ነቀምት ከተማ ነው የተወለዱት። እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ ትምህርታቸውንም በነቀምት ከተማ ነው የተከታተሉት። ከዚያ በወጣትነታቸው የደርግ ሥርዓትን ለመጣል ሲደረግ በነበረው ትግል በ1983 ዓ.ም ኢህአዴግ የተሰኘውን ድርጅት ተቀላቀሉ። እስከ 1986 ዓ.ም ድረስ ኦህዴድ፣ ህወሓት እና ብአዴን ለየብቻ የጦር መሪዎች ነበሯቸው። ግን በዚሁ ዓመት ይህ ነገር ወደ አንድ መምጣት እንዳለበት በመነጋጋር የሀገር መከላከያ መገንባት አለበት ተብሎ በመታሰቡ እርሳቸውም 1986 ዓ.ም ለስድስት ወራት ከፍተኛ የመኮንኖች ኮርስ ትምህርት ቀሰሙ።
በዚህ የስልጠና ወቅት ብዙ ጥያቄ ይጠይቁ ነበር። በትምህርታቸው ወቅት በመጀመሪያ ትምህርት ሲሰጣቸው ኤርትራ ጦርነት እንደምትከፍት ይነገራቸው ነበር። ግን በዚህ ወቅት ለምን ጦርነት ይነሳል ብለው ይጠይቁ ነበር። ሆኖም በቂ መልስ አይሰጣቸውም ነበር። በሀገር መከላከያ ሰራዊት ለመቀላቀል ቢያንስ መሠረታዊ ጥያቄዎች መመለስ አለበት ብለው ይጠይቁ ነበር። አንደኛው የኦሮሞ ህዝብ ጥቅም እንዲከበርና ከጥገኝነት እንዲወጣ ነበር። በፖለቲካው እራሱን የቻለ እንጂ ጥገኛ መሆን የለበትም ብለው ተነሱ። ሁለተኛው ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል እንዲኖርና በአንድ ቡድን የበላይነት አመለካከት ሳይስተካከል በሀገር መከላከያ ውስጥ አልካተትም ብለው ተከራከሩ።
ኮሎኔሉ ጎበዝም ስለነበሩና በስልጠናውም ጥሩ ውጤት አምጥተው ስለነበር ጉዳዩ የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት አቶ መለስ ዜናዊ ዘንድ ደርሶ ነበር። ሆኖም ይህን ጥያቄ መጠየቃቸው በብዙ ዘንድ አልተወደደም። ይህ ጥያቄ የኦነግ እንጂ የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ አይደለም በማለትም አሴሩባቸው። እርሳቸው በዚህ ወቅት ፊንፊኔ የሚባል ብርጌድ ይመሩ ነበር። በዚህ ጊዜ ይህ ሰው ይህን ብርጌድ መምራት የለበትም ብለው ዶለቱ። እርሳቸው በዚህ ወቅት ያቤሎ አካባቢ ነበሩ። በመቀጠል ኮሎኔሉ ላይ ክትትላቸውን አጠንክረውና ሰበብ ደርድረው አሰሩዋቸው። በመቀጠል ወደ አዲስ አበባ አመጧቸው፤ ትንሽ ቆይተው ደግሞ ወደ ጅማ ወስደው አሰሯቸው። በመቀጠል ደግሞ ጦላይ ወደሚገኘው ወታደራዊ ማሰልጠኛ ካምፕ ወስደው የእስር ቤት ግዞተኛ አደረጓቸው። እንደ ሰው ሳይሆን ከውሻ አሳንሰው በጠባብ ክፍል አሰሯቸው፤ አሰቃዩዋቸው። በዚህ ቦታ እጅና እግራቸውን ታስረው ያሰቃዩዋቸው ነበር። ይህ ጉዳይ ጠበቃ፣ ዳኛ፣ ፖሊስ፣ ፍርድ ቤት የሚባል አያውቀውም። እርሳቸውን ሌሊት ሌሊት የማይጠየቅ ጥያቄ በመጠየቅ ያሰቃዩዋቸው ነበር። ጥፋታችን ምንድን ነው ብለው ሲጠይቁም ምላሽ የነበረው እናንተ የምትጠይቁት ‹‹ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል ይስፈን፣ የኦሮሞ ህዝብ መብት ይጠበቅ የሚለው የኦነግ ጥያቄ እንጂ የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ አይደለም›› የሚል ነበር። ይህ አስተሳሰባችሁ ከኢህአዴግ ጋር ስለማይሄድ ለብቻ ይታያል ይሏቸው ነበር። ምንም እንኳ እያሰቃዩዋቸው ቢሆንም ወጣት ስለነበሩ የመብት ጥያቄ ወንጀል ከሆነ ህወሓት እያደረገ ያለውም ነገር በጣም ግፍና አግባብ አለመሆኑን ይነግሯቸው ነበር። የኦሮሞ ህዝብ መብት እስካልተሟላ ድረስ ጥያቄው አይቆምም ይሏቸው ነበር።
አዲስ ዘመን፡- ማረሚያ ቤት የነበረው አያያዝ ምን ይመስል ነበር?
ኮሎኔል ሰብስቤ፡- በእስር ላይ በነበርኩበት ወቅት ድብደባ፣ ቆሻሻ ስፍራ ላይ ማሰቃየት፣ ከአውሬ ጋር አቀራርቦ ማሰቃየት፣ በምግብና ውሃ ጥማት መቅጣት ከፍተኛ ግፍ ይደርስብን ነበር። እጅግ ዘግናኝ ግፎች ሁሉ ይፈፀምብን ነበረ። በ1986 ዓ.ም ታስሬ በ1991 ዓ.ም ተፈታሁ። በዚህ ወቅት ቤተሰቦቼ የት እንዳለሁ አያውቁም ነበር። በወቅቱ የነበሩ የኦህዴድ ባለስልጣናትም የገዛ አካላችን ነው ክህደት የሚፈጽሙብን የሚል አንድምታ ነበር። በመሆኑም ፈላጊ አልነበረንም። በዚህ ሁሉ መከራ ይህ ለምን ሆነ ብሎ የሚጨነቅልንና የሚጠይቀን አንዳችም አካል አልተገኘም። እጅና እግራችንን አስረው ሲያቃዩ የሚደርስ ሰው አልነበረም።
በ1996 ዓ.ም ሰኔ ወር ለዚህ ሀገር አታስፈልግም፤ የአንተ ዓይነት አስተሳሰብ ያለው ሰው ፈፅሞ መኖር የለበትም፤ የሞት ፍርድ ይበየንብሃል፤ ወይንም ስለ ኦነግ የምታውቀውን ሁሉ አውጣ ብለው እንደ ዝንጀሮ አስረው በሌሊት አሰቃዩኝ። እኔ ኦሮሞ ነኝ፤ በዚህ ሀገር ማንም ሰው አስተሳሰቡን የመግለፅ መብት አለው እስከተባለ ድረስ መሰቃየት የለብኝም ብዬ ነገርኳቸው። ከፈለጋችሁ ግደሉኝ አልኳቸው። በወቅቱ ከስቃዩ ሞትን እመርጥ ነበር። ሰው ተርቦ ካልበላ ተጠሞቶ ካልጠጣ ታሞ ካልታከመ ሞት ይሻላል። ከዚያ መከራ ሞት በስንት ጣዕም። በወቅቱ በነበረን አቋም ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በመነጋጋርና በመተባበር እስካልሰሩ ድረስ በህወሓት ፈላጭ ቆራጭነት ብቻ የሚለወጥ ነገር የለም የሚል ነው። እጄን ሰብረውኛል፤ ጥርሴም ወልቋል። ብዙ አካላዊ ጉዳት ደርሶብኛል።
በዚህ ሀገር ፖለቲካ ውስጥ መሳተፍ አትችሉም። ከእስር ቤት ከወጣን በኋላ በመንግስታዊም ሆነ መንግስታዊ ባልሆኑ ተቋማት ውስጥ መሳተፍ አትችሉም የሚል ነበር። በየወሩ መጥታችሁ ሪፖርት ታደርጋላችሁ ተብለን ወጣን። እራሴን አላጠፋም ብዬ መኖር ጀመርኩ። 1997 ዓ.ም በነበረው ምርጫ ደግሞ መልሶ አሰሩኝ። የታሰርኩት ጥፋት ስላለኝ ሳይሆን ኮሽታ በተነሳ ቁጥር አሰራራቸው በሙሉ ትክክል ስላልሆነ እንዲሁም ተጠራጣሪ ስለሆኑና ስለሚፈሩ ነው። በኋላ ከዚያ ወደ ኦሮሚያ ፕሬዝዳንት ሄጄ እንዲህ ከመኖር ሞት ይሻለኛል ብዬ ነገርኳቸው።
ሰው አይደሉም። አካሄዴና እና አካሄዳቸው አንድ አይደለም። እነዚህን ሰዎች ታስቆማላችሁ ወይስ እራሴን አጥፍቼ ልጆቼንም ልበትን ብዬ ጠየኩኝ። እንመካከራለን ብለው መለሱኝ። ከዚያ 2008 እና 2009 ዓ.ም በአራቱም የኢትዮጵያ ማዕዘናት ህዝቡ ሲያጨናንቃቸውና ግራ ሲገባቸው መልሰው አሰሩን። ምንም ጥፋት አልነበረንም። ያለጡረታ እና ደመወዝ አበረራችሁን። ካሣም አልጠየቅንም። በመሰረቱ ለውጥ ባይመጣ ኖሮ በምስራቅ አፍሪካ የደም ምድር ትሆን ነበር። ወጣቶችና ህዝቡ ተነስቶ ነበር። አምላክ ኢትዮጵያን ስለሚወድ ለውጥ መጣ እንጂ፤ ብናምንም ባናምንም ይህች ሀገር በዚህን ጊዜ ሊቢያ፣ የመን ወይንም ሶሪያ ትሆን ነበር።
በሀገሪቱ የትም ቦታ ግጭት ሲኖር፣ ሰው ሲፈናቀልና ቤት ሲቃጠል ትግራይ ክልል ምንም አልነበረም። ይህ ለምን ሆነ ተመችቷቸው ግን አይደለም። የሆነው ሆኖ የመጣው ይህ ለውጥ ስላልጣማቸው በተቃራኒ ሆነው መጡ። በነገራችን ላይ እኔ ከብልጽግና ፓርቲ ጋር ቢጋጩ ወይንም ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ቢጋጩ አንዳች አይሰማኝም። ነገር ግን የሀገር መከላከያ ሠራዊት ማለት የሀገራችን ክብር ነው። የየትኛውም ፓርቲ አገልጋይ አይደለም። እዚያ የሄደው የእናትና አባቱን ሀገር ለመጠበቅ ነው።
ሀገሬን እጠብቃለሁ ብሎ ነው ከቤት የወጣው። በዚህ በሚጠብቀው ሀገር ውስጥ ደግሞ ጋሻዬ ነው፤ ወገኔ ነው ብሎ አብሮ ይኖራል እንጂ ነገ ጠላቴ ይሆናል፣ ያርደኛል፣ ያዋርደኛል፣ ይገለኛል ብሎ አንድም ቀን በአዕምሮው አያስብም። ሌላ ዓላማም የለውም። ነገር ግን የኢትዮጵያን የሀገር መከላከያ ሰራዊት አዋረዱት፤ አቀለሉት፤ ከዱት። ሌላው ቀርቶ በዘመናዊ የጦር መሣሪያ ለመጣው የጣሊያንን ሰራዊትም ሸብረክ አላልንም። የኢትዮጵያ ህዝብ ጀግና ነው። ዛሬ ግን አምኖት አብሮት በሚኖረው ማህበረሰብ ውስጥ ተከዳ። እነርሱ ትናንት ያያዙት እሳት እስከዛሬ አልተለየንም።
እኛ ድሃ ነን፤ ብዙ ነገር እንፈልጋለን። ሀገራችን ድሃ ናት። ትምህርት ቤት፣ የጤና ተቋማት፣ መብራት፣ መንገድ እና ውሃ እንፈልጋለን። በዚህ ችግር ውስጥ እያለን እዚህ ችግር ውስጥ አስገቡን። እዚህ ሁሉ ችግር ውስጥ እያለን ሌላ ችግር ውስጥ ሲያስገቡን የእነርሱን ክፋት ለመግለፅ ቃላት ያጥረኛል። በግሌ ከበደሉኝ በላይ ሀገራችን የበደሏት በጣም ይሰማኛል። እግዚአብሄር ይመስገን እኔ ዛሬ በልቼ አድራለሁ። የጀግና እናት ልጇን ሳትቀብር ወጥቶ ቀረ። በመቀሌ በርሃ አሞራ በላቸው። ብቻ መናገር ይከብደኛል። አሁን የተጀመረው ለውጥ በቆራጥነት ከተሄደበት የተፈለገው ለውጥ ይመጣል።
ብዙ ነገርና በደል ፈጽመዋል። ህዝቡን በመከፋፈል ግፍ ፈጽመዋል። በየትኛው የኢትዮጵያ ክፍል እና አካባቢ ብሎም ተቋማት ውስጥ የህወሓት አባላት ናቸው የተቆጣጠሩት። አመራሮች እነርሱ ናቸው። በሁሉ ነገር ቀዳሚ እነርሱ ናቸው። ይህም ይሁን ግን ከበስተጀርባ የሚሰሩት ነገር ሌላውን ትውልድ አጥፍተው ራሳቸው ብቻ የበላይ ሆኖ መጠቀም ነው። ይህ ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ አይሆንም። ዝም ብለው የኢትዮጵያን ህዝብ ያለትውልድ ለማስቀረት ነው እንጂ መቼም ቢሆን አላማቸው አይሳካም።
እኔ አልሰረኩም እንደነርሱ እንደ አይጥ በየጉድጓድ አልሾክለክም፤ በህዝብ መሃል ሆኜ ነው የምኩራራው። የምቆረቆረው ለህዝቤ ነው። 70 ከመቶ የትግራይ ህዝብ እስከዛሬ በሴፍትኔት እየተረዳ ነው። የተለየ ትምህርት ቤት፣ ጤና ጣቢያ የላቸውም። ግን መንግስት ትግራይ ተጎዳች ሲባል ብዙ ነገር ሲያደርግ ይታያል። ይህ መንግስት በጣም ሆደ ሰፊ ነው። ሰው ብዙ ነገር ይላል፤ ለምን ሃይል አይጠቀምም ይላሉ። ትግራይ ያለው ህዝብ 40 ዓመት ሙሉ ህወሓት ብቻ በውሸት ሲደሰኩርበት ኖሯል። አምላካቸውና አስተሳሰባቸው ጁንታ ብቻ ነው።
አንተ ማር ብታበላቸውና ህወሓት መርዝ ቢያበላቸው አንተ ያበላኸውን ማር እንደ ማር አይቆጥሩትም። ይህ የሆነው በፈጠሩት አስተሳሰብ ነው። ይህን ለማስተካከል ጊዜ ይወስዳል። ኢትዮጵያ ደግሞ መቼም አትፈርስም። እድል ገጥሟቸው የእነርሱ ጀነራሎች ቀድሞ ጓደኞቼ ናቸው፤ ይህን መልዕክት የሚሰሙ ከሆነ እንደማይሳካላቸው ይወቁ። እንቢ አንፈልጋችሁም
አንገሽግሾናል ያላቸው ህዝብ መሆኑን ይወቁ። ወጥቶ መግባትም ቀላል ነገር አይደለም። በአሜሪካ እና አውሮፓ ሴራ የፈራረሱ ሀገራትን ማየት ይገባል። ዓይናቸው እያየ ዜጎቻቸው ላይ ህንፃ እየፈረሰ የወገናቸውን አስከሬን እንኳን ማውጣት አልቻሉም። ይህን ነው ወደራሳችን እየጠራን ያለነው። ትንሽ ችግራችንን ቻል አድርገን ብንሠራ ወደ ተሻለ ደረጃ እናሸጋግራለን።
ከልቤ ነው የምናገረው እያንዳንዳችን ብንሠራ ለውጥ ማየት እንችላለን። ወያኔ እንጀራ እንዳንበላ ያደርገን ነበር። በኦሮምኛ መናገር እናፍር ነበር። ኦነግ ይሉኛል። አሁን ደግሞ መንግስትን አግዘን የምንፈልገውን ለውጥ ማምጣት እንችላለን።
አዲስ ዘመን፡- ወደማረሚያ ቤት ከተወሰዱ በኋላ የነበረው ውጣ ውረድና የቤተሰብ ሁኔታ ምን ይመስል ነበር?
ኮሎኔል ሰብስቤ፡– ሥራ ላይ ሳለሁ ሲያስሩኝ አንድ ልጅ ነበረኝ። እሱ ተወልዶ በሦስተኛው ወር ነው የታሰርኩት። ለስድስት ዓመታት ቤተሰቤ አይጠይቁኝም፤ አያውቁኝም። ስታሰር 86 ኪሎ ግራም ነበርኩ። ከእስር ስፈታ ደግሞ 45 ኪሎ ግራም ሆንኩ። ማንም አያውቀኝም ነበር። የወለደችኝ እናቴ፣ ወንድሞቼ፣ ጓደኞቼ አላወቁኝም። ከእስር ስወጣ በጣም አለቀስኩ። ራሴን ላጠፋ አስቤ ነበር። ወታደራዊ ዩኒፎርም የለበሰ ሰው ባየሁ ቁጥር ሊይዙኝ የመጡ ይመስለኝ ነበር። ማረሚያ ቤት የነበረው ጭንቀት አብሮኝ አለ። የሚገርፉን ይመስለኛል። ቀንም ቢሆን አንድ ሰው ቆሞ ካየኝ እየፈለጉኝ ነው ብየ እጨነቅ ነበር። ያልሸሸሁበት ቦታ የለም። ግራ ሲገባኝ ወደ ባሌ ሸሸሁ። ያለፍነውን መከራ መግለፅ ከባድ ነው። ለምን ተጎዳሁ የሚለው ሳይሆን ሰው ከጉዳት አገግሞ እንዴት ህይወቱን ማስተካከል ይችላል የሚለው ነው።
ትዕግስት ትልቅ ነገር ነው። ሆደ ሰፊና ትዕግስተኛ መሆን ጥሩ ነው። አሁን የትኛውም ቢሮ ስሄድ ራሴን በትክክል ገልጬ ነው። ከ10 ዓመት በፊት ቢሮ መግባት ቀርቶ ‹‹ሊስትሮ›› ጫማ እስከማስጠርግ ይዘው የሚያስሩኝ ይመስለኝ ነበር። ወጣቶቻችን መስራት ይችላሉ። በተናጠል ወይንም በቡድን መሥራት ይችላሉ። እናም ይህን ለውጥ ማስቀጠል ይገባል። እንደ ሌሎች የፈራረሱት ሀገራት መሆን የለብንም።
የኦሮሞ ህዝብም ጥቅም የሌላውን ሃቅ በማጣመም ወይንም በመጉዳት አይከበርም። በመሆኑም ወጣቶቻችን መሥራት አለባቸው። ብዙ የሚሠራ ነገር አለ። በዚያው መጠን የሚሰራ ማህበረሰብ አለ። ይህን ወደ ተግባር መግባት በጎደለው መንግስትን ድጋፍ መጠየቅ ነው። በሀገሪቱ የመልካም አስተዳደር ችግር አለ። ግን የመንግስት ፍላጎት ዜጎችን ይፈልጋል። እንዲደሰቱ እንጂ እንዲከፉ አንፈልግም። የተወሰኑ አመራሮች የህዝብን ችግር አይሰሙም። ቢሆንም ሁሉንም ችግሮች በአንድ ቀን ማስተካከል አይቻልም፤ በሂደት ነው።
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት ምን በመሥራት ነው የሚተዳደሩት?
ኮሎኔል ሰብስቤ፡- 2012 ዓ.ም የተመሰረተ ማርቲሲስ የሚባል ድርጅት አለን። ከማንኛውም አካል ገለልተኛ ነው። በጨርቃጨርቅ ላይ ነው የምንሰራው። ለዩኒቨርሲቲዎችና ሆስፒታሎች ለመሳሰሉት ድርጅቶች የደንብ ልብስ ያቀርባል። አቅም የሌላቸውን ዜጎችም ያግዛል። እናትና አባት የሌላቸውን ህጻናት ያግዛል። በ2014 ዓ.ም ደግሞ አዲስ እቅድ አለን። በየዓመቱ ዩኒቨርሲቲ ለሚመገቡና በውጤታቸው በጣም ከፍተኛ ለሆኑ 10 ተማሪዎች ወጪያቸውን በመጋራት ለማስተማር አስበናል። ዓላማው ደግሞ የተማረ ሰው ብዙ ሀገር ይፈይዳል ብለን ስለምናስብ ነው። ከአሁን በኋላ ቤተሰባቸው በማረሚያ ቤት የተጎዱ አሉ፤ ቤተሰባቸውን እናግዛለን። ስምንት ልጆችን በቋሚነት ብንችል ከዚህ በኋላ ብናግዝ ደስ ይለናል። በአሁኑ ወቅት ስራ እና መማር በግድ ያስፈልጋል። መነሻ ዓላማችን የነበረው የህዝባችንን ጥቅም ማስከበር ነው። ሀገራችን በጣም ማደግ አለባት። ሰዎችን የማግዘው ኢትዮጵን የሚያግዝ ዜጋ ለመፍጠር ነው። በቀጣይ ወደ ኮንስትራክሽን መግባት እንፈልጋለን።
አሁን የክልሉንም ሆነ ፌደራልን መንግስት የምንጠይቀው ገንዘብ ወይንም ሌላ ሃብት ሳይሆን የመስሪያ ቦታ ወይንም መሬት ነው። ከዚህ በተረፈ ሰላም በጣም ያስፈልጋል። በዚህ ሀገር አስተማማኝ ሰላም ያስፈልገል። ልጆችን ለማስተማር፣ ለመኖር እና ለማንኛውም እንቅስቃሴ ቀዳሚው ነገር ሠላም ነው። በመወያየትና በመመካከር በግልጸኝነት በመነጋር ችግሮችን ማረም ይገባል። ኢትዮጵያ ማደግ አለባት። አሜሪካ ብዙ ግዛቶች ተዳምረው ነው ሃያል የሆኑት። እኛ እንደ አሜሪካ ማደግ እንችላለን። ተፎካካሪ ፓርቲዎችም መንግስት ሲሳሳት ይህ መሆን የለበትም ብለው ማረምና ማስተካከል አለባቸው። ከኢትዮጵያ እንደወጡ በዚያው መቅረት አይገባም። ዘመናትን ስንገዳደል እና ስንጎዳዳ ኖረናል፤ ግን ይህ ለሀገራችን አንዳችም ነገር አልፈየደም። በመሆኑም ወደ ትብብር መንፈስ መምጣት ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- አሁን ኢትዮጵያ የገጠማትን ፈተና እንዴት ማለፍ አለባት?
ኮሎኔል ሰብስቤ፡- ኢትዮጵያን ውስብስብ ችግር ውስጥ ያስገባት ወያኔ ነው። በታላቁ ህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ ግብጽ በአንድ በኩል ትፎክራለች። አሜሪካ ታግዛቸዋለች። አውሮፓውያንም በተመሳሳይ መንገድ ይህንኑ ያደርጋሉ። እውነታው ግን የኢትዮጵያ ህዝብ ሥርዓትን የሚያውቅ ሀቀኛ እና ተቻችሎ የሚኖር ህዝብ ነው። ሁሉም ያልፋል ብሎ ነገን በተስፋ የሚያይ ነው። አንድና አንድ ምርጫው ኢትዮጵያ ህዝብ መበልጸግ አለበት። ይህን በማድረግ ጠላቶቹን ማሳፈር አለበት። በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ የገባችበት ቅርቃር ውስጥ ገብታ አታውቅም። ባለፉት 100 ዓመታት ውስጥ እንኳ እንዲህ አልተፈተነችም። በመሆኑም በኢኮኖሚው ረገድም ማደግ ይገባል። በተለይ ደግሞ የጁንታው ርዝራዥዎችን ለማሳፈር ሲል መንግስት በስፋት መሥራት አለበት።
አዲስ ዘመን፡- ጁንታው በአሁኑ ወቅት የኦሮሞ ህዝብ ተጎድቷል፤ አልተጠቀመም በማለት አብረን እንታገል ሲል መጠየቁ ለኦሮሞ ህዝብ በማሰብ ነው?
ኮሎኔል ሰብስቤ፡– ነገሩ የጠፋው ዛሬ ሳይሆን ቀደም ብሎ ነው። ኦሮሞ ህዝብን ጥያቄ ስንጠይቅ ኦነግ ብለው መከራ እና ስቃይ ያሳዩን ነበር። የኦሮሞ ወጣቶችን መከራና የተለያየ ፍዳ ሲበሉ ነበር። ታዲያ ዛሬ የኦሮሞ ህዝብ አልተጠቀመም ማለት ትርጉሙ ምንድን ነው? የኦሮሞ ህዝብን ሲወጋ የነበረ ተከዜ በረሃ ሲደርስ እንዴት ይህን ሊያስብ እንደቻለ ይገርማል።
የኦሮሞ ህዝብ ከሰዎች ጋር የመኖር ልዩ ችሎታ አለው እንጂ ሞኝ አይደለም። እናትና አባት ናቸው የተገደሉበት። ቤቱ ሲቃጠል ነበር። ኦሮሞ እንደ ጅብ እንዲታይ ያደረገው ጁንታው ነው። ሌላ ብሄር ኦሮሞን እንዲጠላ ያደረገው ጁንታ ነው። በሀገሪቱ ትልቅ ህዝብ በመሆኑ ከሌላ ለማጣላት ብዙ ለፍቷል። በተለይ ከ2010 ዓ.ም ወዲህ ጁንታው የሠራው በጣም ፀያፍ ነው። እነ ጌታቸው ረዳ ተከዜ ሲደርሱ እንዴት የኦሮሞ ህዝብ አለመጠቀም ታያቸው ብሎ ማሰብ ይገባል። ለመሆኑ እኔ ስንት ነገር የተጎዳሁበት የኦሮሞን ህዝብ ጥያቄ በመጠየቄ አይደለም? ስንቶች መስዕዋት የከፈሉት ኦሮሞን ህዝብ ያነሳውን በመጠየቃቸው አይደለም? ይህ እንዴትም ሊሆን አይችልም። ትናንት ክብር የነፈገን አካል ተመልሶ ቢመጣ ክብር አይሰጥም። የኦሮሞ ህዝብ ኑሮውን ማሸነፍ አለበት።
ጁንታው ሥራው ይመስክራል። የስንት ጀግና እናት ልጇን እንዳጣች ማሰብ ነው። ገና እኮ ሦስት ዓመታቸው ነው ከተወገዱ። ባለፉት 27 ዓመታት በወያኔ ያልተንኳኳ በር የለም፤ ያልሞተ የለም። ያኔ እኮ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ የሚመራው መንግስትአልነበረም ወያኔ እንጂ። እነርሱ ሊመስላቸው ይችላል፤ ወያኔ ነገር ግን ለኦሮሞ ህዝብ ምንም የሚፈይደው ነገር የለም። ይህ መንግስት አይሆነኝም ብሎ የሚያባርረው ህዝብ የምንሸከመው ጠመንጃ አይደለም። እነርሱ መሣሪያ ስለያዙ ሊመስላቸው ይችላል። በአፋር ወይንም በሱዳን ገብተን የፈለግነውን እናደርጋለን ብለው ሊያስቡ ይችላሉ። ትናንት ወገናችን ነው ብለው ሲጠሩት የነበረውን ህዝብ እየጎዱ ነው። ከሀገሪቱ በቀሙት ነገር ምንም ነገር ገዝተው መሥራት አይችሉም። በህዝብ ላይ የሰሩት ግፍ እንደ እብድ ውሻ እያቅበዘበዛቸው ነው። ከከብራቸው ወርደው መጥፊያ ነው ያጡት።
ችግሮችን በሠላማዊ መንገድ ለመፍታት መንግስት የሃይማኖት አባቶችን፣ አባገዳዎችን፣ ሽማግሌዎችንና እናቶችን ወደ ትግራይ ክልል ልኳል። ይህ አልሆነም። አካሄዳቸው አርጅቷል። በኦሮሚያ ሰርተን መለወጥ ይገባል። በሀገራችን ሰርተን መለወጥ እንችላለን። በእርዳታ ስንዴ መኖር ይበቃል። ምዕራባውያን ለምን ሁሌ እርዳታ መስጠት ይሻሉ። ካሰቡልን ዓሳ ከሚሰጡን ዓሳ ማጥመድን ያስተምሩን። ሁሌ ባሪያቸውና ተመፅዋች ከሚያደርጉን በዓመት እንዴት ሦስቴ ማምረት እንደምንችል ያስተምሩን።
የኢትዮጵያ መንግስት እነዚህን ሁሉ ጥረቶች ሲያደርግ ያደጉት ሀገራት ጥሩ ነው ብለው ለመንግስት ይሁንታ መስጠት አይፈልጉም። ከሐረር፤ ጉራ ፈርዳ፣ ሻሸመኔ፣ ዶደላ፣ እና ሌሎች አካባቢዎች ዜጎች ሲፈናቀሉ ለምን አልጮሁም ነበር? የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ስታጠናቅቅ ሀገሪቱ ከእነርሱ ተረጂነት ትወጣለች። ይህ ከሆነ አካሄዳቸው ይበላሽባቸዋል፤ የቀይ ባህር ፖለቲካም እንዳሰቡት አይሆንም። ስለዚህ ተላላኪ መንግስት ምትክ ይፈልጋሉ። እውነታው ግን መንግስት ይህን ቢፈልግ እንኳን አይቀበልም። በመሆኑም ሰርተን የሀገራችንን ብልጽግና ማረጋገጥ ይገባል። ሀገራችን ሰላም መሆን አለባት። አሁንም ትክክል ነን ብለው ያስባሉ። 17 ዓመት ታግለው 27 ዓመታትን ቀሙን። ግን 27 ዓመት ቀምተውም በቂ የመጠጥ ውሃ ማቅረብ አልቻሉም። ህወሓቶች ለራሳቸው ከሆነላቸው ለሌላው ደንታ የላቸውም። ስድስት ጥርሶቼን ከጥቅም ውጭ አድርገዋል፤ አካሌን አጉድለዋል በጣም ተጎድቻለሁ። እኔ ይህን ሁሉ መከራ አሳልፌ አሁንም አለሁ። ለሁሉም ትዕግስት ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡- ስለሰጡኝ ማብራሪያ አመሰግናለሁ።
ኮሎኔል ሰብስቤ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን መስከረም 13/2014