ኢትዮጵያ በአንድ በኩል በጦርነት በሌላ በኩል በኑሮ ውድነት ከባድ አጣብቂኝ ውስጥ ትገኛለች። የንግዱ ማህበረሰብ ሀገሪቱ ተገዳ የገባችበትን ጦርነት በድል እንድትወጣ ለመከላከያ ሠራዊት በገንዘብ እና በአይነት የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ አለኝታነቱን አሳይቷል። በሌላ በኩል አንዳንድ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት እየፈጠሩት ባለው የኢኮኖሚ አሻጥሮች ምክንያት የዋጋ ንረት እና የኑሮ ውድነት እየተባባሰ ይገኛል።
የንግዱ ማህበረሰብ ግን መከላከያን በመደገፍ ብቻ ሳይሆን ሀገሪቱን እያስጨነቃት ያለውን የኑሮ ውድነትንም ለመቆጣጠር ለሚደረገው ጥረት የበኩሉን መወጣት ግድ የሚልበት ወቅት ላይ እንገኛለን። በተለይም አንዳንድ የመዲናዋ ነጋዴዎች በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የሚካሄዱ የኢኮኖሚ አሻጥር አካል በመሆን የከተማዋን ነዋሪዎች የኑሮ ውድነት የሚያባብሱ ተግባራት ላይ እየተሳተፉ ነው። በዚህም ምክንያት የከተማዋ ነዋሪዎች ከባድ ችግር ላይ ይገኛሉ። የከተማዋን ብሎም የሀገሪቱን ዜጎች ከኑሮ ውድነት ለማላቀቅ ቆርጦ መነሳት በሚያስፈልግ ወቅት ላይ ነን።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤን እና የንግድ ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱልፈታ የሱፍ በተገኙበት በእሊሊ ሆቴል የኢኮኖሚ አሻጥሮችን በመቆጣጠር በከተማዋ የሚስተዋለውን የምርቶች የዋጋ ንረት ለመከላከል እና የኑሮ ውድነትን ለማቃለል ከንግዱ ማህበረሰብ አባላት ጋር በቅርቡ ውይይት ተካሂዶ ነበር። በውይይት መድረኩ ከሁሉም ክፍለከተሞች የተውጣጡ አስመጪና ላኪዎች ፣አከፋፋዮች እና የንግዱ ማህበረሰብ ተወካዮች በተገኙበት የውይይት መድረክ የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች እና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
የውይይቱን መነሻ ጽሁፍ ያቀረቡት የንግድ ቢሮ ኃላፊው አቶ አብዱልፈታ የሱፍ እንደተናገሩት፤ የንግዱ ማህበረሰብ ከለውጡ በኋላ ለውጡን በግንባር ቀደምትነት በመደገፍ ይበል የሚያሰኝ ተግባር እየፈጸመ ቆይቷል። በትግራይ ክልል ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላም ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ ድጋፍ አድርጓል። በአይነትም በገንዘብም። አሁንም ያጋጠመውን ችግር ለመቀልበስ መስራት አለበት። የሀገር መከላከያ ሠራዊት ጦርነቱን በድል እንዲወጣ በገንዘብ፣ በሞራል እና በአይነት ከሚያደርገው ድጋፍ ባሻገር ጥቂት የማይባሉ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት የህዝቡ የኑሮ ውድነት እንዳይባባስ ትርፋቸውን እና ጥቅማቸውን ትተው ለህብረተሰቡ ሸቀጦችንና ምርቶችን እያቀረቡ ያሉ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት አሉ። እነዚህ ጥቅማቸውን ትተው ለሀገር እና ለህዝባቸው ጥቅም የቆሙ ነጋዴዎች ሊመሰገኑ ይገባሉ።
በሌላ በኩል አንዳንድ ባለሃብቶች መንግሥት በጦርነት መጠመዱን እንደ ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ትርፍ ለማጋበስ አሁን ጊዜው ነው በሚል ከፍተኛ ችግር እየፈጠሩ ያሉ ነጋዴዎች መኖራቸውን የጠቆሙት አቶ አብዱልፈታ፤ ወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታን ምክንያት በማድረግ ገበያውን በሞኖፖሊ መያዝ ፣ምርቶችን በመደበቅ ባልተገባ መንገድ ለመክበር የሚንቀሳቀሱ ስግብግብ ነጋዴዎች መኖራቸውን አመልክተዋል።
ምርት በማሸሽ፣ ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ በማድረግና የንግድ ሰንሰለቱን በማርዘም የዋጋ ንረት እንዲፈጠር የሚያደርጉ ነጋዴዎች መኖራቸውን ጠቁመዋል። በነዚህ ላይ ክትትል እና እርምጃ እየተወሰደባቸው መሆኑንም ጠቁመዋል። መሰል ችግሮች በመንግሥት በሚደረግ ቁጥጥር ብቻ መቆጣጠር አይቻልም ያሉት አቶ አብዱልፈታ፤ የንግዱ ማህበረሰብ በራሱ ተደራጅቶ ችግሩን ለመፍታት ጥረት ማድረግ ያለበት ወቅት ነው ብለዋል።
እንደ አቶ አብዱልፈታ ማብራሪያ ወቅቱ የንግዱ ማህበረሰብ ሀገርን ለማዳን ርብርብ ማድረግ ያለበት ወቅት ነው። ከውጭ ሀገራት ምርቶችን በማስመጣት ላይ ያሉ ነጋዴዎች ምርቶቻቸውን በፍጥነት ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት ገበያው እንዲረጋጋ የበኩሉን መወጣት አለበት። ወደብ ላይ የደረሱ ምርቶች በአስቸኳይ ወደ ሀገር መግባት አለባቸው።
ከውጭ ሀገራት የሚያስመጡ አስመጪዎች ከሚያደርጉት ጥረት ባሻገር ሀገር ውስጥ ያለው ምርት ወደ ገበያ መውጣት አለበት ያሉት አቶ አብዱልፈታ፤ ለዚህም አከፋፋዮች ርብርብ ማድረግ አለበት ብለዋል። በአምራች ዘርፎች ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎች የምርታቸውን መጠን ለማሳደግ በትኩረት መስራት አለባቸው።
ያለ ደረሰኝ የሚደረጉ ሽያጮች ለቁጥጥር ስርዓት እና ህገ ወጦችን ለመቆጣጠር እንቅፋት እየሆኑ መሆናቸውን የጠቆሙት አቶ አብዱልፈታ የንግዱ ማህበረሰብ በደረሰኝ ነው መስራት ያለበት ብለዋል።
ከአጠቃላይ ሀገሪቱ የንግዱ ማህበረሰብ ውስጥ ከ30 እስከ 40 በመቶ የሚሆነው በአዲስ አበባ እንደሚኖር የገለጹት የቢሮው ኃላፊው አብዛኛው አስመጪ፣ አብዛኛው አምራች፣ አብዛኛው አከፋፋይ ያለው አዲስ አበባ ነው ብለዋል። የንግድ አሻጥር የሚጀመረውም ሆነ የሚጠናቀቀው አዲስ አበባ ነው። አሻጥሩን ማምከን ካለብን በአዲስ አበባ ካመከንን የትም አካባቢ ተጽዕኖ ማድረስ አይችልም። በአዲስ አበባ ማምከን ከተቻለ በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎችም ማምከን ይቻላል።
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች በበኩላቸው፤ የኢኮኖሚ አሻጥር ላይ የሚሳተፉ አካላት ገንዘብ ለማግኘት ብቻ የሚፈጽሙት ሳይሆን ሀገርን ለማተራመስ የታለመውን ዓላማ ለመደገፍም ጭምር የሚፈጸም መሆኑንም ነው ጠቁመው፤ ህዝቡ በግንባር ላይ የሚደረገውን ጦርነት በገንዘብ እና በአይነት እንዳይደግፍ በኑሮ ውድነት አጣብቂኝ ውስጥ ማስገባትንም ግቡ ያደረገ መሆኑን ያብራሩት ከንቲባዋ፤ በዚሁ የመንግሥትን ጥንካሬ ለመፈታተን ብሎም ደካማ ሀገር መንግሥት መፍጠር እንችላለን በሚል እሳቤ የሚደረግ እንቅስቃሴ ነው ብለዋል።
በኢኮኖሚ አሻጥር ምክንያት እየተፈጠረ ያለው ችግር የንግዱን ማህበረሰብ ጨምሮ ሁሉንም ዜጋ የሚያሳስብ ነው ያሉት ወይዘሮ አዳነች፤ ግንባር ላይ ያለውን ሀይል ለመደገፍ ገንዘብ በማዋጣት፣ ደም በመለገስ እንደተባበረው ሁሉ የኢኮኖሚ አሻጥርንም ለመከላከል መስራት አለበት ብለዋል።
ችግሩ መንግሥት በቁጥጥር ብቻ የሚያቆመው አይደለም ያሉት ወይዘሮ አዳነች፤ በመንግሥት በንግዱ ማህበረሰብ እና በሸማቹ ትብብር ማስቆም ይቻላል ብለዋል። በተለይም የንግዱ ማህብረሰብ ትልቅ ኃላፊነት አለበት ብለዋል። ወቅቱ ከትርፍ በላይ ሀገር እና ህዝብ ስለማትረፍ የምናስብበት መሆኑን የንግዱ ማህበረሰብ ሊገነዘብ ይገባል ብለዋል::
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ነሃሴ 21/2013