የኢትዮጵያ ጠላት ሆኖ ከሩብ ክፍለ ዘመን በላይ ኢትዮጵያን የገዛው ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህ.ወ.ሓ.ት) በኢትዮጵያና በኢትዮጵያውያን ላይ ያልፈፀመው የግፍ ዓይነት የለም።የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ ፖለቲካዊ አፈና፣ የሐብት ምዝበራን ጨምሮ በኢትዮጵያም ይሁን በዓለም አቀፍ ደረጃ ‹‹ወንጀል ናቸው›› ተብለው የተበየኑ ግፎችን ሁሉ ፈፅሟል።
የቡድኑ ወንጀል ከአመሰራረቱ ይጀምራል።በረጅሙ የኢትዮጵያ ታሪክ እጅግ ደማቅ የሆነ የወንድማማችነትና የአብሮነት ታሪክ ያላቸውን እንዲሁም በኢትዮጵያ ምስረታና የአገረ መንግሥት ግንባታ ተግባራት ላይ አኩሪ አሻራቸውን ያሳረፉትን የዐማራንና የትግራይን ሕዝቦች ጨቋኝና ተጨቋኝ አድርጎ በመፈረጅ ራሱን ‹‹ነፃ አውጭ›› አድርጎ አዋቀረ።የዐማራን ሕዝብ ጨቋኝ አድርጎ በመፈረጅ ዓላማው ‹‹የትግራይን ሕዝብ ከዐማራ ጨቋኞች ማላቀቅ›› እንደሆነ ሰበከ።ይህም አልበቃው ብሎ በኢትዮጵያ ምስረታና የአገረ መንግሥት ግንባታ ላይ ወሳኝ ሚና ያለውን የትግራይን ሕዝብ ከኢትዮጵያ በመገንጠል ‹‹የትግራይ ሪፐብሊክ››ን ለመመስረት እንደሚታገል ይፋ አደረገ።ይህኛው ዓላማው በኢትዮጵያዊነቱ በማይደራደረው በአገር መስራቹ የትግራይ ሕዝብ ዘንድ እንደቀልድ የሚቆጠር መሆኑን ስለሚያውቅና ሲያስፈልገው እንደሚጠቀምበት ስላመነ የነፃ ሪፐብሊኩን ጉዳይ ለጊዜውም ቢሆን ትቶት ከወታደራዊው የደርግ መንግሥት ጋር መዋጋቱን ቀጠለ፡፡
ህ.ወ.ሓ.ት በትግል ላይ በነበረበት ወቅት ተዋጊዎቹን በአሰቃቂ ሁኔታ መግደልን ጨምሮ ሌሎች ዘግናኝ ወንጀሎችን እንደፈፀመባቸው የድርጅቱ ነባር ታጋዮች ጭምር የሚመሰክሩት ሃቅ ነው።ከኢትዮጵያ መንግሥትና ከዓለም አቀፍ ለጋሽ ድርጅቶች ለሰብዓዊ ድጋፍ የተሰጠን እርዳታ በመሸጥ ለራሱ ሀብት ያካበተና ‹‹እታገልለታለሁ›› የሚለው ሕዝብ ሕይወት እንኳ ደንታ የማይሰጠው ቁማርተኛ ነው።
የሜጀር ጀኔራል ዚያድ ባሬ መንግሥት ኢትዮጵያን በወረረበት ወቅት ህ.ወ.ሓ.ት ከሌሎች ፀረ-ኢትዮጵያ ቡድኖች ጋር በመሆን ከሶማሊያ ጋር አብሮ ኢትዮጵያን የወጋ ከሃዲ ድርጅትም ነው።ሁሉም ብሄሮች የየራሳቸውን ‹‹ነፃ አውጪ›› ቡድኖች እንዲመሰርቱና ራሳቸውን የቻሉ ‹‹ነፃ አገራት›› እንዲሆኑ ያበረታታ ነበር።ይህ ስልቱ ደግሞ ኢትዮጵያን የመበታተን ዓላማው አንዱ ማስፈፀሚያ ተደርጎ የሚጠቀስ ነው።
አጋር ነፃ አውጪዎችን አቋቁሞ አራት ኪሎ ከደረሰ በኋላም ወንጀለኛነቱን የሚያሰፋበት እድል በማግኘቱ በለመደው ተግባር ውስጥ ለመዘፈቅ ጊዜ አላባከነም።በአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ ፍንዳታዎችን በመፈፀም ንፁሃን እንዲቀጠፉና ንብረት እንዲወድም አድርጓል።ኢትዮጵያን ያገለገለውን ጦር ‹‹የደርግ ጦር›› ብሎ እንዲበተን በማድረግ አገርን ያለጠባቂ ወታደሩንም ያለመተዳደሪያ አስቀራቸው፤ በወታደሩ ላይ የደረሰው የሞራል ስብራትም በቃላት የሚገለፅ አይደለም።
በትግል ላይ በነበረበት ወቅት ያስበው የነበረውን ኢትዮጵያን ከፋፍሎ የማዳከም ዓላማውን ሊያሳኩለት የሚችሉ እኩይ ተግባራቱን በመፈፀም አገር ገዢነቱን ቀጠለ።የአገሪቱን አከላለል ‹‹ለሕዝቦች ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ይሰጣል›› በሚል ሽፋን የግጭት መነሻ እንዲሆን አድርጎ ከለለው።ቀደም ሲል በትግራይ ጠቅላይ ግዛት/ክፍለ አገር አስተዳደር ስር ያልነበሩ ሰፋፊና ለም ስፍራዎችን ወደ ትግራይ ክልል እንዲካለሉ አደረገ።ይህ እርምጃው ቡድኑ ‹‹ትግራይን ነፃ አገር የማድረግ›› እቅዱን ባስፈለገው ጊዜ ሊተገብረው እንዳለመ ማሳያ ነው።
ህ.ወ.ሓ.ት ‹‹ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ›› በተባለው ጥላ ስር ሆኖ ኢትዮጵያን ሲገዛ በነበረበት ወቅት የፈፀማቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፣ ምጣኔ ሀብታዊ አሻጥሮችና ምዝበራዎች፣ አፈናዎች … ተዘርዝረው አያልቁም።የተለየ ፖለቲካዊ አመለካከት ያላቸው ዜጎች ሁሉ ለእስራት፣ ድብደባ፣ ዝርፊያ፣ ስደትና ሞት ተዳርገዋል።በእስራት ላይ ሳሉ የሚፈፀምባቸው አሰቃቂ ድብደባ ለዓይንም ለጆሮም የሚዘገንን ነው።በርካታ ታሳሪዎች ከኢትዮጵያውያን ባህልና ሞራል እጅግ ያፈነገጡ ነገሮች ተፈፅመውባቸዋል።
የይስሙላ ምርጫዎችን እያከናወነና ‹‹በሙሉ ድምጽ አሸነፍኩ›› እያለ በሕዝብና በአገር ሲቀልድ ኖሯል።ብዙ የድርጅቱ አመራሮች ጭምር በይፋ ሲናገሩት የነበረው በሦስተኛው አገራዊ ምርጫ (ምርጫ 97) የመሸነፉ ጉዳይ የሚዋጥለት አልሆን ብሎት ‹‹የሕዝብ ድምጽ ይከበር›› ብለው ተቃውሟቸውን ያሰሙ ሰላማዊ ዜጎችን በግፍ ጨፍጭፏል።ሌሎቹን ደግሞ ለእስራት፣ ድብደባና ስደት ዳርጓል።
ቡድኑ በምጣኔ ሀብት ዘርፍ የፈፀማቸው ወንጀሎች እንኳ ለመስማትም ሆነ ለመረዳት የሚከብዱ ናቸው።የአንዲት ድሃ አገር ገንዘብ ለጥቂት ግለሰቦች አውሮፕላንና መርከብ መግዣ መዋሉ፣ ለስኳር ፋብሪካዎች መገንቢያ የተያዘ 77 ቢሊዮን ብር በጥቂት ሰዎች ቅርጥፍ ተደርጎ መበላቱ፣ አገር ሊመራ በስልጣን ላይ የተቀመጠ ቡድን ራሱ በጥቁር ገበያ ዶላር መንዛሪና እፅ አዘዋዋሪ ማፍያ ቡድን ሲሆን መመልከትና መስማት አይከብድም? አገር የማስተዳደር ኃላፊነት ያለበት አካል ይህን ወንጀል ይፈፅማል ብሎ ማመንስ አይቸግርም? ለመስማት ቢከብድም፣ ለማመንም ቢቸግርም ህ.ወ.ሓ.ት ግን አድርጎታል።
ቡድኑ በሕዝባዊ አመፅ ከአራት ኪሎ መንበሩ ወርዶ ወደ መቐለ ከመሸገ በኋላም እኩይነቱን አልረሳም።በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ግጭቶችን በመደገስ ንፁሃን እንዲገደሉ፣ እንዲፈናቀሉና እንዲዘረፉ አድርጓል።በነዚህ ጥቃቶችና ግጭቶች በርካቶች በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድለዋል፤ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል፤ በቢሊዮን ብር የሚገመት ንብረት ወድሟል።
ይህ ሁሉ አልበቃው ብሎ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም የኢትዮጵያን፣ በተለይም የትግራይን፣ ሕዝብ ከጠላት በሚጠብቀውና ለትግራይ ሕዝብ ብዙ ውለታ በዋለው የሀገር መከላከያ ሰራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ሰንዝሮ የክፍለ ዘመኑን ዋነኛ ክህደት ፈፀመ።ይህኛው ወንጀሉ ቡድኑ ኢትዮጵያን የማፍረስ እቅዱን ለሁሉም ሰው በማያሻማ መልኩ የገለፀበት ተግባሩ በመሆኑ አንዳንድ ነጥቦችን በትኩረትና በስፋት መመልከት ያሻል።በወቅቱ ቡድኑ የሰሜን ዕዝን ሲያጠቃ ስለፈፀማቸው አሰቃቂና አሳዛኝ ድርጊቶች እና በሰራዊቱ ላይ ስለተፈፀመው ክህደት ሌተናል ጀኔራል ባጫ ደበሌ የሚከተለውን ተናግረው ነበር …
‹‹ … በሰራዊቱ ውስጥ ያሉ ትግርኛ ተናጋሪ አባላት ሰራዊቱን ለማፍረስ ካቀደው አካል ጋር በተቀናጀ መልኩ እንዲሰሩ ተልዕኮ ተሰጥቷቸዋል።አንደኛው ተልዕኮ በሰራዊቱ ውስጥ በመሆን ሰራዊቱን የማፍረስ ስራ መስራት ነው።ሁለተኛው ከሰራዊቱ ወጥቶ ሰራዊቱን መውጋት ነው።ሦስተኛው ሰራዊቱ እጅ እንዲሰጥ ማድረግ ነው።በውስጥ የራሳቸውን ሰዎች አሰማርተው የሰራዊቱን መገናኛ/ሬዲዮውን (Chain of Command) እነርሱ በሚፈልጉት መልኩ በሙሉ ወደእነርሱ አዞሩት።የመከላከያ መገናኛ ዋና መምሪያ ኃላፊ የእነርሱ ሰው ነው።የሰሜን ዕዝ ባለባቸው አካባቢዎች ሁሉ የነበረውን የመከላከያን የሬዲዮ ፕሮግራም እነርሱ በሚያውቁት መንገድ ፕሮግራም እንዲሆን ተደረገ።ሬዲዮ ፕሮግራም ሲደረግ የሚያጠራጥር ነገር የለውም።በወታደሮች መካከል መተማመን እንጂ መጠራጠር አይኖርም … የሰራዊቱ ራሽንና ደመወዝ ሲገባ ኦፕሬሽኑ ተጀመረ።
ኦፕሬሽኑ ማታ ሊጀመር በዚያው ዕለት፣ ቀን ላይ ለሰራዊቱ አዛዦች ግብዣ አድርገው በመጨረሻ የሚፈልጓቸውን አዛዦች አፍነው አስቀሩ … ሬሽኑንና ብሩን ወስደው ልዩ ኃይልና ሚሊሻ ብለው ላሰለጠኗቸው አደሉ።ሬዲዮ ግንኙነቱ ስለተቆረጠ የሰራዊቱ አዛዦች እርስ በእርስ መገናኘት አልቻሉም።ይህ ደግሞ የሠራዊቱ ዋና ምሰሶ የሆነውን ተዋህዶ መስራትን ከጥቅም ውጪ አደረገው።ሻለቃዎችን ከበው ‹እጃችሁን ስጡ፤ጠመንጃችሁን እንጂ እናንተን አንፈልግም፤የእኛ መንግሥት የተመረጠ መንግሥት ነው፤ የአዲስ አበባ መንግሥት የተመረጠ መንግሥት ስላልሆነ ፈርሷል› የሚል ማስፈራሪያ አስተላለፉ።ወታደሮቹ ያለምግብና ውሃ ለሦስት ቀናት ቆዩ … ወታደሮቹ ‹አገር ጠብቅበት የተባልኩትን መሳሪያ ለማንም አልሰጥም› ብለው ተዋጉ።መሳሪያ ሰጥቶ ወደፈለገበት ለመሄድ ዝግጁ የሆነ ወታደር አልነበረም።ጀግና ሰራዊት ተፈጥሯል …
በብዙ ቦታዎች ውጊያዎች ነበሩ።በውጊያው ላይ የተሳተፉትና ሰራዊቱን የወጉት ልዩ ኃይል፣ ሚሊሻ፣ ከሰራዊቱ ጋር ዩኒፎርምና መለዮ ለብሰው፤የመለዮውን ቃል ኪዳን የካዱ ትግርኛ ተናጋሪ የሆኑ የሰራዊቱ አባላትና የሸኔ ወታደሮች ናቸው … የሰሜን እዝ አዛዦችን ግብዣ ጋብዘው፣ ለ21 ዓመታት አብረው የኖሩትን፣ ጉርሻ አጉርሰው ሲያበቁ ከግብዣው ሲወጡ እጃቸው ላይ ካቴና ያስገቡ ፍጡሮች ‹የሰሜን እዝ ከእኛ ጋር ተባብሯል› ብለው አስነገሩ …
በኮማንድ ውስጥ አፍኖ ለመውሰድ ማን ዐማራ ነው፣ ማን ኦሮሞ ነው … የሚለውን ነገር ለይተዋል።ማን ጠንካራ ነው፣ ማን ለስላሳ ነው የሚለውንም ለይተዋል።ማን ማንን ይይዛል የሚባለውም ነገር ተለይቷል …
የ20ኛ ክፍለ ጦር አራተኛ ብርጌድ ድጋፍ ሰጪ ብርጌድ ነው።ትጥቁ ሞርታሮች፣ ሮኬቶች፣ መድፎችና አየር መቃወሚያዎች ናቸው።ውጊያው ሲጀመር ብርጌዱን የወጉት የብርጌዱ አባላት የሚያውቋቸው ሚሊሻዎች ናቸው።የተሰውትን የመከላከያ አባላት ልብሳቸውን አውልቀው፣ ራቁታቸውን አድርገው ሬሳቸውን ፀሐይ ላይ አሰጡት … ሬሳቸው ፈንድቶ የአሞራና የጅብ ሲሳይ ነው የሆነው።ለ21 ዓመታት ያህል በአንድ ጉድጓድ አብሮ የኖረን፣ እርሻ ያረሰን፣ እህል ያጨደን፣ ትምህርት ቤት የሰራን፣ አንበጣ የተከላከለን … ሰራዊት ሬሳውን ጅብ አስበሉት።ከገደሉ በኋላ ልብሳቸውን አውልቀው ሬሳቸው ላይ እያጨበጨቡ ጨፈሩበት።የእነርሱን ወገን ሬሳ አንስተው ሲቀብሩ የአገር ጋሻ የሆነውን የመከላከያ ሰራዊት ሬሳ ላይ ግን ጨፈሩበት።
ተዋግቶ የገደለ ሰው በጀግንነት የተዋጋን ሬሳ አንስቶ ይቀብራል።እነዚህ ሰዎች ግን ተዋግተውና ገድለው አያውቁም ማለት ነው።ለ21 ዓመታት ያህል ትግራይ ለኖረው ለሰሜን ዕዝ የሰጡት ክብርና ምላሽ ይህ ነው።ሬሳው ላይ የጨፈረው ይፈር እንጂ ወታደሩ የተሰዋው ለአገሩ በጀግንነት ስለተሰዋ እኛ እንኮራበታለን።ወራዳው ጀግናውን ያልቀበረው ነው …
አፍነው የያዟቸውን ዩኒፎርማቸውን አስወልቀው ነው ራቁታቸውን ወደ ሻዕቢያ ሂዱ ያሏቸው።ራቁታቸውን! በዓይኔ በብረቷ ነው ያየኋቸው! ህሊና ያላቸው ሰዎች ግን ልብስ አለበሷቸው።ጠላት ብለን የተዋጋናቸው የኤርትራ ወታደሮች ልብስ አለበሷቸው።… ››
ይህን የሌተናል ጀኔራል ባጫ ገለፃ ይዘን፣ ተነግሮ የማይዘለቀው ክህደት ሰለባ ከሆኑ ወታደሮች መካከል ጥቂቶቹ የተናገሩትን ደግሞ እንመልከት …
‹‹ … የህ.ወ.ሓ.ት ሚሊሻና ልዩ ኃይሎች የጋንታ አመራሩን በፊታችን ገደሉት።ከገደሉት በኋላ አስፋልት ላይ ሲጎትቱት ነበር።የቲም አዛዦቻችን ተመቱ።ከምሽጉ ውስጥ የቀረሁት እኔ ብቻ ነበርኩ።ስናይፐር ሳይቀር ጠምደው ስለነበር እየተኮሱብኝ ነበር።ከሞትኩም ልሙት ብዬ ወደ ጓደኞቼ ሄድኩ።ወደ ጓደኞቼ ሄጄ ስንዋጋ ከቆን በኋላ ጥይት ሲልቅብን እጅ ሰጠን።የነበረን መሳሪያ ክላሽ ብቻ ነበር።ሁላችንም ታሰርን።የወር አበባ ሕመም በሚያሰቃየን ወቅት የንጽሕና መጠበቂያ እንድናገኝ አሳሪዎቻችንን እንዲተባበሩን ስንጠይቃቸው ‹ሂጂ ወደዚያ!› እያሉ በጥፊ ይመቱን ነበር … ምግብ የለም።ከሲሚንቶና ወንበር ላይ አስተኝተውንና አስቀምጠውን ያድራሉ።ልብሳችንን፣ ገንዘባችንን፣ ስልካችንን፣ ልብሳችንን፣ ዶክሜንቶቻችንን፣ የባንክ ደብተራችንንና የኤቲኤም ካርዳችንን ወስደውታል።ብዙ ሰዎች ሞተዋል … አንዱ ሰው እጅ ከሰጠ በኋላ በታንክ ረግጠውታል።ሲገድሉ ብሔር እየመረጡ ነበር፤ በተለይ ትኩረታቸው ኦሮሞና ዐማራ ላይ ነበር።ሬሳቸውን አሞራ በልቶታል።መትረፍ የሚችሉ ቁስለኞችም ሞተዋል …›› ፲ አለቃ ቤተልሄም በዛ
***
‹‹ … ቤት ውስጥ ተቀምጬ ነበር።ሕፃኑም ተኝቶ ነበር።ቤቴ ላይ ጥይት ተኮሱብኝ።‹ውጪ› ተባልኩኝ።ሕፃን ይዤ አልወጣም አልኩኝ።በመጨረሻም ገና ስድስት ወር የሆነው ሕፃን ይዤ ምሽግ ውስጥ ገባሁ።ለሕፃን እንኳ ርህራሄ አልነበራቸውም … እጅ የሰጡ አመራሮችም
በአሰቃቂ ሁኔታ ተደብድበዋል።አንዱ አመራር እጁ ተቆርጧል።በተለይ ዐማራንና ኦሮሞን እዚያው ነው ያስቀሯቸው።‹እነሱን አንለቅም፤ እንገድላለን› አሉ።የታፈኑ የደቡብ ሰዎችን ደግሞ ዓይናቸው ላይ በርበሬ ይጨምሩባቸው ነበር።በረሃብም የሞቱ አሉ።ይህ ሁሉ ስቃይ ነበር … ›› ኮንስታብል አለምነሽ ገመዳ
***
ከላይ የተጠቀሱት የሁለት ግለሰቦች ንግግሮች በሴት የመከላከያ ሰራዊትና የፌደራል ፖሊስ አባላት ላይ የተፈፀሙ ግፎች መሆናቸውን ልብ በሉ! ከክህደቱ ማሳያዎች ጥቂት እንጨምር …
***
‹‹ … ታግተን 40 ኪሎ ሜትር በእግራችን እንደተጓዝን ምሽት ሆነ።1200 የምንሆን ሰዎች ሻንጣ ተሸክመን እየተጓዝን ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ሲሆን የትግራይ ልዩ ኃይል የጫነ ሲኖትራክ መኪና ከኋላችን መጣ።ከመንገድ እንዳንወጣ ታዘዝን።ሲኖትራኩ በእግሩ የሚጓዘውን ወታደር እየገጨና እየገደለ ሄደ።እኔም እግሬ ተሰብሮ ጉድጓድ ውስጥ ገባሁ … አጨዳ ውለን 11 ሰዓት ነበር የገባነው።‹ተሃድሶ› ተብለን ተጠርተን ነው የታገትነውና የተገደልነው።ሕፃን የያዘች የወታደር ሚስት እንዲሁም የ12 ዓመት ታዳጊም ተገድለዋል።ለሕዝባችን ነበር ስንታገል የነበረው።እንዲህ ዓይነት ነገር ይፈፀምብናል ብለን አልጠበቅንም።የሰው ልጅ የሆነ ፍጡር ይህን አያደርግም … ›› ፶ አለቃ ደረጀ አንበሳ
***
‹‹ … የእኛው የራሳችን ኮሎኔል የነበረ ሰው ነው ቄስ መስሎ መጥቶ አፈና የፈፀመብን … በእግራችን ስንጓዝ ከፊት ለፊት ተኩስ ከፈቱብን።እንዳንመታ ብለን መሬት ላይ ስንተኛ ሲኖትራክ ከኋላ መጥቶ በላያችን ላይ ሄደብን።ከሲኖትራኩ ለማምለጥ እየተንከባለሉ የሄዱትን በጥይት ጨረሷቸው።ዐማራ፣ ኦሮሞ፣ ደቡብ ብለው ወታደሩን በብሔር እየለዩ ሲመድቡ ነበር።እኛ ግን ‹ሁላችንም አንድ ነን፤ ኢትዮጵያውያን ነን› ብለናቸው ነበር …›› ፶ አለቃ ወንድማገኝ ወልደገብርኤል
***
በወቅቱ የሰሜን እዝ ምክትል አዛዥና ከታጋቾች መካከል አንዱ የነበሩት ብርጋዴር ጀኔራል አዳምነህ መንግሥቴ በበኩላቸው ‹‹ … እናትና አባትህ ‹ይክዱኛል› ብለህ በማትጠብቅበት ዓይነት ሁኔታ ውስጥ በሰራዊቱ ላይ ክህደት ተፈጽሟል። ቤታችን ነው፤ ሰላም ነው ባልንበት ቦታ በተደራጀ ኃይል አፈና ተካሂዶብናል።የአፈናው ጊዜ በሙሉ በርካታ ውጣ ውረዶች ያሉት ነው፤ ያለእረፍት በቀንም በሌሊትም ረጅም የእግር ጉዞዎች ነበሩ። ስሜቱን መግለጽ ይቸግረኛል … ›› ብለው ተናግረው ነበር።
***
ህ.ወ.ሓ.ት በማይካድራና በሁመራ የፈማፀቸውን አሰቃቂ ጭፍጨፋዎች በምን ቃላት ማስረዳት ይቻል ይሆን?! ሕፃናትን ለጦርነት ማሰለፉን እንዲሁም የውሸትና የጥላቻ መረጃን በገፍ በማሰራጨት ኢትዮጵያ ብርቱ ዓለም አቀፍ ጫና እንዲገጥማት ማድረጉንም እንዳንዘነጋው።ከዚህ በተጨማሪ ህ.ወ.ሓ.ት በትግራይ ክልል በሚገኙ አገራዊ መሰረተ ልማቶች ላይ ከፍተኛ ውድመትና ዝርፊያ ፈፅሟል።ቡድኑ በሕግ ማስከበር ዘመቻው ወቅት ከመቐለ ከመሸሹ በፊት በትግራይ ክልል ባሉ ማረሚያ ቤቶች ውስጥ የነበሩ የሕግ ታራሚዎችን ሰብስቦ በመቐለ ከተማ ውስጥ በመልቀቅ ዝርፊያ እንዲፈጸም ማድረጉም ተቆጥሮ ከማያልቀው ወንጀሉ ላይ ተጨምሮ ይመዝገብ።
ከተኩስ አቁሙ በኋላ ደግሞ የቡድኑ ተዋጊዎች ወደ ዐማራ አፋር ክልሎች ወረራ ፈፅመው በርካታ ሰዎችን በአሰቃቂ ሁኔታ ገድለዋል፤ የጤናና ትምህርት ተቋማትና ሳይቀር ዘርፈዋል፤ አውድመዋል።የመንግሥት ተቋማትንና የግለሰቦችን ንብረት ዘርፈው ወስደዋል።ከሁሉም በላይ በአጋምሳ፣ በነፋስ መውጫ፣ በጭና፣ በቦዛ፣ በቆቦና በጋሊኮማ የጅምላ ጭፍጨፋ አካሂደዋል።
በአጠቃላይ የህ.ወ.ሓ.ትን ወንጀልና ክህደት ለመግለፅ ቃላት እንኳ ራሳቸው አቅም ያጥራቸዋል።የህ.ወ.ሓ.ት ፀረ-ኢትዮጵያነት ተዘርዝሮ የሚያልቅ አይደለም።የአዲሱ መንግሥት ተቀዳሚ ትኩረትም ቡድኑን በመደምሰስ የኢትዮጵያንና የኢትዮጵያውያንን ስቃይ ማስቆም እንደሚሆን ኢትዮጵያውያን ሁሉ ተስፋ አድርገዋል፡ የመንግሥት ኃላፊነትም ይህን የዜጎች ተስፋ በአፋጣኝ እውን ማድረግ ሊሆን ይገባል!
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን መስከረም 24/2014