ኢትዮጵያና አሜሪካ ከመቶ ዓመታት በላይ ያስቆጠረ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አላቸው።በሊግ ኦፍ ኔሽንም ሆነ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ምስረታ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል።አሜሪካ ለዘመናት የኢትዮጵያ የልማት አጋር ሆናም ቆይታለች።
ይሁንና በሰሜን ኢትዮጵያ ከሚካሄደው ጦርነት ጋር ተያይዞ የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር የተለያዩ ጫናዎችን ከማድረግ ባለፈ በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ማዕቀብ ለመጣል የሚያስችል ትዕዛዝ ከቀናት በፊት ፈርሟል።የአሜሪካ እርምጃዎች በውስጥ ጉዳዮች ጣልቃ ገብነት ነው ያለችው ኢትዮጵያም እርምጃው የሁለቱን አገራት የዘመናት ግንኙነት የሚጎዳ መሆኑንም አሳውቃለች።
ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ የፖለቲካና ዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ምሁራንም፣ በአገራት ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ መግባትና በጉልበት ለመፍታት መሞከር ‹‹ጊዜ ያለፈበት የፖለቲካ አካሄድ ነው፣ አንዱ ሌላውን ገፍትሮ፣ አንዱ የሌላው የበላይ፣ አዛዥና ናዛዥ ሆኖ፤ ሌላኛው ታዛዥ ሎሌ ወይም ባሪያ ሆኖ የሚኖርበት ጊዜ አልፏል።21ኛው ክፍለ ዘመን አገራት ችግሮቻቸውን በአንድነት ተባብረው የሚፈቱበት ዘመን እንጂ አንዱ ሌላኛውን አስፈራርቶ ችግር ሊፈታ አይችልም›› እያሉ ናቸው።
በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የዲፕሎማሲና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር አቶ እንዳለ ንጉሴ፣ ‹‹ኢትዮጵያ የአፍሪካ ቀንድ እምብርት ነች።ቀይ ባህርም የፖለቲካው ነርቭ ነው።ማንኛውም አገር ብሄራዊ ጥቅሙን ለማስጠበቅ ምዕራቡም ሆነ ምስራቁ ከኢትዮጵያ ጋር በሃይል ሳይሆን በፍቅር መስራት ግድ ይለዋል››ይላሉ።
እንደ አቶ እንዳለ ገለፃም፣ አሁን ላይ ሌላው ዓለም የሚፈልገው ሰጥቶ በመቀበል መርህ፣ በመከባበር በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ባለመገባት ነው።ይሁንና ምዕራቡ ዓለም የሃይል ሚዛኑን ማስጠበቅ አቅቶታል፣ የሚሄድበት የዲፕሎማሲ አቅጣጫ ተወናብዶበታል።የተወናበደ አቅጣጫቸውን ከማስተካከል ይልቅ ይባስ ብሎ ሌላ ቀውስ እየፈጠሩ ናቸው።
ፍላጎታቸውም አሻንጉሊት አስቀምጠው ህዝብን እየበጠበጡ፣ መሳሪያም እየሰጡ፣ ማበጣበጥ መሆኑን የሚጠቁሙት መምህሩ፣ ይህን ፍላጎታቸውን እውን ለማድረግ ደግሞ አሸባሪው ህወሓትን የመሳሰሉ ድርጅቶችን እንደሚጠቅሙም ያስገነዝባሉ።
አሸባሪው የህወሓት ቡድን የምዕራባውያን ፍላጎት አስፈፃሚ፣ ሃሳቡም ሆነ በተግባሩ የቅኝ ገዢዎች ወኪል በመሆኑ ለአገር ያስባል ማለት እጅጉን አስቸጋሪ እንደሆነ የሚያመላክቱት አቶ እንዳለ፣‹‹የአሸባሪው ህወሓት ጉዳይ ያለቀለት ነው።ከፖለቲካም ሆነ ከኢኮኖሚ መዋቅሩ ወጥቷል።ከአብዛኛው ዓለም ልብ ውስጥም ወጥቷል።ኢትዮጵያውያን ይህን አሻባሪ ቡድን ፈፅሞ ማየት እንደማይፈልጉ በግልፅ አሳይተዋል›› ይላሉ።
“በአሁን ወቅት ዓለም ከኢትዮጵያ ጎን ነው።ታላላቅ ተቋማትና አገራት ከኢትዮጵያ ጎን ናቸው።ምዕራቡ ዓለም ግን እስካሁን ተስፋ አልቆረጠም።ተስፋ ያልቆረጡት ቡድኑ አልሞተም ብለው አይደለም።የሽብር ቡድኑ ፖለቲካዊ ሞቱ እንደተፈፀመ ያውቃሉ።ይሁንና አሁንም የመደራደር ክፍተት ይኖር ይሆን ሌላ ግርግር ይኖር ይሆን፣ ሌላ እሱን የሚተካ ቡድን እናገኝ ይሆን የሚል የቤት ስራ ነው እየሰሩ ያሉት›› የሚሉት አቶ እንዳለ፣ ይህ ቡድን ተመልሶ ወደ ስልጣን እንደማይመጣ እና እድሉም መቶ በመቶ ዝግ መሆኑን ጠንቅቀው እንደሚያውቁም አፅእኖት ይሰጡታል።
በተለይም ወደ ድርድር መምጣት አለባችሁ የሚለው ጥረት በመንግሥት በኩል ፍፁም ተቀባይነት እንደሌለው በተደጋጋሚ ተገልጿል።የኢትዮጵያ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተሰብስቦ ህወሓትን በሽብርተኝነት ከፈረጀው በኋላ እንደገና ህወሓትን ከዚያ ውስጥ ማውጣትና እንደ መንግሥት ሁለቱን እኩል አድርጎ ለድርድር ግቡ ማለት ‹‹ቅንነት ያለው አይመስለኝም›› ይላሉ።
መንግስት ሽብርተኛ ተብሎ ከተሰየመው ህወሓት ጋር ድርድር ማድረግ ፈፅሞ የማይታሰብ መሆኑንም አሳውቋል።ቡድኑ መልሶ እንዲያንሰራራ የሚደረግ ማንኛውም ሙከራ አሉታዊ ውጤት የሚኖረውና የማይሳካ መሆኑ አፅእኖት ሰጥቶታል።
‹‹ኢትዮጵያ መንግስት ልትመሰርት ስለሆነ ትወያያላችሁ፤ ከተወያያችሁ ማእቀቡን አንጥልም ማለት ምን ማለት ነው›› ሲሉ የሚጠይቁት አቶ እንዳለ፣ ይህም ኢትዮጵያ ላይ ማእቀብ ለመጣል ሲራወጡ ምክንያታዊና ፍትሃዊ እንዳልሆኑ በግልፅ የሚያሳብቅ መሆኑን ይጠቁማሉ።
ዛሬ ብቻ ሳይሆን ትላንትም የአሜሪካኖቹ ማእቀብ በትር ምክንያታዊ እና ፍትሃዊ ብሎም ውጤታማ እንዳልነበር የሚገልጹት አቶ እንዳለ፣ ለዚህም ኢራንን እና ቱርክ፣ ቻይናና ሩሲያ መመልከት በቂ ምስክር እንደሆነ ከታሪከ ያጣቅሳሉ።ማእቀብ እነዚህ አገራትን ይበልጥ ጠንካራ ሆነው እንዲወጡ እንጂ እንዲንኮታኮቱ እንዳላደረጋቸውም ያስገነዝባሉ።
እንደ እርሳቸው ገለፃም፣ እነርሱ የፈለጉት ዜናው እንዲጮህ ነው።ውጤት እንደማያመጣ ጠንቅቀው ያውቃሉ።የሚያቀርቡት በ21ኛው ክፍለ ዘመን የማይመጥን የመደራደሪያ ጥያቄ ነው።የትኛው ቡድን አቅም ኖሮት ሊደራደር እንደሚመጣ እንኳን አያውቁም።ኢትዮጵያ ጉዳዩን ጨርሳለች።ኢትዮጵያውን ጠንክረዋል።
‹‹ኢትዮጵያውያን ብዝሃነት የአሸናፊነታቸው መሰረት ነው።ሁልጊዜ ኢትዮጵያውያን አንድ በሚሆኑ ጊዜ በዲፕሎማሲም ሆነ በአገራቸው ጉዳይ ተአምር ይሰራሉ።ይህ ሲሆን ምዕራባውያኑ ይፈራሉ።ጫናቸው ይበረታል›› የሚሉት አቶ እንዳለ፣ በርካታ አገራት በሰው ጉዳይ ጣልቃ አንገባም እያሉ ናቸው።አሜሪካኖች በአንጻሩ በቀን በቀን ስለ ኢትዮጵያ ያወራሉ።ይህ በዲፕሎማሲ ነውር ነው።እያደር ቁልቁል እየሄዱ መምጣታቸውን የሚያረጋጋጥ ነው ብለዋል።
‹‹ማእቀቡን ስንመለከት የሚያሳድዱት ግለሰብ ነው።የዚህ ምክንያት ከፋፍለህ ግዛ ስልትን ለመጠቀም ዜጎችን እና አመራሮችን እርስ በእርስ ለማጋጨት ነው።ይህ አይነት ስራ በጣም መርዝ ነው።እውነት ከሆነ ኢትዮጵያ ላይ ማእቀብ የሚያስጥል ዜሮ ምክንያት የለም፣ ህጻናትን የሚፈጀው፣ አካባቢ የሚረብሸው፣ በዚህ ዓለም ላይ መጥፎ የተባሉ ነገሮችን ሁሉ የሚሰራው እራሳቸው ያመጡት አሸባሪ ቡድን ነው›› ይላሉ።
የምዕራባውያኑ እያንዳንዱ ተፅእኖ ተግባራቸው ኢትዮጵያውን ከማዳከም ይልቅ የበለጠ አንድ እንዲሆኑ እያደረገ መሆኑን የሚያስገነዝቡት መምህሩ፣ ኢትዮጵያውያን በአገራቸውን ለእያንዳንዱ ጉዳይ በተለያዩ መድረኮች በመገኘት መልስ የሚሰጡት በራሳቸው ተነሳሽነት እንጂ ከመንግስት መመሪያ ተቀብለው አለመሆኑም ለዚህ ጥሩ ማሳያ አድርገው ያቀርቡታል።
እንደ እርሳቸው ገለፃ፣ በአሁን ወቅት አሸባሪ ቡድን ግብአተ መሬቱ እየተፋጠነ ነው።ኢትዮጵያውያን በአሁን ወቅት የማጠቃለያ ስራ እየሰሩ ናቸው።በቅርቡ መንግስት ይመሰርታሉ።መከላከያው አይደለም ለኢትዮጵያ ለአፍሪካም ዋስትና በሚሆን ደረጃ እየተደራጀ ነው።ኢኮኖሚው አገር በቀል እንዲሆን እየተደረገ ነው።ምዕራቡ ዓለም ምንም ነገር ጫና ማሳደር ቢፈልግ፣ አቅም የለውም።ሁሉን ተቀብሎ ከኢትዮጵያ ጋር ብቻ መስራት የግድ ይለዋል።ከዚህ ውጪ የሚደረግ ጫና ተቀባይነት እና አዋጭነት አይኖረውም።
ከመንግስት የተሰጠው ምላሽ በቂ እና መሰረታዊ ጉዳዮችን የተካተቱበት ብሎም የበሰለ መልስ የተሰጠበት መሆኑን ያመላከቱት መምህሩ፣ አሁን ብቻ ሳይሆን ለቀጣይ በርካታ ዓመታት የተንሸዋረረ እይታቸውን እንዲያስተካክሉ የሚያደርግ ስለመሆኑም ነው አፅእኖት የሰጡት።
አቶ እንዳለ ታዲያ ምን ይደረግ ለሚለው ጥያቄም ተከታዩን ምክረ ሃሳብ ሰጥተዋል።ኢትዮጵያ ወቅታዊ ፈተናዎቿን ለመሻገር በዲፕሎማሲው አሁን የያዘችውን የመሃል መንገድ ይበልጥ አጠናክራ መቀጠል አለባት።የትኛውም አገር ብሄራዊ ጥቅሟን እስካከበረ ድረስ ከምስራቁም ሆነ ከምዕራቡ፤ ከሰሜኑም ሆነ ከደቡቡ ጋር በዘርፈ ብዙ ዲፕሎማሲ አብሮ መጓዝ እና መተሳሰር አለባት።
የአገርን ሉዓላዊነት በማስከበር እና በማስጠበቅ ረገድ ገለልተኛ የሚባል የለም።በዓለም ላይ ያሉ ኢትዮጵያውያን ለአገራቸው በተጠንቀቅ መቆም አለባቸው።የተያዘው የዜግነት ዲፕሎማሲም ጠንክሮ መሄድ አለበት።መከላከያን የማጠንከር እና በአቅም የማደራጀት ስራ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት።ከአሁኑ በበለጠ አፍሪካውያንን መያዝ ኢጋድን ማጠንከር ይገባል።‹‹ሁሉም ኢትዮጵያዊ ውስጥ አንድነቱን ማጠናከር እና የዲፕሎማሲው ባለቤት እኛ ነን ማለት አለበት።የሚመሰረተው መንግስት አካታች እንዲሆን ማድረግ ይገባልም ብለዋል።
ሌሎች ምሁራንም በተለይ ሁለቱ አገራት አጋርነት ሁለንተናዊ ወዳጅነት እጅግ ወሳኝ መሆኑን አስምረውበታል።ኢትዮጵያ ካላት መልክአ ምድራዊ አቀማመጥ አንጻር ስትራቴጂክ ቦታ ላይ ከመሆኗም ጋር ተያይዞ አሁንም በምስራቅ አፍሪካም ሆነ በቀጣናው ካሉ አገራት ከኢትዮጵያ የተሻለ ወዳጅ ለአሜሪካ ማግኘት ያስቸግራል ብለው እንደሚያምኑም ይናገራሉ።ኢትዮጵያን የሚተካ አገር በአፍሪካ ቀንድ በቀይ ባህር ቦታ የለም ወደፊትም አይኖርም›› ይላሉ።
ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ እንዲሁም በአፍሪካ ቀንድ ለአሜሪካ ሽብርተኝነትን በመዋጋት ቀኝ እጅ ነበረች፤ አሁንም ናት።ይህ እስከሆነም የአሜሪካን አካሄድ፣ አገራቱ ሽብርተኝነትን በጋራ እንዋጋለን የሚሉትን ፕሮጀክት እንዲቆም አያደርገውም ወይ? ብለው በርካቶች ጥያቄ ያነሳሉ። እርምጃው ቀጣናውን ችግር ላይ የሚጥል እንዲሁም ኢትዮጵያ በፀረ-አልሻባብ የሽብር መከላከልና በሰላም ጥበቃ ላይ ያላትን ሚና በጉልህ የሚጎዳ ሲሉም ይተቹታል።
‹‹ኢትዮጵያ የአፍሪካ ፖለቲካ መዲና ናት››የሚሉት ምሁራን‹‹ኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉት እቀባም አሜሪካንም ሆነ ኢትዮጵያን ይጎዳል››ይላሉ።በተለይም በቀጣናው የደኅንነት ስጋት ቢፈጠር ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ የአፍሪካ ቀንድም ሆነ ወደ ሌሎች አካባቢዎች እንደሚዛመትና ጉዳቱም ሰፋ ያለ መልክ ሊኖረው እንደሚችል አፅንኦት ይሰጡታል።
የህግ ባለሙያው አቶ ውብሸት ሙላትም፣ አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የያዘችው አቋም ምስራቅ አፍሪካ ላይ ሽብርተኝነትን የሚያስፋፋ ነው›› ይላሉ።አሜሪካ ሽብርተኝነትን በግልጽ እንደምትዋጋ ስትናገር ብትቆይም የኢትዮጵያ መንግሥት ሽብርተኛ ብሎ የፈረጀውን የህወሓት ቡድን መደገፉ በምስራቅ አፍሪካ ሽብርተኝነትን የሚያስፋፋ ስለመሆኑም አፅእኖት ይሠጡታል።
አሜሪካ አሸባሪውን ህወሓት መደገፏም ሽብርተኝነትን ለመዋጋት ያላትን ቁርጠኝነት ጥርጣሬ ውስጥ የሚከት ነው›› የሚሉት የህግ ባለሙያው፣ አሜሪካ የወሰደችው አቋምም ሽብርተኝነትን ለመዋጋት የወጡ ዓለም አቀፍ ህጎችንና ስርዓቶችን የሚጥስ ስለመሆኑም ያስረዳሉ።
እንደ እርሳቸው ገለፃም፣ ኢትዮጵያ ሉዓላዊት አገር በመሆኗና በሀገሪቱም ፓርላማ የተወሰነውን የህወሓትን የሽብር ድርጊት አክብሮ መቀበል ከአሜሪካም ሆነ ከሌሎች ምዕራባውያን ሀገሮች የሚጠበቅ ኃላፊነት ነው።ከዚህ ተቃራኒ የሚወሰድ የሽብር ቡድኑን የሚደግፍ አካሄድ አካባቢው ላይ ሽብርተኝነት እንዲነግስ በር የሚከፍት ነው።በተለይም ኢትዮጵያ በውስጧ ሰላም ካልሰፈነባትና አጋርነቷ ከቀረ አሜሪካ በቀይ ባሕር ዙሪያ ደኅንነትንም ሆነ መረጋጋት ለማምጣትም እንዲሁም ተፅእኖ ለመፍጠር ፈተና ይሆንባታል።
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን መስከረም 11 ቀን 2014 ዓ.ም