የኢትዮጵያ የንግድ ማህበረሰብ ለረጅም ዘመን ከተለያዩ ችግሮች ሳይላቀቅ የቆየ ነው፡፡ የንግድ ስርዓቱ በውስን ሀይሎች የሚዘወር መሆን፣ አብዛኞቹ ኢንቨስትመንቶች በውስን አካላት የተያዙ መሆን በተለይም ከሀገሪቱ ኢንቨስትመንቶች አብዛኛው በመንግስት ስም ኢንቨስት የሚደረግ ቢሆንም የመንግስትን ስም በመጠቀም ከጀርባ የሚዘውሩ አካላት መኖራቸው ፍትሀዊ የንግድ ውድድር እንዳይኖር አድርጓል። በዚህም የንግዱ ማህበረሰብ እንዲያማርር ምክንያት ሆኖ ሰንብቷል፡፡
በዚህም ምክንያት በንግዱ ዘርፍ ተሰማርተው የነበሩ በርካቶች ከዘርፉ ለመውጣት ሲገደዱ፣ ቀላል የማይባሉት ደግሞ ገንዘባቸውን እና እውቀታቸውን በሌሎች ሀገራት ለማፍሰስ ተሰደዋል፡፡ የሚስተዋሉ ችግሮችን አልፈው እዚሁ ሀገር ውስጥ መዋዕለ ንዋያቸውን ሲያፈሱ የቆዩት ደግሞ የተለያየ ስም ተሰጥቷቸው በመሸማቀቅ ሲኖሩ ስለነበር ራሳቸውን እና ሀገራቸውን በሚገባው ልክ መጥቀም ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡
ይህንን ነባራዊ ሁኔታ ለመቀየር በ2010 ዓ.ም የተደረገውን ሀገራዊ ለውጥ ተከትሎ የንግዱ ማህበረሰብ ውጤታማነት ላይ ከባድ ችግር ሲያስከትል የነበረውን አስቸጋሪ ሁኔታ ለመቀየር በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡
የአዲስ አበባ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱልፈታ የሱፍ እንደሚሉት፤ ከለውጡ በኋላ የንግድ እንቅስቃሴ ለማስፋፋት አላስፈላጊ የሆኑ በማስቀረት በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡ ቀደም ሲል በተወሰኑ ሀይሎች ብቻ የንግድ ዘርፉ እንዲያዝ ፣ ኢንቨስትመንቱ በውስን አካላት እንዲከናወን የተደረገ እና አብዛኞቹ ኢንቨስትመንቶች ደግሞ በመንግስት ስም የሚሰሩ የኢንቨስትመንት አሻጥሮች ነበሩ፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን ደግሞ ተግዳሮቶን አልፎና ተቋቁሞ ሲሰራ ለነበረው ነጋዴ የተለያዩ ስሞችን በመስጠት ሲሸማቀቅ እና አንገቱን ደፍቶ እንዲኖር ተዳርጓል። በመሆኑም ከለውጡ በኋላ የንግዱን ማህበረሰብ ቀስፈው የያዙ ማነቆዎችን ለመፍታት በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን አቶ አብዱልፈታ ይናገራሉ፡፡
የንግዱን ማህበረሰብ እጅና እግር አስረው አስቀምጠው የነበሩትን አዋጆችን፣ ደንቦችን አሰራሮች ላይ የተለያዩ ማሻሻያዎችን በማድረግ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት በሀገር ውስጥ አቅሙን፣ እውቀቱን እና ክህሎቱን እንዲያወጣ እና እንዲያዳብር ትልቅ ስራዎች መሰራታቸውን ጠቁመዋል፡፡
ከዚህም አንዱ እድሜ ጠገብ የሆነውን የንግድ አዋጅ የማሻሻል ስራ ነው የተሰራው፡፡ የንግድ አዋጅ ለዘመኑ የማይመጥን ነበር፡፡ ለዘመኑ በሚመጥን መልኩ ማሻሻያ ማድረግ አስፈላጊ ስለነበር አሁን ቴክኖሎጂ ከደረሰበት ደረጃ አንጻር አዳዲስ ዘርፎችን ሊያስተናግድ በሚችልበት ሁኔታ ስራ መሰራቱን ነው ያነሱት፡፡
በንግዱ ዘርፍ መሰማራት የሚፈልግ አካል በአሁኑ ወቅት ቤቱ ሆኖ በኦን ላይ የንግድ ፈቃድ እስከማውጣት ድረስ የሚያስችል አመርቂ ስራዎች መሰራታቸውን የሚጠቀሙት አቶ አብዱልፈታ፤ ዘመናትን ባስቆጠረው የንግድ ፈቃድ ላይ የተደረገው ማሻሻያ የንግዱን ሜዳ ለሁሉ እኩል ለማድረግ ያለመ ነው።
የግል የንግድ ድርጅት (ፒ ኤል ሲ)ን ስለመመስረት የወጠው መመሪያ ላይ ፒ ኤል ሲ ሲመሰረት ለብቻ መመስረት ስለማይቻል የግድ ሌሎች ሰዎችን ማሳተፍ አስፈላጊ እንደሆነ ተቀምጦ እንደነበር የሚያስታውሱት አቶ አብዱልፈታ፤ ይህም መመሪያ ማሻሻያ ተደርጎበታል። የዚህ መመሪያ መሻሻል በርካታ ችግሮችን የፈታ ነው፡፡
እንደ አቶ አብዱልፈታ ማብራሪያ፤ በአጠቃላይ የንግድ ስርዓቱን ለማሳለጥ የንግድ ፈቃድ ለማውጣት ይጠየቅ የነበረውን የተለያዩ ቅድመ ሁኔታዎችን በማስቀረት ነጋዴው በቀላሉ ወደ ንግድ እንዲገባ ማድረግ የሚያስችል ስራ ተሰርቷል፡፡ በዚህም ነጋዴው በቀላሉ ወደ ንግድ በመግባት ራሱን እና ሀገሩን እያገለገለ ነው፡፡
የተለያዩ የብቃት ማረጋገጫ የሚጠይቁ ስራዎች የብቃት ማረጋገጫ አሰጣጥ መሰረታዊ በሆነ መንገድ እንዲቀየር መደረጉን ያስታወሱት አቶ አብዱልፈታ፤ በፊት የነበረው የንግድ ፈቃድ አሰጣጥ በጣም ሰፊ ውጣ ውረድ የሚጠይቁ ናቸው፡፡ አላስፈላጊ የብቃት ማረጋገጫ የሚጠይቁ በርካታ ስራዎች ያለ ብቃት ማረጋገጫ እንዲሰራ ተደርጓል፡፡ ወደ አንድ ሺህ የሚጠጉ ስራዎች በብቃት ማረጋገጫ ይሰራ የነበረ ሲሆን አሁን ባለው ሁኔታ 52ቱ ብቻ ናቸው የብቃት ማረጋገጫ የሚጠይቁት፡፡ 52ቱ ለዜጎች ደህንነት አስጊ በሆኑ ዘርፎች ከጤና ጋር በተያያዘ ብቻ ነው የሚተገበሩት፡፡
የአምራች ዘርፉን ለማነቃቃት ሰፊ ስራ ተሰርቷል። በሀገር ውስጥ የሚመረቱ ምርቶችን ፣ ኤክስፖርትን ለማበረታታት፣ የሀገር ውስጥ ምርት በሀገር ውስጥ በስፋት ጥቅም ላይ እንዲውል በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡ እነዚህ የተወሰዱ የማሻሻያ እርምጃዎች በሀገሪቱ የተሟላ ሰላም እና መረጋጋት ተገኝቶ ወደ ተግባር ቢገባ ሀገሪቱን ወደ ብልጽግና ሊያሻግራት የሚችል መሆኑንም አቶ አብዱልፈታ አብራርተዋል፡፡
የመጣው ሀገራዊ ለውጥ እና የተፈጠሩ ምቹ ሁኔታዎችን ተጠቅመው በርካቶች በሀገራቸው መዋዕለ ንዋያቸውን እያፈሰሱ ነው፡፡ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት አሁንም ይህንን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም በሀገራቸው መዋዕለ ንዋያቸውን ማፍሰሳቸውን መቀጠል አለባቸው። በሌላ በኩል ይህንን ምቹ ሁኔታ ለመቀልበስ የሚንቀሳቀሱ አካላትን መታገል አለበት፡፡
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 28/2013