አሜሪካዊው የጥቁሮች መብት ተሟጋች ሪቨረንድ ጄሲ ጃክሰን የተወለደው መስከረም 28 ቀን 1934 ዓ.ም ነው። የትውልድ ቦታውም በአሜሪካ በደቡብ ካሮላይና ግዛት ግሪንቪል ከተማ ነው። እናቱ ሄለን በርንስ እሱን ስትወልድ ገና የ16 ዓመት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ነበረች። የወለደችውም በጎረቤቷ ነዋሪ ከሆነው የ33 ዓመት ባለትዳር ነው።
ወላጅ አባቱ ሉዊስ ሮቢንሰን ቦክሰኛ፤ የጨርቃ ጨርቅ ደላላ እና በአካባቢው ታዋቂ ነበረ። ሆኖም እናቱ ጄሲን ከወለደች በኋላ ባለትዳሩን የጄሲ አባት ትታ ቻርለስ ሄንሪ ጃክሰን አገባች። ይህ ሰውም ጄሲን እንደ ልጁ አድርጎ ለማሳደግ ፈቀደ። ጄሲም መጠሪያው በአሳዳጊ አባቱ ስም እንዲሆን ተወሰነ። ጄሲ ጃክሰንም ተባለ።
አሜሪካ ገና ከዘረኝነት አስተሳሰብ ባልተላቀቀችበት በዚያ ዘመን የተወለደው ጄሲ ጃክሰን፣ እንደማንኛውም የዘመኑ ወጣት በቀለም ከሚመስሉት ጥቁሮች ጋር እየተማረ እና እየተጫወተ አደገ። በስፖርት ውጤታማ ነበር ፣ በቀለም ትምህርቱም ለክፉ የሚሰጥ አልነበረም።
በ1959 እ.ኤ.አ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ሲያጠናቅቅ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ነጸ የትምህርት እድል አግኝቶ መማር ጀመረ፤ በየዩኒቨርሲቲው ያለው የዘረኝነት ሁኔታ ግን የሚቋቋመው ሆኖ አላገኘውም። እንደምንም ብሎ ግን በ1954 እ.ኤ.አ በሶሺዮሎጂ ተመረቀ። ከዚያም በቺካጎ የነገረ መለኮት ትምህርት ቤት ነጸ የትምህርት እድል አግኝቶ ገባ። ነገር ግን ለመመረቅ ሶስት ኮርሶች ሲቀሩት ትምህርቱን አቋርጦ ሙሉ ትኩረቱን ወደ ጥቁሮች የመብት ትግል አደረገ።
ጃክሰን በ1966 እ.ኤ.አ በቋሚነት የጥቁሮችን ትግል ይቀላቀል እንጂ፣ ከዚያም በፊት ቢሆን በትግሉ ውስጥ ነበር። እ.ኤ.አ በ1961 እሱና ሌሎች ሰባት ጥቁር ወጣቶች በትውልድ ከተማቸው ወደሚገኝ ግሪንቪል የህዝብ ቤተመጻህፍት በመሄድ ገብተው ተቀመጡ። ይህን ያደረጉትም ቤተ መጻህፍቱ ለነጮች ብቻ የተፈቀደ በመሆኑ ተቃውሟቸውን ለመግለጽ ነው። በዚህ ተግባራቸውም በስነ ምግባር ጉድለት ተከስሰው ታስረው ከቆዩ በኋላ በዋስ ወጡ።
ከዚያም የማርቲን ሉተር ኪንግ ተቀጣሪ ሆኖ ትግሉን ቀጠለ። እ.ኤ.አ በ1965 በአላባማ ግዛት ነዋሪ የሆኑት ታዋቂ የጥቁሮች መብት ታጋዮች ማርቲን ሉተር ኪንግ ጄምስ ቤል እና ሌሎች ከሰልማ ወደ ሞንትጎመሪ የተሰኘ ታሪካዊ ጉዞ ሲዘጋጁም ተሳተፈ። በወቅቱ በነበረው ቅልጥፍና እና የማደራጀት ብቃት የተገረመው ማርቲን ሉተር ኪንግም ጂሲን የደቡባዊ ክሪስቲያን አመራር ኮንፈረንስ አዘጋጅ አረገው።
እአአ በ1967 ደረጃው ከፍ ብሎ የሀገር አቀፍ አስተባባሪ ሆነ። ነጮች ጥቁሮችን ስራ እንዲቀጥሩ እንዲሁም ጥቁሮች የሚሸጡትን እቃ እንዲገዙ የሚያስገድደውን ‹‹ዘመቻ የዳቦ ቅርጫት›› በብቃት ማስተባበር ቻለ።
በ1968 እ.ኤ.አ ማርቲን ሉተር ኪንግ ተገደለ። ይህን ተከትሎም የጥቁሮችን የመብት ትግል ወደፊት ማስኬድ በጄሲ እና ሌሎች መሪዎች ላይ ወደቀ። ቀስ በቀስም ጄሲ ከሁሉም በተሻለ ተቀባይነት አገኘ።
ጥቁሮች በተለይም በኢኮኖሚው እንዲበረቱ የሚጥረው ጄሲ፣ በዚህ መልኩ ትግሉን እየመራ ቀጥሎ በ1984 እ.ኤ.አ ለአሜሪካ ፕሬዝዳንትነት እጩ እስከመሆን ደረሰ።
በወቅቱ ጄሲ ከሀገር ውስጥ አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃም ታዋቂነት እያተረፈ ነበር። እ.ኤ.አ በ1984 እ.ኤ.አ የአሜሪካ አየር ኃይል አባል የነበረው ሮበርት ጉድማን፣ ሶሪያ በሊባኖስ የያዘቻቸውን ቦታዎች ለመደብደበ እየበረረ ባለበት ወቅት ተመትቶ ይያዛል። የሶሪያ መንግስትም ምርኮኛውን ለመልቀቅ ምንም ፍላጎት አልነበረውም።
እናም ጄሲ ጃክሰን በወቅቱ ወደ ሶሪያ በመብረር በቀጥታ ለሶሪያው መሪ ሀፊዝ አልአሳድ ጥያቄ በማቅረቡ ፕሬዝዳንቱ ምርኮኛውን ለቀዋል። ይህ ጉዳይ በወቅቱ በመላው አሜሪካ ይበልጥ ታዋቂ እንዲሆን ስላደረገውም ራሱን ለፕሬዝዳንትነት እጩ አቀረበ። በተመሳሳይም በፊደል ካስትሮ እና ሳዳም ሁሴን እጅ የነበሩ አሜሪካውያን እንዲለቀቁም ጥረት አድርጓል።
በዚህ መልኩ የፖለቲካ ተሳትፎውን እያጠናከረ እና የጥቁሮችን መብት እያስከበረ እስከአሁን ድረስ ዘልቋል። በነዚህ ጊዜያት በርካታ ሽልማቶች የተበረከቱለት ሲሆን ከነዚህ መሀከል በ2000 እ.ኤ.አ ፕሬዚዳንት ቢል ክሊንተን ያበረከቱለት የሀገሪቱ ከፍተኛ የነጻነት ሜዳሊያ ዋነኛው ነው።
ከኢትዮጵያ ጋር በተያያዘ ጄሲ ጃክሰን በግንቦት 2020 እ.ኤ.አ በአሜሪካ ኮንግረስ የጥቁር የኮንገሬስ አባላት መሪ ለሆኑት ወ/ሮ ካረን ባስ እና 11 የኮንግረስ አባላት በጻፈው ደብዳቤ ይታወሳል። በወቅቱ ጄሲ ጃክሰን ግብፅ ሰሞኑን ለተ.መ.ድ የፀጥታው ምክር ቤት ባስገባችው ደብዳቤ ላይ ጥቁር የአሜሪካ ኮንግረስ አባላት ኮሚቴ (Congressional Black Caucus) ተቃውሞ እንዲያሰሙ ጥሪ አቅርቧል።
ይህ በጄሲ ጃክሰን የተፃፈ ደብዳቤ እንደሚለው፤ ግብፅ የአሜሪካ መንግስትን፣ የዓለም ባንክን እንዲሁም ተ.መ.ድን በመጠቀም የቅኝ ግዛት ውል በ11 የአፍሪካ ሀገራት ላይ ለመጫን እየሞከረች ነው። “መንግስታችንም ሆነ የዓለም ባንክ የአደራዳሪ ሚና እንደሌላቸው ግልፅ ሊደረግ ይገባል… አሜሪካ አረብ ሊግ እና ግብፅ ከወጠኑት የቅኝ ግዛት ውልን በጥቁር አፍሪካውያን ላይ ከመጫን እቅድ ራሱን ሊነጥል ይገባል” የሚለው ደብዳቤው ለጥቁር የአሜሪካ ኮንግረስ አባላት ኮሚቴ መሪ ካረን ባስ የተፃፈ ነው።
(አቤል ገ/ኪዳን)
አዲስ ዘመን መስከረም 30 ቀን 2014 ዓ.ም