
ነገ ልደቱ ነው፡፡ ልደቱ ሲቀርብ ደስ አይለውም። በህይወቱ ምርጥ የሚለውን ነገር በልደቱ ማግስት ያጣ ነው፡፡ አሁንም የሆነ ነገሩን የሚያጣ ይመስለዋል። ምኑን እንደሚያጣ ግን እርግጠኛ አይደለም ምክንያቱም ምንም የለውምና፡፡ በዚህ ሰሞን..በዚህ ስሜት ከቤት መውጣት አይፈልግም ግን አንድ የማይቀርበት ቀጠሮ አለው፡፡
የልጅነት ጓደኛው ከውጪ ሀገር መጥቶ እሱን ለማግኘት እየሄደ ነው፡፡ ልደቱ ደርሶ በሰላም ወጥቶ የገባበት ቀን የለም፡፡ ገደቢስነቱ ከልጅነቱ የጀመረ ነው። ከሶስት ጓደኞቹ ጋር ወንዝ ወርደው ሲዋኙ ደራሽ ውሀ መጥቶ ሁለቱ ጓደኞቹን የነጠቀው በልደቱ ቀን ነበር። በልጅነቱ ስም ጠሪያቸውን ፈንክቶ ለአንድ አመት ከትምህርት የታገደው በዚሁ ቀን ነበር፡፡
እድለ ቢስነቱ ዩኒቨርሲቲ ገብቶም አልተወውም፤ የመጀመሪያ አመት ተማሪ እያለ በጣም የሚወደውን ጓደኛውን በመኪና አደጋ ያጣው ለልደቱ የሚሆን እቃዎችን በመገዛዛት ላይ እያሉ ነበር፡፡ በአመቱ ደግሞ ህያብን አጣት፡፡ ህያብ የህይወቱ የብዙ ነገር መጀመሪያ ናት፡፡ አለም እሷን ተደግፋ የቆመች ይመስለዋል፡፡ ይገርመዋል ዛሬም ድረስ በእሷ እውነት ነው የሚኖረው። በህይወቱ ውስጥ የእሷ አለመኖር ሁሌም ይቆጨዋል። እንዴት እንደተለያዩ ሲያስብ እሷን ለመጥላት አንድ ምክንያት ያገኘ ይመስለዋል..ግን ጠልቷት አያውቅም፡፡ በህይወቱ ውስጥ እንዲሆን የሚፈልገው አንድ ተዐምር ቢኖር የእሷ በእሱ ህይወት ውስጥ ዳግም መብቀል ነው፡፡ ግን መቼም የማይሆን ምኞት ይለዋል…
‹እንዲህ ነበር የተለየችው? መቼም አይረሳውም..። በልደቱ ቀን ላይ ልደቱን እያከበሩ ነበር፡፡ ድንገት ስልኩ አንድ ቴክስት መቀበሉን ጮሆ ተናገረ፡፡ ስልኩ ህያብ ጋ ስለነበር..የተላከውን መልዕክት ከፍቶ ለማየት እድል ነበራት፡፡ መልዕክቱን አየችው..‹የኔ ፍቅር እንኳን ተወለድክልኝ፡፡ በጣም ነው የማፈቅርህ ያንተው ሳምሪ› ይላል፡፡
ከዛ ቴክስት በኋላ ህያብ ዳግም ወደ ህይወቱ አልመጣችም፡፡ ጭራሽ እሱን ላለማየት ብላ ዩኒቨርሲቲ መቀየሯን ሰማ፡፡ በዚህ ሁሉ እውነት ልደቱን ይፈራዋል። በተለይ ሰዎች የሚሞቱበት ቀን ከተወለዱበት ቀን ጋር የተያያዘ ነው የሚል ጽሁፍ ካነበበ በኋላ ስጋቱ በእጥፍ ጨምሯል፡፡ ልደቱ በቀረበ ቁጥር ለሞት የቀረበ ይመስለዋል፡፡ እያጣቸው ያሉት ውድ ነገሮች የሞቱ ዋዜማ ይመስሉታል፡፡ በዚህ ጊዜ ከቤት መውጣት አይወድም፡፡
በህይወቱ ሁለት ሴቶችን አይረሳም..አንዷ መስህብ ናት ፤አንዷ ደግሞ ህያብ፡፡ መስህብ ከህያብ እንዲለያይ በልደቱ ቀን ላይ የውሸት ቴክስት ጽፋ የላከችለት የዲፓርትመንታቸው የመጨረሻ አመት ተማሪ ናት፡፡ እንደምትወደው ብዙ ጊዜ ነግራው የሚወዳት ፍቅረኛ እንዳለችው ነግሯት ነበር፡፡
ህያብ የብዙ ነገር መጀመሪያው ናት..ምድርን ወደ ገነት የቀየረችለት፣ ህይወትን እንዲወድ እንዲያፈቅር ያደረገችው የነፍሱ ውብ ቅኔ፡፡ በመስህብ የውሸት ቴክስት አቅም አጥታ የራቀችው፣እንደዛ ሲለምናትና ሊያስረዳት ሲሞክር የገፋችው..፡፡ እንደ አባትና እናቱ እኚህ ሁለት ሴቶች ህይወቱን ሙሉ ያመራምሩታል። መስህብ ፍቅርን አታውቅም፡፡ ፍቅር ለሚወዱት መኖር እንደሆነ ገና አልደረሰችበትም፡፡ ራሷን በማፍቀር የምትኖር ጭራቅ ናት፡፡ ህያብ ብዙ ፍቅር አላት..ፍቅሯ ግን እውነት የለውም፡፡ ከምታየው ይልቅ በምትሰማው ውስጥ ናት፡፡ እምነቷ መጨረሻ የለውም፡፡ በአእምሮዋ ሳይሆን በአካሏ ውስጥ የበቀለች እንዲህም ናት፡፡ ህያብ እውነት ቢኖራት ኖሮ ዛሬ ላይ አብረው ነበሩ..ደስ በሚል እንግዳ አለም ውስጥ፡፡
ለእሱ ሁሌም ትክክል እናቱ ናት፡፡ የእናቱ ሀቅ አመራምሮት አያውቅም፡፡ በህይወቱ ውስጥ መቼም የማይረሳቸውን ሁለት እውነቶች አስቀምጣለች፡፡ አንዱ የፍቅር እውነት ነው..ከመስህብና ከህያብ የራቀ የፍቅር እውነት፡፡ ፍቅር ሞት የሌለበት አለም ነው፡፡ የሌሎች ጥላቻ የአንተን ህያው ፍቅር እንዳይገልብህ ሁሌም ከላይ ሁን› ስትል አደራ ብለዋለች፡፡ በዚህ እውነት ውስጥ የኖረው ለአጭር ጊዜ ብቻ ነው፡፡
ከእናቱ ህልፈት በኋላ በህይወት ያለ አባቱ የእናቱን የልጅነት እውነት የሚሽር ሌላ እውነት አስተማሩት ‹ፍቅር ሁሌም እውነት አይደለም፡፡ ፍቅር ሁሌም ጸዐዳ አይደለም፡፡ ፍቅር እውነት ቢሆን ኖሮ የመጀመሪያ ፍቅረኛዬን ትቼ እናትህን አላገባም ነበር፡፡ ፍቅር ውስጥ እውነት ብቻ ዋጋ የለውም፡፡ ዋጋህ ያለው በእውነትና በማስመሰል መካከል ነው ብለውታል፡፡
አሁን ላይ በየትኛው እውነት እንደሚኖር አያውቀውም፡፡ እናቱ ትሁን አባቱ ልክ ይሄንንም አያውቀውም፡፡ በህይወቱ ብዙ ቦታ ላይ እናቱን ልክ ሆና አግኝቷታል፡፡ በህይወቱ እጅግ ብዙ ቦታ ላይ የአባቱ እውነት ሲከተለው ደርሶበታል፡፡
ህያብ የማን እውነት ናት? የእናቱ ናት? የአባቱ? አያውቀውም፡፡ በሁለቱም እውነት ውስጥ ያለች ሌላ እውነት ትመስለዋለች፡፡ እሱን ማፍቀሯ..በነፍሷ ውስጥ ነፍሱን ማስቀመጧ የእናቱ እውነት ይመስለዋል። በውሸትና በማስመሰል ትልቅ ፍቅሩን መሻሯ..ትልቅ እውነቱን መግፋቷ፣ ሊያስረዳት ሲሞክር አለማድመጧ ደግሞ የአባቱ እውነት ይመስለዋል፡፡ በየቱ ይኑር? አለም የማን ናት? እውነቷ ምንድነው? ብዙ ጥያቄዎች አንድ ላይ ግር ብለው በልደቱ ዋዜማ ወደተጨናነቀው አእምሮው ገቡ፡፡ በዚህ ጊዜ ከቀጠሮው ቦታ ደርሶ ነበር፡፡
በእናቱና በአባቱ እውነት እየዋለለ፣ ሞቱን እያሰበ ወደ አንድ ህንጻ ሊገባ ሲንደረደር..አንድ መኪና ክላክስ አደረገለት፡፡
ለእሱ ስላልመሰለው ወደ ኋላ አልዞረም..፡፡
ከመኪና ጡሩንባ ጋር የተቀላቀለ ‹ፍትህ..የሚል አንድ ቀጭን የሴት ድምጽ ጆሮ ግንዱ ላይ አንባረቀ፡፡
ቆመ..፡፡ በቆመበት ይሄ ነው የማይለው በመኖርና ባለመኖር መካከል ያለ ስሜት ዋጠው፡፡ እንዲህ የሚጠሩት ሁለት ሴቶችን ያውቃል፡፡ አንዱ እናቱ ናት..አንዷ ደግሞ ህያብ፡፡ ሁለቱም አጠገቡ የሉም..ታዲያ ማን ሊሆን ይችላል? የልደቱ ማግስት አይደል..እየሞተ መሰለው እና ደግሞ ለዘላለም ህያው እየኖረ። የቱን ይመን? በእናቱና በአባቱ እውነት መካከል ቆሞ ወደ ኋላው ዞረ፡፡
በተከፈተ መስኮት ያጮለቀ ቀይ እግዚአብሄራዊ ፊት አለም ላይ ምርጡን ፈገግታ ይዞ ይታየዋል..
‹እየሞትኩ ይሆን? ራሱን ጠየቀ፡፡ አብዛኞቹ መከራዎቹ ከዚህ ቀጥለው የመጡ ናቸው፡፡ አብዛኞቹ ስቃዮቹ ሳቁን ተከትለው የተከሰቱ ናቸው፡፡
ወደ ፊቱ ሁለት ርምጃ ተራመደ፡፡ አይኖቹ በመስኮቱ አልፈው ቀይዋ ሴት ላይ ይንቀዋለላሉ፡፡ መላዐካዊ መልክ ወደ እሱ ፈገግ ብሎ ይታየዋል፡፡
‹ይሄስ ምንድነው? የእናቱ ነው የአባቱ እውነት? ወይስ ያልደረሰበት ሌላ ሰማያዊ እውነት? ሳያስበው ሳቀ..የምንም ነገር መጀመሪያ በሆነ ቀን ላይ የቆመ መሰለው፡፡ እግሮቹ ተራምደው ከፈገግተኛዋ ሴት አጠገብ አደረሱት። ወደ እናቱ እውነት እየቀረበ ይመስለዋል፡፡ አለም በእናት እውነት ውስጥ ያለች መሰለው፡፡ በአባቱ እውነት ያጣውን ፍቅር በእናቱ እውነት አገኘው፡፡ እናት እውነት..አባት እምነት፡፡
ቀይዋ ሴት ህያብ ነበረች፡፡
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ነሐሴ 28/2013