋር ካደረግነው ቆይታ ያጠናከርነውን ፅሁፍ ይዘን አቅርበናል። መልካም ንባብ።
ጉዞ ወደ ሙዚቃ
በየአጋጣሚው ስታዜም የሰሙ ሰዎች የድምፅዋ ቅላፄ እጅግ በጣም ያማረ መሆን ደጋግመው ይነግሯታል። ትምህርት ቤት ሆና አንድ ጌታቸው የሚባል ክራር ላይ ጎበዝ የነበር የሚዚቃ ሰው በክራር እያጀባት የአርቲስት አሰፉ ደባልቄን ሙዚቃ ስታዜም የተመለከቱ ሰዎች ሙዚቀኛ መሆን እንደምትችል እየነገሩ አበረታቷት። እሷም ከዚያን ቀን በኋላ ከትወናው ይልቅ ሙዚቀኛ መሆንን አሰበችና ወደዚያ የሚያቀርባትን አጋጣሚ መጠበቅ ጀመረች።
አካባቢዋ ላይ በሚሰናዱ ልዩ ልዩ ዝግጅቶችና ቀበሌ ውስጥ በሚሰናዱ የሙዚቃ መርሀ ግብሮች ላይ በመሳተፍ በአካባቢያዊ ታዋቂነትና ተወዳጅነት በማትረፍ ቀስ በቀስም ወደ ሌላ ምዕራፍ መሸጋገር ጀመረች። ከአንዲት የትምህርት ቤት ጓደኛዋ እህት ጋር በመሆን የሙዚቃ ባለሙያዎች ቅጥር ውድድር ላይ ለመሳተፍ ፖሊስ ሙዚቃ ክፍል ተያይዘው ይሄዳሉ። ምናሉሽ ከአንዲት ሌላ ድምፃዊት ጋር ከብዙ ተወዳዳሪዎች መሀል አሸናፊ ሆነው እዚያው መዝፈንና በተለያየ ጊዜ የሌሎች ሙዚቃዎችን መድረክ ላይ ማቅረብ ቀጠሉ።
ትውውቅ ከህዝብ ጋር
ወደ ሙዚቃው በሚገባ ለመግባትና ወደ ህዝብ የራሷን ስራ ይዛ ለመቅረብ ሁሌም ፍላጎትና ጥረት ስታደርግ የቆየችው ምንአሉሽ፤ የዛሬ ባለቤትዋ የዛኔ ፍቅረኛዋ አሸብር በላይ (እሱም ድምፃዊ ነው ። “እኔ ነኝ ያለ” በሚል የሙዚቃ ስራው እና በሌሎች ስራዎቹ ይታወቃል) ከእርሷ ርቆ መሄዱ የፈጠረባትን ስሜት በግጥም ገልፃ ወደ ሙዚቃ ባማረ ዜማ አቀረበችው። ወደ ህዝብ ለመጀመሪያ ጊዜ ይዛ የቀረበችው “መራቅህን አልወድም” የተሰኘ ይህ ነጠላ ዜማዋ እጅጉን ተወዳጅነት አትርፎ ብዙዎች አደመጡላት። በተለይም በወቅቱ በቴሌቪዥን ጣቢያዎች ተደጋግሞ ይቀርብም ነበር። በዚህ ነጠላ ዜማ በህዝብ አድናቆትና እውቅናን ማትረፍ ቻለች።
ከዚያም ቁጥራቸው በርካታ የሆኑ በህብረት የተሰሩ አገራዊ ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ያጠነጠኑ ዜማዎች ላይ ከሌሎች ጋር በመካፈል እና ወደ ህዝብ በማቅረብ ይበልጥ ተወዳጅነትን ተቀዳጀች። ከህብረት ዜማ ከስራዎችዋ መሃል ለመጥቀስ እንሞክር፡-
ጀምረናል ጉዞ ጀምረና …ጀምረናል ጉዞ ጀምረናል
ወደኋላ ማን ይመልሰናል
ከእንግዲህ ማን ያስቆመናል …. ጀምረናል ጉዞ ጀምረናል…
በማለት የታላቁ የህዳሴ ግድባችን ስራ ጅማሮ ሂደት በኢትዮጵያዊያን ቆራጥነት የሚሳካ ወደፊትን ኢትዮጵያን የሚያራምድ መሆኑን አብረዋት ከሚያቀነቅኑ ጋር አውጃለች።
በማህበራዊ ጉዳይ ላይም በተለይ የኤች አይ ቪ ኤድስ እጅጉን በተስፋፋበትና ማህበራዊ ቀውስ በነገሰበት ወቅት ላይ ወጣቱ እንዲጠነቀቅ ከበሽታው እራሱን ይጠብቅ ዘንድ ከሌሎች ድምፃዊያን ጋር አብራ በመሆን ያዜመችው የህብረት ሙዚቃ ዛሬ ድረስ አይረሳም።
መታምን ማመን ….. ማመን መታመን
በስሜት ማዕበል … መሆን ይቅርብን
በልቤ ነህ አለህ ውስጤ
ስትደምቅ ጌጥህ ጌጤ
አያገባኝም የለሁበት ….
ማለት ለኔ ላንተም ፀፀት(2)…
እያለ በወቅቱ የነበረው ትኩሳትና ስጋት ህዝብ እንዲጠነቀቅ መክረዋል። በወቅቱ ሙዚቃውን ከታዋቂና ድምፃዊያን ሀይልዬ ታደስ፣ ፀደንያ ገብረ ማርቆስ፣ ጋር ወገኖችዋን ከኤች አይ ቪ ኤድስ ይጠበቁ ዘንድ በመዝፈን ማህበራዊ ሀላፊነትዋንም ተወጥታለች።
በአገራችን እጅጉን አሳሳቢ የሆነው የትራፊክ አደጋና የሚያስከትለውን መዘዝ በተመለከተ ከሞገስ ተካ ጋር “አሽከርክር ረጋ ብለህ” የተሰኘ እስከዛሬ ድረስ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ለዝግጅቶች ማጀበያ በመሆን የሚያገለግለውን ሙዚቃ በህብረት ሰርተው ለህዝብ አቅርበዋል።
የባህል አምባሳደርነት
ምናሉሽ እስካሁን ሁለት ሙሉ አልበምና ቁጥራቸው በርካታ የሆኑ ነጠላ ሙዚቃዎችን እንዲሁም በማህበራዊ ጉዳይና አገራዊ ሁኔታ ላይ ያተኮሩ ጥዑም ሙዚቃዎችን ለሙዚቃ አፍቃሪያን አቅርባለች። የምናሉሽ ስራዎች አንድ ወጥ በሆነ ቋንቋ ሳይሆን በተለያዩ ቋንቋዎች የተዘፈኑ ናቸው። በአማርኛ፣ በጉራጊኛ ከ6 በላይ ሙዚቃዎችን ፤ በሲዳሚኛና በሱዳንኛ (ሁለት ሙዚቃ) ያቀነቀነቻቸው ሙዚቃዎችዋ ተወዳጅነትን አትርፈውላታል።
የራስዋ ስራዎችን ግጥምና ዜማ ራስዋ ትሰራለች። ከአማርኛ ስራዎቿ በተጨማሪ የሰራቻቸው የብሄረሰብ ስራዎች በራስዋ ግጥምና ዜማ የተሰሩ ናቸው። የዘፈኖቹን ይዘት በቋንቋው አዋቂዎች በማስገምገምና አንዳንድ ስራዎችዋን ከሌሎች ገጣሚያን ጋር በማጣመር የተሻሉ ስራዎች መስራት እንዳስቻላት ትገልፃለች። በዚህ ከድምፃዊነት ባለፈ ጎበዝ የግጥምና የዜማ ደራሲነትዋን አስመስክራለች።
ወደፊት
የተሰጣት ሙዚቃ መክሊትዋን ማቀንቀን ነውና በተሰጣት ክህሎት ጠንክራ የመስራት እቅድም አላት። በተለይ ኢትዮጵያን የሚገልፁ የብሄረሰቦችን ያልተነኩ ባህሎች የሚያስተዋውቁ፣ ማህበረሰባችንን የሚያንፁና መልካም ነገርን የሚያስተምሩ ይዘት ያላቸው ሙዚቃዎች የመስራት ሀሳቡ እንዳላት ታስረዳለች። ኢትዮጵያን በጥልቀት በመረመርናት ቁጥር የምናየው አዳዲስና አስገራሚ ታሪክና ተፈጥሮ ብዙ ያሰራል የምትለው ድምፃዊዋ በባህል ጉዳይ ላይ በጥልቀት የመስራት ሀሳብም አላት።
በእረፍት ጊዜ
መፅሀፍት በተለይ ታሪካዊ የሆኑና ልቦለድ መጽሐፍት ለድምፃዊት ምናሉሽ የዕረፍት ጊዜ ምርጫዎች ናቸው። እንደ ልጅነትዋ ትያትር ዛሬም እጅጉን ትወዳለች ። ጊዜ ስታገኝም ዋነኛ መዝናኛዋ ነው። ከቤተሰብዋ ጋር የምታሳልፈው ጊዜ ልዩ ሀሴትን ያላብሳታል። ሳቅ ጨዋታ ባለበት መገኘት ጥሩ ድባብ ፈጥሮ ለሰዎች መልካም ነገር ማድረግ ያስደስታታል።
የኢትዮጵያ ሙዚቃ በምናሉሽ አይን
እርግጥ የኢትዮጵያ ሙዚቃ ከሌላው ዓለም ጋር ሲነፃፀር በእድገት ደረጃ የሚጎለው ነገር ቢኖርም፤ ዘርፉ ግን ቆሞ የቀረ ምንም ያልተለወጠ ነው ለማለት ፈፅሞ የማያስደፍርና እጅግ በጣም ጥሩና ተስፋ ሰጪ ዕምርታ እያሳየ መሆኑን ታስረዳለች። እርግጥ የሙዚቃ ባለሙያው በስራው የሚጠበቀውን ያህል ጥቅም አላገኘም።
እንደ ሀገርም በሙዚቃው ዘርፍ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ አልተቻለም ይሆናል። ነገር ግን የኢትዮጵያ ሙዚቃም መነቃቃቱና እድገት ላይ መሆኑ የሚያመላክቱ ሁኔታዎች አሉ። በየጊዜው ብቅ እያሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተሸላሚ የሚሆኑና በደረጃ ሰንጠረዥ ውስጥ እየገቡ ከፍተኛ ተደማጭ የሆኑ ሙዚቃዎችም አሉን።
በዘመን መቀየር በቴክኖሎጂ እድገትና በሰው ልጆች ስልጣኔ ልክ ከፍታ ላይ የደረሰው ሙዚቃ እንደ አገር የሚጠበቅበት ያህል አድጓል ዘርፉም ተለውጧል፣ የሙዚቃ ባለሙያው የሚበቃውን ያህል ተጠቅሟል ማለት ባያስችልም ሁኔታውን ግን ወደፊት መቀየር አይችልም፤ ማለት እንደማያስደፍር ትናገራለች።
በእርግጥ ኢትዮጵያ የራስዋ የሙዚቃ ስልት እና ተዘግኖ የማያልቅ ባህል ባለቤት እንደመሆንዋ ይህንን በሙዚቃ ለማስተዋወቅና የተሻለ እድገትን ለማምጣት የዘርፉ ባለሙያዎች ቅንጅት ወሳኝ መሆኑንም ምናሉሽ በአስተያየት መልክ ትገልፃለች። በተለይም የሙዚቃ ባለሙያው ስራውን አክብሮና ለስራው ትልቅ ዋጋ ሰጥቶ ህዝብንም አክብሮ ጥሩ ስራ ለሙዚቃ አድማጩ ማቅረብ እንዳለበት በዚህም ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ታስረዳለች።
መልዕክት ለኢትዮጵያዊያን
እኛ ኢትዮጵያዊያን ለዘመናት በጋራ የተለያዩ በጎና በጎ ያልሆኑ ገጠመኞች አሳልፈን በፍቅር ተሳስረን ዛሬ ላይ ደርሰናል። ዛሬ ይህን አንድነትንና ህብረታችን ፈፅሞ ልናጣ አይገባም። እርስ በርስ ከሚያጋጩን ከአንድነታችን ከሚነጥሉን ጉዳዮችና ሀሳቦች መጠበቅ ይኖርብናል። ከሚያጣሉንና ከሚለያዩን ነገሮች ይልቅ ወደ አንድነትና ህብረት የሚያደርሱን ብዙ ምክንያቶች አሉን። ልዩነታችን አክብረን አንድ የሚያደርገንን ነገር በማድመቅ አገራችንን ማሳደግና አብረን በፍቅር መዝለቅ እንችላለን ትላለች።
የዚህ ዘመን ትውልዶች ነንና ሀላፊነት አለብን። እኛ ለቀጣዩ ትውልድና ለልጆቻችን የተሻለች ኢትዮጵያ ማስረከብ ይገባናል። ነገሮችን አስተካክለንና አለመግባባታችን አስወግደን ለአገራችን እድገትና ለውጥ በጋራ መስራት ይጠበቅብናል። አንድ ከሆንና ወደአምላካችን ከተመለስን ወደፊት መልካም ነገር ሁሉ ወደኛ ይቀርባል። አገራችንም ሰላምና አንድነትዋ የተጠበቀ ይሆናል። ” በማለት መልዕክትዋን ለኢትዮጵያዊያን አድርሱልኝ ብላናለች። እኛም ከድምፃዊትዋ ጋር በነበረንን ቆይታ ያጠናከርነውን ፅሁፍ በዚሁ አበቃን፤ ቸር ያሰማን።
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን መስከረም 30 ቀን 2014 ዓ.ም