አቶ አንጋው ሲሳይ ይባላሉ። ከ1968 ዓም ጀምሮ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ አስተዋጽኦ አድርገዋል። ከ1968 ዓም እስከ 1972 ዓም ድረስ የኢህአፓ በመሆን እስከ በረሃ ድረስ በመውረድ ከፍተኛ የሆነ ትግል ያደረጉ ናቸው። በ1983 ዓም ኢህአዴግ መንበረ ሥልጣኑን ሲይዝ ደግሞ ድርጅቱን በመቀላቀል ትግል ማድረግ ጀመሩ። በድርጅቱ ውስጥም የህዝብ ግንኙነት ሥራ ተሰጥቷቸው መላውን ክልል እየዞሩ በመስራት ድርጅታቸውን አገልግለዋል። ነገር ግን ድርጅቱ አመሠራረቱ መልካም ቢሆንም ኋላ ላይ እየሄደበት የነበረው አካሄድ እጅግ ከባድ ስለነበር እኔም አብሮ መቀጠል አልቻሉም።
በተለይ ድርጅቱ የሚያነሳው የመገንጠል ሀሳብ ብሎም ብሔር ብሔረሰቦችን በእኩል ዓይን አይቶ ያለማስተዳደር ሁኔታ ምቾት ስለነሳቸው አብረው ለመቀጠል ተቸገሩ። ነገር ግን ከህወሓት መነጠል እንደ መቀላቀሉ ቀላል አልሆነላቸውም። ምክንያቱም ለህይወትም በጣም አደገኛ ስለነበር እስከ 2004 ዓም ድረስ ህወሓት ጋር መቆየትን ወሰኑ። ሆኖም በ2004 ዓ.ም ያገኙትን ቀዳዳ ተጠቅመው ድርጅቱን ለቀው በመውጣት በተለያዩ ተቋማት ላይ የህግ አገልግሎት ስራን ሲሰሩ ቆዩ።
ከዚያ የለውጡ መንግሥት ወደ ሥልጣን ሲመጣ የኢዜማን ፓርቲ በመቀላቀል ለአገር ይጠቅማል ያሉትን ሥራ መስራት ጀመሩ። በቅርቡም በትግራይ ክልል ተቋቁሞ ለነበረው ጊዜያዊ አስተዳደር በኢዜማ ተወክለው የሥራ ኃላፊነታቸውን ሲወጡ ነበር። “መልስ የሚሹ የህዝብ ጥያቄዎች” በሚልም አጠቃላይ የህዝቡን መሠረታዊ ፍላጎቶች የሚያሳይ እና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን የሚያሳይ መጽሃፍ ለንባብ አብቅተዋል። እኛም አጠቃላይ በድርጅቱ ውስጥ በነበረው ቆይታም ሆነ ከዚያ በኋላ የነበረውን የአሸባሪውን ህወሓት ተግባራት በተመለከተ እና በወቅታዊ ሁኔታዎች ዙሪያ ከአቶ አንጋው ሲሳይ ጋር ቆይታን አድርገናል።
አቶ አንጋው፦ አዲስ ዘመን፦ ከህወሓት ለመነ ጠል ያነሳሳዎት ምክንያት ምን ነበር?
አቶ አንጋው ፦ እንግዲህ ዋናው ምክንያቴ ድርጅቱ የተገንጣይነት መንፈስ ያለው መሆኑ ነው፤ ከዚህ አንጻር ደግሞ ድርጅቱ የተለያዩ ፕሮግራሞችን በማውጣት የመገንጠል ሀሳቤን ትቸዋለሁ በማለት በተለያዩ ጊዜያት ይነግረን ነበር እኔ ግን እንዳልተወው አውቄያለሁ። ካወቁበት መንገደም ለምሳሌ የትግራይ ክልል ምክር ቤት አባል ሆኜ ስሰራ የክልሉ ህገ መንግሥት በሚረቅበት ጊዜ የክልሉን ባንዲራ በሚመለከት የህወሓት አርማ የትግራይ ባንዲራ ይሁን፤ የሚል ሃሳብ ቀርቦ ነበር ፤ በወቅቱ ግን እኔ ባንዲራ ማለት የአንድ ህዝብ መገለጫ ነው፤ ከዚህ አንጻር የትግራይ ህዝብ መገለጽ ያለበት በህወሓት የ17 ዓመት ትግል ሳይሆን በሺህ ዓመት በሚቆጠረው ታሪኩ ነው አልኩ ፤ በዚህም ጥርሳቸው ገባሁ፤ የትግራይ ህዝብ ከሁሉም በላይ ድንቅ የሆነ የምህንድስና ጥበብን ያስተማረ እንደ አክሱም ሀውልት አይነት ስራዎችን በመስራት ያስተዋወቀ፤ በኢትዮጵያ ያሉ ትልልቅ ሀይማኖቶች መነሻ የሆነ ነው፤ ህወሃት ትላንት መጥቶ በ17 ዓመት ትግል ልግለጸው ማለት አይችልም ፤ ስለዚህ ባንዲራው ላይ አርማችሁን አታደርጉም በማለቴ ነው እንግዲህ ልዩነቶች እየሰፉ የመጡት ።
ነገር ግን ይህ ልዩነት ተፈጥሮ እኔ ላይም ብዙ በደሎችን እያደረሱብኝም እንኳን አብሬያቸው ነበርኩ፤ ምክንያቱም ደግሞ ጥዬ ብወጣም የሚደርስብኝ ነገር ምናልባትም ህይወቴንም የሚያሳጣኝ በመሆኑ እንደምንም ብዬ ከክልሉ መንግሥት የስራ ዘርፍ ለመውጣት ሞከርኩ፤ እግዚአብሔር ይመስገን፣ እርሱ ተሳካልኝ።
አዲስ ዘመን ፦ ከህወሓት ጋር ተቀላቅለው ምን ነበር የሚሰሩት?
አቶ አንጋው፦ ከህወሓት ጋር ተቀላቅዬ እሰራ የነበረው ስራ በክልሎች ያለውን ሁኔታ በመከታተል መረጃ መስጠት ማለትም የህዝብ ግንኙነት ስራ ነበር። ነገር ግን ይህ ስራም ሆነ የህወሓት አካሄድ እጅግ በጣም ከመስመር የወጣ፣ በጣም ሰግብግብነት የሚታይበት፣ ለህዝብ ቆመናል ይበሉ እንጂ የሚሰራው ስራ ፍጹም ህዝብን የማይጠቅምና ያላማከለ መሆኑ እኔም ከድርጅቱ ጋር ያለኝን ግንኙነት ለማቋረጥ ጫፍ አደረሰኝ። ነገር ግን እንደነገርኩሽ ከድርጅቱ መውጣት ያን ያህል ቀላል አልነበረም። አባል ሆነሽ እንደውም በዚህን ያህል የስራ ሁኔታ ላይ ተገኝተሽ ባልተመቸሽ ሰዓት ለቅቄ እወጣለሁ ማለት ምናልባትም እስከ ቤተሰብ ድረስ በሚደርስ ከፍተኛ የሆነ ችግር ውስጥ የሚያስገባም ነበር። ‘
እኔም ይህንን ተገንዝቤ በምን መልኩ ልወጣ እንደምችል በተለይም ደግሞ ሰላማዊ በሆነ የኔንም ሆነ የቤተሰቦቼን ህይወት በማያሳጣ መልኩ ለማድረግ በጣም ሳስብ ቆየሁ። በኋለ ግን የህዝብ እንባ ጠባቂ የሚባለው ተቋም ላይ በሙያዬ መስራት ስለቻልኩ እዛ ገባሁ።
እዚህ ላይ የድርጅቱ ውስጠ ደንብ አንድ የሚለው ነገር አለው፤ እርሱም “አንድ አባል ከስድስት ወር በላይ የሚጠበቅበትን ወርሃዊ ክፍያ ካልከፈለ በፍቃዱ እንደተሰናበተ ይቆጠራል” ይላል፤ እኔም ይህንን ክፍተት ተጠቅሜ በሰላም ድርጅቱን ለቅቄ ለመውጣት ቻልኩ።
አዲስ ዘመን ፦አሸባሪው ህወሓትን መለስ ብለው ሲያስቡት ግን አንደዚህ ባለው ሁኔታ አገርን የሚክድ ይመስልዎት ነበር? ይህ ቀን እንደሚመጣስ አስበው ያውቃሉ?
አቶ አንጋው ፦ ከፓርቲው ትልልቅ የሚባሉ ሰዎች ጋር እገናኝና እወያይ ስለነበር ድርጅቱ ለኢትዮጵያ ያልቆመ መሆኑን ከመጀመሪያው ጀምሮ አውቄ ነበር። ምናልባት በዚህ መልኩ እስከ ጦርነት ድረስ በመግባት አገርና ህዝብን ያምሳል፤ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ደረጃ አሸባሪ ተብሎ ይታወጃል ብዬ ባላስብም ነገር ግን አገር የሚበትን መሆኑ ግን በግልጽ ያስታውቅ ነበር።
ይህ እኮ ምንም አዲስ ነገር የለውም፤ በመጀመሪያ መንበረ ስልጣኑን ሲቆጣጠሩት ጀምሮ ያረቀቁት ህገ መንግሥት የአንድ እናት ልጆች የሆኑ ኢትዮጵያውያን ተስማምተው እንዳይኖሩ የሚያደርግና የሚነጣጥል መሆኑን ስለማውቅ ደርጅቱ ለአገራችን ነቀርሳ መሆኑን እገነዘብ ነበር።
እናም ባገኘሁት አጋጣሚ ሁሉ ስለዚህ ጉዳይ ከመናገር ባሻገር “መልስ የሚሹ የህዝብ ጥያቄዎች” በሚል በጻፍኩት መጽሀፍ ውስጥም በሚገባ ገልጬዋለሁ። አሸባሪው ህወሓት የኢትዮጵያ አንድነት እንዳይጠናከር የሚሰራ ድርጅት ከመሆኑም በላይ በተለይም አላማው ከሸፈበት እንጂ ከኤርትራ ጋር በመሆን ሌላ አገር ለመመስረት ያሰበ ድርጅት መሆኑንም በደንብ አውቅ ነበር።
እናም ዛሬ ላይ አገር ለመበተን መነሳቱ ምንአልባት ባህርይውን በቅርበት ለማያውቁ ሰዎች አዲስ ሊመስል ይችል ይሆናል እንጂ ይህ የሚታወቅ እንደውም የሚጠበቅ ነው ። ነገር ግን አገርን ለመበተን እንደማይችል የሚያልመውና የሚያስበው ሁሉ ጉም ሆኖ ሰማይ ላይ አንደሚቀር ደግሞ የእራሱ የድርጅቱ አመራሮች በሚገባ ጠንቅቀው የሚያውቁት ሀቅ ነው።
አዲስ ዘመን ፦ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ን እንዴት ተቀላቀሉ ?
አቶ አንጋው ፦ አዎ ድርጅቱን የተቀላቀልኩት በ2009 ዓ.ም አዲስ አበባ በመጣሁበት ጊዜ ነው። አዲስ አበባ የመጣሁበት ዋና ምክንያት ደግሞ ትግራይ ውስጥ እንኳን የተቃዋሚ ፓርቲ አባል ሆኖ አይደለም፤ ከህወሓት ሌላ ማሰብ እንኳን የማይቻል በመሆኑ እስከ እዛን ጊዜ ድረስ እነሱን መታገል ብፈልግም ሳልችል ቀርቼ ስለነበር ነው። ነገር ግን ኢዜማን በመቀላቀልና ከህወሓት ውጪ የትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ እንቅስቃሴ በማያደርግበት ትግራይ ክልል ላይ ተወካይ ሆኜ እንድሰራ መደቡኝ።
አዲስ ዘመን ፦ ከህወሓት ውጪ ሌሎች ፓርቲዎች ቦታ በሌላቸው ትግራይ ክልል ላይ የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካይ ሆኖ መስራት እንዴት ነው?
አቶ አንጋው ፦ ትግራይ ላይ እንኳን የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አባል ለዛውም ተወካይ ሆኖ መስራት አይደለም ከህወሓት ሀሳብ ውጪ ራሱ ማሰብ ብዙ ችግር የሚያስከትል ነው። እኛም እንደ ኢዜማ ከሚያዚያ ወር 2013 ዓ ም ጀምረን ትንሽ የተንቀሳቀስነው መቀሌ ላይ ነው እንጂ በሌሎች አካባቢዎች አልሄድንም ።
ሌላው ቀርቶ ጊዜያዊ አስተዳደር ተብሎ እንኳን በሚኒስትሮች ምክር ቤት ይሁንታ ተሹሞ የሄደው አካል ስሙ ነው እንጂ የህወሓት ሰዎች የተቆጣጠሩት አስተዳደር ነበር። በመሆኑም በትግራይ ክልል እንደ ተቃዋሚ ፓርቲ መንቀሳቀስ የህዝቡን ንቃተ ህሊና መጨመር የማይታሰብ ነው።
አዲስ ዘመን ፦ ስለ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ካነሳን እንደውም አስተዳደሩ የተጣለበትን ኃላፊነት በአግባቡ እንዳይወጣ የሆነው የተለያዩ ፓርቲዎች ስብስብ መሆኑ በዚህ መካከል ደግሞ የአንድነት ችግር በመፈጠሩና ሁሉም የራሱን ሀሳብና ፍላጎት ብቻ ለማስፈጸም መጣሩ እንደሆነ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ላይ የነበሩ አመራሮች ሳይቀሩ ይገልጻሉና እንደው እርስዎ በዚህ ላይ ያልዎት ሀሳብ ምንድን ነው?
አቶ አንጋው፦ አይ እንደዛ አይደለም፤ እንደውም የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በትክክል ተወክለው ቢሆን ኖሮ እንደውም እዚህ ደረጃ አይደረስም ነበር ባይ ነኝ። ፖለቲካ ፓርቲዎቹ በአግባቡ ስራቸውን ላለመወጣታቸው የራሳቸውን ፍላጎት ለማስፈጸም መጣራቸው ሳይሆን ምክንያቱ የህወሃት ሰዎች አስተዳደሩን ሙሉ በሙሉ በሚባል ሁኔታ የተቆጣጠሩት ስለነበር ነው።
ለምሳሌ ክልል ላይ የሆነ ሴክተር መስሪያ ቤት ሀላፊዎች አዲስ ቢሆኑም የህወሓት አፍቃሪ ደጋፊ ናቸው ፤ ለዚህ ማስረጃው ደግሞ አሁን እንኳን መከላከያ ሲወጣ ዘጠኝ የክልል አመራሮች አንሄድም ብለው እዛው ቀርተዋል። ከዛ በታች ያሉትም ሹመኞች ቢሆኑም እንዲሁ የህወሓት ታማኞች ናቸው። በመሆኑም የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ተብሎ በስም ይጠራ እንጂ መልኩን የቀየረ የህወሓት አስተዳደር ነበር በክልሉ የነበረው።
የሚገርምሽ ነገር እኛ እዛ ውስጥ እየሰራን የህወሓትን ሀሳብ አስፈጻሚዎች የሚሰሩትን ደባ እያወቅን ለመናገር አልቻልንም፤ ደፍረን የተናገርነውንም ሰሚ አላገኘንም። የሚገርምሽ ነገር እኔ በጊዜያዊ አስተዳደሩ ላይ ስሰራ ከሥራ አስፈጻሚው ዶክተር ሙሉ ጋር አንድ ህንጻ ላይ ነበርን፤ ነገር ግን አንዳንድ ነገሮችን ለመጠቆም እንዲሁም ለመወያየት በተደጋጋሚ ሞክሬ አልተሳካልኝም። ጠባቂዎቹ እራሱ የህወሓት አባሎች ናቸው። በፍጹም እንድንገናኝ አይፈልጉም ። በመሆኑም ይህንን ይህንን ስናይ እንደዚህ አይነቱ ቀን እንደሚመጣ ቁልጭ ብሎ ይታይ ነበር።
አዲስ ዘመን ፦ እንደው እርስዎ ከህወሓት አባላት ጋር ቀደም ባለው ጊዜ እንደመስራትዎ አሁንም በጊዜያዊ አስተዳደሩ ላይ ኃላፊነት ወስደው እንደመሳተፍዎ አገራችን ያለችበትን ሁኔታ እንዴት ያዩታል?
አቶ አንጋው ፦ አዎ አሁን አገራችን ያለችው ውጥረት ላይ ነው ። የዚህ ውጥረት መነሻውም መድረሻውም ደግሞ ህወሓት መራሹ ቡድን የያዘው ጸረ ኢትዮጵያ አቋም አሁን ላይ ፈንድቶ በመውጣቱና መጨረሻው ደረጃ ላይ መድረሱ ነው።
አሁን ላይ ጁንታው ጦርነት በአገር ላይ ከፍቷል ፤ የእሱን ሀሳብ የሚያራግቡ የተለያዩ ጽንፈኛ ቡድኖች ደግሞ የእሱ ጋሻ ጃግሬ በመሆን አገርን ተባብሮ ለማፍረስ ላይ ታች እያሉ ነው፤ ይህን ስንመለከት እንግዲህ አሸባሪው ህወሓት ከምስረታው ጀምሮ የማይወደውን ህዝብና አገር የመራ፣ አሁንም ሃገርን ለማፍረስ የተነሳ ጠላት ነው። ነገር ግን አገር የገጠማትን ችግር በተባበረ የልጆቿ ክንድ በመመከትና ህወሓትን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስወገድ እየሄደች ነው።
እነሱ እንደሚፈልጉት እኛ በዘር፣ በጎሳና በጎጥ ተከፋፍለን እርስ በእርሳችን ከተባላንና ይህንን አረመኔ ቡድን ድባቅ መምታት ካልቻልን ወደፊትም ኢትዮጵያ ሰላም ታገኛለች ብሎ መገመት በጣም ከባድ ነው ። በመሆኑም ሰላም ለማግኘትና እንደ አገር ለመቀጠል ትልቁ መፍትሔ ህወሓትንና መሰሎቹን ማስወገድ ብቻ ነው። ነገር ግን ከአሸባሪው ህወሓት ጋር ተለሳልሼ እቀጥላለሁ ማለት አገራችን ዘመኗን ሙሉ ከችግር እንዳትወጣ ማድረግ ነው።
አዲስ ዘመን ፦ ጁንታው ቡድን እስከ አሁን ድረስ የትግራይ ነጻ አውጪ እንደሆነ አድርጎ ነው እራሱን የሚያስበውና እንደው እውነት ይህ ቡድን ህዝቤ የሚለውን ህዝብ ያውቀዋል ማለት ይቻላል?
አቶ አንጋው ፦ በጣም የሚገርመው ነገር እኔ መቼም ከመጀመሪያ ጀምሮ ድርጅቱን ሳውቀው ቡድኑ አንድም ቀን ህዝቤ ለሚለው አስቦ አያውቅም ፤እርሱ የሚያስበውም ሆነ የቆመው ለአንድ ቤተሰብ ነው። ለምሳሌ የህወሓት ማዕካላዊ ኮሚቴ ከአንድ አካባቢ መጥተውና በስጋ ዝምድና የተሳሰሩ ሲሆን አንድም ከእነሱ ቤተሰብ ውጪ ድርጅቱን ለመምራት ማዕከላዊ ኮሚቴውን የሚቀላቀል የለም።
እኔ እንደውም “ህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ” በሚል ስያሜ መጠራቱ በጣም ያስቆጨኛል። ለነገሩ አሁን “ጁንታ” የሚለው ስሙ ትክክለኛ መጠሪያው ሆኗል። በጠቅላላው ግን አሸባሪው ህወሓት አንድም ቀን የትግራይን ህዝብ እንደ ህዝብ አስቦ የማያውቅ ለጥቅሙ ለመስራት ሃሳብ የሌለው ከመጀመሪያ ጀምሮ ለራሱና በዙሪያው ላሉ ጀሌዎቹ ፍላጎት የቆመ ቡድን እንጂ የህዝብ ድርጅት አይደለም።
አዲስ ዘመን ፦ አሁን ላይ ይህንን እኩይ ተግባሩን ለማስፈጸም ህጻናትን ሴቶች እንዲሁም አረጋውያንን ወደጦርነት እያስገባ ነውና እንደው ይህ ሁኔታ ከቀድሞ ባህርይው አንጻር እርስዎ እንዴት ይገልጹታል?
አቶ አንጋው፦ ይህ ሁኔታ እኮ አሁን ለሚሰማው ነው አዲስ ነገር የሚሆነው። ድርጅቱ በቀድሞ የትግል ታሪኩም ቢሆን እነዚህን ምንም የማያውቁ ለማገናዘብ እድሜያቸው የማይፈቅድላቸውን ህጻናት “ማንጁስ” እያለ ነው ወደጦር ሜዳ ሲያስገባቸው የኖረው።
በነገራችን ላይ የጁንታው ቡድን ጭካኔ ተገልጾ አያልቅም፤ ቀድሞ በትግል ጊዜ የትኛውም ልጅ እራሱን ችሎ መንቀሳቀስ እስከቻለ ድረስ እድሜው ጥያቄ ውስጥ አይገባም ነበር፤ ቀጥታ ወደ ጦርነት ወደስለላ ነበር የሚያስገባቸው ፤ በዛ ለጋ እድሜያቸው ቡድኑን ተቀላቅለው አሁን በስልጣን ላይ ያሉም አሉ። በመሆኑም አሁን የሚያደርገው ልማዱን ነው።
እነዚህ ህጻናት ጎበዞች ጨካኞች ትዕዛዝ ተቀብለው የሚያስፈጽሙ ናቸው ስለሚባል እንደውም በትግሉ ጊዜ በጣም ነበር የሚፈለጉት ።
አዲስ ዘመን፦ አሁን ላይ በርካታ ምዕራባውያንና ተቋማቶቻቸው የዚህን ቡድን እኩይ ተግባር ወደጎን በመተው ጫናቸውን እያበረቱ ያሉት የኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ነውና እንደው ይህ ሁኔታ ለእርሰዎ ምን ያመለክቶታል?
አቶ አንጋው፦ አንድ መታወቅ ያለበት ነገር ምዕራባውያኑ የእነሱን ፍላጎት የሚያስፈጽም ካልሆነ በቀር ሊደግፉ አይችሉም። ሁሌም ድጋፍ የሚሰጡት ከራሳቸው ጥቅም አንጻር ነው። በመሆኑም ከዚህ ቀደም ባለው ልምድ ህወሓት ታዛዣቸው አብሮ በዝባዣቸው እዚህ ቦታ ሄደህ ተዋጋ ጦርህን አስፍር ሲባል ለምን ብሎ ሳይጠይቅ የሚሄድ ነበር፤ በጠቅላላው ቀኝ እጃቸው ስለነበር። ከዚህ ቀደም እንኳን በሙስና ሲባልግ የተጭበረበረ ምርጫ ሲያደርግ ምንም ሳይሉ ሲያልፉት ቆይተዋል፤ አሁን ላይ የእርሱን ጥፋት ወደጎን እያሉ መንግሥት ላይ እጃችውን ቢቀስሩ ምንም የሚገርም ነገር የለውም።
በመሆኑም ይህ ቡድን ከኢትዮጵያ አልፎ የምስራቅ አፍሪካ መጠቀሚያቸው ስለነበር አሁን ላይ ይህንን ጥቅም ላለማጣት ድጋፍ ቢያደርጉ የሚገርም አይደለም። በመሆኑም የአገር ፍቅር ያለው ለእነሱ የእጅ አዙር ቅኝ ግዛት ጆሮ የማይሰጥ ቦታ የሌለው አካል ወደ ስልጣን መጣ ማለት የሚያጡት ነገር በዛ ማለት ስለሆነ በሚችሉት ሁሉ ይህንን ቡድን መደገፍና ኢትዮጵያና ህዝቧን ደግሞ ማዳከም ህልማቸው ስለመሆኑ ሁሉም ዜጋ ሊገነዘብ ይገባል።
አዲስ ዘመን ፦ እነዚሁ ምዕራባውያን መንግሥት ከእነዚህ አሸባሪ ቡድኖች ጋር ድርድር እንዲያደርግም ሃሳብ ያቀርባሉና እንደው ድርድር የሚባለው ነገር ለኢትዮጵያና ህዝቦቿ ምን ማለት ነው?
አቶ አንጋው ፦ ድርድር ሲባል እንግዲህ ከጽንሰ ሃሳቡ ጀምሮ ብናየው ሰጥቶ መቀበል ነው። ኢትዮጵያ ደግሞ አሁንም ወደፊት ከህወሓት ሰጥታ የምትቀበለው ነገር የለም። ከአሸባሪው ህወሓት ጋር መደራደር ማለት ለእኛ ከዳቢሎስ ጋር እንደመደራደር ነው።
እንደ ህግ ሰው ሳየው ህገ መንግሥት እንኳን በርካታ መሻሻል የሚገቡት ነገሮች አሉ፤ በነገራችን ላይ የአገሪቱ ትልቅ ችግር ሆኖ ያለው ይኸው የህወሓት ህገ መንግስት ነው። በመሆኑም ይህ አገር የከፋፈለ ህገ መንግሥት እያለ ከህወሓት ጋር ልንደራደር አንችልም። ይህ ደግሞ የአብዛኛው ህዝብ ፍላጎት ነው። ሌላው ደግሞ ይህን አሸባሪ ቡድን የሚመራበት አብዮታዊ ዴሞክራሲ መመራትም የሚፈልግ አለ ብዬ አላስብም። ከዚህ ከዚህ አንጻር ከህወሓት ጋር መደራደር ሳይሆን የሚያዋጣው ቡድኑን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ማስወገድ ነው። ምዕራባውያንና ተቋማቶቻቸው ተደራደሩ እያሉ የሚሉት ከራሳቸው ፍላጎት አንጻር እንጂ ለኢትዮጵያና ለህዝቦቿ አስበው እንዳልሆነ መረዳትም ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን ፦ እንደ ኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበ ራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በዚህ ጉዳይ ላይ የያዛችሁት አቋም ምን ይመስላል ?
አቶ አንጋው፦ አዎ እንግዲህ የኢዜማ አቋም ግልጽ ነው። ከዚህ በፊትም እንደተናገርነው በተለይም የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት በቁጥጥሩ ስር ከነበሩ ቦታዎች ለቆ መውጣቱን ሕወሓት ሀገራችንን ለማተራመስ ከሌሎች አክራሪ ብሔርተኞች ጋር ጥምረት መመስረት የሚችልበት ሁኔታ ሊፈጥር ይችላል ብለን ነበር ። ይህ ሁኔታ ደግሞ በሀገራችን አንድነትና ሰላም ላይ በራሱ ከሚፈጥረው አደጋ በተጨማሪ ለኢትዮጵያ የውጪ ጠላቶች መሣሪያ በመሆን ከፍተኛ አደጋ ሊደቅን እንደሚችል ገልፀን ነበር ። በዚህም መሰረት የኢትዮጵያ አንድነትና ሰላም እንዲረጋገጥ የምንፈልግ ከሆነ በሙሉ አቅማችን ተረባርበን ህወሓትን ልናጠፋም እንደሚገባ ፓርቲያችን ያምናል።
በሌላ በኩልም መንግሥት ግዴታውን ከምንግዜውም በላይ በውጤታማነት መወጣት እንዲችል የወታደራዊ፣ የዓለም አቀፍ ግንኙነቶችና የፕሮፖጋንዳ ስራ ላይ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለበትም ፓርቲው ያምናል። ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ እና እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ዜጎች ማገዝ እንዲሁም የሀብት ማሰባሰብ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ መሠራት ያለባቸው ሥራዎችም በተመሳሳይ መሰራት አለባቸው ።
የሀገር ሰላምንና አንድነትን የማስከበር ኃላፊነቱ በዋነኛነት የፌዴራል መንግሥቱ በመሆኑ አሁን የተደቀነ ብንን አደጋ ለመቀልበስ የሚወሰደው እርምጃ የዛሬውንም ሆነ የወደፊቱን ወቀሳም ሆነ የድል ሽሚያ ማስቀረት በሚያስችል መልኩ አንድ ወጥ የዕዝ ሰንሰለት ኖሮት በፌዴ ራል መንግሥትና በኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት አመራር ሰጪነት ብቻ መወሰድ እንደሚገባው ኢዜማ መግለጫም ሰጥቷል፤ እኔም በግሌ የማምንበት ጉዳይ ነው።
ከምንም በላይ ግን የፖለቲካ ፓርቲዎች ያላቸውን ልዩነቶች ወደጎን በማለት የሀገር ህልውና ፈተና ላይ መውደቁን በቅጡ በመረዳት፤ አባሎቻቸውም የአማፂያኑን እብሪት ለማስተንፈስ በሚደረገው እንቅስቃሴ እንዲሳተፉ ጥሪ ሊያደርጉና በአንድነት በኢትዮጵያዊነት ስሜት መነሳትም በእጅጉ አስፈላጊ ነው።
አዲስ ዘመን ፦ የአገር ዳር ድንበርን ለማስከበር እየተዋደቀ ላለው መከላከያ ሠራዊታችን እን ዲሁ ሁሉም ዜጋ ተፎካካሪ ፓርቲዎችን ጨምሮ የሚችሉትን ሁሉ እያደረጉ ነውና እንደው በኢዜማ በኩልስ ያለው ተነሳሽነት እንዴት ይገለጻል?
አቶ አንጋው፦ መከላከያን ለማገዝ እንግዲህ ፓርቲው የተቻለውን ሁሉ የሚያደርግ ሲሆን እስከ አሁን ላለውም 250 ሺህ ብር ያህል የገንዝብ ድጋፍን ያደረገ ሲሆን በቀጣይም እንደ አስፈላጊነቱ ደጋፊዎቹን በማስተባበር እስከ ቦታው ድረስ በመሄድ አጋርነቱን ለማረጋገጥም ቁርጠኛ ነው።
በሌላ በኩልም የአገርን ሉአላዊነት ለማስከበር በሚደረገው ጦርነት በፌዴራል መንግሥትና በመከላከያ ሀይል ብቻ እንዲመራ ኢዜማ ይፈልጋል፤ ምክንያቱም የተለያዩ ሀይሎች ማለትም ፋኖ ሚሊሻ ልዩ ሀይል እየተባሉ የተሰባሰቡት አካላት በየፊናቸው የሚንቀሳቀሱ ከሆነ ህዝብን እርስ በእርስ አንድ እንዳይሆን እንዳያደርጉ በኋላም የድል ሽሚያ እንዳይፈጠር መጠንቀቅ ያስፈልጋል። በመሆኑም ስራው በማዕከል እንዲመራም ፓርቲው ይፈልጋል።
በዚህ ወቅት በአገሪቱ ያሉ ህዝቦች እንዲሁም ፓርቲዎች በጠቅላላው ከመንግሥት ጋር ተባብረው ይህንን ችግር ለማለፍ መስራት አገራችንም ከገባችበት ቀውስ እንድትወጣ ማድረግ በእጅጉ ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን ፦ ምንም እንኳን አሸባሪው ህወሓት ጦርነቱን ትግራይ ክልል ላይ ይጀምረው እንጂ አሁን ላይ ግን አድማሱን እያሰፋ መጥቷልና ይህ የጦርነት ቀጠናን የማስፋት አካሄድ እንደምታው ምንድን ነው?
አቶ አንጋው ፦ ለጥቂት ጊዜም ቢሆን ጦርነት ላይ ስለነበርኩ ሁኔታውን አውቀዋለሁ፤ ይህ አይነቱ አካሄድ የጦርነት አቅጣጫን በማስፋት የመደራደሪያ አቅምን ማሳደግ ነው፤ ሌላው የመንግሥትን ሁኔታ በማየት ሀይልን ለመበተን ያለመ ነው፤ ነገር ግን አሸባሪው ቡድን ይህንን ያስብ እንጂ እንደማያዋጣው ደግሞ ጠንቅቆ ያውቃል፤ በአጭር ጊዜ ውስጥም እንደሚሸነፍ አውቋል።
አዲስ ዘመን ፦ አሸባሪው ህወሓት በሥልጣን ላይ በነበረባቸው ጊዜያት አሸባሪ ብሎ ፈርጆ ሲያሳድዳቸው ከነበሩ ቡድኖች መካከል አሸባሪው ሸኔ አንዱ ነበር፤ አሁን ደግሞ ከዚህ ቡድን ጋር ጥምረት ፈጥረናል እያሉ ነውና ይህ ምን ዓይነት መልዕክት አለው ለእርስዎ ?
አቶ አንጋው ፦ መልዕክቱማ ግልጽ ነው፤ ከዚህ በፊትም እኮ ቢሆን ህዝብ ያላወቀው ይፋ ያልወጣ ስምምነት ነበራቸው። አሁን ግን በይፋ ግልጽ አደረጉት ማለት ነው። አሁን ላይ ደግሞ አሸባሪ ብሎ ሲያሳድደው ከነበረ ቡድን ጋር መጣመሩ እራሱ በትክክል ወደ አሸባሪነት እየተቀየረ መሆኑን የሚያመላክትና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ቡድኑን ሽብርተኛ ብሎ መወሰኑ የአካሄዱን ትክክለኝነት ያሳያል።
ይህ ህብረት ግን በተለይም በእነሱ አላማ ምናልባት ኦነግን ከያዝን የህዝብ ድጋፍ እናገኛለን ከሚል ሀሳብ የመነጨ ሊሆን ይችላል፤ በዚህ ስሜት ህዝብን በማነቃነቅ መንግሥትን ገልብጠን ሥልጣን እንይዛለን ከሚል ቀቢጸ ተስፋ የመነጨ ነው ። ነገር ግን ተስፋቸው እንደ ጉም የማይጨበጥ ከመሆኑም በላይ እነሱ የተማመኑበት ሸኔ ምንም ድጋፍ የሌለው መሆኑን የሚያሳየው መንግሥት የክተት አዋጅ ሲያውጅ ኦሮሚያን ጨምሮ ከሁሉም ክልሎች መከላከያን ለመቀላቀል የተመመው ወጣት ነው። በመሆኑም የጁንታው ግምትም በጣም የተሳሳተና እንደውም ለውድቀቱ መንገድ የሚከፍትለት መሆኑን መረዳትም ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን ፦ እነዚህ ሁለቱ አሸባሪ ቡድኖች ግን ቆመንለታል፤ እንታገልለታለን ብለው ለሚሉት ህዝብ ያላቸው እውነታ ወይም ያደረጉላቸው ነገር ምንድን ነው? እውነት ቆምንለት ለሚሉት ህዝብስ አገልግለውታል?
አቶ አንጋው፦ በፍጹም፤ ሁለቱም ቡድኖች ህዝቤ የሚሉትን የሚያስታውሱት ችግር ላይ ሲወድቁ ወይንም ደግሞ በስሙ ነግደው የሆነች ትርፍ ለማግኘት ሲያስቡ ብቻ ነው። ከዛ ውጪ ባለው የእነሱ ሀሳብና ፍላጎት የግል ጥቅማቸውን ማሳደድ ብቻ ነው።
ሸኔ ቀድሞም አሁንም ቢሆን የኦሮሞ ህዝብ ጠላት እንጂ ወዳጅ እንዳልሆነ በተግባር እያሳየ ነው። ነገር ግን ከኦሮሞ ህዝብም በጣም ጥቂት የሆኑና የሽብርተኛውን ቡድን እኩይ ተግባር ያልተረዱ ወይንም ደግሞ ለጥቅማቸው ያደሩ አይኖሩም ተብሎ ማሰብ ከባድ ነው። ነገር ግን አብዛኛው አሁን ላይ እኩይ ተግባሩን እየተረዱት በመሆኑ ተቀባይነቱ ለውጤት የሚያበቃ አይደለም። ህወሓትም በተመሳሳይ ነው።
አዲስ ዘመን ፦ ይህ ችግር ተቀርፎ ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ ግን ከማን ምን ይጠበቃል?
አቶ አንጋው፦ በጠቅላላው የኢትዮጵያ ህዝብ በአገሩ ጉዳይ ላይ ድርድር እንደማያውቅ ሆ ብሎ በመነሳት በተግባር እያሳየ ነው። ይህን በስሜትና በሞራል የተነሳን ህዝብ በትክክል መርቶ ማታገል የመንግሥት ኃላፊነት ነው። የህዝብን ንቅናቄ በትክክል መምራት መቻል አለበት ሲባል ደግሞ ቀደም ብዬ እንዳነሳሁት በተበታተነ ሁኔታ እየመጣን ያለን ሀይል የተማከለ በሆነ ሁኔታ የሚመራ አካል ሊፈጠር ይገባል። በዚህም ሀይን የመጠቀም ስልጣን የመከላከያ መሆኑን በማስገንዘብና ሀይል አጠቃቀምንም በመመሪያ በመደገፍ መስራት የግድ ይላል።
በቀጣይ ግን ከህገ መንግሥት ጀምሮ መሻሻል ያለባቸው ነገሮች ስላሉ እነሱን ማየት ያስፈልጋል። ከሁሉም በፊት ግን ህገ መንግስቱ እንዳልጠቀመን እንዳለያየን በተግባር ያየን በመሆኑ እዚህ ላይ የሚሠራው ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሎ ህዝብ ያመነበት ፌዴራሊዝም እንዲፈጠር መስራትም እጅግ የሚያስፈልግ ነገር ነው።
አዲስ ዘመን፦ ለነበረን ቆይታ በጣም አመሠግ ናለሁ።
አቶ አንጋው፦ እኔም አመሠግናለሁ
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ነሃሴ 21/2013