
የነጻነት ተምሳሌት የአፍሪካውያን ኩራት የሆነች ሀገር ኢትዮጵያን ከአፍራሽና አጥፊዎቿ ለመታደግ ኢትዮጵያውያን ሁሉ በአንድ ሆነው ዋጋ እየከፈሉ ይገኛሉ። አሸባሪው የህወሓት ቡድን ‹‹ከወደቁ ወዲያ መንፈራገጥ ለመላላጥ›› እንዲሉ በየደረሰበት እንደ ክፉ ወረርሽኝ በሰላማዊ ዜጎች ላይ እያደረሰ ያለው የፈሪ ዱላ አጠቃላይ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችን እያደናቀፈ ይገኛል።
ታድያ ድል ያለመስዋትነት አይገኝምና ኢትዮጵያውያን ኢትዮጵያን ለማዳን ጸረ ኢትዮጵያ የሆነውን አሸባሪ ቡድን ለመቅጣት ከፍተኛ መስዋትነት እየከፈሉ ባሉበት በዚህ ወቅት ‹‹ግርግር ለሌባ ይመቻል›› እንዲሉ ጦርነቱን ምክንያት በማድረግ እዚህም እዚያም ኢኮኖሚያዊ አሻጥር በሚፈጥሩ አካላት ምክንያት የኑሮ ውድነቱ ተባብሷል። ያልተገባ ጥቅም ለማጋበስ በሚደረግ ሩጫም ዜጎች መኖር እስኪያቅታቸው ሆኗል። የኑሮ ውድነቱ ተባብሶም እንዲቀጥልና ዜጎች ወደ አመጽ እንዲገቡ የተለያዩ ኢኮኖሚያው አሻጥሮችን እየፈጠረ ባለው የአሸባሪው የህወሓት ቡድንና ተባባሪዎቹ ኢኮኖሚው ተቀዛቅዟል፤የብር የመግዛት አቅምም ተዳክሟል።
ይሁን እንጂ ዜጎች ከመንግሥት ጎን በመሰለፍ በተለያየ መንገድ ኢኮኖሚውን መደገፍ የሚያስችል ሥራ ሲሰራ ይታያል። ህዝቡ ካለው ላይ ቀንሶ ለሀገር መከላከያ ሠራዊት የሚያደርገው ድጋፍ አንዱ ማሳያ ነው። መንግሥትም የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት እንዲሁም እያንሰራራ የነበረ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በጦርነቱ ምክንያት ወደ ቁልቁለት እንዳይንደረደር የተለያዩ ማስተካከያዎችን በማድረግ ኃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል።
በዚህም መሰረት ከሰሞኑ ብሔራዊ ባንክን ጨምሮ ሌሎች ተቋማትም የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት
የበኩላቸውን እየተወጡ ይገኛሉ። በዚህም በኢኮኖሚ ውስጥ የሚዘዋወረውን የገንዘብ ስርጭት ለመቀነስ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ቁጥብ የገንዘብ ፖሊሲ ተግባራዊ ማድረጉ ይታወሳል። ከመስከረም 1 ቀን 2021 ጀምሮ ባንኮች ከሚሰበስቡት የተጣራ ቁጠባ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እንዲያስቀምጡ የሚገደዱትን የመጠባበቂያ መጠን ከነበረበት 5 በመቶ ወደ 10 በመቶ ከፍ እንዲል አድርጓል።
ባንኮች ለአጭር ጊዜ የሚገጥማቸውን የገንዘብ እጥረት ለመፍታት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሚበደሩበት ዓመታዊ ወለድ ምጣኔ ከ13 በመቶ ወደ 16 በመቶ ከፍ እንዲል ማድረጉ የሚታወስ ሲሆን፤ ከዚህ በተጨማሪም በባንኮች በኩል ባለው የውጭ ምንዛሬ አጠቃቀም ላይም ማሻሻያ አድርጓል።
ብሔራዊ ባንክ ያወጣው የዚህ መመሪያ እንድምታው ምንድነው? በማለት ላነሳነው ጥያቄ በአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ በኢኮኖሚክስ ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር ወንዳፈራሁ ሙሉጌታ የሚከተለውን ምላሽ ሰጥተዋል።
በዋናነት የሀገርን ህልውና ለማስከበር እየተደረገ ባለው ጦርነት ምክንያት የኑሮ ውድነት ተከስቷል። ለዚህም የተለያዩ መሰረተ ልማቶች ከመስተጓጎላቸው በተጨማሪ ኢኮኖሚያዊ አሻጥረኛ ነጋዴዎችም ምክንያት ሆነዋል። ይሁንና ሀገር እንዲህ ያለ ችግር ሲገጥማት ኑሮውን ለማረጋጋትና ኢኮኖሚው እንዳያሽቆለቁል የተለያዩ መንግሥታዊ የሆኑ እርምጃዎች ይወሰዳሉ። ከዚህም መካከል ብሔራዊ ባንክ የወሰደው እርምጃ አንዱ ነው።
ባንኮች ብድር በሰጡ ቁጥር ገንዘቡ ወደ ኢኮኖሚው ውስጥ ይገባል። ይህ ደግሞ የኑሮ ውድነቱን ይበልጥ ያባብሰዋል። ስለዚህ የባንኮችን የማበደር አቅምን በመወሰን በከፍተኛ መጠን ወደ ኢኮኖሚው የሚገባውን ገንዘብ በመቀነስ የኑሮ ውድነቱን በመጠኑ ለማረጋጋት ያለመ ነው። ይህም በአሁኑ ወቅት በኢኮኖሚው ውስጥ ያለውን እሽክርክሪት የማረጋጋት እንደምታ ይኖረዋል።
ብሔራዊ ባንክ ካደረገው ማስተካከያ በተጨማሪ በህልውና ዘመቻው ምክንያት የተፈጠረውን የኑሮ ውድነት ለማረጋጋት ሌሎች ሴክተሮችም የበኩላቸውን መወጣት ይገባቸዋል ያሉት ዶክተር ወንዳፈራሁ፤ ለአብነትም የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የምግብ ሸቀጣ ሸቀጦች ከቀረጥ ነጻ ሆነው እንዲገቡ በማድረግ የዋጋ ንረቱን ለመከላከል ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስታውሰዋል።
እንዲህ መሰል ተቋማት የፖሊሲ ማሻሻያ በማድረግ ወቅታዊ ሁኔታውን በማገናዘብ ኢኮኖሚውን ለመደገፍ ይሰራሉ። በተለይም ብሔራዊ ባንክ በአሁኑ ወቅት ያደረገው ማሻሻያ በዘላቂነት የሚቀጥል ሳይሆን ሀገር ወደ ሰላሟ ስትመለስና ኑሮው ሲረጋጋ ደግሞ ባንኮች አበድረው ኢኮኖሚው እንዲነቃቃ ለማድረግ ባንኮች የሚያበድሩትም ሆነ ተቀማጭ የሚያደርጉትን የገንዘብ መጠን ዝቅ ያደርገዋል።
በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ የሆነ የውጭ ምንዛሪ እጥረት በመኖሩ፣ በጦርነቱ ምክንያት በተለያዩ አካባቢዎች የምርት መዛባትና መቀነስ እንዲሁም እዚህም እዚያም ኢኮኖሚያዊ አሻጥር አለ። እነዚህ ችግሮች ተደማምረው የኑሮ ውድነቱ ከፍ እያለ በመምጣቱና ህዝቡም በደጀንነት በመቆሙ የኑሮ ውድነቱን ሊያረጋጉ የሚችሉ የተለያዩ ተግባራትን ማከናወን ከሚመለከተው ሁሉ የሚጠበቅ ይሆናል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመኖሪያ ቤት ኪራይን አስመልክቶ ለሶስት ወራት ያወጣው መመሪያም የዚሁ አካል ስለመሆኑ ያስረዳሉ ።
ሀገር አሁን ከገባችበት ቀውስ ወጥታ በአዲሱ ዓመት ተስፋ ወደምታደርገው ሰላሟ ተመልሶ ሁሉም ነገር ሰላም ሲሆን እንዲሁም ህዝቡ አሁን ባለው ተነሳሽነት ሲቀጥል ምርትና ምርታማነት ያድጋል።ያኔ ብሔራዊ ባንክ የወሰደውን እርምጃ ወደ ቀድሞ ቦታው የሚመለስ ይሆናል። በአጠቃላይ መሰል ችግሮችን ለመፍታት እንዲህ ያሉ መፍትሔዎች የግድ ናቸው ያሉት ዶክተር ወንዳፈራሁ፤ በተለይም ብሔራዊ ባንክ ኢኮኖሚውን ለማረጋጋት ከዚህ ቀደምም የተለያዩ መመሪያዎችን ሲያወጣ መቆየቱን አስታውሰው ሊሻሻል ካልቻለ የሚወሰዱ እርምጃዎች ቀጣይነት የሚኖራቸው መሆኑን ተናግረዋል።
ፍሬህይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ጳጉሜን 5/2013