የሸቀጣ ሸቀጦች ዋጋ ንረት የሚያሳድረው ጫና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየበረታ መምጣቱን ተከትሎ በህብረተሰቡ ላይ የሚያሳድረውን ጫና ለመቀነስ መንግሥት መሰረታዊ ሸቀጦች ላይ የታክስና የቀረጥ ማሻሻያ ማድረጉን አስታውቋል።በዚሁ መሰረት ስንዴ ፣ ዘይት፣ ስኳር እና ሩዝ ከቀረጥና ታክስ ነጻ እንዲሆኑ እንዲሁም ፓስታ፣ ማካሮኒ እና እንቁላል ደግሞ ተጨማሪ እሴት ታክስ እንደተነሳላቸው የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ኢዮብ ተካልኝ በቅርቡ በሰጡት መግለጫ አስታውቀው ነበር።
መሰረታዊ የምግብ ሸቀጦችን የጉምሩክ ቀረጥና ታክስ ማሻሻያ በማዘጋጀት ከነሐሴ 28/2013 ዓ.ም ጀምሮ ላልተወሰነ ጊዜ በመሰረታዊ የምግብ ሸቀጦቹ ላይ የጉምሩክ ቀረጥና ታክስ ማሻሻያ እንዲደረግ ተወስኗል። በዚሁ መሰረትም ስንዴ ከውጭ ሲገባ ከጉምሩክ ቀረጥና ታክስ ነጻ እንዲሆን፤ የምግብ ዘይት ከውጭ ሲገባም ሆነ በአገር ውስጥ ግብይት ሲፈጸምበት ከማንኛውም ቀረጥና ታክስ ነጻ እንዲሆን ተደርጓል።በሌሎቹም ምርቶች ላይ እርምጃው መወሰዱን አብራርተዋል።
የዋጋ ንረት በታክስ ብቻ የሚፈለገውን ውጤት ስለማያመጣ አቅርቦትን ለመጨመር መንግሥት በከፍተኛ ወጪ በመግዛት በዝቅተኛ ዋጋ ለህብረተሰቡ ከሚያቀርባቸው ከነዚህ መሰረታዊ የምግብ ሸቀጦች በተጨማሪ በሌሎች አካላት የሚገባውን በማከል አቅርቦቱ በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ ለስድስት ወር ተፈቅዶ የነበረው ያለውጭ ምንዛሪ ሸቀጦችን የማስገባት አሰራር ለሌላ ተጨማሪ ስድስት ወራት እንዲራዘም መደረጉንም ነው የገለጹት፡፡
ዶክተር ኢዮብ እንዳሉት፤የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት ነጋዴዎችም ኃላፊነት አለባቸው። በተመጣጣኝ ዋጋ ሸቀጦችን ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል።ያልተገባ ጭማሪ በሚያደርጉት ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ እና ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ፣የጉምሩክ ኮሚሽን መመሪያውን እንዲያስፈጽሙ መመሪያ መተላለፉን ተናግረዋል፡፡
መንግሥት የመሰረታዊ ሸቀጦች ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ጭማሪ እያሳየ በመሆኑ ይህንን ሁኔታ ለመቆጣጠር እርምጃውን የወሰደ ቢሆንም፤ አሁንም ቅኝት ባደረግንባቸው ሱፐር ማርኬቶች እና ሱቆች አካባቢ በመሰረታዊ ሸቀጦች ዋጋ ላይ ቅናሽ አላየንም።
ወይዘሮ ዘውዲቱ ለዩ በተለምዶ ጨርቆስ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነዋሪ ናቸው።ስቴዲየም አካባቢ በሚገኘው ኪዩንስ ሱፐርማርኬት ነው ያገኘናቸው፤ ብዙውን ጊዜ ሱፐር ማርኬት የመጠቀም ልምድ እንደሌላቸው ይናገራሉ።በአካባቢያቸው በሚገኙ አነስተኛ ሱቆች አምስት ሊትር ዘይት 600 ብር እየተሸጠ ነው ።ይህም ወራትን ያስቆጠረ ዋጋ መሆኑን ያስታውሳሉ።፡ ኪዩንስ ሱፐርማርኬት የዘይት ዋጋ ቅናሽ አለ የሚል መረጃ ስላገኙ ወደ እዛ መጥተው 5ሊትሩን ዘይት በ580 ብር ገዝተዋል። ይሄም ቢሆን ቅናሽ አሳይቷል ብሎ ለመናገር አዳጋች መሆኑን ይናገራሉ።የሌሎች መሰረታዊ ሸቀጦች ዋጋም ቅናሽ አለማሳየቱን ነው ያብራሩት፡፡
ወይዘሮ ሰላም አስራት ደግሞ ከዚህ ቀደምም የሱፐርማርኬት ተጠቃሚ መሆናቸውን ነግረውናል።ከጎረቤታቸው ጋር በመሆን ለበዓል መሰረታዊ ሸቀጦችን ለመግዛት ወደ ሱፐርማርኬቱ ማቅናታቸውን ጠቁመዋል፡፡ከኪዩንስ ሱፐርማርኬት መኮሮኒ፣ ዘይት እንዲሁም የተበለተ ዶሮ ገዝተው ሲወጡ ነው ያገኘናቸው። ከአንድ ቦታ ሁሉንም ነገር መገበየት በመቻላቸው ደስተኛ መሆናቸውን ጠቁመዋል። ገበያው በብዙ መሰረታዊ ሸቀጦች ላይ ከፍተኛ ጭማሪ እንዳለው ይገልጻሉ ።
አንድ ኪሎ መኮሮኒ ከወራት በፊት 40 ብር እንደነበር ያነሱት ወይዘሮ ሰላም፤ አሁን አንድ ኪሎ መኮሮኒ በ60 ብር መግዛታቸውን በማሳያነት በመግለጽ የታክስ እና የታሪፍ ማሻሻያው ገበያው ላይ ለውጥ እንዳላመጠ ተናግረዋል፡፡ምንም እንኳ የመሰረታዊ ሸቀጦች ዋጋ ከፍተኛ ጭማሪ ያሳየበት ወቅት ቢሆንም በዓሉን እንደ አቅማቸው ለማክበር መዘጋጀታቸውንም ነው ወይዘሮዋ ያብራሩት፡፡
በሰሜን ማዘጋጃ አካባቢ ከሚገኝ ሱቅ እንቁላል፣ የዳቦ ዱቄት እና ፓስታ ገዝታ ስትወጣ ያገኘናት ወይዘሪት ሮዛ አስራት በበኩሏ፤ እንቁላል፣የዳቦ ዱቄት እና ፓስታ ላይ ምንም ቅናሽ አለመታየቱን ተናግራለች።የሀበሻ እንቁላል ስምንት ብር የነበረ ሲሆን አሁንም በዚያው ዋጋ እየተሸጠ ነው። የፈረንጅ እንቁላል ደግሞ በሰባት ብር ከሃምሳ ሳንቲም እየተሸጠ መሆኑን ተናግራለች።በተመሳሳይ አንድ ፓስታ 60 ብር የነበረ ሲሆን አሁን 5 ብር ጭማሪ ተደርጎበት በ65 ብር መግዛቷን ገልጻልናለች።እንዲሁም አንድ ኪሎ የዳቦ ዱቄት በ50 ብር መግዛቷን ነው የተናገረችው።
መንግሥት የመሰረታዊ ሸቀጥ ዋጋ ንረት ለመቆጣጠር ያደረገው የታክስ እና የታሪፍ ማሻሻያው ይበል የሚያሰኝ ቢሆንም፤ መንግሥት የወሰደው እርምጃ በመሬት ላይ ወርዶ የሸማችን የመግዛት አቅም እየተፈታተነ ያለውን የሸቀጦች ዋጋ ማረጋጋት አልቻለም።በመሆኑም መንግሥት መመሪያው ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረጉን መከታተል ይገባል። መንግሥት ለህብረተሰቡ ዋጋን ለማረጋጋት ያደረገው ድጎማ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ሊያደርግ እንጂ የነጋዴዎችን ኪስ ሊያደልብ አይደለም። ስለዚህ የክትትልና የቁጥጥር ሥራው ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ጳጉሜን 5/2013