ኢትዮጵያ በሕዝቦቿ የተባበረ ክንድ የመጡባትን ጠላቶች ሁሉ እያሳፈረች በመመለስ ሉዓላዊነቷን ሳታስደፍር የኖረች ሀገር ብቻ ሳትሆን ሊጫንባት የነበረውን የባርነትን ቀንበር በመሰባበር ለጥቁር ሕዝቦች ፋና ወጊም ነች። ይቺ ታላቅ ሀገር ዛሬ የውስጥ ሰላሟ ተናግቶ ሕዝቦቿ የተለያዩ ሰቆቃዎች እየደረሰባቸው ይገኛል። ለሀገሪቱ ሰላም መደፍረስ ያለፉት 27 ዓመታት ምን አስተዋጽኦ ነበራቸው? የትግራይ ሕዝብ ልጆቹን በጦርነት እየገበረ ኖሮ ምን አተረፈ? የጥፋት ቡድኑ ባልተለመደ መልክ ንጹኃን ላይ፣ እንስሳት ላይ ፣ የእምነት እና የአገልግሎት ተቋማት ላይ ጥቃት በማድረስ ከኢትዮጵያ እሴት ያፈነገጡ ተግባራትን የሚፈጽመው ለምንድነው? ዓለምአቀፉ ማህበረሰብ አሸባሪዎች በንጹኃን ላይ የሚፈጽሙትን ዘግናኝ ግፍና በደል እያየ ለምን ማውገዝ ተሳነው? አዲሱ የመንግሥት ምስረታ ችግሮቹን ለመፍታት ለአመራሩም ሆነ ለሕዝቡ ምን አቅም ይፈጥርለታል? በሚሉትና በሌሎችም ጉዳዮች ዙሪያ አዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህርና ተመራማሪ ከነበሩት ዶክተር አየለ በከሬ ጋር ደረገውን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርቧል።
አዲስ ዘመን፡- አሸባሪው የህወሓት ቡድን ኢትዮጵያን ያስተዳደረባቸውን 27 ዓመታት እንዴት ያዩታል?
ዶክተር አየለ፡- ከታሪክ አንጻር ያለፉትን 27 ዓመታት ስንመለከታቸው ሌላ ገላጭ ነገር ስለሌለ አሳዛኝ የታሪክ ሂደት ነበር ማለት ይቻላል። አንድ ሀገር መረጋጋት እና ወደፊት መገስገስ የምትችለው ሕዝቦቿ ሰላምና ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ማንኛውንም እንቅስቃሴዎች ማድረግ ሲችሉ ነው። በነዚህ 27 ዓመታት ውስጥ ግን ምንድነው የተደረገው ካልን ሕዝቦችን በዘር መከፋፈል ነው። መከፋፈል ብቻ ሳይሆን እርስ በእርስ ማጋጨት ያንን ተከትሎ ለመስማት እንኳን የሚዘገንኑ ድርጊቶች ናቸው የተፈጸሙት። የሀገራችን ሕዝቦች በአንድነት ቆመው ትኩረታቸውን ወደ ልማት ከማድረግ ይልቅ የተዛቡ ታሪኮች እየተነገሯቸው ሀገሪቱ ምስቅልቅሏ እንዲወጣ ብዙ ተደርጓል። ጠቅለል ባለ መልኩ ቡድኑ ሀገሪቱን ያስተዳደረባቸው 27 ዓመታት የጨለማ ጊዜዎች ነበሩ ማለት ይቻላል።
ለአንድ ሕዝብ ወይም ለአንድ ዜጋ ታሪኩ የማንነቱ መገለጫ ነው። ታሪክ ያለፈውን ያስታወሰናል፤ ያለንበትን ጊዜ በአግባቡ ተጠቅመን ወደፊት እንድንገሰግስ ያደርገናል። ታሪክ ድርጊት ነው። ምን ተደረገ? የሚለውን ጥያቄ የሚመልስልን ነው። እናም ቀደም ሲል የተደረገው ለአሁኑ አስተማሪ፤ ለወደፊቱም ራዕይ ይሆናል። እናም ቁልፍ የሆነውን የሰዎችን ማንነትና ህልውና ማረጋገጫ ታሪክን ማጥፋትና ማዛባት አጥፊው ቡድን ምንም ዓይነት ዓላማና እቅድ የሌለው የዕለት ኑሮው ላይ ብቻ የተመሰረተ መሆኑን የሚያሳይ ነው። ለማንኛውም የታሪክ ገላጩ ሰው ነው። ሰው እስከ ኖረ ድረስ ታሪክ አለ። ታሪክ የሚሰራውም ህዝብ ነው። ያንን ማጥፋትና ትክክለኛው ነገር ለሕዝቡ እንዳይደርስ ማድረግ ታሪክን ማጥፋት ነው።
ታሪክ ሰራን የምንለው ለምሳሌ የትምህርት፣ የጤና የንግድ የሃይማኖት ተቋማትን መገንባትና ወደፊት ማሻገር ስንችል ነው። እነዚህን ስናጠፋቸው ግን ታሪክ አጠፋን ማለት ነው። የስልጣኔ አካል ከመሆን ወጣን ማለት ነው፤ ሕዝባችን ታሪክ እንዳይኖረው አደረግን ማለት ነው። አሁን እየተፈጸመ ያለው እንዲህ ዓይነት ድርጊት ነው። እንዲህ ዓይነቱ ታሪክ ተሰምቶም ታይቶም አይታወቅም።
እንግዲህ ባለፉት 27 ዓመታት የተሰሩት ክፉ ሥራዎች ያሳደሩብንን ተጽእኖ አሁን እያየን ይመስለኛል። ዛሬ ሕዝብ የሚፈናቀለው፣ የሚገደለው፣ ንብረት የሚወድመው ትናንት በተሰራው መጥፎ ሥራ ነው። እነዚህ ጸረሰላም ቡድኖች በበረሃ በነበሩ ጊዜ እራሱ በማኒፌስቷቸው ላይ ሕዝብን ወይም ብሔርን ጠላት አድርገው መነሳታቸው ዛሬ ለሚታየው ቀውስ ምክንያት ሆኗል። ኢትዮጵያውያን እርስ በእርሳቸው እንዳይተማመኑ አንዱ ሌላውን እንደጠላት እንዲፈርጀው የተሰራው ባለፉት 27 ዓመታት ውስጥ ነው። አሁን እያየን ያለነው ውጤቱን ነው።
አዲስ ዘመን፡- የውጭ ጣልቃ ገብነቱንና ጫናውን እንዴት ያዩታል?
ዶክተር አየለ፡- የውጭ ኃይሎችም ተባብረው ኢትዮጵያን ለማዳከም እየተሯሯጡ ነው። አደጋው ደግሞ የውጭ ኃይሉና የውስጥ ኃይሉ እየተናበቡ የሚሰሩ ናቸው። የውጭ ኃይሉ ኢትዮጵያን ማዳከም የሚፈልግበት ምክንያት ምንድነው ከተባለ ኢትዮጵያውያን የረዥም ዘመን ታሪክ ያለንና ለማንም የማንንበረከክ ጠንካራ ሕዝቦች በመሆናችን፤ የራሳችን ጠባይ የራሳችን እሴት ያለንም ስለሆነ፤ የእነርሱ ተገዢ ሊያደርጉን ስለፈለጉ አንድነታችንን ለማጥፋት እና ሕዝቡን በታትኖ እንደሚመቻቸው ለማድረግ እየተንቀሳቀሱ ነው። እንደሚታወቀው መላው አፍሪካ በቀኝ ግዛት ሲወድቅ ክብሯን አስጠብቃ የኖረችው ኢትዮጵያ ነች።
ኢትዮጵያ እንደተምሳሌት ሆና እንዳትቀጥል፤ እንድትበጣጠስ፤ ታሪኳ እንዲጠፋ የመቀራመት ሥራ የሚሰሩ ይመስላል። ሕዝቦቿ ለፈረንጆች በተለይም ለካፒታሊስት ኃይሎች ተገዢ እንዲሆኑ፤ ሀብቷ እንዲበዘበዝና ታሪክ አልባ እንድትሆን እየጣሩ ነው። የውስጥ ኃይሎች ምናልባት ኮሚሽን ሊከፈላቸው ይችል ይሆናል። ይህ አሁን ላለው ቀውስ ዋነኛ ምክንያት ሆኗል ማለት ነው።
ከኃያላን መንግሥታት ጀምሮ እስከ ዓለምአቀፍ ድርጅቶችና ሚዲያዎች በተደራጀ መልክ ይችን ሀገር መጀመሪያ ጥላሸት መቀባት፣ ከዚያ በኋላ ከውስጥ ኃይሎች ጋር ሆነው እንድትበታተን ለማድረግ እየሰሩ ነው። የሚገርመው ነገር ይህን ሁሉ ጥረት እያደረጉም ተቋቁመናል። ምክንያቱም የኢትዮጵያ ሕዝብ የረዥም ዘመን የአብሮነት እሴት ያለው ስለሆነ አንድነቱን የበለጠ አጠንክሮ ሀገሩን ለማዳን እየታገለ በመሆኑ ነው። ሕዝባችን ሰላሙን በንቃት እየተከታተለ ነው። ለምሳሌ ከሰሞኑ የመስቀል በዓል ሲከበር ሕዝቡ ርችት እንዳይተኩስ የተላለፈለትን ትእዛዝ በማክበር ከሁለት ሺ በላይ ባሉ ቦታዎች የደመራ ሥነሥርዓት ሲከናወን አንድም ሰው ርችት አለመተኮሱ ሰላሙን ለመጠበቅ ያለውን ቁርጠኝነት ያየንበት ነው። ያምብቻ ሳይሆን ሰላማዊ የምርጫ ሂደትን በማከናወንም ዴሞክራሲን ለዓለም ሕዝብ ያሳየ ነው።
ሕዝቡ በህዳሴው ግድብ ላይ ያሳየው ትብብርና አሁንም ለመከላከያ ሰራዊቱ እያደረገ ያለው ድጋፍና ደጀንነት ጥንካሬው የሚገለጽበትና ላለፉት 27 ዓመታት ያጣነውን አንድነት እያመጣን መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው። ኢትዮጵያውያን እስከተባበሩ ድረስ ማንኛውም ኃይል ቢመጣ ያፈርሱታል እንጂ በምንም ዓይነት ይህችን ከ3ሺ ዓመት በላይ የቆየች ሀገር በማይረቡና ርህራሄ በሌላቸው ፤ ሰው ምን እንደሆነ በማያውቁ፤ ተቋም ምን እንደሆነ በማያውቁ ዓላማ በሌላቸው ሰዎች ልትበታተን አትችልም።
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ በቀኝ ግዛት ስር ላለመውደቅ ከወራሪዎች ጋር ስትታገል ከጠላት ጋር የሚተባበሩ ባንዳዎች ነበሩ አሁንስ ያለው ሁኔታ እንደዚህ ዓይነት መልክ ያለው ነው?
ዶክተር አየለ፡- እርግጥነው፤ በአደዋ ጦርነት ጊዜ ከጠላት ጋር የተሰለፉ ወገኖች ነበሩ። ለምሳሌ ራስ ስብሃት አምባላጌ ላይ በተደረገው ውጊያ ሀገራቸውን ከድተው ከጣሊያን ጋር አብረው ሲዋጉ ነበር። በኋላ ግን አድዋ ላይ በተደረገው ውጊያ ከኢትዮጵያ ወገን ሆነው ጣሊያንን ተዋግተዋል። በመጨረሻው ሰዓት ህሊናቸው ሊፈቅድላቸው ባለመቻሉ እንዲያውም መሣሪያ ይዘው መጥተው ለሀገራቸውና ለሕዝባቸው በመወገን ጣሊያን ላይ ፊታቸውን አዙረዋል። ሌሎችም እንደ ደጃዝማች ሀጎስን የመሰሉት ከጠላት ወገን ተሰልፈው ሲያበቁ እንደገና ይቅርታ ጠይቀው ሀገራቸውን ከወራሪዎች በመታደግ ለድሉ አስተዋጽኦ አበርክተዋል። እንዲህ ዓይነት ታሪክ አለን።
አሁን የምናየው ግን ከዚህም የተለየ ነው። ኢላማ የሚያደርጉት ያልታጠቁ ንጹኃን፣ ሴቶችን ልጆችን አዛውንቶችን ነው። በማይካድራ፣ ጋሊኮማ፣ አጋምሳ፣ ጭና፣ ንፋስ መውጫ፣ ደብረ ታቦር፣ ክምር ድንጋይ፣ ሰቆጣ፣ ቆቦ የተደረገው ጭፍጭፋ ንጹኃን ላይ ያነጣጠረ ነው። መዝረፍ፣ መድፈር፣ ንብረት ማውደም፣ የሃይማኖት ተቋማትን፣ በሺ የሚቆጠሩ የጤና እና የትምህርት ተቋማትን ማውደም የመሳሰሉ እኩይ ተግባራትን ሲፈጽሙ ነው ያየናቸው። ስለዚህ ለሀገርና ለሕዝብ እቆማለሁ የሚል እንዲህ ዓይነት ተግባራትን አይፈጽምም።
ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረ ጊዜ እራሱ እንዲህ ዓይነት የጭካኔ ሥራ አልተሰራም። ይህ ለየት ያለ ነው። ሀገር እና ሕዝብን ለማጥፋት የተደረገ የጭካኔ ሥራ በመሆኑ ከባንዳነትም በላይ ነው። በታሪክ እንደምናውቀው ባንዳዎች በተለያዩ ነገሮች ተደልለው ለጠላት መረጃ በመስጠት እና አብሮ በመሰለፍ ይሰራሉ እንጂ ተደራጅተው የሀገራቸውን ሕዝብ ሲጨፈጭፉና ሃይማኖታዊና አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ሲያወድሙ አልነበረም። ምናልባት የአሁኖቹንና የቀድሞዎቹን ባንዳዎች የሚያመሳስላቸው ሀገር ከድተው ከውጭ ኃይል ጋር መተባበራቸው ብቻ ነው። ከዚያ ውጪ በአድራጎታቸው ለንጽጽር የሚቀርቡ አይደሉም።
አዲስ ዘመን፡- የዚህ ቡድን ፍላጎት ምንድነው? ስልጣን ይዞ ሕዝብን ለማስተዳደር መፈለግ ነው ብለው ያምናሉ?
ዶክተር አየለ፡– በፍጹም ሊሆን አይችልም። እንዴት አድርጎ ትልቅ ግፍና በደል የፈጸመበትን ሕዝብ አስተዳድራለው ብሎ ያስባል። እንዴትስ ነው ያሉትን ተቋማት በሙሉ አውድሞ ከጨረሰ በኋላ ሀገር ሊገነባ የሚችለው፤ ቡድኑ 27 ዓመት እንዲሁ ስፈጽም የነበረውን እኩይ ሴራ በገሀድ ለኢትዮጵያም ሆነ ለዓለም ሕዝብ ማንነቱን የገለጸበትን አድራጎት ነው የፈጸመው። ነገ ሕዝብን አስተዳድራለሁ ብሎ የሚያስብ ኃይል በሕዝብ ላይ ግፍ አይፈጽምም። የሀገርን ሀብትም አያወድምም። በኢትዮጵያ ታሪክ ወገን በወገኑ ላይ ይፈጽማል ተብሎ የማይታሰብ ግፍ ነው እየፈጸመ ያለው። ኢትዮጵያን ለማስተዳደር በማሰብ ሳይሆን ቡድኑ ከዚህ በፊት እንዳሳወቀው ሂሳብ አወራርዳለሁ ያለውን በዚህ መልኩ እያከናወነ ይመስላል። እንዳሉት አራትኪሎ ለመግባት አይደለም። ይህ ሕዝብ አራት ኪሎ እንዲገቡ እንደማይፈቅድላቸውም ያውቃሉ።
አዲስ ዘመን ታሪካዊ ጥቅም ያላቸው ሃይማኖታዊ የማንነት መገለጫዎች ላይ ትኩረት የሚያደርገው ለምንድነው?
ዶክተር አየለ፡– ቡድኑ ጥንታዊ አብያተ ክርስቲያንንና ገዳማትን ይዘርፋል፤ መዝረፍ ብቻ ሳይሆን ጥቃትም ያደርስባቸዋል። ምናልባትም የሚዘርፈውን ቅርስ ሸጦ ጥቅም ለማገኘት ከመፈለግ ይሆናል። ቅርስ የአንድ ማህበረሰብ መገለጫ፤ ከፍ ሲልም የአንድን ሀገር ያለፈ የሥልጣኔ ደረጃን የሚገልጽ የህልውና ወይም የማንነት ምስክር ነው። ቅርሶች ታሪክን፣ ትርክትን በሥርዓት ለመዘርዘርና ለማስረዳት ይጠቅማሉ።
እነዚህ የጥፋት ኃይሎች ቅርሶችና የማንነት መገለጫዎች ላይ ትኩረት አድርገው መንቀሳቀሳቸው ምን ያህል ከሥልጣኔ እንደራቁ የሚያሳይ ነው። ለምሳሌ ጨጭሆ መድሃኔ ዓለም ከሦስት መቶ ዓመት በላይ ታሪክ ያለውና በውስጡ በርካታ ጥንታዊ ነዋየ ቅድሳትን የያዘ ነው። ቡድኑ እንደዚህ ዓይነት አብያተ ክርስቲኖችንም፣ እንደዋልድባ ያሉ ገዳማትና እንደ አልነጃሺ ባሉ መስኪዶች ላይም ጥቃት አድርሷል። አሁን ደግሞ ላሊበላ ምን እንደሚደረግ አናውቅም። የላሊበላ ቤተክርስቲያን በዓለም ላይ በስስት ከሚታዩ ቅርሶች አንዱ ነው። እንዲህ ዓይነት ቅርስ በሌላ የዓለማችን ክፍል የለም።
እንዲህ ዓይነት ቅርስ ላይ የሚፈጸም ሕገወጥ ተግባር በታሪካችን ላይ ቁስል ሊፈጥር ይችላል። እነዚህ የቡድኑ ተዋጊዎች አብዛኛዎቹ የዓለምአቀፍ ህግ የሚደነግገውን ደንብ ጥሰው ዕድሜያቸው ሳይፈቅድ የጦር መሳሪያ ያነገቡ ሕፃናት በመሆናቸው ይህንን ማገናዘብ የሚችሉ አይደሉም። በአጠቃላይ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል እየሆነ ያለው ሆን ብሎ ሰውንም፣ ቅርስንም፣ ተቋማትንም የማጠፋት የክፋት ሥራ ነው። እንስሳት ሳይቀሩ በግፍ እየተገደሉ ነው። ከዚህ ሁሉ መውጣት የምንችለው ደግሞ ተባብረን ይህንን ኃይል ማጥፋት ስንችል ነው። የውጭ ኃይሉም ሥራቸውን የሚደግፍላቸው ኢትዮጵያን ለመቀራመትና በቀጠናው ያላትን ተሰሚነት ለማዳከም ነው። ከሀገራችን የሚፈልጉትን ጥቅም ለማስጠበቅ በማሰብ ነው።
አዲስ ዘመን ፡- ባለፉት 27 ዓመታት የዚህ ቡድን አመራሮች ሀገር ሲያስተዳድሩ በነበር ሰዓት ፌዴራላዊ ሥርዓትን ዘርግተን ፍትህን፣ እኩልነትን፣ዴሞክራሲን አስፍነናል ይላሉ አባባላቸው ይገልጻቸዋል?
ዶክተር አየለ፡- እነዚህ አካላት ዘርግተናል የሚሉት የፌዴራል ሥርዓት የተሳሳተ ሲስተም ነው። በቋንቋ ብቻ የተለዩ ሕዝቦችን ያቀፈ ነው። የሕዝቦች ማንነት በቋንቋ ብቻ ሊገለጽ አይችልም። የኢትዮጵያ ሕዝብ የረጅም ዘመን ማንነት ያለው በመሆኑ በዚህ ረዥም ጊዜ ውስጥ በብዙ ሁኔታ የተሳሰረና የተጋመደ ሕዝብ ነው። ሕዝቡ የተሳሰረ ብዝሃነት እንዳለው እየታወቀ የሚለያይበትን ግድግዳ በየመሃሉ አቁሞ በቋንቋ ለይቶ ማስቀመጥ ስህተት ነው። እንደውም የአሁኑን ማህበራዊ ቀውስ የፈጠረብን ይህ ቋንቋ ላይ መሰረት ያደረገው አደረጃጀት ነው። ምክንያቱም ኢትዮጵያ ውስጥ በማንኛውም ቦታ አንድ ቋንቋ ተናጋሪ ብቻውን የኖረበት አጋጣሚ የለም። ትግራይን ጨምሮ ማለት ነው።
ትግራይ ክልል ለምሳሌ ኩናማ፣ ሳሆ፣ ኢሮብ አለ። ሁሉም ክልል እንዲሁ ነው። ይህ ተቀላቅሎ የመኖሩ ሁኔታ የሀገራችን ሕዝቦች ለረዥም ዘመን ተጋምዶ በመኖራቸው ምክንያት የፈጠሩት ጠንካራ መስተጋብር ነው። ብዝሃነት የሚገለጸው በቋንቋ፣ ብቻ ሳይሆን በሃይማኖትም በባህልም ነው። ኢትዮጵያውያን መገለጫችን ብዙ ነው፤ ያንን አልተከተልንም። የነበረው የፌዴራሊዝም ሥርዓት ክልል ብሎ ለከፋፈላቸው እራሱ እኩል መብት የሚሰጥ አልነበረም። በፓርቲዎቻቸው አማካኝነት አንዳንዶቹ አጋር አንዳንዶቹም እናት እየተባሉ በሀገራቸው ጉዳይ እኩል የመወሰን እና ሥልጣን የመጋራት ዕድል አልነበራቸውም። ለምሳሌ እንደ አፋር ጋምቤላ ሱማሌ ቤኒሻንጉል የመሳሰሉት እንደ ኦሮሚያ፣ አማራ፣ ትግራይና ደቡብ ክልሎች ሥልጣን የማግኘት መብት አልነበራቸውም። በዚህም ላይ እያንዳንዱ ክልል የሚመራው በራሱ በመረጣቸው ሰዎች ሳይሆን በህወሓት ተወካዮች ነው። ስለዚህ ሁሉንም ክልሎች ይመራቸው የነበረው አንድ ፓርቲ ብቻ ነበር ማለት ይቻላል። ስለዚህ የዴሞክራሲ ሥርዓት ነበር ማለት አይቻልም። እንደውም ዴሞክራሲን ያየነው ባለፈው ሰኔ በተደረገው ስድሰተኛው ሀገራዊ ምርጫ ላይ ነው። አዲስ አቅጣጫ ያየነው አሁን ነው። ግልጽና ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ምርጫ አካሂደን ለመጀመሪያ ጊዜ መንግሥት ለመመስረት የተዘጋጀነው አሁን ነው።
አዲስ ዘመን፡- የህወሓት አሸባሪ ቡድን በሚያደርገው ጦርነት የትግራይ ሕዝብ በተለይም የትግራይ እናቶች እየተጎዱ ነው ሕዝቡ ምን ማድረግ ይኖርበታል?
ዶክተር አየለ፡- በትግራይ ክልል ብዙ ዓመት ስለኖርኩኝ የሕዝቡን ሥነ ልቦና በደንብ አውቃለሁኝ። ምን ያህል ለሰው ፍቅር ያለው ደግና ቸር ሕዝብ እንደሆነ አውቃለሁ። አሁን በአፋር በወሎና ጎንደር ሕዝብ ላይ እየተደረገ ያለው ዘግናኝ ግፍ የትግራይን ሕዝብ አይወክልም። በተለይም ገጠር አካባቢ የሚኖሩት ሰዎች ሰው የጠገበ የማይመስላቸው፤ እንግዳ አክባሪዎች፤ ያላቸውን ሳይሰስቱ የሚያቀርቡ ናቸው። ምናልባት ይህ ቡድን የተለያዩ ነገሮችን እያላቸው ወደ ጦርነት ያስገባቸው ይኖራሉ። እነዚህ ሰዎች አብዛኛዎቹ ተገደው የሚገቡ ናቸው። የአማራና የአፋር ሕዝብ የደረሰበትን በደል ከትግራይ ሕዝቦች ጋር አያይዞ በቀለኛ እንዳይሆን መጠንቀቅ ይኖርበታል።
ድርጊቱን የፈጸሙት ሂሳብ እናወራርዳለን ብለው ሲዝቱ የነበሩ የጥፋት ቡድኑ አመራሮች ናቸው። ቂም መያዝ ማለቂያ ወደሌለው ግጭት ስለሚያስገባ ሕዝቡ ታጋሽ መሆን ይኖርበታል። የትግራይን ሕዝብ በምንም ዓይነት ከኢትዮጵያዊነቱ አሳነሰን ማየት የለብንም። እንደውም ለችግራቸው የመጀመሪያ ደራሽ በመሆን ከገቡበት አጣብቂኝ ልናወጣቸው ይገባል። ይህ የጥፋት ኃይል እስካልተደመሰሰ ድረስ ጥፋቱን ስለማይተው ተባብረን በማጥፋት የብዙዎችን ሕይወት ልንታደግ ይገባል።
የትግራይ ሕዝብ በኢትዮጵያዊነቱ የሚደራደር አይደለም። የዛሬዪቱን ኢትዮጵያ ከመገንባት አንጻር ትልቅ ድርሻ የነበረው ሕዝብ ነው። የክርስትናም ይሁን የእስልምና ሃይማኖት አስተምሮችን ተቀብሎ ለተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ያስፋፋ እና በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ትልልቅ ተግባራት የተከናወኑበት ስፍራም ነው። ስለዚህ ጥላቻ በጥላቻ መመለስ አያስፈልግም። ሕዝቡ ያለበትን ችግር መረዳት ይኖርብናል።
አዲስ ዘመን፡- የህወሓት አሸባሪ ቡድን ቀደም ሲሉ የቀረቡለትን የሰላም አማራጮች ሁሉ ትቶ ጦርነትን ብቸኛ አማራጭ አድርጎ የገባው ለምንድነው?
ዶክተር አየለ፡- እንደሚመስለኝ ከዚህ በፊት የነበረው ተሞክሮ አዋጭ መስሎ ስለታየው ነው። ከዚህ በፊት ባደረገው ጦርነት የትግራይን ሕዝብ በማስራብ በእርዳታ ስም ሀብት ያካበተ ቡድን ነው። ቡድኑ በስጋ ዝምድና እና በጋብቻ ተሳስሯል። በአንድ በኩል ባለፉት 27 ዓመታት በሰራው ወንጀል እንዳይጠየቅ በሌላ በኩል ጥቅሙን ለማስጠበቅ ሲል ነው የትግራይ ሕዝብን እንደከለላ የተጠቀመው። ያም ብቻ ሳይሆን ዕድሜያቸው ለውትድርና ያልደረሰ ሕፃናትን እየሰበከና እያስገደደ ወደ ጦርነት የሚያስገባው። የትግራይ ሕዝብ በሰላሙ ጊዜ እንኳን እየተቸገረ የሚኖር ነው። አምስት ስድስት ልጆችን ይዘው የሚለምኑ ሰዎች አሉ። አብዛኛው ሕዝብ ተጠቃሚ አይደለም።
የተወሰኑ ጥቂት ሰዎች የክልሉንም የፌዴራሉንም ሥልጣን ተጠቅመው የበዘበዙትን ሀብት ለማስጠበቅ ሲሉነው የድሃ ልጆች አሰልፈው ጦርነት ውስጥ የገቡት። ቡድኑ በደርግ ሥርዓተ መንግሥት አብረውት ሲታገሉ ለነበሩ ጉዳተኞች እንኳን ቦታ የሚሰጥ አይደለም። አሁን የመጣውን ነጻነት ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ወንድሞቻቸው ጋር አጣጥመው የተሻለ ህይወት እንዳያዩ ነው እያደረጓቸው ያለው። እናም የቡድኑ አባላት እራሳቸው ብቻ የኖሩትን ያን ጣፋጭ ኑሮ ለማስቀጠል በማሰብ ነው ወደ ጦርነት የገቡት። ከዚህ ውጪ ግን ሕዝቡ ይህንን ጦርነት በምንም መንገድ አይፈልገውም ከጦርነቱ እንደማይጠቀምም ያውቃል።
ሌላው ወደ ጦርት እንዲገቡ ያደረጋቸው ደግሞ ከእኛ በቀር ማንም የለም የሚል እብሪት እና ተራ ጀብደኝነት ነው። ለዚህ ነው ሁልጊዜ ከአንድ ጦርነት ወደ ሌላ ጦርነት መግባት የሚፈልጉት። ይህ አስተሳሰብ የትግራይን ሕዝብ ሲጎዳው እንጂ ሲጠቅመው አልታየም። አሁን ለጥቂጦች ጥቅም ሲባል ነው ሀገር እየተተረማመሰ ያለው ይህ እንዲሆን ደግሞ ማንም አይፈቅድም።
አዲስ ዘመን ፡- እስከ አሁን የነበረውን የለውጥ ሂደት እንዴት አዩት?
ዶክተር አየለ፡- በዚህ ሦስት ዓመት ውስጥ ስጋትም ተስፋም ታይቷል። ለውጡ ባልጣማቸው አካላት በሚሰሩ ደባዎች ኢትዮጵያ ስትታመስ ከርማለች። ሰዎች በማንነታቸው ምክንያት ተገድለዋል፤ ተፈናቅለዋል ፤ በርካታ ንብረትም ወድሟል። ይህ ሁሉ ግን ላለፉት 27 ዓመታት የተሰራው የፖለቲካ ደባ ያመጣብን ጣጣ ነው። በሌላ በኩል ግን ሀገራችን ተስፋ ተሞልታለች። ተስፋው ምንድነው ካልን የዴሞክራሲ አሰራር መስመር እንዲይዝና ጥልቀት እንዲኖረው በአመራሩ በኩል እየተደረገ ያለው ቁርጠኝነት ነው።
ባለፉት ሦስት ዓመታት ድሮ የነበረው የአንድነትና የመተባበር መንፈስ እየመጣ መሆኑ ያስደስታል። በተለይ የህዳሴ ግድቡ ሥርዓት ባለው መንገድ እየተከናወነ መሆኑና ይዞ የመጣው ተስፋም በሰዎች ዘንድ የፈጠረው ደስታ ቀላል አይደለም። ሕዝቡ ምንም ዓይነት ጫና ሳይደረግበት ሰላማዊና ዴሞክራሲዊ ምርጫ ማከናወኑም የመጪዋን ኢትዮጵያ ተስፋ ያሳየ ጉዳይ ነው። ቁርጠኛና በሀገሩ ጉዳይ የማይደራደር ሕዝብ መሆኑን ለዓለም ያሳየበት አጋጣሚም ሆኗል። ጸረ ኢትዮጵያ አቋም ያላቸው የውጭም የውስጥም ኃይሎች ተስፋ እንዲቆርጡ ያደረገም ነው።
አዲስ ዘመን፡- መስከረም 24 የሚካሄደው የመንግሥት ምስረታ ኢትዮጵያን ወደ አዲስ ምዕራፍ ያሸጋግራታል ብለው ያምናሉ፤ ለለውጥ ኃይሉስ ምን አቅም ይፈጥርለታል?
ዶክተር አየለ፡- የመንግስት ምስረታው ታሪካዊ እና የመጪዋ የኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ የሚወሰንበት ዕለት እንደሆነ ይሰማኛል። በመጀመሪያ ደረጃ የመንግሥት ምስረታው ለሕዝቡም ሆነ ለአመራሩ በራስ የመተማመን መንፈስ ያላብሳል። ያሉትን መሰናክሎች እንዲያስወግድ የበለጠ አቅም ይፈጥርለታል። የውጭም የውስጥም ጠላቶች በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ ላይ ከባድ ጫና ለማሳደር የሚጥሩት የመንግሥት ምስረታውን ለማኮላሸት ነው። የመንግሥት ምስረታው ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚሰሩ ኃይሎችን ቅስም ይሰብራል ከምርጫው ጀምሮ አደናቃፊ ሥራዎችን ሁሉ ለማድረግ ቢጥሩም ሁሉ ታልፎ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ተደርሷል። ሕዝቡ ድምጽ የሰጣቸውን አመራሮቹን ይዞ ሰላሙን በማስጠበቅ ልማቱን የሚያረጋግጥበት አዲስ ምዕራፍ የሚጀምርበት ታሪካዊ ዕለት ነው።
አዲስ ዘመን፡- ሕዝቡ ከአዲሱ መንግሥት ምን ይጠብቅ?
ዶክተር አየለ፡- ታሪካችን እንደሚያስረዳን ጠላት ሊያጠቃን ሲመጣ ዘው ብለን ወደ ጦርነት አንገባም። አደዋን እንኳን ያየን እንደሆን ዘጠኝ ዓመት ድረስ በዲፕሎማሲ ቋንቋ ለማነጋገር ሞክረናል። በርካታ የማግባባት ሥራዎች ተሰርተው አልሆን ሲልነው ወደ ጦርነት የተገባው። አሁንም ዲፕሎሚሲያችንን በማጠናከርና ትክክለኛውን ምስል ለዓለም ሕዝብ በማሳየት የውጭ ኃይሎች ኢትዮጵያ ላይ የያዙትን የተሳሳተ አቋም እንዲቀይሩ አዲሱ መንግሥት መስራት አለበት። የሀገርን ሰላምና ደህንነት በማረጋጋት የሕዝቦችን በሰላም ወጥቶ በሰላም መግባት ማረጋገጥ ይኖርበታል። ሕዝቡ ፊቱን ወደ ልማት በማዞር የኢትዮጵያ ብልጽግና እንዲረጋገጥ የማንቃትና የማትጋት ሥራዎችን መስራት አለበት። የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መፍታት በሕዝቦች መካከል መተባበርና አንድነት እንዲፈጠር በማድረግ ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ደረጃ ማሻገር ከአዲሱ መንግሥት ይጠበቃል።
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን መስከረም 24/2014