አሁን ላይ ባለው ነባራዊ ሁኔታ ህገወጥ የጦር መሳሪያዎች ዝውውር እየተበራከተ መምጣቱ ይነገራል። በተለይ አሁን ካለው ሀገራዊ ሁኔታ ጋር ተያይዞ በህግ የተከለከሉ የጦር መሳሪያ ዝውውሮች መያዛቸው በስፋት ይስተዋላል። ህገወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር የሚካሄደው በተለያዩ ግለሰቦች እና ተቋማት ጭምር እንደሆነም መረጃዎች ያመላክታሉ። በተለይ ሰሞኑን የተለያዩ ስልቶች በመጠቀም የጦር መሳሪያዎችን ሲያዘዋውሩ የተያዙ ሰዎችና ተቋማት መኖራቸው በመገናኛ ብዙኃን እየተነገረ ይገኛል።
በተመሳሳይ እንደ ገጀራ፣ ሳንጃ እና ሜንጫ የመሳሳሉት መሳሪያዎች ዝውውር በስፋት እየተስተዋለ መሆኑን ከአዲስ አበባ ፖሊሲ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል። መረጃው እንደሚያሳየው እንደነዚህ አይነት መሳሪያዎች በህገወጥ መንገድ በመጋዘን ተከማችተው መገኘታቸው እና በግለሰቦች አማካይነት ሲዘዋወሩ መያዛቸውን ያመላክታል።
በዚህ ጠይቁልኝ በሚለው አምድ ሥር በርካታ ጥያቄዎች የሚስተናገዱ እንደመሆኑ መጠን የዛሬው ጥያቄ በዚሁ መሠረት ከደረሱን ጥያቄዎች አንዱ ነው። ይህ ጥያቄ ከላይ ከተጠቀሰው ወቅታዊ ጉዳይ ጋር የሚያያዝ ሆኖ ትኩረት ያደረገው ገጀራ እና የመሳሰሉት መሳሪያዎች ህገወጥ ዝውውር መበራከት ያሳሰባቸው ግለሰቦች የጠየቁት ነው። ጠያቄዎቹ ለዝግጅት ክፍላችን ገጀራና የመሳሰሉት መሳሪያዎች ዝውውር በህግ ያለው ተጠያቂነት ምን ይመስላል የሚለው ጥያቄ አንስተዋል።
ለጥያቄው ምላሽ ለመስጠት የሚችለው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የወጣው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የጦር መሳሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ ቁጥር 1177/2012 ዓ.ም ነው። በዚሁ መሠረት አዋጁ የጦር መሳሪያ አስተዳደር እና ቁጥጥርን ምንና ምን ነገሮች አካትቷል የሚለውን ማየት ተገቢ ነው። አዋጁ ያስፈለገበት ዋና ዓላማ የዜጎችን ሰላምና ፀጥታ ለማስጠበቅ እንዲሁም የሕዝብን መብትና ደህንነት ለማስከበር በስራ ላይ ባሉ ህጎችና አሰራሮች ያልተሸፈኑ ጉዳዮችን በዝርዝር ህግ በመደንገግ እና ወጥነት ያለው ስርአት መፍጠር አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ነው።
በአዋጁ መሠረት የጦር መሳሪያ ማለት በአስነሺ ኃይል የሚፈነዳ ወይም በፍንዳታ ኃይል ጥይትን፣ አረርን፣ ቦምብን፣ ፈንጂን፣ ሚሳይልን፣ ሮኬትን እና ማናቸውም ተተኳሽ ነገር በማስፈንጠር በሕይወት፣ በአካል ወይም በንብረት ላይ ጉዳት ሊያደርስ የሚችል መሳሪያ ሲሆን ጥይትን እና ተያያዥነት ያላቸውን አባሪዎችን ይጨምራል። በተመሳሳይ አነስተኛ የጦር መሳሪያ የሚለውን በግለሰብ ደረጃ ሊያዝ የሚችል ማንኛውም አይነት ሽጉጥ ሲሆን፤ ቀላል የጦር መሳሪያ በነፍስ ወከፍ ደረጃ የሚያዝ አውቶማቲክ፣ ግማሽ አውቶማቲክ ወይም አውቶማቲክ ያልሆነ የጦር መሳሪያ እንደሆነም አስቀምጧል ።
በዚሁ አዋጅ ጉዳት አድራሽ ዕቃዎች ተብለው የተጠቀሱት ደግሞ በስለታማነታቸው ምክንያት ወይም የኤሌክትሪክ ኃይል በመጠቀም ወይም መርዛማ በመሆናቸው በሰው አካልና ህይወት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ለማድረስ የሚችሉ እንደ ሳንጃ፣ ገጀራ፣ ሜንጫ፣ ጦር፣ ቀስት፣ ጎራዴ፣ ሴንጢ እና መሰል መሳሪያዎችን የሚያጠቃልል መሆኑን ያሳያል።
በዚህ አዋጅ መሰረት ከተፈቀደለት ሰው ውጪ ማንኛውም ሰው፤ የፀና ፍቃድ ሳይኖረው የጦር መሳሪያ እና መለዋወጫዎች ወይም አብረው ጥቅም ላይ ሊውሉ የሚችሉ መሳሪያዎችን፣ ወደ ሀገር ማስገባት እና ማስወጣት፣ መያዝ፣ ማከማቸት፣ መገልገል፣ መደለል፣ መሸጥ፣ መግዛት፣ ማስተላለፍ፣ ማዘዋወር፣ ማጓጓዝ፣ ማምረት፣ ማሰልጠን፣ መጠገን ወይም ማስወገድ የሚሉት ከተከለከሉ ተግባራት መካከል ይገኙበታል።
በተመሳሳይ የፀና ፍቃድ ሳይኖረው ለልማት ሥራ የሚውሉትን ሳይጨምር ብዛት ያለው የጉዳት አድራሽ እቃ ወደ ሀገር ማስገባት፣ ከሀገር ማስወጣት፣ መያዝ ወይም ማስቀመጥ፣ ማከማቸት፣ መደለል፣ መሸጥ ወይም መግዛት፣ ማዘዋወር፣ ማጓጓዝ፣ ማምረት የተከለከለ መሆኑን በአዋጁ ተደንግጓል።
በአዋጁ መሠረት የጦር መሳሪያ ፈቃድ የሚሰጥበት ሁኔታ ለግለሰብ የሚፈቀደው አንድ አነስተኛ ወይም አንድ ቀላል የጦር መሳሪያ ብቻ ነው። ለድርጅትም ቢሆን የሚፈቀደው የጦር መሳሪያ አይነት አነስተኛ ወይም ቀላል የጦር መሳሪያ ሲሆን፤ ዝርዝሩ እና የጥይት ብዛት በተቆጣጣሪው ተቋም በሚወጣ መመሪያ የሚወሰን መሆኑን ያስቀምጣል። በዚህ መሰረት ለግለሰብ የሚሰጥ ፈቃድ ለሁለት ዓመት ሲሆን፤ ለድርጅት የሚሰጥ ፍቃድ ደግሞ ለሦስት ዓመት ፀንቶ የሚቆይ መሆኑ ተቀምጧል።
በዚሁ አዋጅ የጦር መሳሪያ አጠቃቀም ግዴታዎች በተመለከተ ፍቃድ የተሰጠው ማንኛውም ሰው የጦር መሳሪያውን በአዋጁ መሰረት ብቻ የመጠቀም፣ የጦር መሳሪያውን ሲይዝ የፈቃድ ወረቀቱን አብሮ የመያዝ፣ ፍቃድ ካገኘበት የጥይት መጠን በላይ በአንድ ጊዜ አለመያዝ፣ የሚቻል እስከሆነ ድረስ የጦር መሳሪያው በግልፅ ሊታይ በማይችል ሁኔታ መያዝ፣ የጦር መሳሪያው ሲበላሽ፣ ሲጠፋ፤ ሲሰረቅ፣ ሲቀማ ወይም በማንኛውም ምክንያት ከቁጥጥሩ ውጪ ሲሆን ለተቆጣጣሪው ተቋም ወዲያውኑ ማሳወቅ፣ የጦር መሳሪያ በማናቸውም መልኩ ለሌላ አሳልፎ ያለመስጠት፣ ያለማዋስ የሚሉት የሚያጠቃልል ነው።
በጦር መሳሪያ መነገድ በወንጀል ሕግ አንቀጽ 481 የተጠበቀ ሆኖ፤ ማንኛውም ሰው በዚህ አዋጅ የተመለከተውን ክልከላ እና ግዴታ የተላለፈ ከአንድ ዓመት እስከ ሦስት ዓመታት በሚደርስ ቀላል እስራት እና ከአምስት ሺህ እስከ አስር ሺህ ብር በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ ይቀጣል ሲል ተደንግጓል።
በዚሁ አዋጅ አንቀጽ ሁለት የተፈጸመው ወንጀል ብዛት ባለው የጦር መሳሪያ ሲሆን ቅጣቱ ከአምስት ዓመት እስከ አስራ አምስት ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት እና ከሀምሳ ሺህ እስከ መቶ ሺህ ብር በሚደርስ ገንዘብ የሚያስቀጣ መሆኑ ተደንግጓል።
ማንኛውም ሰው በዚህ አዋጅ የተመለከተውን ክልከላ እና ግዴታ በመተላለፍ ጉዳት አድራሽ እቃዎችን በብዛት ያስቀመጠ፣ የተቀበለ፣ ያከማቸ፣ ያጓጓዘ፣ ያዘዋወረ፣ የደበቀ፣ የተገለገለ፣ ያሳየ፣ የያዘ፣ የገዛ፣ የሸጠ፣ ለሽያጭ ያቀረበ፣ የደለለ፣ በማናቸውም መንገድ ያስተላለፈ፣ ወደ ሀገር ያስገባ፣ ከሀገር ያስወጣ፣ ያመረተ፣ ያስወገደ የጠገነ እንደሆነ ከአንድ ዓመት በማይበልጥ ቀላል እስራት እና ከአንድ ሺህ እስከ አምስት ሺህ ብር በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ ይቀጣል ሲል ያስቀምጣል።
በአጠቃላይ ለጠያቂዎቻችን ግንዛቤ የሚረዳ ፅሁፍ በዚህ መልኩ አቀረብን እንጂ አዋጅ ውስጥ የተካተቱትን ዝርዝር ጉዳዮች በርካታ ናቸው። በመሆኑም ለበለጠ መረጃ የጦር መሳሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ ቁጥር 1177/2012 ዓ.ም ይመልከቱ መልዕክታችን ነው።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ነሃሴ 21/2013