
ኢትዮጵያ ባለፉት ጊዜያት እንዳየነውና አሁን እንደምናየው በርካታ ፈተናዎችን እየተጋፈጠች ትገኛለች። ምናልባት ከፋሽስት ወረራ በኋላ ከውስጥና ከውጭ ኢትዮጵያን እጅግ ከባድ ፈተና የገጠማት በዚህ ዘመን ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም።
ባለፉት ሶስት ተከታታይ ዓመታት ካጋጠሙን ፈተናዎች መካከል የሚጠቀሱት ከውጭ የህዳሴው ግድብ ሙሌትን ተከተሎ የተነሳው የግብፅ ወዮታና የምዕራባውያን ሃገሮች ጫና እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተከስቶ የነበረው የኮረና ቫይረስ ስርጭት እንዲሁም በውስጥ ደግሞ በሰሜንና ሰሜን ምስራቅ ኢትዮጵያ ተነስቶ የነበረው የበረሃ አንበጣ እና ከለውጡ ማግስት ጀምሮ የሽብር ተግባር እዚህም እዛም ሲፈፅም ከርሞ ሀገር እስከማፍረስ ደረጃ የደረሰው የአሸባሪው ህወሓት የሴራ ጥንስስ ዋና ዋናዎቹ ናቸው።
ከሁሉም የባሰው ደግሞ ከውስጥ የተነሳው አሸባሪው የህወሓት ቡድን በግፍ በህዝብ ልጆች ላይ የከፈተው ጦርነት ነው። ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በአሸባሪው ህወሓት ሴራ ሰበብ ከውጪ ሃይሎች ጋር የህልውና ጦርነት ገጥማለች። ይህም ባለፈው ጥቅምት ወር ላይ ከተወሰደው ህግ ማስከበር ዘመቻ ተከትሎ መንግስት ወቅቱን ያገናዘበ የተናጠል የተኩስ ማቆም ውሳኔ ቢያደርግም አሸባሪው ህወሓት ግን እድሉን ወደ ቼዝ ጨዋታ ቀይሮ ሰብዓዊ እርዳታዎችን በማስተጓጎል፣ በአጎራባች ክልሎች ላይ ጦርነት ዳግም በመክፈት ብዙ እልቂት እንዲፈጠር በማድረግ እየሰራ ነው።
አሸባሪን አሸባሪ ማለት ያቃታቸው አንዳንድ የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪና ጠበቃ ነን ባይ ሀገራት በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት ከአሸባሪ ቡድን ጋር ድርድር እንዲደረግ በመወትወት በመንግስት አሉታዊ ጫና እንዲፈጠር በከፍተኛ ሁኔታ በመንቀሳቀስ ላይ ናቸው። ከዚህ በተቃራኒ ግን መላ የኢትዮጵያ ህዝብ ከዳር እስከ ዳር በህብረት ወጥቶ አሸባሪውን ቡድን ለመፋለም ቆርጦ መነሳቱ በችግር ውስጥ የተገኘ ድል ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል። ጀግኖች እናቶችና አባቶች የውጭ ወራሪዎችን ብቻ ሳይሆን የውስጥ ባንዳዎችን ጭምር በማንበርከክ የዛሬይቱን ኢትዮጵያ በነፍሳቸው ተወራርደው አቆይተዋታል።
አዎ ሃገራችን በዘመናት መካከል ያጋጠሟትን ፈተናዎች እና ያጋጠሟትን የክፋት ኃይሎች ሁሉ ድል በማድረግ ታፍራና ተከብራ ነጻነቷን አስጠብቃ መኖር ችላለች። በታሪክ አጋጣሚ ኢትዮጵያ ያጠባ ጡቷን፣ ያጎረሰ እጇን የሚነክሱ ከሃዲዎች፣ ሊያዳክሟትና ሊበትኗት ከውስጥና ከውጭ ኃይሎች ጋር አብረው ተሰልፈዋል። ይሁንና እነዚህ ኃይሎች ያልገባቸው ነገር ቢኖር ኢትዮጵያ ፈተናዎች ሲጋረጡባት ምንግዜም የማይሸረሸር የአይበገሬነት ወኔ እና ምንግዜም የማይበጠስ የአንድነት ገመድ በፅኑ ህዝቦቿ ልብ ውስጥ ያለ መሆኑ ነው።
በኢትዮጵያውያን አኩሪ አንድነት በአገር አቅም፣ ጥረትና ንዋይ የተገነባው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ከምርጥ የዲፕሎማሲያዊ ድል ጋር ወደ አፍሪካ ኅብረት በመመለስ የውሃ ሙሌቱ ሁለተኛ ዙሩን አጠናቋል። የኮረና ቫይረስ ስርጭትን በተመለከተም ከመጀመሪያው ጀምሮ በኢትዮጵያዊነት እና አፍሪካዊነት በተሰራው ግንባር ቀደም የዲፕሎማሲ ስራ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ጠንካራ የኮሮና መከላከልና መቆጣጠር ስርዓት በመከተል አቅም ከፈጠሩ ግንባር ቀደም አገራት አንዷ ለመሆን በቅታለች።
በርግጥም የገጠሙን እጅግ ከባድ ፈተናዎች ወደ ወሳኝ ምዕራፍ የሚያሸጋግሩን በር እየሆኑ መጥተዋል፤ ኢትዮጵያ ከምንጊዜውም በላይ ወደ ተሻለ የሰላም፣ የዴሞክራሲና የብልጽግና ምዕራፍ ለመሻገር የሚያስችሉ ወሳኝ ድሎች አሁን ተገኝተዋል።
ምንም ጨለማው ቢበረታና ከባድ ፈተና ቢያጋጥመንም ተሻግረን የንጋት ኮኮብ ለማየት እየተቃረብን ነውና ለዚህ ነው ኢትዮጵያውያን ዕድለኞች ነን የምንለው። እነዚህ ፈተናዎች መልካም አጋጣሚ ይዘውልን እንደመጡ ልንገነዘብ ይገባል። ችግሮች ቢበዙ እና ፈተናም ቢበረታ የኢትዮጵያ ሕዝብ ክብሩን እና ነፃነቱን ጠብቆ ወደ ብልፅግና ማማ ከመውጣት የሚያግደው አይኖርም። እነዚህን መልካም አጋጣሚዎች ማጣጣም የሚቻለው ደግሞ በመካከላችን የተጠናከረ ህብረት፣ በኢትዮጵያዊነት የተገመደ ፍቅርና ይቅርታ እንዲሁም መደጋገፍ ሲኖር እንደሆነ ልብ ልንል ይገባል!
አዲስ ዘመን ነሐሴ 25/2013