አሸባሪ ህወሓት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት በመሰንዘር የእናት ጡት ነካሽ መሆኑን በሚገባ ካስመሰከረበት ቀን ወዲህ መላው ኢትዮጵውያን በተባበረ ክንድ አሳደው በመቅበርና ወደተፈጠረበት የጥፋት በርሃም እንደመለሱት ይታወቃል። ሆኖም ሳይንሳዊ በሆነው ጦርነት ሲሸነፍ በንጹሃን ላይ የፈሪ በትር በማሳረፍ በአማራ እና አፋር ክልሎች ጭፍጨፋ ፈጽሟል። በደቡብና ሰሜን ወሎ ዞኖችም ጉዳት አድርሷል። በአሁኑ ወቅት አከርካሪው እየተመታ ቢሆንም አሁንም በፍርሃት እየተሹለከለከ የሚያደርሳቸው ጥፋቶች መኖራቸው ይታወቃል። በዛሬው እለትም አሸባሪው ህወሓት ወረራ ከፈፀመባቸው ዞኖች አንዱ የሆነው ደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሠይድ ሙሐመድ ጋር ቆይታ አድርገን ስለሁኔታው ሃሳባቸውን አካፍለውናል፤ መልካም ቆይታ።
አዲስ ዘመን፡- አሸባሪው ህወሓት የሀገር መከላከያ ሰራዊትን ለማጥቃትና አማራን ለመውረር ያሰበው ምን ዓላማ አንግቦ ነው?
አቶ ሰይድ፡– አሸባሪው ህወሓት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም የፈፀመው አስነዋሪ ተግባር በደንብ ታሪካዊ ስሪቱንና ባህሪውን ለተገነዘበ ብዙም ላያስገርም ይችላል። እኔ ባህሪውን ከ1967 ዓ.ም ማኒፌስቶ ጀምሮ ስመረምረውና ዓላማው ምን ለማሳካት እንደተጓዘ አንብቦ እንደተገነዘበ ሰው ስወስደው የሚጠበቅና ከባህርይው የሚመነጭ እንደሆነ ይገባኛል። ጁንታው የተመሰረተው ታላቋ ትግራይን የመመስረትና የመገንባት ዓላማ ይዞ ነው። ይህን ለማሳካት ደግሞ ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር ይዞ ዋንኛ ግቡን ለማሳካት መጠቀም ነው።
ከመሃል አገር አስፈላጊውን ካፒታል ወደሚፈልጉበት ቦታ ማንቀሳቀስና የኢኮኖሚ አሻጥር መሥራት ብሎም ኢ-ፍትሃዊ አሰራር ማንገስ ነበር። ላለፉት 27 ዓመታት ሠብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብት ጥሰት፣ የሥነ ልቦና ውድቀት እንዲፈጠር ሲሰሩ ነበር። ታላቋን ትግራይ ለመመሥረት ሲባል ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም። ይህን ዓላማ ለማሳካት ደግሞ እንደ ህዝብ አማራ አንድ ሆኖ እንዳይቆም በሥነ ልቦና መከፋፈል ኢትዮጵያኖች በአንድነት እንዳይቆሙ በሃይማኖት፣ ቋንቋ፣ ባህልና ጎጥ የተከፋፈሉ ያነሱና የተደቆሱ እንዲሆኑ ያልተገባ ትርክት ሲያስተላልፍ ቆይቷል።
በርካታ ሀገራት የሚፈልጉትን ለማሳካት፣ ለመከበርና ለመደመጥ ሲያስቡ ቀድሞ አራት ነገሮችን ይፈጽማሉ። የመጀመሪያው የመከላከል አቅምን ማሳደግ ሲሆን ሁለተኛው የተማረ የሰው ኃይል መፍጠር ነው። ሦስተኛው የቴክኖሎጂ አቅም ማሳደግ ሲሆን አራተኛው የኢኮኖሚ አቅምን ማጎልበት ነው። አሸባሪው ህወሓትም ዓላማውን ለማሳካት የሀገር መከላከያን ማዳከምና መምታት ብሎም እነርሱ ሊገነቡ ለሚፈልጓት ሀገር ስጋት እንዳይሆን ማድረግ እንደ አንድ ወሣኝ ነገር ወስደውት ስለነበር ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ያንን ዘግናኝ ጭፈጨፋና ታይቶ የማይታወቅ ክህደት በሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ አድርሰዋል። እኔም እንደ አንድ ዜጋ እና አመራር ሳስበው ድርጊቱ እጅግ ልብ የሚሰብር ከኢትዮጵያዊነት ያፈነገጠና አስናዋሪ ድርጊት መሆኑን እገነዘባለሁ።
አዲስ ዘመን፡- አሸባሪ ህወሓት በወሎ ህዝብ ላይ በተለየ ሁኔታ ያደረሰው ጉዳት ምንድነው ይላሉ?
አቶ ሰይድ፡– አሸባሪው ህወሓት ባለፉት 27 ዓመታት በኢትዮጵያ ላይ ቦታዎችን ለይቶ ህዝብን ጨቁኗል። በተለይ ደግሞ ወሎ ህዝብ ላይ ያመጣው ጣጣና ጉዳት ስፍር ቁጥር የለውም። የወሎ ህዝብ በታሪኩ እንደሚታወቀው በዘመነ መሳፍንትም ብዙ ግለሰቦችን የፈጠረና በሀገረ መንግስት ግንባታ ትልቅ ሚና ያላቸውን ሰዎች ያፈራ ነው። አንድ ማዕከላዊ መንግስት ሲመሰረትም ሆነ በተማሪዎች ንቅናቄም ትልቅ ድርሻ ያበረከተ አካባቢና ህዝብ ነው። በአሁኑ ወቅትም የተከበሩ አባቶች፣ ምሁራን ብሎም አመራሮች የወጡበት አካባቢ ነው። ሀገረ መንግስት ላይ የሚደራደር ህዝብ አይደለም።
የወሎ ህዝብ በማናቸውም ሁኔታዎች ውስጥ ኢትዮጵያዊነትን የሚያስቀድምና የማይደራደር ሰውኛ ባርይን ማዕከል የሚያደርግ ህዝብ ነው። ለወሎ ህዝብ ሰው መሆን በቂ ነው። ሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች በጋራ የሚኖሩበት አካባቢ ናት። ሌላው ቀርቶ በአሁኑ ወቅት ጦርነት በአማራ ህዝብና ኢትዮጵያ ላይ ታውጆ በርካታ የትግራይ ተወላጆች በኮምቦልቻ እና ደሴ ይኖራሉ፤ ዞርም ብሎ የሚነካቸው የለም። ሰው የሚለካው በአዋዋሉ እና በተግባሩ ነው። ምልከታው እጅግ ጥልቅና ረቂቅ ተራማጅ እሳቤ ያለው ማህበረሰብ ነው። ስለዚህ የሚወደው እሴቱን በመቀማት ነው የጎዳው። ህወሓት አንዱ ጥቃት ያደረሰው ዋናው እሴቱን በመቀማት ነው። ቀምቶ ጨርሷል ወይ የሚለው ግን ሌላ ጉዳይ ነው፤ እንደፈለገው አይሳካም። እሴቱን በመቀማት ነው የጀመረው።
ኢትዮጵያዊነቱን ለኢትዮጵያ ያለውን ክብር ለኢትዮጵያ የሚከፍለውን ጀግንነቱን በማዳከም ነው ጥቃት የፈፀመው። ስለዚህ የሥነ ልቦና እሴቱን ቀምቷል። ወሎ ላይ ሙስሊም እና ክርስቲያን ተጋብቶ ተዋልዶ የሚኖርበት ነው። እኔ ራሱ እናቴ የክርስትና እምነት አባቴ ደግሞ የእስልምና እምነት ተከታይ ሲሆኑ እኔ የእነርሱ ፍጡር ነኝ። ግን ይህ ህዘብ ያልተገባ ፍረጃ እየተሰጠው እርስ በእርስ እንዲጠራጠርና ሰው በነፃነት እምነቱን እንዳይከተል ተደርጓል። ወሎ ብዙ ጸጋ ያለው ቢሆንም ሰው ሰርቶ ከመለወጥ ይልቅ በባህር ላይ ወደ አረብ ሀገር እንዲሰደዱ የተደረገበት ዘመንም ነው።
ባለፉት 27 ዓመታት የኢኮኖሚ አሻጥር ከተሰራባቸው አካባቢዎች አንዱ ወሎ ነው። ትክለለኛ በጀት እንዳያገኝ፣ የመንገድ መሰረተ ልማት እንዳይሟላ በአንጻሩ የቴክኖሎጂ እድገትና ሽግግር የሚያመጡ ፕሮጀክቶች ወደ አካባቢው እንዳይሄዱ በማድረግና በአንፃሩ የእርዳታ እህል በመስፈር አካባቢውን ያደቀቀው ህወሓት ነው። ስለዚህ አሸባሪው ህወሓት የወሎን ህዝብ እሴት በመቀማት፤ ኢኮኖሚውን በማድቀቅ እና ማህበራዊ ኑሮውን በማናጋት ግፍ ሠርቶበታል።
በአሁኑ ወቅት በርካታ የወሎ ወጣቶች በየመንገዱ ጫት ሲቅሙ ሲጠነዝሉ ይውላሉ። ጫት መቼ ነው ወደ አካባቢው የመጣው፣ ለምን መጣ፣ ዓላማውስ ምንድን ነው የሚሉት ጉዳዮች ብዙ ጥናትና ክትትል የሚፈልግ ቢሆንም ወሎን እንደ ህዝብ ቀጣይነት ባለው መንገድ ትውልዱ ነቅቶ ራሱን እንዳይከላከል ለሀገርም ጠቃሚ እንዳይሆን በጫትና ሱስ ውስጥ ጠንዝሎ እንዲውል የተደረገው የህወሓት አንዱ ሴራ ነው። የጤፍ እና ፍራፍሬ መሬታችን ወደ ጫት ማምረት ተቀይሯል። ይህ ሆን ተብሎ የተደረገ ሲሆን፤ በትግራይ ክልል ጫት ማብቀል በህግ የተከለከለ ነው። በወሎ ህዝብ ላይ የተሰናሰለ ሴራ ሲሠራ ቆይቷል።
በወሎ ትልልቅ እሴቶች አሉ። በክርስትና ብንወስድ እጅግ ጥልቅና ረቂቅ እሴቶች አሉ። የግማደ መስቀሉ ቀኝ ክንፍ የሚገኝበት ግሸን ደብረ ከርቤ፣ የኢትዮጵያ የመጀመሪያ ዩኒቨርሲቲ የሚባለው ሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳም፣ ተድባበ ማርያም፣ መስቀለ ክርስቶስ እና የመሳሰሉት እሴቶች ያሉበት ትልቅ ታሪካዊ አካባቢ ነው። ነገር ግን አርተፊሻል (ሰው ሠራሽ) መስቀል በመሥራትና መቀሌ ላይ በመስቀል ‹‹ጎግል›› ላይ በማስገባትም ግሸን እንዳናከብር መስቀሉ ያለው ከእኛ ዘንድ ነው በሚል የሚያጭበረብር ታሪክና እሴት የሚቀማ ጁንታ ነው።
በእስልምናም የመጀመሪያው መውሊድ የወጣበት እዚህ የኢትዮጵያ ጀማ ንጉስ ነው። እነ ሙፍቲ ሃጂ ዑመር፣ መሻሂቆች፣ ትልልቅ አባቶች የፈለቁት ቦረና፣ ደገም፣ ደባቶች፣ ጫሊ፣ ገታ፣ ምስላይ የወጡበት ነው። የዛሬውንም የነገውንም ሲተንብዩ የነበሩ ዓይናማው ሼህ ሁሴን ጅብሪል የፈለቁበት ምድር ነው። ይህን እሴት ሲቀማ ነበር። ይህን እሴት በመውሰድ እንዳንንከባከብ፣ ዞረን እንዳንመረምር፣ እንዳላማው እንዳንጠይቅ ወደ ራሱ በመውሰድ በደል ፈጽሟል።
በእስልምና ነጃሺ ትልቅ ታሪክ ያለው ነው። ነገር ግን ትልቁ ታሪክ የሚቀዳበትን ምድር ትቶ ሁኔታውን ወደዚያ ጎትቶ ወስዶ ታሪክ ሲሻማ ነበር። በክርስትናም እያደረገ የነበረው ይህንን ነው። ሁሉንም የሃይማኖት እሴቶችን ሲቀማ ነው የኖረው። በሥነ ጥበብም አንቺሆዬ፣ ባቲ፣ አምባሰል እና ትዝታ መገኛው ወሎ ምድር ነው። የሰው ዘር መገኛ ‹‹ሃዳር›› የተሰኘው መገኛም አጎራባች ቦታ ነው። ስለ ሰውነትና ሰላም ሲወራ ይህን አካባቢ አለማንሳት አይቻልም፤ ጥልቅ ትንታኔ ያለበት ቦታ ነው። ታዲያ አሸባሪው ህወሓት በዚህ ምክንያት የዜጎችን ሰብዓዊ መብት ጥሷል፣ ብዙዎችን ገድሏል፣ አኮላሽቷል፣ አሰቃይቷል፣ ከአካባቢውም እንዲፈናቀል አድርጓል። ባለፉት 27 ዓመታት ሁሉንም ስቃዮችና ጸያፎች በወሎ ምድር ላይ አድርሷል።
አዲስ ዘመን፡- አሸባሪው ህወሓት የወሎን ህዝብ መልካም እሴት ለጥፋት መጠቀሚያ አድርጓል ለሚለው ማሳያ ምንድን ነው?
አቶ ሰይድ፡– ወያኔ ጠላቴ ናቸው ብሎ ከፈረጃቸው አንዱ የአማራ ህዝብ ነው። ይህም አንድ ጎረቤት በመሆኑ፣ ሁለተኛው ህዝብ ብዛት ስላለው እና ሦስተኛው የአሸናፊነት ሥነ ልቦና እና ታሪክ አለው ብሎ ስለሚያስብ ነው። ይህ ህዝብ በዚህ ከቀጠለ ለሚመሰርታት ታላቋ ትግራይ እንቅፋት ይሆናል ብሎ ያስባል። ይህንንም በማኒፌስቶ ለይቷል።
ሁለተኛው ጠላቴ ብሎ ያሰበው ትልልቅ የሃይማኖት አባቶችና ተቀባይነት ያላቸው ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦችን ነው። በተለይ ህዝብ የሚያዳምጣቸውና የሚከተላቸው ከሆነ ጠላት ብሎ ይፈርጃል። ወሎ ላይ ያደረገው በእስልምናም በክርስትናም ይህንን ነው። ወሎ እስላምና ክርስቲያኑ በአንድ የሚኖር ነው። ድራማ በመስራትና ያልተገባ ፍረጃ በመስጠት እርስ በእርስ እንዲገዳደሉ ከሁሉ በላይ ሙስሊም እና ክርስቲያኑ በጥቃቅን ጉዳይ እንዲጋጭ ያልተጎነጎነ ሴራ የለም።
በወሎ ላይ በሃይማኖት መጋጨት አይቻልም። ከተቻለም ቤት ውስጥ ነው የሚጀምረው። ምክንያቱም ሁሉም ሃይማኖቶች ቤት ውስጥ አሉ። ልጅ የፈለገውን ሃይማኖት ነው የሚመርጠው። እናት አባት የፈለጋቸውን ሃይማኖት ነው ይዘው የሚኖሩት። ሰው መሆን በቂ ስለሆነ በፍቅር ይኖራሉ። በመሆኑም ግጭት ከተነሳ ቤትነው የሚጀምረው። የሃይማኖት ግጭት ከተጀመረ ደግሞ እጅግ የከፋ ሁኔታ የሚስተናገድበት አካባቢ ይሆናል። ምክንያቱም ከቤት ስለሚጀምር። ሩዋንዳ ውስጥ ሁቱ እና ቱትሲን እርስ በእርስ ለፍጅት ያበቃቸው መጀመሪያ አንድ የሚደርጋቸውን እሴት ጨምቀው አወጡ።
ወሎንም ያልተገባ ግጭት ለማስገባት ሙስሊምና ክርስቲያኑን አንድ አድርጎ በጋራ የያዘውን እሴቱት ቀለም በመቀባባት ላለፉት 27 ዓመታት ለማጋጨት ሲጥሩ ነበር። አሁን በጥቂቱ የሚስተዋሉበትም የተሰራበት ደባ እና ሴራ ነው። አንዳንዶቹ የወሎን እሴት የማያውቁ ግን አስተማሪ ሆነው ከሌላ ቦታ የመጡና በእስልምናውም በክርስትናውም ያልተገባ ቅስቀሳ የሚጠቀሙ ሰባኪዎች እና ዳዕዮች ነበሩ። እነርሱን ግን ሙስሊሙም ሆነ ከርስቲያኑ እረፉ ሲላቸው ወዲያውኑ መስመር ይይዛሉ። ዋናው የፀብ ጠማቂ ግን አሸባሪው ህወሓት ነበር።
አዲስ ዘመን፡- አሸባሪው ህወሓት በጦርነት መሸነፉን ከማመን ይልቅ ወሎን ጨምሮ በሌሎች አካባቢዎች ላይ ንፁሃንን መጨፍጨፍ የፈለገው ለምን ይሆን?
አቶ ሰይድ፡- ብዙ ምክንያት አለው። ዋናው ወደ መሃል ሀገር ለመሄድ ጁንታው ጦርነት በወሎ ላይ የከፈተባቸው ምክንያች አሉ። ዋናው ታላቋ ትግራይን መገንባት ነው። ለዚህ ደግሞ አማራ የሚባል ህዝብን በኢኮኖሚና በሥነ ልቦና ማድቀቅ ነው። በዚያውም ኢትዮጵያን ማዳከም ነው። ሂሳብ አወራርዳለሁ የሚለውም ዓላማው የሚታወቅ ነገር ነው። በፍቅር አብሮ ከመኖር ይልቅ ይህን እኩይ ዓላማውን ለማሳካት ዘረፋ እና ጦርነትን መርጧል።
ወደ ወሎ ጦርነቱን ያመጣበት ምክንያት አለው። በዚህ ምድር ያለው የሃይማኖት፣ የብሄርና የሥነ ልቦና ስብጥር ብሎም ደግነቱን በማሳነስና ለጦርነት አልተዘጋጀም አይመክተኝም በሚል የተዛባ ግምገማ ነው። ሰተት ብሎ ማለፍ እንደሚችል ያስብ ነበር። የአማራ ህዝብም እንደ ቀድሞው ወደማዕከላዊ ያሳልፈኛል ብሎ ነበር። ግን ህዝብ አንድ በመሆን መክቶታል።
ሁለተኛው ዓላማ ደቡብ ወሎን ከተሻገረ ‹‹ሸኔ›› ከሚባለው አሸባሪ ቡድን ጋር ግንባር ለመፍጠር ወሳኝ ቦታ ነው ብሎ በማሰብ ነው። ከዚያም ወደ መሃል ሀገር ለመግባት ቀላል መንገድ ነው የሚል ስልት ነበር። ሦስተኛው ዓላማ ደቡብ ወሎን በተለይም ደግሞ ደሴ እና ኮምቦልቻን መያዝ ማለት የአፋርን ሚሌ እንደመያዝ ይቆጠራል። ምክንያቱም የሀገሪቱ ወጪ እና ገቢ ምርቶች መስመር በማቋረጥ የኢትዮጵያን ጉሮሮ በመዝጋት ማዕከላዊ መንግስትን በማስገደድ ወደ ድርድር ማምጣት ነው። ስለዚህ ኮምቦልቻን በመያዝ ገርባ፣ ደጋን፣ ባቲ ብሎ ሚሌ በመያዝ የውስጥና ውጭ ምርቶችን ለመቆጣጠር ያስችላል በሚል ስሌት ይህን ሦስተኛ አማራጭ አድርጓል።
በሌላ መንገድ ደሴ እና ኮምቦልቻን መያዝ ለዓለም አቀፍ ማህበረሰቡም እና ለጂኦ ፖለቲክሱም ሆነ ለፕሮፓጋንዳው ትልቅ ጥቅም አለው ብሎ በማሰብ ነው። በተጨማሪም የትግራይ እናቶችን ልጆቻችን የት ደረሱ ብሎ ለሚጠይቀው ጥያቄ እና እልቂቱን ለመደበቅና ለፖለቲካ ጨዋታ ለመጠቀም ነበር። የህዝብን ግፊትና ተቃውሞ ለማብረድ ሲል ወሎ ላይ ማዕከል አድርጎ ሴቶች፣ ህፃናትና አዛውንቶችን ብሎም ንፁሃንን ጨፍጭፏል። በዚህ አካባቢ 70 ከመቶ አቅሙን ለመጠቀም ሞክሮ ነበር።
መጀመሪያ ጫናው ወደ አፋር አስቦ ነበር። ወሎ ላይም በተመሳሳይ መንገድ። ወደ ጎንደር በመግፋትም ወደ ሱዳን የመውጫ ኮሪደር መያዝና በዚያ አካባቢ ያለውን የሀገር መከላከያ ሰራዊት ኃይል ለማዛባት በሚል የተዛባ እሳቤ ለማምለጥና ለመሹለክ በማሰብ የከፈተው ጦርነት ነው። ዞሮ ዞሮ መላው የወሎ ህዝብ ለፍቅር እንጂ ለዕብሪት እንደማይንበረከክ በሚገባው ቋንቋ እያሳየው ነው። ጠላትን በተባበረ ክንድ በመምታት ወደ መጣበት እንዲፈረጥጥም በማድረግ ላይ ነው።
አዲስ ዘመን፡- በወሎ ግንባር የተሰለፈውን የሀገር መከላከያ ሰራዊትና የልዩ ኃይል ተጋድሎ የማሳነስ አዝማሚያዎች መነሻቸው ምንድን ነው?
አቶ ሰይድ፡- እውነት ለመናገር የሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ የአማራ ልዩ ኃይል፣ አጠቃላይ ህዝባዊ አደረጃጀቶች ሚሊሻው ከፍተኛ ተጋድሎ አድርገዋል። ጁንታው በፈለገው መንገድ አንዳይሄድ እያደረገው ያለው ጀግናው የመከላከያ ሰራዊታችን እና ልዩ ሃይሉ ከማህበረሰቡና ከሚሊሻው ጋር ባደረገው ተጋድሎና የተናበበ ሥራ ነው። ደሴን፣ ኮምቦልቻን እና ሐይቅ ከተሞችን የታደገው ይህ ኃይል መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል። እነዚህን አካላት መውቀሱ ተገቢ አይደለም።
አዲስ ዘመን፡- ስም የሚያጠለሹት እነማን እንደሆኑ መረጃ አላችሁ?
አቶ ሰይድ፡- አሸባሪው ህወሓት በፊትም ሲያደርግ የነበረው ሥም በሀሰተኛ አካውንቶች ወሎ ሆን ተብሎ በጦርነቱ እንዲጎዳ፣ የሀገሪቱና የክልሉ መንግስት ረስቶታል የሚሉና ሌሎች የተዛቡ መረጃዎችን መበተን ነው። ለዚህም አብዛኛው ፕሮፓጋንዳ ማሽን ራሱ የአሸባሪ ህወሓት ያሰለፋቸው የዲጂታል ክንፍ ነው። ባለፈው የፌዴራል መንግስት ኔት ወርክ ሲዘጋ ሁሉም በወሎ ስም የተከፈቱ አካውቶች ዝግ ሲሆኑ ተመልክተናል። ለምሳሌ ሃይቅ ተቀምጠው ስለ ወሎ አዛኝ መስለው የተተዛባ መረጃ ሲያሰራጩ የነበሩ የአሸባሪው ህወሓት ተላላኪዎችን አግኝተናል፤ እርምጃም ወስደናል። ወሎ ክልል ይሁን፣ ወሎ የከፋ ችግር ገጥሞታል፣ ወሎን የሚታደገው የለም በሚል የሚፅፉትም የዲጅታል ወያኔ ተከፋይ መሆናቸውን ደርሰንባቸዋል።
በአሁኑ ወቅት ከየትኛውም በላይ ወሎን ለመታደግ እየሠራና የህይወት መስዕዋት እየከፈለ ያለው የሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ የአማራ ልዩ ኃይል እና ሚሊሻው ነው። ጁንታው ሐይቅ ላይ ከደረሰ በኋላ አከርካሪው ተመትቶ እንዲመለስ የተደረገው በእነዚህ ኃይሎች ጀግንነት፣ የተቀናጀና የተናበበ ሥራ ነው። ስለዚህ ይህን ጥረት ማሳነስ እና ያልተገባ ፍረጃ የሚሰጠው ጁንታው ነው። የአማራ ህዝብ በአንድነት እንዳይቆም፣ እንዳይተጋገዝ፣ በሃይማኖትና በጎጥ እንዲከፋፋል እያደረገ ያለው ጁንታው ነው። የአማራ ህዝብ በትንንሽ አጀንዳዎች እንዲጠመድና በጎጥ እንዲከፋፈል መሥራትም ጁንታው የተለመደ አጀንዳ ነው። ጠላት ወዳጅ በሚል ጎራ በመከፋፋል የሚፅፉ ማህበረሰብ አንቂዎችን በየቦታው ሰግስጓል። አሁን ባለው ጦርነት ግን የመላው ኢትዮጵያ የጋራ ተቋም የሆነው የሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ መከታ የሆነው ልዩ ኃይል፣ በተጠራበት የሚገኘው ወጣትና ሚሊሻ በተባባረ ክንድ እየረመረሙት እንጂ የተለየ ኃይል በመምጣቱ አይደለም።
አዲስ ዘመን፡- ከጦርነቱ ባሻገር የልማት ሥራዎች እንዴት እየተከናወኑ ነው?
አቶ ሰይድ፡- በደቡብ ወሎ ዞን 30 ወረዳዎች እና 603 ቀበሌዎች አሉ። በዚህ ውስጥ ደግሞ 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ ይኖራል። ምንም እንኳን ችግሮች ቢኖሩም የክረምት የግብርና ሥራዎች በሥርዓቱ እየተከናወኑ ነው። ጦርነት ቢኖርም በኢኮኖሚው ሥራ ላይ ለአፍታም ሳንዘናጋ ኮሚቴ እና ግብረ ኃይል ተቋቁሞና በእኔ ልዩ አማካሪ እየተመራ የልማት ሥራው እየተገመገመ እና እየተመራ ነው ያለው። ስለዚህ ከአጭር ጊዜ አኳያ የተፈናቀሉ ወገኖቻችን አሸባሪው ህወሓት ጨውና በርበሬ እንኳን ሳይቀር ልቅም አድርጎ ስለወሰደው ወደቀያቸው ሲመለሱ እህልና ውሃን አገናኝቶ ለመጠቀም የማያስችል ቁመና ላይ እንዳደረሳቸው ተገንዝበናል፤ ለዚህም እለታዊ ድጋፍና እርዳታ አድርገናል። በዘላቂነት ግን መሬትና ሰብሉን ስናየው የፌዴራልና ክልልመንግስትም ኢኮኖሚውን ለማነቃቃት ጦርነቱ ያመጣውን ጉዳት ከግምት ውስጥ ባስገባ መልክ ለመደገፍ ትኩረት ስለሚሰጠው አርሶ አደሩን መልሰን በዘላቂነት ለማቋቋም እንሠራለን።
አዲስ ዘመን፡- ጦርነቱ የሚፈጥረውን የኢኮኖሚ ጫና ለመቋቋም ምን እየተሠራ ነው?
አቶ ሰይድ፡– አሸባሪው ህወሓት በከተሞች ላይ ከዚህ በላይ ዘረፋዎችን ለማካሄድ አስቦ ስለነበር አልተሳካለትም። በተለያየ መንገድ ህብረተሰባችን በተረጋጋ ሁኔታ ኢንቨስትመንቱን እንዳይመራ ለከተማ ልማት ገቢ እንዳያመነጭ፣ ሰዎች እንዳይረጋጉ በብዙ መንገዶች ሲረብሽ ከርሟል። እነዚህ ከተሞች ደግሞ በከፍተኛ ደረጃ ተፈናቃዮችን ተሸክመዋል። ይህም በአጠቃላይ በቀጣይ ኑሮ እና በማህበረሰቡ ህይወት ላይ የሚያመጣው የኢኮኖሚ ጫና ይኖራል። ነገር ግን በውጭና በሀገር ውስጥ ካሉ ኢትዮጵያውያን ጋር በመሆን ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የሚያደርጉትን እገዛ ማዕከል አድርገን በዘላቂነት ከህብረተሰባችን ጋር ተጋግዘን እናልፋለን። ከዚህ በኋላም አሸባሪው ህወሓት ለኢትዮጵያ እና ለአማራ ህዝብ ሥጋት በማይሆንበት ደረጃ ማድረስም ይጠበቅብናል።
ጦርነት በራሱ አውዳሚ ነው። ከፍተኛ ኢኮኖሚ ይወስዳል። መሬት ላይ ከምናለማው በላይ ህዝባችን ካለው ላይ እየቀነሰ ለጦርነት እየዋለ ነው። የአርሶ አደሩን በሬ እየወሰደ ነው። ይህን ለማስተካከል የሚወስደው ጊዜ መኖሩ አይቀርም። በጋራ በመሆን ከገባንበት ችግር እንወጣለን። ከኢኮኖሚው በላይ ዋናው ኢትዮጵያን ማስቀጠል ነው። ኢትዮጵያውያኖች ለአንድነታቸው ለሀገራቸው የማይበገሩ መሆናቸውን ለዕብሪተኞች ደግሞ አንድነታቸውን አጠናክረው በሚገባው ቋንቋ ማናገር የሚችሉበትን ሁኔታ አመላክተው እስካለፉ ድረስ በጦርነት የጎደለው ነገር ከግምት ውስጥ ገብቶ በቀጣይ እየተሟላ ይሄዳል።
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት ደሴ እና ኮምቦልቻ ከፍተኛ ተፈናቃዮችን አስጠልለዋል። በከተሞች ያልታሰበ ቀውስ እንዳይፈጠርስ ምን እየሰራ ነው?
አቶ ሰይድ፡- የኑሮ ውድነቱ እንዳይባባስ ባለብሀቶች በሀገር ውስጥና ውጭ ያሉ ኢትዮጵውያንና ባለሀብቶች ተፈናቃዮችን ለመርዳት፣ ጦርነቱ በአጭሩ እንዲቋጭ በማገዝ እጅግ ከፍተኛ ድጋፍ እያደረጉ ነው፤ ለዚህም ትልቅ አክብሮት አለን። በአንፃሩ ደግሞ እኛ ውስጥ ያሉ ነጋዴዎች በአንድ በኩል የዋጋ ጭማሪ በማድረግ በሌላ በኩል ምርት በመከዘንና እጥረት እንዲፈጠር በማድረግ የኑሮ ውድነቱ እንዲባባስ የሚያደርጉ ጥቂት ስግብግብ ነጋዴዎች መኖራቸውን ለይተናል። የኑሮ ውድነቱ አንዱ ዓለም አቀፍ ደረጃ ከተከሰተው የኮረና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር የሚያያዝ ሁኔታ ቢኖርም ዋንኛው ግን እኛ ውስጥ ያሉ ያልተገባ ዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ ምርት የሚከዝኑ ንፁሃን በጦርነት ተጎድተውና ከቀያቸው ተፈናቅለው ምንም ሳይዙ በባዶ እጃቸው የመጡትን ጭምር በማሰቃየት በንፁሃን ደም ላይ ለመክበር የሚሯሯጡ ነጋዴዎችን ለይተናል። ይህን ሥርዓት ለማስያዝም ግብረ ኃይል አዋቅረን ወደ ሥራ አስገብተናል።
እስካሁን ባለለው ሁኔታ ከ2000 በላይ የንግድ ድርጅቶች በምን ሁኔታ ላይ እየሰሩ እንደሆኑ የቤት ለቤት አሰሳ ተደርጓል። ከእነዚህ ውስጥ ህጋዊ የንግድ ፈቃድ የሌላቸው፣ ህጋዊ የዋጋ ዝርዝር ያልለጠፉ፣ ያለአግባብ ምርት የከዘኑ፣ ለኑሮ ውድነቱ ሁሉንም ነገሮች የተጠቀሙ 800 በላይ ድርጅቶች ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል። 769 ድርጅቶች ታሽገዋል። 25 ድርጅቶች ላይ ክስ ተመስርቶ ጉዳያቸው ወደ ፍርድ ቤት ሄዷል። በመሆኑም በዚህ ረገድ ጠንከር ያለ እርምጃ እየተወሰደ ነው። ስለዚህ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ፣ ያለአግባብ ምርት የሚከዝኑትንና ህገወጥ ድርጊት ላይ የተሰማሩት ድርጅቶችን በመለየት እርምጃ መውሰድ ተጠናክሮ ቀጥሏል።
ሌላው እርምጃ በመውሰድና የንግድ ድርጅቶችን ወደ ትክክለኛው መንገድ ብቻ በማምጣት የማይፈታው የአቅርቦት ችግር አለ። በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ተፈናቃዮች በመኖራቸው የአቅርቦት ችግር ለማቃለል ምርት ካለበት አካባቢ መሠረታዊ የህብረት ሥራዎችን እና ዩኒየኖችን በመጠቀም ከፍተኛ መጨናነቅ ወደሚስተዋልባቸው ደሴ እና ኮምቦልቻ አካባቢዎች ህብረተሰቡን መሸከም የሚችል ምርት በማቅረብ ላይ እንገኛለን። በዚህም መሠረት 880 ኩንታል ጤፍ፣ 790 ኩንታል በቆሎ፣ 650 ኩንታል ማሽላ፣ 1 ሺ220 ኩንታል የዳቦ ዱቄት እና 550ሺ ሊትር ዘይት ከሌሎች አካባቢዎች በደቡብ ወሎ ዞን ውስጥ በሚገኙ ዋና ዋና ከተሞች ገብቷል። በዚህም የምርት አቅርቦቱን በማሻሻል እና ከመስመር የወጡ ድርጅቶች ህጋዊ ንግድ ሥርዓቱን እንዲከተሉ በማድረግ የኑሮ ውድነቱን እንዳይባባስ እና ዜጎች ከዚህ የባሰ ጫና ውስጥ እንዳይገቡ እየተሠራና በየጊዜው ክትትል እየተደረገ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ለተጎጂዎች እየተደረገ ያለው ድጋፍ እንዴት እየተከናወነ ነው?
አቶ ሰይድ፡- ድጋፍን በተመለከተ ባለን ሁኔታ በውስጥና በውጭ ያሉትን መላ ኢትዮጵያውያንና ዓለም አቀፍ ድርጅቶችን በግልጽ ጠይቀናል። ምክንያቱ ደግሞ ከፍተኛ ተፈናቃይ በእጃችን ላይ ወድቋል። እነዚህ ዜጎች እለታዊ አልባሳትና ምግብ ይፈልጋል። ሁለተኛውና ዋንኛው ድጋፍ ጦርነቱ ሲቋጭ በቋሚነት ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ማቋቋም ያስፈልጋል። ቤት የተቃጠለባቸው፣ ንብረት የወደመባቸው፣ እንስሳት የታረዱባቸው፣ የተበሉባቸውና የተገደሉባቸው ጥሪታቸው የተሟጠጠባቸውን ዜጎች በዘላቂነት ማቋቋም ያስፈልጋል።
ይህን ለማሳካት ጉዳዩን በባለቤትነት የሚከታተል ግብረ ኃይል አቋቁመን በእያንዳንዱ አካባቢ የደረሰውን ጉዳት መጠን ለይቶ ማምጣትና በእርሱ ላይ ተመስርቶ የማቋቋም ሥራ ይሠራል። ስለዚህ መላው ኢትዮጵያውያን፣ የክልሉና የፌዴራል መንግስት ባደረግነው ጥሪ መሠረት በተሻለ መንገድ ዜጎችን ለመታደግ እየሠራን ነው። ጦርነቱን በአንድ በኩል እየመራን በሌላ በኩል ጉዳቱን ለመቋቋም ከፌዴራል ጀምሮ እስከ ታች ድረስ የመንግስት መዋቅር በጥሩ ቅንጅት እየተሰራ ነው። ሀገር ውስጥ ያሉ ግብረሠናይ ድርጅቶች አቅም በፈቀደ መንገድ እገዛ እያደረጉ ነው።
ትልቁ ችግር ያለው ዓለም አቀፍ ድርጅቶች፤ ጦርነት ባለበት ቀጣና የመግባት ሙሉ ሥልጣን ያላቸው ድርጅቶች ወሎ ምድር ላይ ወይንም አማራ ክልል ባሉ ጦርነቶች ላይ በአግባቡ ገብተው ተገቢውን ድጋፍ እያደረጉ ነው ብዬ አልወስድም። ምክንያቱም ዓለም አቀፍ ፖለቲካው ያልተገባ ግምገማ ጋር ሊያያዝ ይችላል።
ጁንታውን ለመደገፍና በተለያዩ መንገዶች በመደገፍ ወደ መሃል ሀገር ለማምጣት የሚፈልጉ የተለያዩ ሀገራት አሉ። ስለዚህ እነዚህ ድርጅቶች ከሞላ ጎደል አማራ እና አፋር ክልል ውስጥ የጎደለውንና የወደመውን ንብረት ከሚያሳስባቸው ይልቅ ጁንታው የሚለቀው ያልተገባው የውሸት ፕሮፓጋንዳ ያሳስባቸዋል። ስለዚህ በፍጥነት በእነዚህ አካባቢዎች ያለውን የሰብዓዊ ቀውስ ለመፍታት የተጀመረው ጥረት በሚፈለገው መንገድ ችግሩን እየፈቱ ነው ብዬ ልወስድ አልችልም።
አዲስ ዘመን፡- ጦርነቱ የአሸባሪውን ህወሓት ህልም ከማክሸፍ የዘለለ ትርጉም አለው ብለው ያስባሉ?
አቶ ሰይድ፡– ጦርነቱ በአማራ፣ በአፋርና በመላው ኢትዮጵውያን ላይ ትልቅ ጉዳት አድርሷል። ከሁሉ በላይ ንጹሃን ዜጎች ያልተገባ መሥዋእትነት ከፍለዋል። ቆስለዋል፣ ሞተዋል፣ ተደፍረዋል፣ ሀብት ንብረታቸውን አጥተው ከቀያቸው ተፈናቅለዋል። ይህ ጦርነት ከኢኮኖሚ ጉዳት በላይ በሠብዓዊነት ላይ ያመጣውን ጉዳት የባሰ አስከፊ ያደርገዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ ጦርነቱ አንድ ትልቅ እድልም ሰጥቶን አልፏል። ከሁሉ በላይ ጠላት ላይ የተሟላ እውቀት ኖሮን ካልተገባ መከፋፈል ወጥተን አንድ እንድንሆን እድል ፈጥሯል። አሸባሪው ህወሓት ባለፉት 27 ዓመታት አማራ ህዝብን በጎጥ በመከፋፈል ቢቆይም በአንድ ላይ ሲቀብረን አይተናል። ሙስሊም ክርስቲያን እያለ ሲከፋፍል የነበረ ሁላችንም በአንድ ላይ ሲቀብር ተመልክተናል። የአማራ ህዝብን የማጥፋት አጀንዳ እንዳለው ተገንዝበን ከየትኛውም ጊዜ በላይ የአማራ ህዝብ አንድነቱን አጠናክሮ መውጣት የጀመረበት፤ ትክክለኛው የአማራ ሚሊሻ፣ ፋኖ፣ ልዩ ኃይል፣ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ህዝብና ምሁር በአንድነት ሆኖ ጠላቱን ማወቅና መገንዘቡ ብቻ ሳይሆን መታገል መጀመሩ ቀጣይነት ባለው መንገድ ጠንካራ ህዝብና አንድነት ለመገንባት ትልቅ እድል ሰጥቷል።
ባለፉት 27 ዓመታትም አማራውን ትምህክተኛ፣ ተስፋፊና የተለያዩ ስያሜዎችን በመስጠት ከሀገር መከላከያ ሰራዊት እንዲወጣ ተደርጎ በራሳቸው አምሳል ብቻ መከላከያውን ቀርጸውታል። ይህን ሴራ የሚቀይር ነባራዊ ሁኔታም ተፈጥሯል። የአማራ ወጣቶች በተደራጀ አግባብ የሀገር መከላከያ ሰራዊትንና ልዩ ኃይሉን ለማጠናከር እየተመሙ እና እየዘመቱ ያለበት እልህና ቁጭት የተፈጠረበት ወቅት ሲሆን የመከላከል አቅም በማደጉ ከውስጥም ሆነ ከውጭ ያለ ጠላት ጥቃት ከመሰንዘሩ በፊት ደጋግሞ እንዲያስብ የተደረገበት ሁኔታዎች ተፈጥረዋል።
አዲስ ዘመን፡- ከዝግጅት ክፍላችን ጋር ለነበረው ቆይታ አመሰግናለሁ።
አቶ ሰይድ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን መስከረም 20/2014