በቀደሙት ጊዜያት ልጆቻቸውን ወደ ዘመናዊ ትምህርት ቤት የሚልኩ ወላጆች ልጆቻቸውን ለማስተማር በሳዩት ፈቃደኝነት ብቻ ከመንግስት የማበረታቻ ሽልማት ይሰጣቸው ነበር፡፡ በንጉሱ ዘመን ልጆቻቸውን ወደ ዘመናዊ ትምህርት ቤት የሚሉኩ የአካባቢ ገዥዎችም (እነ ደጅ አዝማች ፣ ቀኝ አዝማች ፣ ግራ ዝማች ፣ የጭቃሹሞች ወ.ዘ.ተ) ለማበረታቻ በሚል ከፍ ያለ ስልጣን ይሰጣቸው ነበር፡፡
ምክንያቱም በቀደሙት ጊዜያት ወደ ዘመናዊ ትምህርት ቤት የሚላኩ ልጆች የፈረንጅ አፍ (የውጭ ቋንቋና ባህል) ስለሚለምዱ ባህላቸውን እና ሃይማኖታቸውን ይዘነጋሉ የሚል ከፍተኛ የሆነ ስጋት በማህበረሰቡ ዘንድ ስለነበር ልጆቻቸውን ወደ ዘመናዊ ትምህርት ቤት አይልኩም ነበር፡፡ ስለሆነም ባለፉት ጊዜያት ልጆቹን ወደ ዘመናዊ ትምህርት ቤት ልኮ የሚያስተምር ሰው ፈልጎ ለማግኘት መሞከር ከክምር ጭድ ውስጥ መርፌ ፈልጎ የማግኝት ያህል ከባድ ነበር፡፡
በእኔ እድሜ ከሁለት አስርት አመታት በፊት በአንድ ገጠር ትምህርት ቤት አንድ ርዕሰ መምህር ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት ያልላኩ ወላጆችን በርዕሰ መምህርነታቸው ከተሰጣቸው ስልጣን በላይ እንደፍርድ ቤትና ፖሊስ በመሆን ወላጆችን በማሰር ልጆችን ወደ ትምህርት ቤት አንምዲመጡ ሲያደርግ ተመልክቼአለሁ። በዚያን ጊዜ የአየሁትን የአርሶአደሮች የትምህርት መጥላት እና የርዕሰ መመህሩ ወገኖቹን ወደ ትምህርት ገበታ ገብተው ትምህርት እንዲቀስሙ ሲያደርግ የነበረውን ትግል ሳስብ እካሁን ድረስ ይገርመኛል፡፡ የሚገርመው በዚያች የገጠር ትምህርተ ቤት የነበሩ መምህራንም የስራ አፈጻጸም የሚለካውም ምን ያህል ወላጆችን አስሮ እና እሰገድዶ ልጆችን ወደ ትምህርት ቤት አመጣ በሚል ነበር፡፡
አሁን ላይ አብዛሃኛው የህብረተሰብ ክፍል የመማርን ጥቅም ተገንዝቦ ልጆቹን ወደ ትምህርት ቤት እየላከ ይገኛል። በተለይም በከተሞች አካባቢ ወላጆች ልጆቻቸው ጥሩ ትምህርት እንዲያገኙ ወደ ግል ትምህርት ቤቶች የሚወስዱ ወላጆች ቁጥር ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ መሆኑን ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ ይሁን እንጂ ለትምህርት ቤቶች የሚከፈለው ክፍያ ደግሞ ወላጆችን ክፉኛ እያማረረ መሆኑን በተለያዩ አጋጣሚዎች ይሰማል፡፡
ከክፍያ ጋር ተያይዞ የወላጆችን መማረር የተመለከቱ የመንግስት አካላትም የግል ትምህርት ቤቶች ክፍያ ምን መምሰል እንዳለበት የተለያዩ የህግ ማዕቀፎች ሲወጡ ይስተዋላል፡፡
ይሁን አንጂ አሁንም ችግሩ ተባብሶ መቀጠሉን የሚያሳዩ ነገሮችን እየተመለከትን ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ በአዲስ አበባ የሚገኙ ልጆቻቸውን በግል ትምህርት ቤት የሚያስተምሩ ወላጆች “የትምህርት ቤት ክፍያ ከአቅማችን በላይ ሆኗልና ስለ ጉዳዩ የሚመለከተውን አካል ጠይቁልን” ሲሉ ለዝግጅት ክፍላችን ጠይቀዋል፡፡
የዝግጅት ክፍሉም ጠይቁልኝ በሚለው አምዱ የግል ትምህርት ቤቶች የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ እያደረጉ በመሆናቸው ወላጆች በግል ትምህርት ቤቶች እየተማረሩ ነው ፡፡ ስለዚህ በጉዳዩ ላይ ምን ትላለችሁ ስንል የኢትዮጵያ የግል ትምህርት ቤቶች ፕሬዝዳንት የሆኑትን አቶ አበራ ጣሰውን ጠይቀን የሰጡንን ምላሽ እንደሚከተለው ይዘን ቀርበናል፡፡
የአስተማሪ ደመወዝ በየአመቱ ይጨምራል ፣ የትምህርት ቤት ግብዓቶች በየአመቱ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመሩ ነው የሚሉት አቶ አበራ፤ በመሆኑም አሁን ላይ ትምህርት ቤቶች እንደ ትምህርት ቤት ለመቆም ተቸግረዋል፡፡ በዚህም ትምህርት ቤቶች ሳይወዱ በግድ የክፍያ ዋጋ ለመጨመር መገደዳቸውን ይናገራሉ፡፡
አቶ አበራ እንደሚሉት አሁን ላይ ብዙ ትምህርት ቤቶች ክፍያ ጨምረውም እንኳን ህልውናቸውን ማስቀጠል አቅቷቸው እየተዘጉ ነው ፡፡ ለዚህም ዋናው ምክንያት ደግሞ የአስተማሪ ደምወዝ መክፍል አለመቻላቸው እና ተገቢውን የትምህርት ግብዓት ለማሟላት የአቅም ውስንነት መኖሩ ነው ፡፡ አስተማሪ ከሌለ ደግሞ አንድ ትምህርት ቤት ትምህርት ቤት ሊሆን አይችልም ፡፡ አስፈላጊ ግብዓቶችም ካልተሟሉም እንደዚሁ ትምህርት ቤቶች አንደ ትምህርት ቤት ሊቀጥሉ አይችሉም። እነኝህ ቁልፍ ነገሮች በአንድ ትምህርት ቤት ካልተሟሉ ተማሪዎች በአግባቡ ሊማሩ አይችሉም ፡፡ ስለዚህ የግል ትምህር ቤቶች ያላቸው እድል ወይ ከወላጆች አልያም ከተማሪዎች ጋር መጣላት ነው፡፡
ዝቅተኛ ወርሃዊ የትምህርት ክፍያ እያስከፈሉ ለተማሪዎቹ ጥራት የሌለው የፅህፈት መሳሪያ እና ብቃት የሌለው አስተማሪ በማቅረብ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ቤት መጥራት በተማሪዎች ህይዎት ላይ መቀለድ ስለሆነ ከተማሪዎች ጋር ያጣላል የሚሉት አቶ አበራ፤ የሚሻለው የተሻለ የፅህፈት መሳሪያ እና ብቃት ያለው አስተማሪ ቀጥሮ የክፍያ ማሻሻያ አድርጎ ከወላጆች ጋር መጣላት እንደሆነ ይናገራሉ ፡፡
እንደ አቶ አበራ ገለጻ፤ ወላጆች ትምህርት ቤቶች የሚያወጧቸውን ወጪዎች ምን ያህል አንደሆነ ያውቁታል፡፡ ወጪውን እያወቁት ከፍያ ይጨምር ሲባል “ለምን?” ይላሉ ፡፡ ነገር ግን ማንኛውም ምክንያታዊ የሆነ ሰው ጉዳዩን ቢመለከት ትምህርት ቤቶቹ እየተበደሩ በኪሳራ ማስተማር ይገባቸዋል ሊል አይችልም ፡፡ ትምህርት ቤቶች አንደኛ የንግድ ድርጅቶች ናቸው። ስለሆነም ያልተጋነነ ትርፍ ማግኘት እንደሚገባቸው ተናግረዋል፡፡
በወላጆች እና በግል ትምህርት ቤቶች መካከል የሚፈጠረውን ውዝግብ ለመፍታት ማህበሩ ብዙ ሺህ ብር ወጪ አድርጎ ጥናት ማስጠናቱን አቶ አበራ ጠቁመው፤ በተጠናው ጥናት መፍትሄ ለማምጣት መጀመሪያ ላይ የጥናቱ ተግዳሮቶች ተነቅለው ወጥተዋል። በመቀጠልም የመፍተሄ ሃሳቦች ተለይተዋል፡፡ ከተለዩ የመፍትሄ ሃሳቦችም መካከል ለትምህርት ቤት የሚውሉ ግብዓቶች ከቀረጥ ነጻ የሚመጡበት መንገድ ይመቻች፤ ቤት ተከራይተው ለሚሰሩ ትምህርት ቤቶች የቦታ ፍቃድ ይሰጣቸው፤ ትምህርት ከሌሎች የንግድ አይነቶች ስለሚለዩ በትምህርት ላይ የሚጣለው ግብር 30 በመቶ ሊሆን አይገባውም ወዘተ የሚሉ የመፍትሄ ሃሳቦች የጥናቱ ግኝት አመላክቷል፡፡ ነገር ግን የመፍተሄ ሃሳቦችን ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ቢደግፉአቸውም አንዳቸውም መፍተሄ ሃሳቦችን መሬት ላይ አውርደው ልተገብሩ አልቻሉም ብለዋል፡፡
ለምሳሌ አንድ ሰው ሆቴል ልስራ ቢል መሬት በነጻ ይሰጥዋል፤ ለህንጻው የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን በሙሉ ከቀረፅ ነጻ ከውጭ እንዲያስገባ ይፈቀድለታል፤ የግብርም እፎይታ ጊዜም ይሰጡታል የሚሉት አቶ አበራ፤ ትምህርት ቤቶች ግን መሰል እድል እየተሰጣቸው እንዳለሆነ ይናገራሉ፡፡
በትምህርት ቤቶች ላይ የሚጣለው ግብር እንደሌሎች የንግድ አይነቶች 30 በመቶ ባይሆን እና ለመማር ማስተማሩ አስፈላጊ ግብዓቶችን ትምህርት ቤቶች ከቀረጥ ነጻ የሚያስገቡበት መንገድ ቢመቻች፤ በእርግጠኝነት በግል ትምህርት ቤቶች የሚታየው የክፍያ ውዝግብ አይፈጠረም ነበር። ነገር ግን ከላይ የተጠቀሱት ችግሮች ባለመቀረፋቸው የትምህርት ቤቶችን ስራ ነፍስ ውጭ የነፍስ ግቢ ማድረጉን አቶ አበራ ገልጸዋል፡፡
ሙሉቀን ታደገ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 28/2013