አሁን ላይ በዓለም በተለያዩ ሀገራት የሚኖሩት ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ዲያስፖራዎች ከመቼው ጊዜ በላይ ከሀገራቸው ጎን መቆማቸው በተግባር እያሳዩ ነው፡፡ በዕውቀት ፣በክህሎት፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በንግድ፣ በኢንቨስትመንትና የውጭ ምንዛሪን ህጋዊ በሆነ መንገድ ወደ ሀገር በመላክ የሚያደርጉት ተሳትፎ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ፣ እየጨመረ እና እየጠነከረ መምጣቱን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
ዲያስፖራው በህዳሴ ግድብ ፣ በተለያዩ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች እና በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ እያደረገ ያለው ድጋፍ አበረታች ነው፡፡ በተለይ የ2013 በጀት ዓመት የዲያስፖራውን እንቅስቃሴ ከሌላው ጊዜ በእጅግ እየተሻሻለ መምጣቱን የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲ መረጃ ያመላክታል፡፡
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት እንዳስታወቁት፤ በ2013 በጀት ዓመት ዲያስፖራው በሁለት ፕሮጀክቶችና በሁለት ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ተሳትፎ አድርጓል ፡፡ ከፕሮጀክቶቹ አንዱ ለሆነው የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ዲያስፖራው የሚያደርገው ድጋፍ ቀደም ባሉት ጊዜያት እምብዛም እንዳልነበር ጠቅሰው፤ ከመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት በኋላ ግን መነቃቃት መፈጠሩን ጠቁመዋል፡፡ በመሆኑም በዘንድሮ በጀት ዓመት 272 ሚሊየን ብር በላይ በስጦታ እና በቦንድ ግዥ መሰብሰብ የተቻለ ሲሆን፤ ይህም እስካሁን ኢትዮጵያ ለህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ከዲያስፖራው ካገኘቸው ድጋፍ ከፍተኛው መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በሌላ በኩል በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ያለ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ሥራ በመስራት በመካከለኛ ምስራቅ ሀገራት በአረብኛ ፣ በሌሎችም ሀገራት በፈረንሳይኛ ፣በእንግሊዘኛ እንዲሁም የተለያዩ ቋንቋዎች በመጠቀም የህዳሴውን ግድብ የገጽታ ግንባታና የኢትዮጵያ አቋም በማስረጃ በማስደገፍ የአለም አቀፉ ማህበረስብ እንዲረዳው ተደርጓል፡፡ በፐብሊክ ዲፕሎማሲ ሥራው በርካታ ለውጥ ማምጣት ተችሏል ፡፡
በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ከ80 በላይ የሆኑ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድኖች መኖራቸው የሚናገሩት ወይዘሮ ሰላማዊት፤ እነዚህ ቡድኖች በየጊዜው ከኤጀንሲውና ሚሽኖች ጋር በመገናኘት መረጃ የሚለዋወጡበት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ዲያስፖራው አባላት በሀገራችን ጉዳይ ላይ የሚወጡ የተዛቡና የተሳሳቱ መረጃዎች የሚያስተካክሉበት ፣የሚከራከሩበትና መቃወም በሚገባቸው የሚቃወሙበት ሁኔታ መኖሩን ጠቁመው ፤ ተቃውሟቸውን በተለያየ መንገድ በመግለጽ በርካታ ሥራዎች እየሰሩ መሆኑን አስረድተዋል ፡፡
ከዚህም ባሻገር ኤጀንሲው በየሳምንቱ ከሠላሳ በላይ ከሚሆኑ የዲያስፖራ ሚዲያዎች ጋር የመረጃ ለውጥ ሥራዎችን እንደሚሰራ ዋና ዳይሬክተሯ ገልጸዋል፡፡ በዚህም የዲያስፖራ ሚዲያዎች ሀገራችን ያለችበት ነባራዊ እውነታ በማስረዳት ትክክለኛ መረጃ የሚያገኙበት መንገድ ለማህበረሰቡም ሆነ ሌሎች አካላት የሚያስረዱበትን ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች የለጠፉት እስከሚያወርዱ ድረስ ሚዲያ ላይ የሚወጡ ነገሮች እንዲስተካካሉ ፤ውሳኔዎች እንዲቀየሩ የማድረግ ሥራ መስራት ተችሏል፡፡
ዜጎች ለሀገራችው አምባሳደር እንዲሆኑ በማድረግ ብዙ ሀገራት ተጠቃሚ ሆነዋል ያሉት ወይዘሮ ሰላማዊት ፤ ይህንን ተጠቅሞ የተሻለ እድል መፍጠር እንደሚቻል ጠቁመዋል፡፡ በዚህም ከ50 በላይ የቲውተር ዘመቻዎች በማድረግ በተለያዩ ርእስ ጉዳዮች ላይ በርካታ መልዕክቶችን ማስተላለፍ ተችሏል፡፡ ዲያስፖራው አባላት በዓለም አቀፍ መድረኮች ብዙ ቦታዎች ላይ በመገኘት ስለ ሀገራቸው እንዲሞግቱ የተደረገ መሆኑን ጠቁመው፤ በዚህም ውሳኔዎች እስከማስቀየር እና የተሳሳተ መረጃቸውን እንዲያርሙ ማድረግ ተችሏል ብለዋል፡፡
በተመሳሳይ ገበታ ለሀገር ከዲያስፖራው ወደ 30 ሚሊየን የሚጠጋ ብር መሰብሰቡ ተጠቁሟል ፡፡ እንዲሁም በአገራዊ ጥሪም በኮቪድ ወረርሽን ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ በአይነትእና በገንዘብ ከግማሽ ሚሊየን በላይ ብር ድጋፍ የተደረገ ሲሆን፤ በበጀት ዓመቱ 282 ሚሊየን ብር በላይ ተሰብስቧል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በህግ በማስከበር ዘመቻ ወቅት በአጭር ጊዜ ውስጥ ለሀገር መከላከያ ሠራዊትና ለተጎዱ ወገኖች በመጀመሪያ ዙር ከ700 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ የተደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ ሁለተኛ ዙር ሶስት ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውሰጥ 36 ሚሊየን ብር ድጋፍ መደረጉን ገልጸዋል፡፡
ኤጀንሲ ዲያስፖራዎች ኢንቨስትመንት ላይ እንዲሳተፉ ለማድረግ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር የመከታተል ኃላፊነት አለበት ያሉት ወይዘሮ ሰላማዊት ፤በዚህም ረገድ በኢንቨስትመንትና በንግድ 3 ነጥብ 9 ሚሊየን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ፕሮጀክቶች ወደ ሥራ መግባታቸው ጠቁመዋል፡፡ በእነዚህ ፕሮጀክቶች ለ13ሺህ ዜጎች የሥራ እድል መፍጠር መቻሉ አመላክተዋል፡፡
የውጭ ምንዛሪ ፍሰት በተመለከተ በበጀት ዓመቱ 3ነጥብ 6 ቢሊየን ዶላር ገቢ የተገኘ ሲሆን፤ ይህም ሀገራችን በውጭ ኤክስፖርት ከምታገኘው የውጭ ምንዛሬ የተሻለ ገቢ እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡ በዚህም 6ሺ 914 የዲያስፖራ አባላት በሀገር ውስጥ የውጭ ምንዛሬ አካውንት በመክፈት የሚያንቀሳቀሱ መሆኑን ጠቅሰው፤ 7ሚሊየን 542 ሺህ 231 ዶላር ተቀማጭ የሆነበት ወይም የተንቀሳቀሱበት ሁኔታ መኖሩ አመላክተዋል፡፡ ይህም ሆኖ በሚፈለገው ልክ ማግኘት የሚገባ የውጪ ምንዛሬ እየተገኘ አይደለም የሚሉት ወይዘሮ ሰላማዊት፤ በጣም ከፍተኛ አቅም ያለንን በመሆኑ ብዙ ሥራዎች መስራት ይጠብቅበናል ብለዋል ፡፡
ዲያስፖራው ገንዘቡን በህጋዊ መንገድ ብቻ በመላክ በኢትዮጵያ ላይ እየተፈጠሩ ያሉ ጫናዎችን ለመቋቋም የጀመረውን ተግባር አጠናክሮ መቀጠል አለበት ያሉት ወይዘሮ ሰላማዊት፤ በዚህ ረገድ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ በመወጣት ሊሰራበት የሚገባው ጉዳይ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ አክለውም ቀጣዩ አዲስ አመት እንደመሆኑ መጠን ዲያስፖራው ማስተላልፍ የምንፈልገው ሆነ ለቤተሰቦቹ የሚልከውን ገንዘብ ልክ ህጋዊ በሆነ መንገድ መላክ ይገባዋል ሲሉ አሳስበዋል ፡፡
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ነሐሴ 26/2013