ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ መጋቢት 24/2010 ዓ.ም ወደ ስልጣን በመጡበት ወቅት ኢትዮጵያ፣ በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ምስቅልቅል ህልውናዋ አደጋ ላይ ወድቆ እንደነበር የሚታወስ ነው። የወቅቱ መንግስት ተሰሚነት ብሎም ተዓማኒነቱ አጥቶ ውስጣዊ ሰላምና መረጋጋትን ማስፈን ተስኖት ከአንድም ሁለት ጊዜ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማወጅ የተገደደበት ነበር።
ተረጋግቶ መስራትና መኖር አዳጋች የሆነበት፣ እዚህም እዚያም ግጭቶችና ትርምሶች የሚፈሉበት፣ በማንኛውም ቅፅበት ኢትዮጵያ በሁከት ልትናጥ እንደምትችል የምታስፈራበት፣ ኢኮኖሚው ተንገጫግጮ በጣረ ሞቱ ላይ የተገኘበት በተለይ የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ ጫፍ የደረሰበትም ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ስልጣን ከተረከቡ በኋላም በኢትዮጵያዊነቱ የመጣውን ለውጥ ተከትሎም ቀደም ካሉት ዓመታት የተንከባለሉትን ጨምሮ አዳዲስ ችግሮች ተደራርበው በተለይ በመጀመሪያዎቹ ሁለት ዓመታት መንግስትን ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ እንዲያልፍ አስገድደውታል።
ይህንን ምስል በመቀየር ረገድም የጠቅላይ ሚኒስትሩ አመራር ባለፉት ሦስት ዓመታት የተለያዩ ተግባራትን እንዳከናወነ ይነገራል። ለመሆኑ በእነዚህ ዓመታት በተለይ በዲፕሎማሲ፣ በኢኮኖሚና በሰላምና ደህንነት ረገድ የተገኙ ስኬቶችና ድክመቶች ምን ይሆኑ፣ አዲስ የሚዋቀረው መንግስት በእነዚህ መስኮች ምን እንዲሰራ ይጠበቃል የሚል ጥያቄዎች በማንሳት የተለያዩ ምሁራንን አናግረናል።
በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የዲፕሎማሲና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር አቶ እንዳለ ንጉሴ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አመራር ከፍተኛ ልዩነት ከፈጠሩባቸው ጉዳዮች አንዱ የውጭ ግንኙነት ስለመሆኑ ያስረዳሉ። ይህን ጠንቅቆ ለመረዳት ግን ኢትዮጵያ ከሦስት ዓመት በፊት የነበረችበትን ሁኔታ መለስ ብሎ ማስታወስ የግድ ስለመሆኑ አፅእኖት ይሰጡታል።
እንደ ዲፕሎማሲና ዓለምአቀፍ ግንኙነት ምሁሩ ገለፃ፣ ኢትዮጵያ በወቅቱ ገዢ መንግስት በነበረው አሸባሪ የህወሓት ቡድንና አጫፋሪዎቹ ምዕራባውያን ሴራ ሦስት ዓመት በፊት በማህበራዊ በኢኮኖሚያዊና በፖለቲካው መስክ ቅኝ ገዢዎች ባስቀመጡት አቅጣጫ ስትጋዝ ነበር። ተከፋፍላና ተዳክማ አፍሪካንም ሆነ የዓለም ጥቁር ሕዝቦችን እንዳትወክል ተደርጋ ነበር።
በሳይንስ ዲፕሎማሲ የሚወክለው አገርን ነው። ቡድንን ወይንም አንድን መንግስት አይደለም። ይሑንና ከዚህ ቀደም የነበረው ዲፕሎማሲ ወቅቱ በሚመጥነውና በሚፈልገው አቅጣጫ አልተቀረፀም። አሸባሪው ቡድን የኢትዮጵያን ዲፕሎማሲ የሰራው በራሱ ልክ ነው። በትንሽነትና በጠባብነት ነው፡ ፡በኔትዎርክና በቡድን የተደራጀና የመቀመረ ከሁሉም በላይ ለቡድኑም ሆነ ለቅኝ ገዢዎቹ የግል ፍላጎት ብሎም አስተሳሰብ እንዲመች ተደርጎ የተቀረፀ ነበር። ቡድኑ በስልጣን ቆይታው የተንጠለጠለው በምእራቡ ዓለም ላይ ነበር። ጎረቤቱቹን ከወዳጅነት ይልቅ በጥርጣሬ የሚመለከት ነበር።
ይሕም የኢትዮጵያ ምስል በሚገባው ልክ ከፍ እንዳይል አድርጓል። ቡድኑም ኢትዮጵያን የሚያኮስስና የሚያዋርድ ስራ ሲሰራ ቆይቷል። በቅርቡም በግልፅ በአደባባይ ኢትዮጵያን ለማፈራረስ እንደሚሰራ ሳይቀር ሲገልፅ ተሰምቷል። ከኢትዮጵያ ይልቅ ሱዳን ትሻለኛለች ሲል ተሰምቷል።
በሳይንስ ዲፕሎማሲውን የሚጀምረው ከውስጥ በመሆኑ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አመራር ይሕን ምስል ለመቀየር የወሰነው ከውስጥ ነው። በዚህም ተዳክሞ የነበረው ኢትዮጵያዊነት፣ በጋራ መኖርና ህብረ ብሄራዊነት እንዲያገነግን ማድረግ ችሏል።
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ እየተከተለች የምትገኘው ዲፕሎማሲ አቅጣጫም ይሕን ሙሉ በሙሉ ከመሰረቱ የለወጠ ነው። በጠቅላይ ሚኒስትሩ አመራርም ለአሸባሪው ቡድን ታስቦና ተቀርፆ የተሰራው የዲፕሎማሲ አቅጣጫ ኢትዮጵያን እንዲወክል ተደርጓል።
ጥቂት ዲፕሎማቶች የሚሰሩት ስራ ምንም የአገርን ምስል ከፍ ሊያደርግና ብሄራዊ ጥቅምን ሊያስከብር እንደማይችል ታሳቢ በማድረግ በዜግነት ዲፕሎማሲ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በውስጥም ሆነ በውጭ ያለ ለአገሩ የዲፕሎማሲ አካል እንዲሆን እድል ሰጥቷል። የዲፕሎማሲው አቅጣጫና ፍልስፍና መቀየርም ኢትዮጵያውያን የአገራቸው ባለቤት በሁሉም ዘርፎች የዲፕሎማሲ ወኪልና አምባሳደር እንዲሆኑ አድርጓል።
ከሁሉ በላይ ‹‹ያለፈው ሦስት ዓመት ከሁሉ በላይ ምእራቡ ዓለም ቤት ድረስ በመሄድ በፍትሃዊነት የጋራ ጥቅም መበልፀግ ከፈለችሁ በትብብር ለመስራት ፈቃደኛ ነን፣ ከዚህ ውጭ የእናንተን የቅኝ ግዛት አስተሳሰብ አንቀበልም›› የሚል ቆፍጣናና አገር የሚያስከብር ውሳኔ የተወሰነበትና የህዳሴ ግድብ ውሃ የተሞላበት ነው›› የሚሉት አቶ እንዳለ፣ ይሕ አይነት ተግባርም በማንም አፍሪካዊ አገር የማይሞከር፣ የሚያስመሰግንና የሚያኮራ ስለመሆኑ አፅእኖት ይሰጡታል።
ኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ አቅጣጫዋን ማስተካከሏን ስኬት የሚያነሱና በተለይ ለጉረቤት አገራት ቅድሚያ መስጠቷን የሚያደንቁ የመኖራቸውን ያሕል ለጎረቤት አገራት ቅድሚያ መስጠታችንን የሚተቹ ምሁራንም አሉ። ለዚህ እሳቤአቸው አመክንዮ የሚያቀርቡት ደግሞ ‹‹ምእራባውያንን መዘንጋት ኪሳራው ከባድ ነው›› የሚል ነው።
አቶ እንዳለ፣ ከጎረቤት ይልቅ ከዓለም አቀፍ ኃያላን ቅድሚያ መስጠት ያስፈልጋል የሚለው ፈፅሞ አይዋጥላቸውም። ከሩቅ ይልቅ ለጎረቤት አገራት ቅድሚያ መስጠት ትርፍ እንጂ ኪሳራ እንደሌለው አፅእኖት ይሠጡታል።
‹‹ኢትዮጵያ የአፍሪካ ቀንድ እምብርት እንዲሁም ሦስት ታላላቅ አህጉራትን የሚያገናኘው ቀይ ባህር ቀዳሚ ተዋናይ ናት። የምትቀርፀውና የምትተገብረው ዲፕሎማሲ ወደ የትኛውም አቅጣጫ ሳያደላ የመሃሉን መንገድ ይዞ መሄድ አለበት። ብሄራዊ ጥቅሟን ከፍ እስካላደረገ ድረስ ከየትኛውም አካል ጋር መስራት ይጠበቅባታል›› ብለውም ያምናሉ።
እንደ እርሳቸው ገለፃም፣ ትክክለኛ ዲፕሎማሲ የሚጀምረው ከቤት ወይንም ከውስጥ ነው። ከውስጥ ቀጥሎ የሚመጣው ጉረቤት ነው። የኢትዮጵያ ትልቅ ህዝብ፣በርካታ ሃብት ያላት አገር ናት። እነዚህን ሃብቶች የምትጋራው ደግሞ ከጎረቤቶቿ ጋር ነው። ቢያንስ 12 የሚሆኑ ወንዞች ከኢትዮጵያ ተነስተው ወደ ጉረቤት አገራት ይፈሳሉ። እነዚህ ወንዞች ደግሞ የግጭትም የልማትም ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ። በዲፕሎማሲ ጎረቤትን መንከባከብ ራስን መንከባከብ ብሎም ብልህነት ነው። ለራስ ሰላም እና እድገት መሰረት ነው።
‹‹ይሕ እንደመሆኑም ኢትዮጵያ የምትከተለው ዲፕሎማሲ ዘርፈ ብዙና ሁሉንም በአንድ የሚመለከት እንዲሆን ተደርጓል፣ ኢትዮጵያ በጋራ ሰላም እድገትን ለማረጋገጥ ለጎረቤት አገራት ቅድሚያ መስጠት ተገቢነት ያለው ነው፣ ሊጎዳት አይችልም›› የሚሉት አቶ እንዳለ፣ ኢትዮጵያ ከኤርትራ፣ ከጅቡቲ፣ ከሶማሊያ በመስማማት ብሎም ወዳጅነቷን በማስቀጠል እየተጠቀመች እንጂ እየተጎዳች አለመሆኑን ለዚህ በቂ ምስክር መሆኑን ያስገነዝባሉ።
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ያለችበትን ወቅታዊ ሁኔታ ተከትሎ እንዲሁም በተባበሩት መንግስታት ከሰባት ጊዜ በላይ የኢትዮጵያ ጉዳይ ለምክክር ሲጠራ፣ ሙሉ በሙሉ ድጋፍ የሰጡን ምእራባውያን ወይም አሜሪካኖች ሳይሆኑ አፍሪካውያንና አንዳንድ ወዳጅ አገራት መሆናቸውን ማስታወስ እንደሚገባም ሳያስገነዝቡ አላለፉም።
ይሕ እንደመሆኑም በአሁኑ ወቅት ‹‹ኢትዮጵያ የምትሄድበት የዲፕሎማሲ አቅጣጫ በሳይንሱ ከተመለከትነው መቶ በመቶ ትክከል ነው›› የሚሉት የዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ምሁሩ፣ ይሕ ለጎረቤት፣ ለአፍሪካ ብሎም ለአንዳንድ ወዳጅ አገራት የምትሰጠው ቅድሚያ ትኩረት ይበልጥ መጠናከር እንዳለበትም ነው አጽእኖት የሰጡት።
እንደሚታወቀው፣ አሸባሪው የህወሓት ቡድን የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት በመሰንዘር በገሃድ ጦርነት መክፈቱን ተከትሎም ኢትዮጵያ በቡድኑ እብሪትና ጥቃት ምክንያት ሳትፈልግ ጦርነት ውስጥ ለመግባት ተገዳለች። ምእራባውያንና አንዳንድ መገናኛ ብዙሃንም በአንፃሩ ለአሸባሪው ቡድኑ በግልፅ ሲወግኑ እየተስተዋለ ይገኛል። ይሕ የምእራባውያን የተንሸዋረረ እይታ ታዲያ ምሁራን በሁለት አቅጣጫ ይመለከቱታል።
አንዳንዶች የዲፕሎማሲው ሥራ ድክመት አድርገው ይወስዱታል። ‹‹መሰል የአንድ ወገን ውሳኔዎችና ጣልቃ ገብነቶች እንዲበረከቱ ያደረገውና ጫናዎች እዚህ ደረጃ ያደረሱት፣ ትልቁም ትንሹም እንዲሁም ተራ የሚባል መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ሳይቀር እንደፈለገ የሚፈነጨው ዲፕሎማቶቹ በአግባቡ ስራቸውን ስላልሰሩ ነው›› ይላሉ። ሌሎች ደግሞ የግል ፍላጎት ብሎም ድጋፍን መሰረት ያደረገ በአድሎአዊነትና በጫና የተፀነሰ እርምጃ በመሆኑ የዲፕሎማሲ ጥረትም የሚፈታው አይደለም›› ሲሉት ይደመጣል።
አቶ እንዳለ በአንፃሩ፣ ወቅታዊው የምእራባውያን ጫና የዲፕሎማሲ ስራ ድክመት ሳይሆን የሁለት ምክንያቶች ድምር ውጤት ስለመሆኑ ያስረዳሉ። አሸባሪው ቡድን በእኩይ ተግባሩ ለምእራባውያን የተመቸ መሆኑ አንደኛው ሲሆን ከመካከላቸው ይበልጥ የኢትዮጵያን ትንሳኤ የማይፈልጉ መኖራቸው ደግሞ ሌላኛው ነው።
የዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ምሁሩ እንደሚያስረዱት፣ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ብቻ ሳይሆን ለዓለም የነፃነት ምልክት ናት። ይሑንና አንዳንዶቸ ኢትዮጵያ በዚህ ተምሳሌትነት በዓለም አቀፍ ደረጃ እንድትታወቅ አይፈልጉም። ኢትዮጵያ እንደተከፋፈለች እንድትቆይ እንጂ ለውጥ አካሂዳ፣ የህዳሴ ግድብ ሞልታ፣ ምርጫ አካሄዳ መመልከት ፈፅሞ አይፈልጉም።
በአሁኑ ወቅት ምእራባውያኑ ለአርባ ዓመታት የወከሉትና ኢትዮጵያን የሚበጠብጥ ብሎም የሚያሳንሰው አሸባሪው የህወሓት ቡድን በመላ ኢትዮጵያውያን የጋራ ርብርብ መሪር የሽንፈት ፅዋን እየተጎነጨ ወደ መቃብር እየገሰገሰ መሆኑን እጅጉን እያበሳጫቸው ይገኛል። ይሕ በመሆኑም በተቻላቸው መጠን ብስጭታቸውን በማሳየት ላይ ተጠምደዋል። ‹‹ጫናውም የዚህ ሁሉ ድምር ውጤት ነው›› ይላሉ።
‹‹በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ አሁን የያዘችው ዲፕሎማሲ አቅጣጫ በትክክለኛ አቅጣጫ እየተጓዘ ነው፣ አቅጣጫውም በቀጣይ ሁለትና ሦስት መቶ ዓመታት ወደ ፊት የሚያራመድ ነው›› የሚሉት የዲፕሎማሲ ምሁሩ፣ ይበልጥ ጠንክሮ መቀጠል እንዳለበት ሳያስገነዝቡ አላለፉም።
በፈረንሳይ ፓሪስ ‹‹school of advanced studies in social sciences Paris –/EHESs/የፒኤች ዲ ተማሪ የሆኑት ጌታነህ ውድነህ ግን ወቅታዊውን የኢትዮጵያ ሁኔታ በሚመለከት የዲፕሎማሲው ሥራ በድክመት የታጀበ ነው። ይሑንና ‹‹በህዝብም ሆነ በመንግስት የተለያዩ የዲፕሎማሲ ተግባራት ባይከናወኑ በተለይ ከዚህ በላይ ጫናዎችን ሊያስከትል ይችል ነበርም›› የሚል እምነት አላቸው። ባለሙያዎቹ በዲፕሎማሲው መስክ በቀጣይ ሊጠናከርና ሊሻሻል ይገባል የሚሉትን ምክረ ሃሳብም አጋርተዋል።
እንደ አቶ እንዳለ ምክር ሃሳብ፣ የምእራቡ ፕሮፖጋንዳ፣ ሴራ፣ ከፋፍለህ ግዛ እንዲሁም የውክልና ጦርነት ቀጣይነት ሊኖረው ይችላል። ይሕ እንደመሆኑም ጫናውን ለመከላከል የኢትዮጵያውያን አንድነትና የዜግነት ዲፕሎማሲ ይበልጥ ብርቱ መሆን ይኖርበታል። መንግስትም የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም ለማስቀጠል አሁን የያዘውን ትክክለኛና ውጤታማ አቅጣጫ ብሎም አቋም ይበልጥ ማጠናከር ይጠበቅበታል።
በአቶ ጌታነህ ውድነህ ምክር ሃሳብ እንደተመላከተው ከሆነ ደግሞ፣ በአሁን ወቅት ዓለም አቀፍ ተፅእኖና የዲፕሎማሲው ተግዳሮት ከፍታው ጨምራል። ይሕ እንደመሆኑም ቀደም ሲል ሲሰራበት የነበረውን አቅጣጫ መቀየር ያስፈልጋል።
ወቅቱን ያገናዘበና ዓለምአቀፍ የፖለቲካ ምህዋሩን በተከተለና በተመጣጠነ መልኩ ቀደም ሲል ጫናዎችን ለመከላከል ጥቅም ላይ ከሚውሉ እስትራቴጂዎች የተለዩ መንገድን መከተል የግድ ይላል። አገሪቱን በተለያዩ ዓለምአቀፍ መድረኮች ላይ ጠንካራ የመደራደር አቅም ያላት ማድረግ ይገባል። ባለሙያን መሰረት ያደረገ ዲፕሎማሲ ማራመድና ትክክለኛ የመደራደር አቅም ያላቸውን ባለሙያዎች ለዚህ ሥራ መመደብ ያስፈልጋል።
ኢኮኖሚውን ስንቃኝ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ስልጣን ከመምጣታቸው ቀደም ባሉት ሦስት ዓመታት በውስጥዊ መረጋጋት አለመኖር የአገሪቱ ኢኮኖሚ ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ መግባቱ የሚታወስ ነው። በተለይ የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ አቅም ወራትን እንኳን የማይዘልቅ አልነበረም። ሸቀጦች ላይ ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ጭማሪ ተፈጥሮ፣ የኑሮ ውድነቱም በሁለት አሃዝ የሚጠቀስ ሆኖ እንደነበር ይታወሳል።
የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሃብት መምህሩ ፍሬዘር ጥላሁንም፣ ኢትዮጵያ ላለፉት ሦስት ዓመታት አርፋ ማሰብ እስኪከብድ የተጨነቀችበት ወቅት እንደነበር ይስማሙበታል። ‹‹ኢትዮጵያውያን መልካም መልካሙን ወደ ጎን በመተው መጥፎውን ብቻ የምንዘክር መሆናችን እንጂ በተለይ በኢኮኖሚ ረገድ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ አስተዳደር ለማመን የሚከብዱ፣ የተሰሩ የማይመስሉ በሪፖርት ደረጃ ሲቀርቡ የሚያስደነቁ በርካታ ውጤታማ ተግባራት አከናውኗል›› ይላሉ። ለውጡና አመራሩም ዓለም አቀፍ ፋይንናስ ተቋማት፣ የእርዳታ ድርጅቶችና አገራት ሳይቀር ከፍተኛ ድጋፍ ያገኘና እስከ ሦስት ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ያደረገበት መሆኑንም ያስታውሳሉ።
እንደ እርሳቸው ገለፃም፣ዶክተር ዐቢይ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላም፣ ተንኮታኩቶ በመውደቅ ላይ የነበረውን የአገሪቱ አቢይ እና ንዑስ የኢኮኖሚ ዘርፍ ወደነበረበት ለመመለስ የተለያዩ ጥረቶች ተደርገዋል። የኢኮኖሚ አቅጣጫውን መቀየር የሚያስችሉ ጥናቶች ብሎም ፍኖተ ካርታዎች ለማዘጋጀት፣ የወጪ ንግድ ለማሳደግ፣ የንግድ
ሚዛን ጉድለቱን ለማጥበብ እንዲሁም የውጭ ምንዛሪ እጥረቱን በማቃለል፣በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ የአገሪቱን የውጭ ዕዳ ክፍያ ጫናን ለማቃለል የመክፈያ ጊዜን ከአበዳሪዎች ጋር ተደራድሮ ለማራዘም የተሄደባቸው ርቀቶች ይበል የሚያሰኙ ናቸው።
የተቀናጀ የግብርና ውጤት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ማስመረቅ፣ በግብርናው ዘርፍ ምርትና ምርታማነትን ለማሻሻል በመስኖ ማምረት የሚቻልበትን መንገድ መቀየስ በተለይም በቆላማው የአገሪቱ ክፍል የግብርና ምርቶችን ማምረት ከማስቻል አኳያ የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶችም በውጤታማነት የሚጠቀሱ ናቸው።
‹‹በእነዚህና በሌሎችም ተግባራት ባለፉት ሦስት ዓመታት ከሁሉ በላይ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከገባበት አዘቅት ብሎም ይገጥመዋል ተብሎ ከተጠበቀው ከባድ አደጋ ማዳን ተችሏል›› የሚሉት የምጣኔ ሃብት ምሁሩ፣ ኢኮኖሚውን ለማረጋጋት በፋይናንስ ደህንነት ረገድ ከተከናወኑ ድንቅ ተግባራት መካከል የብር ኖት ቅያሬው አንዱ መሆኑን ያስገነዝባሉ።
ስለ ኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ሲነሳ የተለያዩ የምጣኔ ሃብት ምሁራ ያለፉት ሦስት ዓመታት የነበረው ቀውስ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ለውጦች በገሃድ እንዳይታዩ እድል መንፈጉን ሲገልጹ ይሰማል። በዚህ እሳቤ የሚስማሙት አቶ ፍሬዘር እንደሚያስረዱትም፣ በተደጋጋሚ በአገሪቱ ሲከሰቱ የቆዩት የፖለቲካ አለመረጋጋቶች ኢኮኖሚው በፀና መሠረት ላይ ተመሥርቶ እንዳያድግና ፈጣን ዕድገት እንዳይመዘገብ ማነቆ ሆኖበታል። የኮንትሮባንድና የሕገ-ወጥ ንግድ እንዲሁም የኢኮኖሚያዊ አሻጥሮች ከፈተናዎቹ ግንባር ቀደም ሆነው ይጠቀሳሉ።
ባለፉት ሦስት ዓመታት የተከሰቱ ቀውሶች በሰው ሰራሽ ብቻም ሳይሆን በተፈጥሮ ፈተና የታጀቡ መሆናቸውን የሚጠቁሙት አቶ ፍሬዘር፣ ‹‹ከፖለቲካው ጡዘት እና ቀውስ ባለፈ በተፈጥሮ ረገድም በተወሰኑ አካባቢዎች የአንበጣ ወረርሽኝ፣ የዝናብ እጥረትና የጎርፍ አደጋ መከሰቱንም ያስታውሳሉ። ይሕ በሆነበት ‹‹የአገሪቱ ኢኮኖሚ ዛሬ ባለበት ደረጃ ላይ ማድረስ አይደለም፣ እድገቱ ቀርቶ በነበረበት ማስቀጠል መቻል በራሱ እንደትልቅ ስኬት መቆጠር አለበትም›› ይላሉ።
ፖለቲካዊ ቀውሱ እንዳለ ሆኖ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጉዳት አስከትሏል። በተለይም የአምራች ዘርፉን በመፈተን፣የውጭ ንግድና በቱሪዝም አገልግሎት ላይ የጎላ የተባለውን ተፅእኖ አሳድሯል። ዓለምአቀፍ ተቋማትም በወቅቱ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በወረርሽኙ ተጽዕኖ ደርሶበት ሁለት በመቶ ገደማ ብቻ እድገት እንደሚያስመዘገብ አስታውቀው ነበር።
አቶ ፍሬዘር እንደሚገልፁት ከሆነ ግን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እንደ ሌሎች አገራት ኢትዮጵያ ላይ ብርቱ ጡንቻውን ማሳየት አልቻለም። ‹‹ሌላው ቀርቶ ምንም እንዳልተፈጠረ ሆነው የዘለቁ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶችን አስመልክቶናል›› የሚሉት የምጣኔ ሃብት ምሁሩ፣ የኮሮናን ቫይረስ ሁለንተናዊ ተፅእኖውን ተቋቁሞ መቀጠል በራሱ ትልቅ ስኬት ስለመሆኑም አፅእኖት ይሰጡታል።
የፌዴራል መንግስትም ቢሆን የወረርሽኑ ተጽእኖ እንደተፈራና እና እንደተገመተው ጉዳት አለማድረሱን በመግለፅ፣ ኢትዮጵያም በዓመቱ ስድስት በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገቧን ይፋ አድርጓል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድም የዚህ ዕድገት መሠረቱ አገር በቀል ኢኮኖሚ ፖሊሲው እንደ ሆነ ደጋግመው አንስተዋል።
ባለፉት ሦስት ዓመታት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከመስመር እንዳይስት በማድረግ ረገድ የተሰሩ ተግባራት እንዳሉ ሆነው ደካማ አፈፃፀም የታየባቸውና ለማስተካከል ያልተቻሉ ችግሮችም የተለያዩ የምጣኔ ሀብት ምሁራንን በአንድ ድምፅ ያስማማል።
‹‹መልካም ነገሮች እንደነበሩ ሁሉ ያጋጠሙ ተግዳሮችም በርካታ ናቸው›› የሚሉት ምሁራኑ፣ የኢኮኖሚው አለመረጋጋት ከፍተኛ የገበያ ዋጋ ንረትን፣ ሥራ አጥነትና እንዲሁም የውጭ ምንዛሬ እጥረት መሠረታዊ የሚባሉት ግብአቶች አቅርቦቶች ሳይቀር በሚፈለገው መጠን ለማስገባት ማነቆ እስከመሆን መሻገሩንም ይገልፃሉ።
በተለይ የኑሮ ውድነትን በማረጋጋት ረገድ የተከናወኑ ተግባራት ውጤታቸው የሚያረካ አልሆነም። የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መንግስት በከፍተኛ መጠን ከተፈተነባቸው ችግሮች መካከል አንዱም የዋጋ ንረት፣ የኑሮ ውድነት ነው። መንግሥት የዋጋ ንረት አሳስቦት ወደ ነጠላ አኃዝ ለመቀየር ዕቅድ አስቀምጦ የነበረ ቢሆንም፣ ላለፉት ሦስት ዓመታት ዕቅዱን ማሳካት ብሎም የዋጋ ንረትን መቆጣጠር አቅቶታል።
አቶ ፍሬዘርም በዚህ ይስማማሉ። ይሑንና የኑሮ ውድነቱ ከዚህም በበለጠ መልኩ እንዳይቀጥል በታክስ ላይ በተደረጉ ማሻሻያዎች፣ የዋጋ ቁጥጥር ላይ የሚሰሩ ተግባራትን ጨምሮ የተለያዩ ጥረቶችን ስለመታዘባቸው ይጠቁማሉ። እነዚህ ተግባራት እንዳሉ ሆነው ግን፣ የኑሮ ውድነት ችግሩ በአሁኑ ወቅት ወቅታዊ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ከባድ ራስ ምታት እና ፈተና ስለመሆኑ አፅእኖት ይሰጡታል።
አገሪቱ የገባችበት ቀውስ ፈር እየያዘ ሲመጣም በሁሉ ረገድ ለውጦች እንደሚኖሩ ጥርጥር ባይኖቸውም ይሑንና ሁለንተናዊ ኢኮኖሚውን በማሳደግ በተለይም ወቅታዊውን የኑሮ ውድነት ፈር በማስያዝ ረገድ አዲሱ መንግስትም ከባድ የቤት ሥራዎች ጠረጴዛው ላይ እንደሚጠብቁት ነው ያሰመሩበት። አቶ ፍሬዘር፣የአገሪቱን ኢኮኖሚ በማጎልበት ረገድ አዲስ የሚመሰረተው መንግስት ቀጣይ የቤት ስራውን በስኬት ለማጠናቀቅ ማድረግ ስለሚገባው ተግባራት ሲጠቁሙም፣ የትኩረት አቅጣጫን በመወሰን በተለይም አገሪቱ ያላትን ሃብትና እምቅ አቅም ቅድሚያ መለየት እንዳለበት ነው ያስገነዘቡት።
እንደ እርሳቸው ገለፃም፣ ሁለት እግር አለኝ ተብሎ ሁለት ዛፍ ላይ መውጣት አይታሰብም። አምራች የሚባለውን ዘርፍ መለየት ብሎም መምረጥ የግድ ይላል። በተለይም የአገሪቱ ሁነኛ የሃብት ምንጭ ለሆነው ግብርና ዘርፍ ከፍተኛ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል። ምክንያቱም ግብርናው ሲዘምን ለኢንዱስትሪ ግብአት ይሆናል። የምግብ ዋስትና ችግር ይቀርፋል። አገሪቱ ከራሷ አልፋ ወደ ውጭ የተለያዩ ምርቶችን እንድትልክና በዚህም ተጠቃሚ እንድትሆን አቅም ይፈጥራል። አገሪቱ ከውጭ ምርቶችን ለማስመጣት የምትገፈግፈውን ከፍተኛ መጠን ያለው የውጭ ምንዛሬ ለማስቀረት ያስችላል።
በመሆኑም አዲስ መንግስት አመራርና ህዝብ በቁርጠኝነት፣ በጋራ አላማና ግብ ውጤታማ ለመሆን በገጠርም ሆነ በከተማ ከዓመት ዓመት ማምረት ብሎም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በተለይም ለዘመናዊ ግብርና ልዩ ትኩረት መስጠት የግድ ይላቸዋል። የአገሪቱን እዳ በማቃለል ረገድም በተለይ የዲፕሎማሲ አቅምን ይበልጥ በመገንባት እዳ ከማራዘም ባሻገር እዳን ማሰረዝ የሚቻልባቸው ሁኔታዎች መፍጠር ይገባል።
አዲስ የሚመሰረተው መንግስት ባለፉት ሦስት ዓመታት በኢኮኖሚ ዘርፍ ፈተና የሆኑበት ኢ ፍትሃዊ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት፣ የኑሮ ውድነት፣ የስራ እጥነት፣ አገራዊ የእዳ ጫናን እንዲሁም የውጭ ምንዛሬን ችግሮችን መፍታት ላይ እንደሚያተኮር አሳውቋል።
ከቀናት በፊት በተካሄደው ‹‹የአዲስ ወግ›› የውይይት መድረክ ላይ የፕላንና ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ፍፁም አሰፋ ‹‹አዲስ የሚመሰረተው መንግስት፣ ማህበራዊ ፍትህን ማስፈን፣ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ማረጋገጥ፣ የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋትን ማስፈን ዋና የትኩረት አቅጣጫ አድርገን ይሰራል፣ እነዚህም ከኢኮኖሚ አንፃር ዋና ዋና ተብለው የተያዙ ግቦች ናቸው ሲሉ››ተደምጠዋል።
ሰላም እና ደህንነትን ስንመለከት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ባለፉት ዓመታት የስልጣን ቆይታቸው ለኢትዮጵያ ፖለቲካ ስክነት ብሎም ለህዝብ ሰላምና ደህንነትን ዋስትና በተለይም የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት ረገድ የተለያዩ ተግባራትን አከናውነዋል።
ከሁሉም በላይ ከሀገር ውጪ ነፍጥ አንግበው ሲታገሉ የነበሩና ‹‹በአሸባሪነት›› የተፈረጁ ፓርቲዎች ‹‹ከአሸባሪነት መዝገብ ተፍቀው›› ወደ ሃገር እንዲገቡ ተደርገዋል። የፖለቲካ አመራር እስረኞችን ፈተዋል። የፖለቲካ ፓርቲዎችን ‹‹ተፎካካሪ›› እያሉ ጠርተዋል። አብረው እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።
ድምፅና ምስላቸውን ለማፈን በርካታ ገንዘብ ይወጣባቸው የነበሩ ሚዲያዎችን አገር ውስጥ ገብተው እንዲሰሩ አድርገዋል። ታግተው የነበሩ በርካታ ድረ ገፆችንና ጦማሮችን ነጻ ለቀዋል። እነዚህ ውሳኔዎች ተከትሎም መንግስትን በመቃወም ለበርካታ ዘመናት በውጭ አገራት ተሰደው የኖሩ ግለሰቦችና ድርጅቶችም ሳይቀር ወደ ኢትዮጵያ ገብተዋል። አንዳንዶቹም ከለውጡ ጎን ቆመዋል።
በዚህ ሂደትም የተገኙ አዎንታዊ ለውጦች የመኖራቸውን ያህል በርካታ አሉታዊ ክስተቶችም ተከስተዋል። በተለይ ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ንጹሃንን ዒላማ ያደረጉ በርካታ ጥቃቶች ተሰንዝረዋል። ዜጎች ሀብትና ንብረት ካፈሩባቸው ቀያቸው ተፈናቅለዋል። ተደጋጋሚ ጥቃትና ሞት ደርሷል። የዜጎች ሰብአዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ተጥሷል።
ኅዳር ወር 2013 በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይም፣ ማዕከላዊ መንግስቱና ህወሓት የገቡበትን ግጭት ሳይጨምር በሁለት ዓመት ተኩል ውስጥ በሁሉም የአገሪቱ ክልሎች በድምሩ 113 ግጭቶች ከትግራይ ክልል በስተቀር መከሰታቸውን ገልጸዋል።
የተለያዩ ምሁራንም፣መንግስት ባለፉት ሦስት ዓመታት የዜጎችን ደህንነት በመጠበቅና ሰላምና መረጋጋትን ከማስፈን አኳያ ድክመቶች እንደነበሩበት ሲናገሩ ተደምጠዋል። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ጥቅምት 24/2013 በነበራቸው መደበኛ ስብሰባ ባልተለመደ መልኩ በእንባና በቁጣ ታጅበው መንግስት የዜጎቹን ደህንነት እንዲጠብቅ መጠየቃቸውና ማሳሰባቸው የሚታወስ ነው።
ለመሆኑ ባለፉት ሦስት ዓመታት የህዝብን ደህንነት በማስጠበቅ ህግና በማስከበር ረገድ የመንግስት ተግባራት እንዴት ተመለከቱት ስንል ጥያቄ ካቀረብንላቸው ምሁራን መካከልም የዋቻሞ ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህር ፀጋዬ ደመቀ አንዱ ናቸው።
እርሳቸውም፣«በጠቅላይ ሚኒስትሩ አመራር ባለፉት ዓመታት በተለይ የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት ረገድ እንዲሁም ከህግ አንጻር በርካታ ማሻሻያዎች ተደርገዋል። የተለያዩ ሥራዎች ተከናውነዋል። በዚህም የተለያዩ ለውጦች ተገኝተዋል። ከዚህ በተቃራኒም በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የተለያዩ ቀውሶና ጥፋቶች ደርሰዋል›› ይላሉ። መሰል ቀውሶም በተለይም መንግስት በሽግግር ወቅት ላይ በሚሆኑበት ወቅት መከሰታቸው የማይቀር መሆኑን ያስገነዝባሉ።
ከሁሉ በላይ በአገሪቱ የተከሰቱ ቀውስና ጥፋቶች ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ የመንግስት እጅ ለመጠምዘዝ ለውጡን ለማደናቀፍ የተጠነሰሱ ስለመሆናቸው አፅእኖት የሚሰጡት አቶ ፀጋዬ፣ ይሑንና በመንግስትም በኩል በተገቢው መንገድ አስቀድሞ መከላከል ብሎም አፋጣኝ የሆኑ እርምጃ በመውሰድ ረገድ ግልፅ ድክመት መስተዋሉንም ይጠቁማሉ።
በአብዛኛው ችግሮች ከደረሱ በኋላ ምላሽ ለመስጠት መረባረብ ማስተዋላቸውን የሚገልፁት ምሁሩ፣ ለደረሰው ቀውስ ተዋናይ የሆኑትን በጊዜ በህግ ቁጥጥር ስር ማዋል ቢቻል አደጋውን መቀነስ ይቻል እንደነበርም ያሰምሩበታል። በአሁኑ ወቅት አገሪቱ ለገባችበት ቀውስ አትዳረግም ነበርም›› ይላሉ።
በተለይ ህግና ሥርዓትን በማስከበር ረገድ የህወሓት የሽብር ቡድን ዋነኛ ተዋናይ የነበሩ አመራሮች ላይ እርምጃ መውሰድን ጨምሮ በህይወት የተያዙትን በህግ ጥላ ስር እንዲገቡ በማድረግ ረገድ የተከናወኑ ተግባራትን ቀሪ ስራዎች እንዳሉ ሆነው በስኬታማነት የሚነሱ መሆናቸውን ያስረዳሉ።
መንግስት በሁለት እግሩ መቆም ሲጀምር ያለፉ ቀውሶች ሊደገሙ እንደማይገባ የሚያስገነዝቡት የህግ ምሁሩ፣ አዲስ የሚመሰረት መንግስት ልማት ሊኖር የሚችለው አገርና ህዝብ ሲኖር መሆኑን ይበልጥ መረዳት እንዳለበትና ከልማት ሁሉ በፊት ለህዝብ ደህንነትና የዜጎች መብት መከበር ቅድሚያ ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባውም ነው አጽእኖት የሰጡት።
በአዲስ የመንግስት አደረጃጀት በተለይ የአገሪቱን ደህንነት የሚመሩ ሰዎች በጣም ጠንካራ አቅም ያላቸውና የአገሪቱን ሰላም ማረጋገጥ አስፈላጊን መስዋትነት ለመክፈል የተዘጋጁ መሆን እንዳለባቸው የሚያስገነዝቡት የህግ ምሁሩ፣ ይሕ ሳይሆን ቀርቶ ግድያና መፈናቀሉ የሚቀጥል ከሆነም እንደ ከዚህ ቀደሙ መንግስትን የሚታገስ ህዝብ ላይኖር እንደሚችል ታሳቢ ማድረግ እንደሚያስፈልግም ሳያስገነዝቡ አላለፉም።
እንደ እርሳቸው ሁሉ የአገረ መንግስቱን ፅኑእነት ለማረጋገጥ አገራዊ አቅሙን መሰረት ባደረገ መልኩ በጸጥታና ደህንነት ረገድ ቆራጥና ተጨባጭ መሆን ይጠበቅበታል የሚሉም በርካቶቸ ናቸው። ከቀናት በፊት በተካሄደው ‹፣የአዲስ ወግ››ውይይት መድረክ ላይ የታደሙት በመከላከያ ሚኒስቴር የጥናትና ምርምር ማእከል ዳይሬክተር ኮሎኔል ፍቅረእየሱስ ከበደ በዚህ እሳቤ ይስማማሉ።
‹‹እንደ አገረ መንግስት ለመቀጠል በተለይ ለህልውና ለሉአላዊነት እንዲሁም ብሄራዊ ጥቅሞችን ለማከበርና ለማስጠበቅ ልዩ ትኩረት ማድረግ ግድ ስለመሆኑ አፅእኖት የሚሰጡት ኮሎኔሉ፣ ‹‹ቀጣዩ ጉዞም እነዚህን በአንድነት አስተሳስሮ የሚደረግ ይሆናል ነው›› ያሉት።
ይሁንና ለዚህ ትግበራ የፀጥታና ደህንነት ተቋማት ነጻና ገለልተኛ መሆን የግድ መሆኑን በርካቶ ይስማሙበታል። በዚህ የሚስማሙት ኮሎኔል ፍቅረእየሱስም፣ለዚህም የመከላከያ ሰራዊት ግንባታውን ጅማሮ ማሳያ ያደርጋሉ። «በሰራዊት ግንባታ እስትራቴጂው ላይ የሚመሰረተው ሰራዊት ከማንኛውም የፖለቲካ ወገንተኝነት ነፃ የሆነ ነው፣ ይሕም ነፃነት እንዲኖው፣ ተልእኮና ግዳጁ ላይ እንዲያተኩር፣ ተቋሙም እንደ ተቋም ቀጣይነት እንዲያረጋገጥ ያደርገዋል ነው›› ያሉት።
የፀጥታና የደህንነት ተቋማት የኢትዮጵያ ውክልና ያለባቸው እንዲሆኑ ማድረግ ወሳኝ መሆኑም ይነሳል። በመከላከያ ሚኒስትር የጥናትና ምርምር ማእከል ዳይሬክተር ኮሎኔል ፍቅረእየሱስ፣መከላከያ የሁሉም ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ተዋፅኦ ያረጋገጠ መሆን አለበት፣ ተቋሙ የአንድ ወይንም የተወሰኑ ብሄሮች ሳይሆን የሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚሳተፍበት ብሎም ተዋፅኦውን የሚያረጋግጥበት መሆን መቻል አለብትም ነው›› ያሉት።
የኢትዮጵያ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ስር የሰደዱና ረጅም ዘመናት ያስቆጠሩ በመሆናቸው ችግሮቹን ለመፍታት ጊዜ የሚወስዱ ቢሆንም ‹‹አዲስ መንግስት ግን በፍጥነት ወደ መፍትሄዎቹ መራመድ ይገባዋል›› የሚለው የአስተያየት ሰጪዎቹ የጋራ እሳቤ ነው።
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን መስከረም 24/2014