‹‹ለብሳ የማታውቀውን የሰው ጃኖ ለብሳ ተይ መልሺ ቢሏት እንዴት ትመልሳ ›› ይላል ያገሬ ሰው። መቼም የሰውን ድርሻ የወሰደች በተለይ በብዙዎች ዘንድ ብርቅ የሆነን እንደድንቅ የሚታየውን የተዋሰች ደረቅ፤ የተዋሰችውን ወይም ያለአግባብ የወረሰችውን የሰውን ድርሻ ለመመለስ መቸገሯ አይቀርም። እንደውም ከፈለገች የኔ ነው ብላ ድርቅ ልትል ትችላለች። ስለመዋሷ የሰውን ስለመውሰዷ ካለማመኗም በላይ እንደማይገባት ቢነገራትም ‹‹አውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት …›› እንደሚባለው አልሰማም ከማለት አልፋ ምናልባት ጊዜ ለማራዘም የይጣራልኝ ጥያቄ ታቀርባለች ልክ አሸባሪው የህወሓት ቡድን እንዳለው ማለት ነው። በመጨረሻ ከተጣራ አይቀር ህወሓት ለ27 ዓመታት ኢትዮጵያን ሲያስተዳድር መቆየቱን ጨምሮ ሁሉም ነገር በገለልተኛ አካል ይጣራልኝ ማለቱም እየተሰማ ነው።
በዓለም ዓቀፍ ሚዲያ በገለልተኛ አካል ነገሩ ይጣራ በማለት ልዩ ቅስቀሳ ፤ ቅስቀሳ ነው ትንኮሳ? ማካሄድ ጀምራለች አሉ። የህወሓት አሸባሪ ቡድን መሪዎች መቼም እፍረት የሚባል ነገር የሌላቸው፤ ኧረ እንደውም እንኳን እነርሱ እፍረት ሊሰማቸው ይቅርና የሚያፍር አይተው የሚያውቁ አይመስሉም። እንደውም በገለልተኛ አካል ይጣራልን ያሉት ጉዳይ ብዙዎችን ያስገርም ይዟል።
በማይካድራ በንፁሃን ዜጎች ላይ ከአንድ ሺህ አምስት መቶ ያላነሱ ሰዎች ላይ የጅምላ ጭፍጨፋና የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈፅሞ ሲያበቃ፤ በጎ እንደሰራ ገድል እንዳፃፈ ሲሸልል ቆይቶ አሁን ደግሞ በተገላቢጦሽ ድርጊቱ ግፍ ነውና አላደረግኩትም በገለልተኛ አካል ይጣራ እያለ ነው አሉ።
ከህወሓት በተቃራኒው የቆሙ አካላት እንደውም ከተጣራ አይቀር በገለልተኛ አካል መጣራት ያለበት ኢትዮጵያን ለማፍረስ በህወሓት በኩል የነበረው ምንድን ነው? የሚሉ ሰዎች የህወሓት ምኞት፣ ሃሳብ፣ ቅዠት እና ህልም መጣራት አለበት ሲሉ፤ እርሱ ደግሞ በተቃራኒው በጣም አስገራሚ በገለልተኛ አካል ይጣራልን የሚሉ ሌሎች አስቂኝ ጥያቄዎችን እንዳቀረበ እየተሰማ ነው። ከይጣራልን ጥያቄዎች መካከል ጥቂቶቹ የህወሓት አሸባሪ ቡድን ኢትዮጵያን ለማፍረስ አስቦ እና አልሞ መስራት ከጀመረ ዘመናት አልፈዋል። የሚለው ወሬ በገለልተኛ አካል መጣራት አለበት በሚለው ላይ ከመስማማት አልፎ እርሱም ይህንኑ ሃሳብ አቅርቧል።
ኢትዮጵያውያኖች ከምላሳቸው ስለአገራቸው ‹‹አገሬ›› ብለው እንዳይናገሩ መሸማቀቃቸው፤ ስለ ኢትዮጵያዊነት የፃፉ፣ የዘፈኑ፣ የተናገሩ ብቻ ሳይሆኑ አንዳንዴ ያሰቡ ሳይቀሩ በእስር ቤት በተለያዩ የሐሰት የክስ ጭብጦች ሲሰቃዩ እንደነበር ይህም ድርጊት በህወሓት መፈፀሙ በራሱ አምኗል ቢባልም፤ ይህ ድርጊት በህወሓት ላይ እየተላከከ በመሆኑ በገለልተኛ አካል መጣራት አለበት በሚል የሽብር ቡድኑ መሪ ጠይቀዋል።
እንዲያውም ከተጣራ አይቀር ህወሓት በጫካ እያለ የትግራይ ህዝብ የሃውዜን ጭፍጨፋ በማን ታቅዶ ምን ታስቦ እንዴት እንደተተገበረ መጣራት አለበት። ይህ ብቻ አይደለም፤ ከሦስት አሥርት ዓመታት በፊት በነበረው የጫካ ትግል ለእውነት የወጡ፣ ከሃዲዎችን የተጠየፉ የጠየቁና ያስጠየቁ የትግራይ ልጆች ታፍነው እንዲጠፉ የተደረገው በማን እንደሆነ በገለልተኛ አካል መጣራት አለበት የሚል ጥያቄንም የአሸባሪ ቡድኑ መሪዎች አቅርበዋል።
ኢትዮጵያ በቀላሉ የምትገፈተርና የምትወረወር አገር አይደለችም። ነገር ግን ሊወረውሯትና ሊገፈትሯት ለፈለጉ የውጪ ጠላቶች መሳሪያ የነበረው እና አሁንም ድረስ መሳሪያ የሆነው ማን ነው? የሚለውም መጣራት እንዳለበት ከህወሓት አሸባሪ ቡድን ጥያቄ ተሰንዝሯል።
ማህበረሰብ አልፎ ተርፎ ህዝብ የጋራ እሴቱን ትቶ እንደጋሪ ፈረስ በግድ በአንድ አቅጣጫ ብቻ እንዲመለከት እንዲከፋፈል፤ አብሮ እንዳያብር እንዲሰባበር፤ ሲሰራ የነበረው እና አሁንም እየሰራ ያለው ማን እንደሆነም መጣራት አለበት ሲሉም የህወሓት ጭፍሮች መጠየቃቸውን መረጃዎች እያመላከቱ ናቸው።
ለ27 ዓመታት በወልቃይት፣ በጠገዴ፣ በጠለምትና በሑመራ ጥያቄ አንስታችኋል እየተባሉ ሲሳደዱ፤ ሲገደሉ እና ሲጨፈጨፉ የነበሩ ሰዎች ድርጊቱን ሲፈፅምባቸው የነበረው ማን እንደነበር መጣራት አለበት ሲል ምንም እንኳን ሰዎች በቴሌቪዥን መስኮት ቀርቦ በገለልተኛ አካል እንዲጣራ ጥያቄውን ያቀረበው ማን እንደሆነ ባያረጋግጡም ቡድኑ ይህንን እያለ መሆኑም እየተገለፀ ነው።
በአጠቃላይ ባለፉት 27 ዓመታት በእስር ቤት ሲሰራ የነበረው ግፍ፤ ሰዎች ህሊናቸውን እስኪስቱ የደረሰባቸው ሰቆቃ በማን እና እንዴት እንደተፈፀመ መጣራት አለበት የሚል ጥያቄንም እንዳቀረቡ ታውቋል። እንደውም አልፈው ተርፈው ለ27 ዓመታት ከአገሪቱ ተመዝብሮ ከአገር ውጪ የወጣው 36 ቢሊየን ዶላር በማን እና እንዴት እንደወጣ ይጣራ በማለት ይህንንም የህወሓት አሸባሪ ቡድን በገለልተኛ አካል የይጣራልኝ ጥያቄን እንዳቀረበበት ተሰምቷል።
በእነዚህ ዘመናት ኢትዮጵያን ለማስተዳደር ሥልጣን የተቆናጠጠው እና እንደፈለገ ሲፈልጥ እና ሲቆርጥ የነበረው ሃይል ስልጣን ላይ የቆየው በጉልበት ነው ወይስ በህዝብ ፍቃደኝነት? የሚለውም ቢጣራ ሳይሻል አይቀርም በማለት ፤ በገለልተኛ አካል ይጣራ የሚል አባዜ የተጠናወተው አሸባሪው ህወሓት ጥያቄውን እንዳቀረበ ተነግሯል።
ያመነውንና የጠበቀውን ሠራዊት በመክዳት፤ ያገዘ፣ የረዳንና የተዋለደ ባለውለታ ላይ ስለት ሰንዝሮ ያቆሰለ፤ በክህደት እንባ ሳይሆን ደም ያስለቀሰ አባትን ከእናት፤ ልጅን ከእናት ነጥሎ የገደለ ሬሳን ሜዳ ላይ ጥሎ ለአሞራ እያስበላ የፎከረው ማን እንደሆነ ህወሓት ይጣራልኝ ብሏልና ይህም በገለልተኛ አካል ቢጣራ መልካም ነው ተብሏል።
ግፍ እንደማይለቅ ዘንግቶ በአፋር ክልል በፈንቲ ረሱ በጋሊኮማ ጊዜያዊ መጠለያ ተጠልለው በነበሩ ሕጻናት፣ ሴቶችና አርብቶ አደሮች ላይ አሰቃቂ ጭፍጨፋ የፈፀመው ማን ነው? 107 ህፃናትን፣ 89 ሴቶችን እና 44 አዛውንቶችን በድምሩ 240 ንጹሐን በጭፍጨፋው ሕይወታቸው እንዲያልፍ ትዕዛዝ ያስተላለፈው የትኛው ሰው ነው? በመጋዝን ተከማችቶ የነበረ የአስቸኳይ ምግብ እርዳታ ሙሉ በሙሉ ያወደመው እና ታሪክ የማይረሳውን አረመኔያዊ ጭፍጨፋ የፈፀመው ማን ነው? ይህንንም ይጣራልን ማለታቸው እየተነገረ ነው።
እነሰው ጤፉ፣ እነ ነውር ጌጡ ዕድሜያቸው አጭር መሆኑ ባያጠያይቅም በቀናት ውስጥ በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ብለው ይህም መጣራት አለበት ማለታቸው እንደማይቀር ይገመታል።
በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን በአጋምሳ መንደር በከባድ መሳሪያ የታገዘ የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ በማካሔድ ንፁኃን ህፃናትና ሴቶች በመንደሯ አንድም ሰው ሳይቀር ሁሉም እንዲያልቅ ያደረገው ማን እንደሆነ መጣራት አለበት በማለት፤ ይህንን ጥያቄ የህወሓት አሸባሪ ቡድን መጠየቁ እንደማይቀር ይጠበቃል።
ኮረም፣ አላማጣ፣ ዋጃንና ጥሙጋ እንዲሁም በቆቦ ዞብል፣ ተኩለሽ፣ ካራይላ፣ አርበት እና አራዱም በሚባሉ ስፍራዎች የተካሔደውን ዝርፊያ እንዲሁም ምንም የማያውቁ እንስሳትን በጥይት ተኩሶ እስከመግደል የደረሰ የዘቀጠ ተግባር መፈፀም አለመፈፀሙን እና በማን እንደተፈፀመ በገለልተኛ አካል እንዲጣራ ጥያቄ ማቅረባቸው አይቀርም ተብሏል።
በአጠቃላይ ስለገድላቸው ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ስለማሴራቸው፣ ለዚህም ለዘመናት ስለመስራታቸው፣ የኢትዮጵያን ህዝብ ስለማሰቃየታቸው ስለመግደላቸው እና በግፍ ስለመግፋታቸው እንዲሁም ስለመዝረፋቸው ስጋውን ግጠው በአጥንቱ ስለማስቀረታቸው በገለልተኛ አካል ይጣራልን እያሉ ቢሆንም፤ በቀጣይ ሌሎች በገለልተኛ አካል ይጣራልን የሚሉ ጥያቄዎችን ማቅረባቸው አይቀርም እየተባለ ይገኛል።
ደግነቱ ይህ ቡድን የጀርመኖችን አባባል አያውቀውም። ወይም ቢያውቀውም አያምንበትም። ነገር ግን የጀርመኖች አባባል እውነት ነው። ‹‹ሃሰት ይደረስባታል ቅልጥሟ አጭር ነው ሮጣ አታመልጥም›› እንደሚሉት እያንዳንዱ ድርጊት በገለልተኛ አካል ተጣርቶ እውነቱ ወጥቶ የህወሓት ዘግናኝ ተግባር በይፋ በአደባባይ ለዓለም መሰጠቱ አይቀርም። ድርጊቱን ፈፃሚዎችና አስተባባሪዎች ደግሞ በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት በዘር ማጥፋት ወንጀል መጠየቃቸው አያጠራጥርም።
ያው መጨረሻ የሚሉት ወደ ላይ ዘለልኩኝ
ፈረጥኩኝ
ጮህኩ አበድኩ
ኡኡ አልኩ
በየጊዜው ለወቅታዊ ስሜቴ ተገዛሁ
ህዝብን አገርን ረሳሁ ለዚህም ይከፈለኝ ዋጋው
ብለው መጠየቃቸው አይቀርም። ነገሩ መጠየቃቸው ባይቀርም በገለልተኛ አካል ሁሉም ነገር ተጣርቶ ምላሽ ሲሰጥ ወደ ቀልባቸው ተመለሱ ሲባል፤ ወደ ፊት ታሪክ በምን መልክ እንደሚዘክራቸው ማወቅ እንፈልጋለን ብለው በድጋሚ በገለልተኛ አካል መጠናት አለበት የሚል ጥያቄ ያቀርባሉ የሚል ተስፋ አለኝ። ምክንያቱም በይጣራልን አባዜ ተወጥረው መሳሪያ ያልታጠቀ ሊገድል የማይችል ሰው ገድለው፤ በተለይ የህፃናትን አሁን ደግሞ የእንስሳትን ህይወት በጥይት አጥፍተው የተለመደ ሰቅጣጭ እልልታቸውን እያቀለጡ ጥሩ እንደሰራ ገድለኛ አሁንም ገድል ይፃፍልን ብለው ይጠይቁ ይሆናል። በተቃራኒው ደግሞ ይኸው በገለልተኛ አካል ይጣራ ማለታቸው አይቀርም። ማን ያውቃል?
አሟሟቴን ያሳምርልኝ ይባላል። ሰው ከሞቱ ይልቅ ስላሟሟቱ ያስባል። ተከብሮ መሸኘት ተለቅሶ መቀበር ይፈልጋል። ቢቻል ከሞቱ በኋላ ስሙ በደግ እንዲነሳ ይጥራል። ስለዚህ በስህተት ሲዋሽ እንኳን ደንግጦ ብረት ይነክሳል፤ ሞትን ሳይሆን አሟሟትን ይፈራል። ምክንያቱም ሁሉም ሟች ነው። ሞት ለማንም አይቀርም። ሞት አያስፈራም። የሚያስፈራው አሟሟት ነው። ነገር ግን እነእንቶኔ የአገር እና የህዝብ ጠላት ሆነው ተጠልተው እና ተዋርደው በበረሃ መሞት ከሞት ሁሉ የከፋ ነው ብለው አያምኑም። ሃሳባቸው እና ህልማቸው በተፈለገው የደም ዋጋ ቦታቸውንና ስልጣናቸውን ማግኘት ብቻ ነው።
እነአያ ደፋር ሞትን እንጂ አሟሟትን አይፈሩም። ስማቸው ለዘለዓለም በጨካኝነት ቀለም በደማቅ ቢፃፍ ግድ የላቸውም። የሚጥሩት እንዳይሞቱ ብቻ ነው። የማንም አሟሟት እነርሱን አያሳዝናቸውም። ስለዚህ ንፁሃንን ገድለው አስክሬን ላይ ይጨፍራሉ። በስሜት ተነድተው የድሃ ጎጆ አቃጥለው ስለጀግንነታቸው ስለጦረኝነታቸው ያወራሉ። አሟሟታቸው ሳይሆን ሞታቸው አስፈርቷቸው በዓለም አደባባይ ሃሰት ይናገራሉ። አይናቸውን አፍጥጠው ወተቱን ጥቁር ነው ብለው ይከራከራሉ፤ መልሰው አላልኩም ብለው ይክዳሉ። ምክንያቱም እነርሱ ግፍ ገድላቸው ነው። ቅዠት እና ህልማቸው ደግሞ ስልጣን ብቻ ነው።
ሲቀበሩ መሬት ተከፍታ እነርሱን ለመዋጥ አንገራገረች፤ መሬት አልቀበልም ብላ ተፋቻቸው ቢባል ለእነርሱ አይገርማቸውም። እነርሱ ህልማቸው የሰውን መንጠቅ እና ሰው አናት ላይ በግድ መቀመጥ ነው። ስልጣን የህዝብ ነው፤ አውራጅ እና ሿዋሚም ህዝብ ነው ቢባሉም አይሰሙም። ሁልጊዜም ጆሯቸው ለመስማት ያልተዘጋጀ ድፍን፤ አይናቸው አይቶ ለማመን ያልተዘጋጀ ዝግ ነው። ማንም ምንም ቢላቸው አይሰሙም። ስራቸው ግፍ፤ በግፉ ደስታ ከጀርባ ደግሞ ደባ እየሰሩ ወይ ስልጣን ይይዛሉ፤ አሊያም አገር ያፈርሳሉ።
ውጊያ ውስጥ ገብተው ማሸነፍ አቅቷቸው የቆሙበት መሬት ሲከዳቸው ሰማይ ሲደፋባቸው፤ ማልቀስ ይጀምራሉ። የሰሩት ግፍ እንደሌለ ለፍልፈው ለዓለም ህዝብ ተናገረው ሁሉም ነገር በገለልተኛ አካል ይጣራልን ይላሉ። ገለልተኛ ካለ፤ ገለል ያለ ነው የተባለለት አካል እውነተኛ ውጤቱን ሲያወጣ እጅ በሰንሰለት ሲታሰር፤ በበሽታ መጥመልመል ሲመጣ፤ የዛን ቀን ሞት ሳይሆን አሟሟት ምን ያህል ሊታሰብበት እንደሚገባ ይረዱት ይሆናል። ለጊዜው ግን ይጣራ በሚል ሹፈት ንፁሃን ኢትዮጵያውያንን እየፈጁ እና እያስፈጁ ቀን እስከሚያልፍ ያልፉ ተብሎ ተፈቅዶላቸዋል።
ምህረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 20/2013