ዶክተር ሞገስ ደምሴ ይባላሉ፡፡ ከመጀመሪያ እስከ ሶስተኛ ዲግሪ የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ጥናት ትምህርትን ተከታትለዋል፡፡ በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ለ15 ዓመታት በዚሁ ትምህርት ክፍል መምህር እና ተመራማሪ ሆነው አገልግለዋል፡፡ አሁን ደግሞ በሰላም ሚኒስቴር የሚንስትሯ አማካሪ ሆነው በመሥራት ላይ ይገኛሉ፡፡ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተቋማትን ዓላማ እና በኢትዮጵያ ያላቸውን ፍላጎት በሚመለከት እና በሌሎችም ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ቆይታ አድርገን የሰጡንን ማብራሪያ እንዲህ አቅርበንላችኋል፤ መልካም ንባብ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ማለት ምን ማለት ነው፤ እነዚህን መብቶች ለማስከበር ሰው ከመሆን ያለፈ ልዩ የሚያመፃድቅ አቅም ያስፈልጋል?
ዶክተር ሞገስ፡- የሰብአዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብት ስንል በተለይ የሰብአዊ መብት በዋናነት የሰው ልጅ ሰው በመሆኑ ብቻ ያለ ልዩነት ሊያገኛቸው እና ሊጠበቁለት የሚገቡ ጉዳዮች ናቸው። በሂደት ሰብአዊ እና ዴሞክራሲያዊ ተብለው ቢከፋፈሉም በመጀመሪያ የነበረው እሳቤ ሁሉም የሰው ልጆች የሚያመሳስላቸው እና አንድ የሚያደርጋቸው እሳቤዎች አሏቸው። ሰው ሆነው በመፍጠራቸው እና ክቡር በመሆናቸው ክብራቸውን የሚመጥን አያያዝ፤ አገልግሎት የመሳሰሉት መከበራቸው በሰብአዊ መብት ውስጥ ይካተታሉ።
በሂደት ደግሞ ዴሞክራሲያዊ መብት ተብለው ተለይቷል። አሁን እነዚህ መብቶች እየተቀያየሩ እንጠቀምባቸዋለን። ሙሉ በሙሉ ይህ ሰብአዊ መብት ነው። ይሔ ደግሞ ዴሞክራሲያዊ መብት ነው በማለት ከፋፍሎ ለማስቀመጥ አይቻልም። ምክንያቱም ይወራረሳሉ። በቀጥታ ሰብአዊ መብት ይህ ነው። ይህ ደግሞ ዴሞክራሲያዊ መብት ነው። ብሎ ለማስመር ቢያዳግትም ትንሽ የሚለያቸው ነገርም አለ።
በአብዛኛው ዴሞክራሲያዊ መብቶች የሚከበሩት ዴሞክራሲዊ ሥርዓትን በሚከተሉ አገራት ውስጥ ነው። ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን የማይከተሉ አገራት በአብዛኛው ዴሞክራሲያዊ የሚባሉ መብቶችን ሲጨፈልቁ እና ሲደፈጥጡ ዜጎቻቸውን ተገቢ ባልሆነ መልኩ ሲይዙ ይታያል። ዴሞክራሲያዊ አገር ባለመሆናቸው ለአያያዛቸው ተጠያቂ አይሆኑም። ምክንያቱም ዴሞክራሲ በሌለበት አገር ውስጥ ሃላፊነትን መውሰድ የለም።
ሰብአዊ መብት ግን በአምባገነንም ሆነ በዴሞክራሲያው መንግስት የሚከበሩ ናቸው። አምባገነን መንግስትም ቢሆን በአገር ውስጥ ለሚኖሩ ህዝቦች የግድ እኩል የሰብአዊ መብቶችን ማስጠበቅ አለበት። ሰብአዊ መብቶች በማንኛውም መንግስት የማይገረሰሱ እና የማይጣሱ ናቸው። ለምሳሌ በህይወት የመኖር መብት፤ የአካል ደህንነት የመጠበቅ መብት የሚባሉት አንድ አገር ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ተከተለም አልተከተለ ማክበር ይጠበቅበታል።
ሰብአዊ መብት ሰፋ ያለ እና ብዙ ነገሮችን አጠቃሎ የያዘ በሁሉም አገር የሚከበር ነው። ዴሞክራሲያዊ መብቶች ግን ምንም እንኳ ሁሉም ሰዎች ማግኘት የሚፈልጓቸው ቢሆኑም፤ እነዚህን መብቶች መስጠት የሚችሉት ጥቂት ዴሞክራሲን የሚከተሉ እና ዴሞክራሲን ባህል ያደረጉ አገራት ናቸው። ከዚህ አንፃር የተወሰነ ልዩነት ሊቀመጥ ይችላል። ነገር ግን በአጠቃላይ ደግሞ ሁለቱም ሊተካኩ እና ሊወራረሱ የሚችሉበት ሁኔታ አለ።
አዲስ ዘመን፡- ዴሞክራሲያዊ እና ሰብአዊ መብቶችን ለማስከበር ሰው ከመሆን ውጪ የተለየ ሃብት ይጠይቃል?
ዶክተር ሞገስ፡- ሰብአዊ መብት መሰረቱ ሰውነት ነው። በየትኛውም የዓለም አቅጣጫ አሜሪካም ሆነ አፍሪካ ኤዢያም ሆነ የትም ሰው የሚባል ፍጡር እስካለ ድረስ እነዚህ መብቶች መከበር አለባቸው። አሜሪካን ሲሆን መከበር አሜሪካን ካልሆነ የማይከበርበት ሁኔታ መኖር የለበትም። የሰብአዊ መብቶች በሁሉም ቦታ ያለብሔር ልዩነት፣ ያለመደብ እና ያለሃብት ልዩነት ሁሉም በእኩልነት የሚከበሩ ናቸው። ነገር ግን እነዚህ በመርህ ደረጃ ያሉ ናቸው። ወደ መሬት ይውረዱ ሲባል ተግባር ላይ ብዙ ፈተናዎች ይመጣሉ።
አንዳንድ አገሮች የደረሱባቸው ደረጃዎች እነዚህን መብቶች ለማስከበር የሚያስችል ቁመና ላይ ይገኛሉ። ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ቴክኖሎጂያዊ፣ ጂኦግራፊያዊ ሁኔታዎች አሉ። እነዚህ በተሻለ መልኩ በሚገኙባቸው አገራት በተሻለ መጠን እየተከበሩ ይገኛሉ። ምክንያቱም እነዚህን መብቶች ለማክበር ተቋማት ያስፈልጋሉ። እነዚህ መብቶች እንዲከበሩ የሚታገሉ፤ እነዚህ መብቶች እንዲከበሩ የሚያስችሉ አደረጃጀቶች ያስፈልጋሉ። እነዚህ ተቋማት በጥሩ ቁመና ላይ ያሉ፤ አቅምም ያላቸው መሆን አለባቸው። ተቋማት ከሌሉ የሰብአዊ መብቶች የሚከበሩት እና የማይከበሩበት ሁኔታ ከፍ ዝቅ ሊል ይችላል። ከዛ አንፃር አንዳንድ አገራት በራሳቸው አገር የሰብአዊ መብትን ከማስጠበቅ ባለፈ በሌሎች አገሮችም ለማስጠበቅ ሚና የመውሰድ ጉዳይ ይኖራል። አንዳንድ አገሮች ዘለግ ያለ እጅ እና አቅም ያላቸው ራሳቸውን የሰብአዊ መብት ጠባቂ፤ ተከራካሪ አድርገው የመሾም እና የመውሰድ እንዲሁም በሂደቱ በሌሎች አገሮች ጉዳይ ላይ ጣልቃ የመግባት ሁኔታ አለ ማለት ነው።
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ ውስጥ የሰብአዊ መብት ተቋማት አሉ። እነዚህ ተቋማት የሰብአዊ መብቶችን ከማስከበር አንፃር ያሉበትን ደረጃ እንዴት ያዩታል?
ዶክተር ሞገስ፡- የሰብአዊ መብት አስተሳሰቡ ራሱ ዛሬ የደረሰበት ደረጃ ላይ የደረሰው በሂደት እየዳበረ መጥቶ ነው። ለምሳሌ እ.አ.አ በ1966 ዓለም አቀፍ የሲቪል እና የፖለቲካ መብቶች ኮንቬንሽን ሲታይ አገራት ሲስማሙ አሁን ባሉበት ደረጃ ላይ አልነበሩም። ብዙ አገራት የተሻለ ደረጃ ላይ የደረሱት በሒደት ነው። የመጀመሪያው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብት (ዩ.ዲ.ኤች.አር) በ1948 የተስማሙት ኮንቬንሽን ተሳታፊዎቹ ጥቂት አገራት ነበሩ። አንዳንድ አገራት በተለይም ብዙ አፍሪካውያን በዛ ወቅት ነፃ አልወጡም ነበር። በቀኝ ግዛት ውስጥ ስለነበሩ ስለኮንቬንሽን እና ስለሰብአዊ መብት ተነጋግረው ሊስማሙ የቻሉት ጥቂት አገራት ብቻ ነበሩ። በሒደት ግን አገራት ከጭቆና አገዛዝ ነፃ እየወጡ ከራሳቸው የፖለቲካ መሻሻል አንፃር እያደጉ ሲሔዱ እነዚህ መብቶችን ወደ ማስጠበቅ ደረሱ። ስለዚህ መብቱን የማስከበር ሂደት እየዳበረ የመጣው በሒደት ነው ማለት ይቻላል።
በኢትዮጵያም በሒደት እያደገ መጥቷል። ስለሰብአዊ መብት ማውራት የጀመርነው ዛሬ አይደለም። በንጉሱ ዘመንም ስለሰብአዊ መብት ይወራ ነበር። በተወሰነ ደረጃ በተሻሻለው የ1948ቱ ህገመንግስት ላይ የተወሰኑ አንቀፆች ስለሰብአዊ መብት ተቀምጦባቸዋል። ነገር ግን ያ የመልካም ምኞት ያህል እንጂ በተግባር ወርደው የዜጎች መብቶች ሆነው የሚፈፀሙበት ዕድል ጠባብ ነው። ለምሳሌ ዜጎች በነፃነት ሃሳባቸውን ለመግለፅ የመደራጀት፣ የመፃፍ የመቃወም ነገር ውስጥ ላይገቡ ይችላሉ። ነገር ግን በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት መርሆች ከብዙ ጊዜ ጀምሮ ተዋውቀዋል። ለረዥም ጊዜም ሥራ ላይ ውለዋል። በደርግ ዘመነ መንግስትም የነበረው ህገመንግስት ለሰብአዊ መብቶች በሰፊው ዕውቅና ሰጥቷል። ነገር ግን በተግባር እነዚህ የዜጎች መብቶች እና ነፃነቶች ተጠብቀዋል የሚለው ሲታይ ብዙ ጥያቄ ሊያስነሱ የሚችሉ ነገሮች ነበሩ።
እ.አ.አ ከ1991 ዓ.ም ጀምሮ ወይም በ1983 ዓ.ም ያለው ስርዓትም ሲታይ በመርህ ደረጃ ችግር የለበትም። አደጉ በሚባሉ አገራትም ጭምር ያሉ የሰብአዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በኢትዮጵያ ህገመንግስት ውስጥ ተካተው ይገኛሉ። በተግባር ላይ እንዲውሉም አንዳንድ ሥራዎች የተሰሩ ሲሆን ሰብአዊ መብት ኮሚሽን፣ ዕንባ ጠባቂ እና ፍርድ ቤቶችን የመሳሰሉ ሰብአዊ መብትን ለማስጠበቅ የሚስችሉ ተቋማት ተመስርተዋል። ነገር ግን ሲንቀሳቀሱ የነበሩት በምን መልክ ነው? ከሰው ሃይል ጀምሮ እስከ የአሰራር ነፃነታቸው ድረስ አደረጃጀታቸው ምን ይመስላል? ሲባል ለሰብአዊ መብት ሊታገሉ በሚያስችላቸው ደረጃ ላይ ነበሩ ብሎ ለመናገር ያስቸግራል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን አገሪቱ የለውጥ ሒደት ውስጥ በመሆኗ አንዳንድ በተግባር ሊታዩ የሚችሉ እርምጃዎች በመወሰድ ላይ መሆናቸውን ሁላችንም እየተገነዘብን ነው። ለምሳሌ የፍርድ ቤቶች ነፃነት በተወሰነ ደረጃ ምን ያህል ነፃ በመሆን ላይ መሆናቸው በሚወስኑት ውሳኔ እየታየ ነው። ውሳኔያቸው ለህግ አስፈፃሚው የማይዋጥ ቢሆንም ለመወሰን እየቻሉ ነው። ስለዚህ በነፃነት የመወሰን አቅም እየፈጠሩ እንደሆነ ማየት ችለናል። እንደዚሁም የሰብአዊ መብት ተቋም ምን ያህል ከአመራሩ ጀምሮ ገለልተኛ እየሆነ እንደመጣ እየታየ ነው። ከዚህ በፊት አመራሩ ለፓርቲ ካለው ታማኝነት አንፃር የሚታይ እና ከፓርቲ ጋር የተጣበቀ ተቋም ነበር። ሰብአዊ መብትን እያስከበረ ነው ቢባልም የአንድን ፓርቲ ህይወት የሚያራምዱ ሰዎች ያሉበት ተቋም ነበረ። አሁን ከዛ በተፋታ መንገድ በአመራርም በአሰራርም ገለልተኛ እየሆነ እና በሒደት እየዳበር እንደመጣ እየታየ ነው። ከዚህ በፊት በአሰራር የሚደፈሩ የማይመስሉ ነገሮችን እየመረመረ ነው። አንዳንድ ጊዜ የሚያወጣቸው ሪፖርቶች ለአስፈፃሚው የሚጎረብጡ ይመስላሉ። ነገር ግን ቢጎረብጣቸውም ወደ ኋላ እየተያዘ አይደለም። በሚፈለገው ደረጃ አድጎ ጠንካራ የሰብአዊ መብት ተከራካሪ እና ተሟጋች ባይሆንም በሒደት ግን የአገሪቱ የዕድገት ደረጃ መታያዎች ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡- ስለዚህ የሰብአዊ መብት አጠባበቅ የሚያድገው በሂደት ነው። በኢትዮጵያም በሂደት እየተሻሻለ ነው ማለት ይቻላል።
ዶክተር ሞገስ፡- በእኔ እይታ ስለ አሁናዊው የኢትዮጵያ የዴሞክራሲ እና የፖለቲካ ሁኔታ ከሆነ እየተሻሻለ ነው። የሚወራው ካለፈው ስርዓት ጋር የሚነፃፀር ከሆነ በእውነት ሁለቱ ለንፅፅር የሚቀርቡ አይደሉም። ተገቢም አይደለም። አሁን ያለው የፖለቲካ ሥርዓት በፊት ካለ አምባገነናዊ ስርዓት ጋር ማነፃፀር ተገቢ አይደለም። ይልቁኑ ኢትዮጵያ አሁን በደረሰችበት ጊዜ ከሌሎች አገሮች አንፃር መወዳደር አለባት። ለምሳሌ ከኬኒያ፣ ወይም ከዑጋንዳ ወይንም ከሌሎች አገሮች አንፃር መወዳደር አለብን። ከሌሎች አገሮች አንፃር ከታየ አገራችን ገና ጅምር ላይ ናት። መልካም በጎ በጎ የሚባሉ ጅምሮች አሉ። በዴሞክራሲ ደረጃ ከታየ ፖለቲካው በተወሰነ ደረጃ ክፍት ሆኗል። ከዚህ በፊት ተሰደው የነበሩ ድርጅቶች፤ በፖለቲካ አመለካከታቸው ከአገራቸው ሸሽተው የነበሩ ዜጎች ተመልሰው ራሳቸውን አደራጅተው በነፃነት መንቀሳቀስ የጀመሩበት ጊዜ ነው። ይህ ማለት ግን በዘፈቀደ ልቅ መሆን አለበት ብዬ አላስብም። ምክንያቱም ፖለቲካው መለቀቁ አገርን ወደ አደጋ እና ወደ አለመረጋጋት ይከታል። መርህ ያለው ልዩነትን ሊያስተናግድ የሚችል ሰፊ ምህዳር እየተፈጠረ ነው። ሙሉ ለሙሉ ተፈጥሯል፤ ዳብሯል፤ በልፅጓል ማለት ግን አይቻልም።
አዲስ ዘመን፡- ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተቋማት የተነሱበት አላማና አሁን ያላቸው ቁመና ምን ይመስላል ? እዚህ ላይ ምን ይላሉ?
ዶክተር ሞገስ፡- ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተቋማት በሁለት ዋና ዋና መንገድ መከፈል አለባቸው። አንደኛው በመንግስታት ስምምነት የሚፈጠሩ (Intergovernmental human right institution) የአገራት መንግስታት አባላት የሆኑበት ነው። መንግስታት ጉዳዮቻቸውን አቅርበው የሚወያዩባቸው ተቋማት ናቸው። ሁለተኛዎቹ ደግሞ ዓለም አቀፍ የሆኑ እና ለሰብአዊ መብት እንታገላለን የሚሉ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት አሉ። እነዚህ በተለያየ አገር ያሉ ዜጎች ፍላጎት የተመሰረቱ ናቸው። ለምሳሌ በመጀመሪያ ከተጠቀሰው በመንግስታት ስምምነት ከተፈጠረው ውስጥ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አንዱ ሆኖ የሚጠቀስ ነው። የተባበሩት መንግስታት አገራት ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ የእዚህ ተቋም ፈራሚ እና አባል ናቸው። በእነዚህ ህጎች እና ደንቦች ይመራሉ፤ ይገዛሉ ማለት ነው። በሌላ በኩል ያሉት ለሰብአዊ መብት እንታገላለን የሚሉ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ደግሞ የተለያዩ አገራት ዜጎች በአብዛኛው በፍላጎት ላይ የተመሰረተ ዓለም አቀፍ ባህሪ ያላቸው የሰብአዊ መብትን ለማስከበር ያገባናል ብለው የተነሱ ናቸው። አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና ሁዩማ ራይትስ ወች በዚህ ውስጥ ይካተታሉ።
በመንግስታት ስምምነት ስለሚመሰረቱት የሰብአዊ መብት ተቋማት ስለተባበሩት መንግስታት ካነሳን በህግ እና በሥርዓት በተባበሩት መንግስታት ቻርተር አማካኝነት የሚመሩ ናቸው። የአገራትን ነፃነት በሚሸረሽር መልኩ
ጣልቃ የመግባት መብት የላቸውም። ከመንግስታቱ ጋር አብረው በትብብር በሰብአዊ መብት ጉዳይ ላይ ይሰራሉ። የሰብአዊ መብት በትምህርት እንዲስፋፋ ኢንቨስት ሊያደርጉ ይችላሉ። የሰብአዊ መብት ተቋማት እንዲጠናከሩ፤ በሰው ሃይል፣ በገንዘብ ዕርዳታ ወይም በሰው ሃይል ስልጠና በተለያየ መልኩ ከመንግስታት ጋር በትብብር ይሰራሉ።
በዓለም ባሉ አገሮች የሰብአዊ መብት እንዲከበር ምቹ ሁኔታ የመፍጠር ሂደት ላይ ይሳተፋሉ። ከዛ ውጪ የመክሰስ እና ጣልቃ የመግባት እንዲሁም የማስገደድ መብት የላቸውም። ነገር ግን በአንዳንድ ልዩ ሁኔታዎች ውስጥ ለምሳሌ ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት በሚፈፅሙ አገራት ላይ አንዳንድ ቅሬታዎችን የማንሳት እና በጉዳዩ ላይ ውይይት እንዲካሔድ የማድረግ አንዳንዴ መንግስታቱ በሰብአዊ መብት ጥሰት ውስጥ እጃቸው ካለ የእርምት እርምጃ እንዲወስዱ ሃሳብ የሚያነሱበት ሁኔታ አለ። ከዛ ባለፈ ግን ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት፣ የዘር ማጥፋት እና ሌሎችም በሰዎች ላይ የሚፈፀሙ ጥፋቶች ሲፈጠሩ ደግሞ ሌሎች ተቋማት አሉ። በሰብአዊ መብት ላይ የተቃጡ ተገቢ ያልሆኑ ሰብአዊ መብትን የሚሸረሽሩ እና የሚጥሱ ጉዳዮች ሲፈጠሩ ህጋዊ ዕውቅና የተሰጠው ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት (International criminal court) እና ዓለም አቀፍ የወንጀል ችሎት (International crime tribunal) የሚባሉ ተቋማት አሉ። የመክሰስ እና አገራትን ተጠያቂ የማድረግ ሃላፊነት የተሰጣቸው ተቋማት ናቸው። እነዚህ ተቋማት አብረው በትብብር ይሰራሉ።
በአብዛኛው እነዚህ ተቋማት በማን ጫና ውስጥ ሆነው እንደሚንቀሳቀሱ ይታወቃል። አሁን እየሆነ ያለው እና ትልቅ ችግር እየመጣ የሚገኘው በተለይም የተባበሩት መንግስታትን የመሳሰሉ ተቋማት ባደጉ አገራት ጫና ውስጥ ያሉ መሆናቸው ነው። ምክንያቱም ገንዘብ የሚሰጧቸው አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ፣ ካናዳ እና አውስትራሊያ የመሳሰሉ አገራት ናቸው። በቀጥታም ባይሆን በተዘዋዋሪ ጫና ይፈጠራል። ለምሳሌ ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት (International criminal court) ባለፉት ሁለት እና ሶስት ዓሥርት ዓመታት የተከሰሱት መሪዎች ሲታዩ ከአውሮፓ አንድ የሰርቢያን መሪ ብቻ ለፍርድ አቅርበዋል። ከኤዢያ አንድ መሪ ሲያቀርቡ በአብዛኛው ትኩረታቸው አፍሪካ ላይ ነው። መነሻቸው አፍሪካውያን እነዚህን የመብት ጥሰቶች መርምሮ አጣርቶ ትክክለኛ ውሳኔ ሊሰጥ የሚችል ተቋም የላቸውም በሚል አስተሳሰብ ነው። ይህ ከቀኝ ግዛት አስተሳሰብ ያልተላቀቀ አስተሳሰብ ነው።
በአብዛኛው እነዚህ ተቋማት ትኩረታቸው አፍሪካ እና ያላደጉት አገራት ላይ ነው። ከዚህ አንፃር ትልቅ ጫና እንዳለ ይታወቃል። በሰብአዊ መብት ጉዳይ ላይ ምዕራባውያኑ እኛ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች እና ተከራካሪዎች ነን የሚል የትም ቦታ የሚፈጠር የሰብአዊ መብት ጥሰት እኛን ያገባናል። ስለዚህ እኛ ከቻልን በስምምነት ካልሆነ ጫና አድርገንም ቢሆን ልካቸውን የማሳየት ሃላፊነት አለብን የሚሉ ይመስላል። ለዛም በተቋሞቻችን በገንዘብ አቅማችን ይህንን ለማስከበር እንሰራለን የሚል አቀራረብ አላቸው። ይህ ልማድ አዲስ አይደለም። የቀጠለ ነው። ምናልባት አሁን ላይ እየመጣ ያለው አካሄድ በቀጥታ ሳይሆን በተዘዋዋሪ አገራት ላይ ጫና በመፍጠር መንግስታቱ በሙሉ አቅማቸው በነፃነት እንዳይንቀሳቀሱ አጥሮ የመያዝ እና የማስፈራራት የተለያዩ ተግዳሮቶችን የመጣል ሁኔታ አለ።
አዲስ ዘመን፡- ከ20ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ጀምሮ የሰብአዊ መብት ጉዳይ የምዕራቡ ዓለም አንድ የፖለቲካ መሳሪያ እንደሆነ በስፋት ይነገራል፤ ይህ ምን ያህል እውነት ነው፤ ማሳያዎቹስ ምንድን ናቸው?
ዶክተር ሞገስ፡- የእነዚህ የዓለም አቀፍ ተቋማት መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ሲታዩ በአብዛኛው መነሻቸው በመርህ ደረጃ ከፊት ለፊት የሚታየው ማንኛውም ጤነኛ የሆነውን ሰው ሊያስማማ የሚችል የሰብአዊ መብት ጉዳይ ነው። እንደዚህ የሰብአዊ መብት የሚጥሱ አገራት መንግስታት ሃላፊነት እንዲወስዱ እንታገላለን። በትምህርትም በማስተዋወቅም የሰብአዊ መብት እንዲስፋፋ እናደርጋለን ይላሉ። ይህንን የማይቀበል መንግስትም ዜጋም በዓለም ላይ የለም። ነገር ግን እነዚህ ተቋማት በአሰራር እና በአደረጃጀት ጭምር በአብዛኛው የተወሰኑ የዓለም አገራትን አስተሳሰብ፣ ርዕዮት እና ባህል ለማስረፅ የሚሰሩ ሆነው ይገኛሉ። ይህ የሚደርግበት ዋነኛው ምክንያት አብዛኛዎቹ የተቋማቱ መነሻ የምዕራብ አገራት ናቸው። አነሳሳቸው እና የሚያራምዱት አስተሳሰብ የምዕራባውያኑን ነው። በአብዛኛው ትኩረታቸው የግለሰብ መብቶች እና ነፃነቶች ላይ ነው። በራሳቸው አገር ላይ የማያደርጉትን በሌላው አገር የግለሰብ መብቶች እና ነፃነቶች ያለገደብ እንዲከበሩ ያነሳሳሉ። እነዚህ መብቶች እና ነፃነቶች በሌሎች አገሮች ምን አንድምታ አላቸው ብለው አያስቡም።
የሌላው ዓለም ባህል እና እሴት እንደኋላ ቀር መተካት እንዳለባቸው ያስባሉ። ስለዚህ ምንም ያህል የዳበረ የእርስ በእርስ የመተሳሰብ አብሮ የመኖር ባህል ያለው ማህበረሰብ ያለበት አገር ላይም እነዚህን አብሮ የመኖር የመተሳሰብ ባህል ትታችሁ በግለሰባዊነት ተኳቸው ይላሉ። አስበው ብቻ ሳይሆን ሳያስቡም እንዲህ ሊያደርጉ ይችላሉ። ምክንያቱም የተቀረፁት በምዕራባውያን ነው። ከጀርባ ለተቋማቱ ገንዘብ የሚሰጣቸው ማን ነው? የሚለው ሲታይ የምዕራባውያን ኩባንያዎች የገንዘብ ፍላጎት መኖሩም ይታያል። የእነዚህ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ድርጅቶች ወጪያቸውን የሚሸፍኑት ምዕራባውያን ናቸው። ምዕራባውያን ሲባል ደግሞ የተለያዩ የቢዝነስ ኩባያዎች ናቸው። እነዚህ ካምፓኒዎች ለእነርሱ የማይመቹ መንግስታት እንዲከሰሱላቸው፤ እንዲወቀሱላቸው ከተቻለም በእነርሱ መንግስት ጫና እንዲደረግባቸው እና ከስልጣን እንዲነሱ ለእነርሱ ምቹ የሆነ ከባቢ እንዲፈጠር ይገፋሉ። ስለዚህ በድርጅቶቹ የሚወጡ ፅሁፎች፤ በየጊዜው በሚያቀርቧቸው ጥናታዊ ፅሁፎቻቸው እና በሪፖርቶቻቸው በአብዛኛው ያልተመቿቸውን የሶስተኛው ዓለምን እና ያላደጉ አገራትን መንግስታት ይኮንናሉ፤ ይወቅሳሉ።
ከኋላ ያለው ፍላጎታቸው ምንድን ነው? ከተባለ ይህን የሚያደርጉት በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ግሎባላይዜሽን በመሆኑ የምዕራባውያኑ ድንበር ዘለል የፋይናንስ ካምፓኒዎች የገንዘብ ፍላጎታቸውን ለማስፈፀም ርካሽ የሰራተኛ ጉልበት እና ርካሽ ጥሬ ዕቃን የሚፈልጉ በመሆኑ እነዚህን በምቹ ሁኔታ ማግኘት የሚችሉበትን መደላድል መፍጠር ነው። ድርጅቶቹ ከላይ ሲታዩ ዓላማቸው እና ሽፋናቸው ሰብአዊ መብት ቢሆንም፤ ከጀርባ በርካታ ፍላጎቶች አሏቸው። የቢዝነስ፣ የጦር መሳሪያ ሽያጭ እና የሌሎችም ፍላጎቶች ያሏቸው ሲሆን፤ የተገነቡትም በምዕራባውያን እሴት ላይ ነው።
የሰብአዊ መብት ድርጅቶቹ በአሰራር እና በአደረጃጀት ጭምር የተወሰኑ የዓለም አገራትን አስተሳሰብ ባህል ለማስረፅ እና ለማስፋፋት የሚሰሩ ተቋማት በመሆናቸው በጦርነት ባይሆንም አገር የተገነባበትን እሴት በመሸርሸር አገራትን ያፈራርሳሉ። የባህል ወረራ ያደርጋሉ። አገር የሚገነባው በባህል ነው። ባህሉ እና እሴቱ በተሸረሸረ ቁጥር በጊዜ ሂደት ተንዶ አገር የምትቆምበት መሰረት ይናጋል። ለእዚህ ነው ምንም እንኳ አሸባሪዎች ምክንያታቸውን ለመናገር ቢከብድም መነሻቸውን ከምዕራባውያን ባህል ወረራ ጋር ያያይዙታል። የናይጄሪያው ቦኮሃራም ምዕራባዊ የሆነውን ትምህርት እና እሴት ባህላችንን ሸረሸረ ይላል።
ቦኮሃራሞች የሚከተሉት መንገድ በምንም መልኩ ተቀባይነት ባይኖረውም በዚህ አይነት አስተሳሰብ ያደጉት አገራት የሶስተኛውን ዓለም አገራት እየወረሩ መሆኑ አይካድም። ማንነታችንን እንድንተው እና ማንነታችን እንዲሸረሸር ሳይፈለግ የተገዛ አዕምሮ እንዲኖረን ይደርጋል። ከዚህ የበለጠ የዳግም ቀኝ ግዛት የሚባል ነገር የለም። እነዚህ ተቋማት በፊት ለፊት ጠመንጃ ተሸክመው ሲሄዱ አይታዩም፤ ነገር ግን ከስር ተከፍተው ሲታዩ መሳሪያ ተሸክመው የሚሄዱትን ይደግፋሉ። በአንድ ወገን መሳሪያ የሚሸከሙትን ይደግፋሉ፤ በሌላ በኩል መንግስትን ይወቅሳሉ ማለት ይቻላል።
አዲስ ዘመን፡- ስለዚህ የሰብዓዊ መብት ተቋማቱ የምዕራባውያኑ መሳሪያ ናቸው ማለት ይቻላል?
ዶክተር ሞገስ፡- አዎ! በእኔ እይታ በሶስተኛ የዓለም አገራት ለምሳሌ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተቋማት በአፍሪካ አዎንታዊ ሚና ሲጫወቱ አልታዩም። በአብዛኛው የታዩት መልካም እና ተራማጅ መሪዎችን የሚያስገድሉ፤ አገራዊ አስተሳሰብ ያላቸው ነፃነትን የሚያቀነቅኑ መሪዎችን የማይፈልጉ ናቸው። ተለጣፊ ለምዕራቡ አስተሳሰብ ተገዢ፤ የእነርሱን ጥቅም የሚያስከብሩ ሰዎችን የሚደግፉ ናቸው።
እነአሜሪካ በግልፅ ከአምባገነን መሪዎች ጋር እንደሚሰሩ ታይተዋል። ዴሞክራሲን በዓለም ላይ ለመትከል አጥማቂዎቹ እኛ ነን ብለው ራሳቸውን ቢሾሙም፤ በተግባር ግን የእነርሱን ጥቅም እና ፍላጎት የሚያስከብር መስሎ ከታያቸው ከማንኛውም አምባገነን ጋር ሲሰሩ ታይተዋል። በዚህ ስራቸው እንደውም በተግባር ዴሞክራሲን ሲያንኳስሱ እየታየ ነው። ምክንያቱም ዴሞክራሲ ለአገሩ ዜጎች ፍላጎት እና ጥቅም ቅድሚያ የሚሰጥ ነው። ለሌላ አገር ፍላጎት ቅድሚያ የሚሰጥ መሆን የለበትም። ይህ አካሔድ ለሃያላን አገሮች ጥቅማቸውን ለማስከበር የሚመች አይደለም። ስለዚህ በአብዛኛው በድሃ አገሮች ዴሞክራሲ እንዳይሰፍን እና መንግስታቱም ውጤታማ እንዳይሆኑ፤ ዴሞክራሲ መሰረት እንዳይዝ እና እንዳያብብ እንዲሁም እንዳይበለፅግ ይሰራሉ። በተዘዋዋሪ አንዳንዴም ፊት ለፊት በተለያዩ የአፍሪካ አገራት አማፂያንን ሲደግፉ ተስተውሏል። ከዚህ አንፃር አገር እንዳይረጋጋ እና ባለመረጋጋት ውስጥ ምዕራባውያን ጥቅማቸውን የሚያስከብሩላቸውን መንግስታት ወደ ሥልጣን ያመጣሉ። በአጠቃላይ ሂፖክራት ናቸው። በመርህ እንደዚህ ነን ይላሉ። በተግባር ግን ሲገለጡ ሌላ ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- የሰብአዊ መብት ተቋርቋሪ ነን የሚሉ ሀገራት የሰብአዊ መብት አጠባበቃቸው፤ የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪ የሚያደርጋቸው ነው ብለው ያምናሉ ?
ዶክተር ሞገስ፡- በእርግጥ በዓለም ላይ ሙሉ ለሙሉ ያለምንም እንከን የሰብአዊ መብትን ማስጠበቅ ይቻላል ተብሎ አይታሰብም። ነገር ግን የሰው ልጅ እስከሚችለው ድረስ እነዚህን መብቶች እና ነፃነቶች ለማስከበር የሚያስችሉ ሥራዎችን መስራት ይቻላል። ከአቅም በላይ የሆነ ነገር አላደረጋችሁም ብሎ መክሰስ አስቸጋሪ ነው። የሰው ልጅም ሆነ የአገራት አቅም የተወሰነ ነው። እነዚህ አገራት ከራሳቸው አገር የሰብአዊ መብት አጠባበቅ አንፃር ከታየ ትርጉም ያለው መንገድ እንደሔዱ መካድ አይቻልም።
በሰብአዊ መብት ውስጥ የሚካተቱ መርሆች በአብዛኛው የሚከበሩበትን ሁኔታ ፈጥረዋል? ብሎ መናገር ይቻላል። ነገር ግን በቂ ነው ወይ የሚለው ላይ መነጋገር ይቻላል። የእነርሱ ሰብአዊ መብት ለሁሉም ይሰራል ወይ? ከተባለ ያጠያይቃል። ሰብአዊ መብት አጠባበቁ ለተወሰነ ቡድን ያደላ ነው። ለተወሰነ መደብ የሰብአዊ መብታቸው እንዲከበር የሚቻለው ሁሉ ይደረግላቸዋል። ለምሳሌ በምዕራባውያን ለነጮች በአብዛኛው ሰብአዊ መብታቸው ይከበርላቸዋል። በአብዛኛው ፍርድ ቤት በደንብ ጉዳያቸው ይታያል። ነገር ግን የሌሎች ቡድኖች መብት ከታየ በአሜሪካም ገና ጅምር ላይ ነው።
የሰብአዊ መብቶቻቸው እንዲከበር ገና ትግል ላይ ናቸው። ለምሳሌ በአሜሪካ ለረዥም ጊዜ ትግል ነበር። እነማርቲን ሉተር ኪንግ እና ማልኮሜክስ የ1960ዎቹ እና የ1970ዎቹ ትግል ምን ያህል የአሜሪካንን የፖለቲካ ሁኔታ ሊለውጥ እንደቻለ ከታሪክ መረዳት ይቻላል። ነገር ግን አሁን ምን ላይ ደረሰ ከተባለ ብዙም ፈቅ አላለም። እንደውም ተቋማዊ ዘረኝነት መጥቷል። ተቋማቶች የሆነ ቡድንን የሚያዩበት የተለየ መነፅር አላቸው። በአብዛኛው የሚቀጠሩት ከሆነ አንድ ቡድን ነው። ከዛ ደግሞ በሆነ አይነት አስተሳሰብ ይጠመቃሉ። የፅንፈኛ የነጮች አስተሳሰብን ያራምዳሉ። በመርህ ደረጃ በፖሊስ ተቋማት ይህ የለም። ፊት ለፊት ማንኛውም ሰው የሚቀበለውን ሃሳብ ቢያቀርቡም በተግባር የሚሰሩት ሌላ ነው። የሚሰሩት በ21ኛው ክፍለ ዘመን አደገች ከተባለች እና የዓለም ቁንጮ ከሆነችዋ አሜሪካ የሚጠበቅ አይደለም። አሁንም በቅርቡ ያደረጉት ሲታይ የዘረኝነት ነገር እያደገ መሆኑን ማየት ይቻላል። ይህ በግለሰብ ደረጃ ብቻ ሳይሆን በተቋም ውስጥም ጭምር ነው። ይህንን ለመለወጥ ከአብዮት በላይ ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡- ይህ ሁሉ እየታየ የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪ ናቸው ማለት ይቻላል?
ዶክተር ሞገስ፡- በውጪ የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪ ነን ይላሉ። ነገር ግን በቤታቸው የሚታየው ግልፅ ነው። በአሜሪካ የጥቁር አሜሪካኖች አያያዝ፣ የኤዢያ አሜሪካውያን አያያዝ ከታየ አሜሪካ ከሌሎቹ ድሃ እና የአፍሪካ አገራት የተሻለ ሪከርድ የላትም። ምናልባት የባሰባትም ትሆናለች። በሁሉም ቦታ ዘረኝነት አለ። በትምህርት ቤቶች፣ በህክምና ተቋማት፣ በእያንዳንዱ የመገልገያ ተቋማት መብቶች እና ነፃነቶች ሲጨፈለቁ እና ሲሸረሸሩ ይታያል። ስለዚህ የተሻለ ሪከርድ ኖሯት ራሷን የሰብአዊ መብት ቀንዲል አድርጋ የምታይበት ሁኔታ በአገሯ ላይ የለም። ነገር ግን ሃይል ነውና ሃይል ሁሉንም ወክሎ ሁሉንም ደፍጥጦ እና ጨቁኖ እውነታን የያዝኩት እኔ ነኝ ይላል። ሃይል ያለው እውነት አለው ይባላል።
ሃይል ስላላቸው የሚናገሩት ነገር በግድም ቢሆን ተቀባይነት ያገኛል። በዓለም አቀፍ ደረጃም የሚታየው ይኸው ነው። የአሜሪካን አቋም የተባበሩት መንግስታት አቋም ነው። የተባበሩት መንግስታት ከእርሷ ከወጣ በማግስቱ ምን እንደሚያጋጥመው ያውቃል። ስለዚህ ወዶም ሆነ ተገዶ የእርሷን ፍላጎት ይቀበላል። ከዚህ አንፃር እነርሱ የሰብዓዊ መብት የዓለም ተሟጋች ነን ብለው ቢያቀርቡም እውነታውን የደረሰበት ያውቀዋል። እነሶሪያ፣ እነአፍጋኒስታን፣ እነሶማሊያ እነሱዳን ያውቁታል።
አዲስ ዘመን፡- ስማቸውን ከመጥቀስ ባለፈ ምዕራቡ ዓለም በሰብአዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብት ስም ያፈራረሷቸው ሀገራትን ጉዳይ እንዴት ያዩታል?
ዶክተር ሞገስ፡- ለምሳሌ በ1990ዎቹ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሶማሊያ ጣልቃ ሲገባ ጣልቃ የተገባው በሰብአዊነት ሥም ነበር። ጣልቃ የተገባው የሰው ልጆችን ከሰብአዊ ሰቆቃ ለመታደግ የሚል ነበር። በጊዜው ሶማሊያ የእርስ በእርስ ግጭት ውስጥ ነበረች። በግጭት ምክንያት የተፈጠሩ ከባድ ችግሮችን እንቀንሳለን ብለው ቢገቡም መውጣት በማይችሉበት ሁኔታ ራሳቸው የግጭቱ አካል ሆነው አንደኛውን ወገን መደገፋቸውን ተከትሎ መጨረሻ ላይ በውርደት ወጥተዋል። ያሉትንም የሰውን ሰቆቃ በአግባቡ ሳይቀንሱ ጥለው ሄደዋል።
ያን ጊዜ የተከሉት መርዝ ይኸው ሶማሊያዎች እስከ ዛሬ ድረስ መንግስት አልባ ሆነው ተከፋፍለው፤ ማህበረሰባቸው እና ኢኮኖሚያቸው ደቆ ሐገራዊ ህልውናቸው ፈርሶ ለአልሸባብና ለሌሎች ፅንፈኛ ሃይሎች መሰረት ሆነዋል። ስለዚህ ለአፍሪካውያን ለሶማሊያውያን ቢሉ ኖሮ አንድ ጠንካራ መንግስት አቋቁመው ሁሉንም ነገር ያ መንግስት እንዲያስተካክል ረድተው ይወጡ ነበር። እያንዳንዱ የገቡባቸው አገሮች ከታዩ መንግስታቶቻቸውን አፈራርሰው ወጥተዋል። ይህ ደግሞ ለመግዛት አስቸጋሪ የሚሆንበትን ሁኔታ ይፈጥራል። በሶሪያ፣ በሊቢያም የታየው ይኸው ነው። ከዛ እነርሱ ከጀርባ ሆነው መሳሪያ እያስታጠቁ እና እየሸጡ የእነርሱ የመሳሪያ ኢንዱስትሪ ከጦርነት ትርፍ እንዲሰበስብ ያደርጋሉ። ከፊት ለፊት የሰብአዊ መብት ተቋሞቻቸው ይጮኻሉ፤ እነርሱ ከጀርባ የመሳሪያ ሽያጭ ያከናውናሉ።
አዲስ ዘመን፡- ይህን ሁኔታ ከኢትዮጵያ አንፃር ስናየው ደግሞ ከለውጡ በኋላ የምዕራቡ ዓለም በኢትዮጵያ የውስጥ ችግሮች ዙሪያ በሰብአዊ መብት ስም የሚያደርገውን ጣልቃ ገብነት እና ጫና እንዴት ያዩታል?
ዶክተር ሞገስ፡- ምናልባት እዚህ ላይ ግልፅ መደረግ ያለበት ጉዳይ አለ። ከለውጡ በኋላ ሲባል መጀመሪያ ላይ በተወሰነ ደረጃ በለውጡ ላይ ተቃውሞ አልነበራቸውም። በተለይም በለውጡ አንድ ዓመት አካባቢ የተዋወቁ ጉዳዮች የፖለቲካው መከፈት እና የኢኮኖሚ ነፃነት እንዲሁም የተወሰዱ የተለያዩ እርምጃዎችን የመደገፍ ሁኔታ ነበር። እንደውም የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለውጡን ለመሩት ሰውም ዕውቅና ሳይቀር ሰጥቷል። ዕውቅናው እንዲሁ የመጣ አይደለም። በአገር ደረጃ የውስጥ ሰላም ከማምጣት ጀምሮ ከጎረቤት ጋር በተሰራው ሥራም ጭምር ነው። ነገር ግን የለውጥ ሂደቱ ጠንከር እያለ እና መሰረት እየያዘ አገራዊ እሴቶች ላይ መገንባት ሲጀመር እና አገር በቀል ሲሆን ፍራቻ እና ድንጋጤ ውስጥ ገቡ።
እነርሱ የሚፈልጉት ምዕራባዊ አስተሳሰብን መጫን ነው። ይህኛው መንግስትም ልክ እንደከዚህ በፊቱ የምዕራባውያኑን ጥቅም በዛው ልክ ያስጠብቃል የሚል ሃሳብ ነበራቸው። ከዛ አሁን ያለው መንግስት ጠንከር ብሎ አንዳንድ የቢዝነስ ፍላጎቶች ከምዕራቡ ጋር ተገቢ ያልሆኑ ግንኙነቶች መቆረጥ ሲጀምሩ፤ አገር በሚጎዱ ጉዳዮች ላይ ከእነርሱ ጋር የነበረው ግንኙነት ገደብ እየተጣለበት ሲመጣ ሰዎች ተጠያቂ መሆን ሲጀምሩ ‹‹እንዲህ አይነት ነገር አለ እንዴ?›› ብለው ደንግጠዋል። ስለዚህ ጫናው የመጣው ለእነርሱ ታማኝ የነበረ ስልጣን ላይ የቆየው አካል በአብዛኛው በማንኛውም መልኩ አስተሳሰባቸውን እና ፍላጎታቸውን የማይጋፋ ሥርዓት መቀጠል አለመቻሉ ስጋት ውስጥ ከቷቸዋል።
አሁን ያለው ሥርዓት እንደበፊቱ ቢሆን እና የምዕራቡ ዓለም ጥገኛ ቢሆን ጫናው አያስፈልግም ነበር። ስለዚህ በተወሰነ ደረጃ ወደ ራሳችን መመልከታችን፣ አገር በቀል
ኢኮኖሚ መባሉ አልተመቻቸውም። ገበያውን ልቅ ማድረግ እና እነርሱ እንደፈለጉ የሚገቡበት እና የሚወጡበት እንዲሆን ይፈልጋሉ። ይህንን እነርሱ የሚፈልጉት ቢሆንም፤ ይህንን ማድረግ አገር ማፍረስ ነው። ስለዚህ የፖለቲካም ሆነ የኢኮኖሚ ሽግግሩ በአግባቡ የሚመራ መሆን አለበት። በመንግስት የሚሰጡ መብቶች እና ነፃነቶች በማዕቀፍ ውስጥ በገደብ መሆን እንዳለባቸው በመታመኑ፤ ይህንን በአግባቡ የሚመራ ሽግግር በጥርጣሬ ማየት ጀመሩ። ምክንያቱም እነርሱ የሚፈልጉት ሙሉ ክፍት የሆነ እነርሱ እንደፈለጉ የሚገቡበት እና የሚወጡበት የማይጠየቁበት እንዲሆን ይፈልጋሉ።
ነገር ግን ይህ ልቅ ስርዓት አገርን ምን ያህል እንዳደቀቀ ብዙ አስረጂ አያስፈልግም። አፍሪካ ውስጥ ብዙ አገራት ውድቀት አጋጥሟቸው ታይተዋል። እነ ዛምቢያ እና የቅርቧን ኬኒያ መጥቀስ ይቻላል። ጋና እና ናይጄሪያ ገበያውን ሙሉ ለሙሉ ክፍት አድርገው፤ ኢኮኖሚያቸው ሲዳሽቅ እና የፖሊሲ አውጪነት ነፃነታቸውን ሲቀሙ ታይተዋል። ምዕራባውያኑ ጫና እንዲፈጥሩ ያስገደዳቸው ያንን የማጣታቸው ሥጋት ነው። አሁን በተነፃፃሪነት አገራዊ ነፃነት የፖሊሲ የማውጣት ነፃነት አለ። የሚከተለውን የኢኮኖሚ ፖሊሲ የመወሰን እና በማንኛውም ጉዳይ ላይ የሚከተለውን የፖለቲካ መርህ የመወሰን ነፃነትን ይጨምራል። እነዚህን ነፃነቶች አጠንክሮ ወሰደ ማለት እነርሱ እንደፈለጉ አያዙትም። በሒደት ደግሞ የምዕራቡ ዓለም ተፃራሪ ተደርገው የሚወሰዱት የቻይና እና የራሺያ ተፅዕኗቸው መጉላት ሌላው ስጋታቸው ነው።
ስለዚህ በቻይና ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎችም የአፍሪካ አገራትን ልናጣ ነው በሚል ስጋት የበለጠ በተነሳሽነት አስበው እንዲሰሩ አድርጓቸዋል። ይህ ደግሞ ከሚመጣው መንግስት ጋር ይያያዛል። የጆ ባይደን መንግስት ለምን በዚህ ላይ ሰራ? የትራምፕ መንግስት በዚህ ደረጃ አልሰራም ነበረ። ምክንያቱም የጊዜው መንግስታት የሚሔዱበት ፖሊሲ ነው። ባይደን ገበያው ለምዕራባውያን ክፍት እንዲሆን በትኩረት ይሰራል። ማንኛውም አገር የአሜሪካን ተፃራሪ ሆኖ ከታያቸው ማንኛውንም ነገር ከማድረግ ወደኋላ አይሉም። ስለዚህ አሜሪካ በአብዛኛው ጣልቃ የምትገባው በዲሞክራቶች ዘመን ነው። ታሪክ እንደሚያሳየው በአሜሪካ በዴሞክራቶች ዘመን በሌሎች አገሮች በጣም ጣልቃ ገብነት ይኖራል። ኮንሰርቫቲቮቹ ደግሞ በጣም ወደ ራሳቸው ያያሉ። የቡሽ መንግስት ብቻ በአፍጋኒስታን ጣልቃ ገባ እንጂ፤ በአብዛኛው ራሳቸውን የሚያዩ ናቸው። ስለዚህ በተወሰነ መልኩ ጣልቃ ገብነቱ ከእነርሱ የወቅቱ መንግስት ጋርም የሚያያዝ ነው።
አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያ ያለውን ጣልቃ ገብነት ስናስብ፤ አሁን ላይ ጫና እየተፈጠረ ያለው እንደፈለጉት ስላልሆንን ነው። ላለፉት 27 ዓመታት በሀገሪቱ ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ሲካሄድ ዝም ብለው የቆዩበት እውነታስ ከምን የመነጨ ነው?
ዶክተር ሞገስ፡- ይህንን የሚወስነው በዛ ጊዜ የነበረው መንግስት ቀደም ሲል ኢትዮጵያዊ ባህል እና እሴት እንዲገነባ ምን ያህል ቁርጠኛ ነበረ የሚለው ነው። በነዛ ዓመታት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ምን ነበር? ሲባል በዋነኛነት ልማት እና ከድህነት መውጣት ነው። ነገር ግን የልማት ሃይሎች ተብለው የተቀመጡ የተወሰኑ ቡድኖች እና ድርጅቶች ነበሩ። እነዚህ አካላት ግለሰቦች እና ድርጅቶች ከምዕራቡ ዓለም ጋር እጅና ጓንት ሆነው የሚሰሩ ናቸው። ስለዚህ በመርህ ደረጃ የሚያጣላቸው ነገር የለም። በፍላጎት አይጣሉም። ምክንያቱም የእነርሱን ፍላጎት እዚህ ሆኖ የሚፈፅምላቸው አለ።
አሁን ግን ይህንን አስተሳሰብ የሚመታ የሚቃወም አገራዊ ዕሳቤ ለምሳሌ ኢትዮጵያዊ አገር በቀል ኢኮኖሚ፣ አገራዊ ሰላም እንገንባ የሚል ዓይነት መንግስት ሲመጣ በእነርሱም ላይ ጫና ሊፈጥር ይችላል የሚል ሥጋት ውስጥ ገብተዋል። ለምሳሌ ኢትዮጵያ በነፃነት ትግል ውስጥ ለአፍሪካ ምሳሌ ናት። ያላት ቦታም ጠንካራ ነው። በደቡብ አፍሪካ እና በአንዳንድ ቀኝ በተገዙ አገራት ኢትዮጵያኒዝም የሚል ንቅናቄ ነበር። እንደኢትዮጵያ ነፃ ለመሆን ምን አይነት መንገድ መከተል አለብን ብለው ለምሳሌ ኢትዮጵያዊ ቤተ ዕምነቶችን አቋቁመው ነበር። እነዚህ ተቋማት ቀኝ ግዛትን ይታገላሉ አይቀበሉም የሚል መነሻ ነበራቸው። ስለዚህ ኢትዮጵያዊ ነፃ የሆነች አገር እንደዚህ ነፃ የሆነ ፖሊሲን መከተል እና ማራመድ ከጀመረች ለሌሎቹም ተምሳሌት ትሆናለች። በሒደት ይህንን ምዕራባዊ አስተሳሰብ የመቃወም፣ የመጋፋት፣ የመታገል ሁኔታ ይጨምራል። ኢትዮጵያ ሌላውንም ታሳምፅብናለች፣ ታስነሳብናለች የሚልም ጭምር ነበር። በፊት የነበረው ግን በአስተሳሰብ ደረጃ ኢትዮጵያዊ አስተሳሰብ አልነበረውም። የሆነ ቡድንን እስከጠቀመ ድረስ ከማንም ጋር ቢሆን አብሮ ይሰራል። የበፊቶቹ ለኢትዮጵያ ተሰምቷቸው ኢትዮጵያዊ ጥቅምን ለማስጠበቅ በዛ ደረጃ ተንቀሳቅሰዋል ከተባለ አይደለም። አሁን ባለው እና በፊት በነበረው መካከል ያለው ልዩነት ይህ ነው።
አዲስ ዘመን፡- በጊዜው ሰብአዊ መብት ቢጣስም ጫና ያልፈጠሩት ለዚህ ነበር?
ዶክተር ሞገስ፡- በፊት ለምን ጫናው አልነበረም ከተባለ መልሱ የእነርሱን ጥቅም የሚነካ ነገር ስላልነበረ ጫና ለመፍጠር አይፈልጉም። ምዕራባውያኑ እኮ አምባገነኖችን ሲደግፉ በተግባር ታይተዋል። በዴሞክራያዊ ምርጫ ስልጣን የያዘን መንግስት በሴራ ከጀርባ የሚያስገድሉ ናቸው። ፓትሪስ ሉሙባ (patrise lumuba) አገሩን ከቀኝ ግዛት ያወጣ ሰው ነው። ነገር ግን እንደጠላት ታይቶ ተወግዷል። በጊኒም በተመሳሳይ መልኩ ተፈፅሟል። አገራዊ እሴትን እና አገራዊ ራዕይን የሚያራምድ መንግስት በእነርሱ እንደጠላት ይታያሉ።
አዲስ ዘመን፡- ስለዚህ እንደዚህ አይነት መንግስትን ለማስወገድ ሰሞኑን በኢትዮጵያ እንደታየው በዕርዳታ ስም መሳሪያ የሚያቀብሉበት ሁኔታ ይኖራል ማለት ነው። በዚህ ላይ ምን ይላሉ?
ዶክተር ሞገስ፡- በተለይ ዓለም አቀፍ እንደተባበሩት መንግስታት ዓይነት ተቋማት በአፍሪካ የእርስ በእርስ ግጭት ውስጥ በሰፊው ተሳትፈዋል። በኢትዮጵያም ግጭት ውስጥም መሳተፋቸው አዲስ አይደለም የለመዱት ነው። በደቡብ ሱዳን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ለአማፅያን መሳሪያ ጭነው ሲያስተላልፍ የተያዘበት ጊዜ ነበር። በዜናም ጭምር ተገልጿል። በሴራሊዮን፣ በኮንጎ በድብቅ የሚፈልጉትን አድርገዋል፤ እጃቸው ረዥም ነው። አንዱን ደግፈው ሌላውን ያስወጋሉ። በፊት ለፊት ግን የሰብአዊነት እና የርህራሔ ጥግ ላይ መድረሳቸውን በመግለፅ ከረሃብ ለመታደግ የሚሰሩ ተቋማት እንደሆኑ ያስመስላሉ። በተግባር ግን ጦርነቱ እንዳያልቅ እንዲቀጥል ያደርጋሉ። የሃይል ሚዛን እንኳ አግኝቶ አንዱ ጦርነቱን የሚያሸንፍበት ሁኔታ እንዳይፈጠር የሃይል ሚዛን እንዲመጣጠን የገንዘብ እና የዕውቀት የስትራቴጂ ድጋፍ በማድረግ በሒደት ከዚህ የሚያተርፉትን ያገኛሉ። በኢትዮጵያም የተፈጠረው ይኸው ነው።
የትኛው ድርጅት እንደሆነ መንግስት በግልፅ ባይናገረውም እጃቸው እንደሚኖር ማየት ይቻላል። ይህ የሚያስደንቅ አይደለም። ምክንያቱም እነዚህ የሰብአዊ መብት ተቋማት የምዕራባውያን መጠቀሚያ መንገዶች ናቸው። በእነዚህ ተቋማት የአፍሪካ አባል አገራት መኖራቸው ለአይን መመለሻ ያህል እንጂ በጣም አስፈላጊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የሚወስኑት 5ቱ አገራት ብቻ ናቸው። ሌላው ተስማማ አልተስማማ ምንም ዋጋ የለውም። ሌላው ቀርቶ አምስቱ አገራት ባይስማሙ እንኳ የአሜሪካን ጥቅም ይነካል ተብሎ ከታመነ የተባበሩት መንግስታትን ትተው ለብቻቸው የሚሔዱበት ሁኔታ አለ። በዛም አገራትን ሲያፈርሱ አይተናል። ለምሳሌ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ወደ ኢራቅ እንዲገባ አልፈለገም ነበር። ነገር ግን እነርሱ ገብተዋል። ስለዚህ ጃኬታቸው ዓለም አቀፍ መብቶች እና ነፃነቶችን ማስከበር ቢመስልም ከውስጥ በጣም የሚጠነቀቁለት ጉዳይ አላቸው። ያንን የሚነካ መንግስት አመራርም ሆነ ግለሰብ ከማስወገድ ወደ ኋላ አይሉም። ስለዚህ ጫናቸው መነሻው ይኸው ነው።
አዲስ ዘመን፡- በትግራይ ባለው ተጨባጭ እውነታ መንግስትን በሰብአዊ መብት ዙሪያ የመጠየቁ እውነታ ምን ትርጉም ይኖረዋል ?
ዶክተር ሞገስ፡- ማንኛውም የእነርሱን ጥቅም ይጋፋል ተብሎ የታሰበውን በጫና ውስጥ መክተታቸው የተለመደ ነው። በቅርቡ የጣሉት ማዕቀብ ራሱ መንግስት ላይ አሉታዊ ጫና የማድረግ እና አሁን በግብር እየደገፉት ላለው አካል መንግስት እንዲንበረከክ ለማድረግ ነው። ነገር ግን መንግስት የያዘው አቋም ለአገራዊ አንድነት እና ለኢትዮጵያ ሰላም የሚጠቅመውን አደርጋለሁ የሚል ነው። ለአገረ መንግስቱን ህልውና የሚጠቅመውን ማድረግ እንጂ የመንግስት ምላሽ ለአሜሪካን ኮንገረስ እና ሴኔት ውሳኔ የሚሰጥ ምላሽ አይደለም።
የአገረ መንግስቱ ነባራዊ ሁኔታ ከመረዳት ለአገሪቱ ህልውና የሚጠቅመውን ያደርጋል። አንዳንድ ጊዜ ግራ የሚያጋቡ የሚመስሉ ውሳኔዎችንም ያስተላልፋል። ያ የፖለቲካ ተፈጥሮ ነው። ምክንያቱም ፖለቲካ ተለዋዋጭ ነው። እነዚህ ተለዋዋጭ ነገሮችን መሰረት ተደርጎ ሲወሰን አንዳንዴ ለዜጎች ግልፅ ያልሆኑ የሚመስሉ ውሳኔዎች ይተላለፋሉ። በሒደት ግን ግልፅ እየሆኑ ይመጣሉ። ስለዚህ ከዛ አንፃር ምዕራባውያን የሌሎች አገራትን መክሰሳቸው አዲስ አይደለም። ለምሳሌ ወደ ራሳቸው ሳያዩ አሜሪካ ለረዥም ዘመን በሰብአዊ መብት አያያዝ ቻይናን ትከሳለች። ቻይና ውስጥ ባለ አንድ ግዛት ያሉ ሙስሊሞች ላይ የሰብአዊ መብት ጥሰት እየተፈፀመ ነው በማለት በተደጋጋሚ ይከሳሉ። በተግባር ግን እነርሱ በአገራቸው ውስጥ በጥቁሮች ላይ፣ በኤዢያን እና በላቲኖች ላይ የሚፈፅሙት በደል እና የሰብአዊ መብት ጥሰት ጥያቄ አይነሳበትም። በራሳቸው ፍርድ ቤት እንኳ በአብዛኛው አይታይም። ስለዚህ ነው እነርሱ ላይ ሲሆን አይሰራም፣ ሌላው ላይ ይሰራል የሚባለው።
አሜሪካን ላይ የትኛውም የሰብአዊ መብት ተቋም ጥያቄ አያነሳም። ምክንያቱም ሃይል ያለውን ማን ይከሳል? እነርሱ ጠፍጥፈው የሰሩት ተቋም እንዴት እነርሱን ይከሳል። እንደእነርሱማ ቢሆን በጣም በርካታ በሰብአዊ መብት ጥሰት እና በዘር ማጥፋት የሚጠየቁ የአሜሪካ መሪዎች ይኖሩ ነበር። አሜሪካ በቬትናም ላይ የፈፀመችው ድርጊት ያ ሁሉ ሰው ያለቀው አሜሪካ በከፈተችው ጦርነት ነው። ጃፓን ሂሮሺማ እና ናጋሳኪ ላይ የጣለችው አውቶሚክ ቦንብ ዛሬ ድረስ የሚወለዱ ህፃናት አካላቸው ከመጉደሉ በተጨማሪ አዕምሯቸው ላይ ችግር የሚፈጠረው አሜሪካውያን ባስተላለፉት ተገቢ ያልሆነ ውሳኔ ነው። በአፍሪካም ተመሳሳይ ሊያስጠይቅ የሚችል ብዙ ጥፋት አጥፍተዋል። በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ይዳኙ ቢባል በርካታ የአሜሪካን ፕሬዚዳንቶች ለፍርድ ይቀርቡ ነበር። ነገር ግን እነዚህ ተቋማት ለአሜሪካ ጥርስ የላቸውም፤ የአፍሪካ ድሃ አገራት ላይ ግን ጥርስ አላቸው።
አዲስ ዘመን፡- አሻባሪው ህወሓት እየፈጸማቸው ያሉ የታሰቡ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ዓለም አቀፉ ህብረተሰብ ለማውገዝ ፈቃደኝነት ማጣቱ ለምንድን ነው ?
ዶክተር ሞገስ፡- እውነት ለመናገር ወደ እዚህ ግጭት የተገባው በግድ እንደሆነ ይታወቃል። አንደኛው አካል ፈልጎ አቅዶ ሥርዓት ለመቀየር አስቦ የገባበት ጦርነት ነው። ያ ጦርነት በአጭር ጊዜ ለመቋጨት ታስቦ የተገባበት ቢሆንም መንግስት ከጥቅም ውጪ አድርጓቸው አሁን ላለንበት ደረጃ ደርሰናል። ነገር ግን እነዚህ ምዕራባውያን፣ የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪ ነን የሚሉ አካላትም ሆኑ ሚዲያዎቻቸው በሙሉ በኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት በሁለቱ መካከል እየተደረገ ባለው ግጭት አይናቸው ሁልጊዜ የኢትዮጵያ መንግስት ላይ ነው። የኢትዮጵያ መንግስት ምንም በጎ ነገር ቢያደርግ አይናቸው እርሱ የሚያደርገውን አያይም። መንግስት አንዲት ስህተት ቢፈጥር በዓለም አቀፍ ሚዲያዎቻቸው በሙሉ ያወጡታል። ያንን እንዲያደርጉ በሺ የሚቆጠሩ የፌስቡክ ሰራዊቶች ቀድመው በፊት ተደራጅተዋል። ያንን ደግሞ ያደረገው ከዓለም አቀፍ ልሒቃን ጋር አስተሳስሮ እነዚህን ተቋማት ጭምር የማወናበድ ተግባር ውስጥ የገቡበት ሁኔታ አለ። አካሔዳቸው የተቀናጀ ነው።
ለምዕራባውያን መንግስታት አጀንዳ የሚሰጡት እነዚህ ሚዲያዎች ናቸው። ሚዲያዎቹ መረጃውን ከእነዚህ ቀድመው ከተደራጁ የሶሻል ሚዲያ ጦረኞች ያገኛሉ። ከዛ ሥርዓት የተጣበቀ ግንኙነት ካላቸው ዓለም አቀፍ ልሒቃን የሚሰበሰብ መረጃ ወደ ፖሊሲ አውጪዎች ይሔዳሉ። የአሜሪካ ሴኔት በሎቢስቶች የሚመራ ነው። ስለዚህ እነዚህ የተከፈላቸው ሎቢስቶች መረጃን የሚያጣምሙ ተገቢ ያልሆነ ውሳኔ እንዲወሰን የሚያደርጉ፤ የሴኔቱ አባላት ተገቢውን መረጃ ቢያገኙ እንኳ ትክክለኛ ውሳኔ እንዳይወሰን ጫና የሚያደርጉ ናቸው። ስለዚህ በእነዚህ ምክንያት የሚወሰነው ውሳኔ ለአንድ ወገን ያደላ፤ መንግስት ምንም አይነት አወንታዊ እርምጃዎችን ቢወስድ ለእነዚህ አወንታዊ እርምጃዎች እውቅና ካለመስጠት አልፈው መንግስት የበለጠ እንዲጠየቅ የሆነው በተዘረጋው ዓለም አቀፍ ኔትወርክ ጭምር ነው።
ሌላው በመንግስት ደረጃ ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብ እና ተቋማት መረጃ ያለማድረስ የተወሰነ ክፍተት አለ። መንግስት እውነታ አለው። እውነታው ብቻ በቂ አይደለም። እውነታውን አሳውቆ እና አሳምኖ ሌሎች የዕውነታው ተጋሪ እንዲሆኑ መሰራት አለበት። ሰዎች፣ ተቋማት እና አገራት እውነታውን እንዲደግፉ መሰራት አለበት። እውነታ ይዞ መሸነፍ አለ። እውነታ ይዘን አሸንፈን ነገር ግን በድርድሩ የተሸነፍንበት ሁኔታ አለ። እውነታውን በአግባቡ ማስቀመጥ ያስፈልጋል። በደንብ ለዓለም አቀፍ ተቋማት እና ለሚዲያዎች ተደራሽ መሆን አለባቸው።
አሁን በመንግስት በኩል እውነታዎች ይነገራሉ። ነገር ግን የሚነገረው ለአገር ውስጥ ብቻ መሆን የለበትም። ትክክል ነው፤ ዜጎች መንግስት እየሰራ ያለውን እና አቋሙን አውቀው ሊደግፉት ይገባል። ነገር ግን ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም እውነታውን እንዲያውቅ እና የራሱን ውሳኔ እንዲወስን ማስቻል ያስፈልጋል። ጫናው ዓለም አቀፋዊ ስለሆነ ፍሰት ያለው መረጃ መተላለፍ አለበት። በዛ ደረጃ የተወሰኑ ክፍተቶች ስላሉ እዛ ላይ መስራት ያስፈልጋል። በዛ በኩል ያለውን ችግር ማቃለል ይቻላል። ነገር ግን እውነታውን ሳያውቁት ቀርተው አይደለም። እውነታውን ያውቁታል። አውቆ የተኛን … እንደሚባለው ሆነው ነው።
እነርሱ ትልቅ ዓላማ እና አጀንዳ አላቸው። ፍላጎታቸው የዜጎች ደህንነት ጉዳይ አይደለም። ተኩስ አቁም እንዲኖር ሲጠይቁ ነበር። መንግስት የተኩስ አቁም ሲያደርግ ለምን ሌላኛው አካል ተኩስ አቁም እንዲያደርግ ጫና አልፈጠሩም ከተባለ ፍላጎታቸው የጥያቄያቸውን ቀጥተኛ መልስ አይደለም። መንግስት ለዕርዳታ በሩን ይክፈት ብለው ነበር። መንግስት ለዕርዳታ በሩን ሲከፈት፤ የበለጠ ደግሞ ፍተሻ አይኑር አሉ። ያ ደግሞ አገርን አደጋ ላይ ይጥላል። አሁን ደግሞ በዚህ ይከሳሉ። ፍላጎታቸው ማለቂያ የለውም። ማንኛውም መንግስት የሚወስዳቸውን እርምጃዎች አያረካቸውም ተብሎ አገር አይፈርስም። መንግስት የራሱ ቀይ መስመር ይኖረዋል። የሚደራደርበት ይኖረዋል፤ የማይደራደርበትም ይኖረዋል። ስለዚህ በማይደራደርበት ጉዳይ ላይ አይደራደርም።
አዲስ ዘመን፡- ሌሎች የሐሰት መረጃዎችን ለማሰራጨት ተግተው ይሰራሉ። በተቃራኒው በመንግስት በኩል የተያዘ እውነታ ያን ያህል ጎልቶ ሲነገር አይሰማም። ይህ ለምን ሆነ?
ዶክተር ሞገስ፡- መረጃ የሚተላለፈው በሚዲያ ነው። በአጋጣሚ ትልልቆቹ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን የማን እንደሆኑ ይታወቃል። ስለዚህ የሚፈጥሩት አጀንዳ ምዕራባውያኑ የሚሰጧቸውን እና ምዕራባውያኑ የሚፈልጉትን ነው። ሆን ብለው የሚያሰማሯቸው ጋዜጠኞች የሚያዩት በሁለቱም አይናቸው አይደለም። በሆነ ጋዜጠኛ ሪፖርት ተነስተው ውሳኔ ያስተላልፋሉ። የሪፖርቱን ትክክለኛነት ሳያረጋግጡ፤ በሌላ በኩል ያለውን መረጃ ሳያዩ እና ሳይጠይቁ በተሳሳተ መረጃ ላይ ተነስተው ለውሳኔ ግብአት ያደርጉታል። ሚዲያዎቹ የማን ሚዲያዎች ናቸው። ለእነዛ ሚዲያዎች የሚመግቡት እነማን ናቸው።
ሌሎች እውነታ እና እውቀት ያላቸው መረጃ ለመስጠት የሚችሉ ቢመጡም ሚዲያው በሩን አይከፍትም። ምክንያቱም እነርሱ ከተገኙ መረጃውን ለዓለም ያደርሳሉ። ዓለም እውነታውን ካወቀ፤ ከእነርሱ ጋር አይቆምም። ስለዚህ እውነታውን ለማሳወቅ ለሚችሉ ዕድሉን አይሰጧቸውም። ነገር ግን ዕውነታውን ለማሳወቅ የሚችሉ በጣም ብዙ ኢትዮጵያውያን በዓለም ዙሪያ አሉ። ነገር ግን እነዚህ ትልልቅ አጀንዳን የሚስቀምጡ የመንግስትን ፖሊሲ ማስቀየር የሚችሉ ተቋማት ለሚፈልጉት በራቸውን ከፍተው ለማይፈልጉት በራቸውን ይዘጋሉ። ነገር ግን ደግሞ ሌሎች አማራጮችን ማየት ያስፈልጋል። መንግስት ያንን እያደረገ ነው። በሌላ በኩል መንግስት የሚከተለው የዲፕሎማሲ አካሔዶች አሉ። መቼ ምን ማድረግ አለብኝ የሚለውን የሚያውቀው መንግስት ነው። መንግስት ከቻይና እና ከሩሲያ ጋር የቆየ እና የጠበቀ ግንኙነት አለው። ያንን ግን ወደ አዲስ የተሻለ ደረጃ ማድረስ ያስፈልጋል። ያንን መንግስት እያሰበ ነው ብዬ አስባለሁ። ነገር ግን በመንግስት የሚሰሩ ሥራዎች አሉ።
አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ስም እጅግ አመሰግናለሁ።
ዶክተር ሞገስ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
ምህረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 22/2013