በኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ ሰፊ የጋራ እሴቶች አሉ።የተለያየ ቋንቋ እና ባህል ያላቸው ኢትዮጵያውያን ልዩነት ብቻ ሳይሆን አንድ የሚያደርጋቸው ብዙ ጉዳዮች አሏቸው።ከዚህ መካከል ተጠቃሹ የጠነከረ የእርስ በርስ ግንኙነት እና መተባበር አንደኛው ነው።እነዚህ ኢትዮጵያውያን በአገር ውስጥ የሚኖሩት እንዳሉ ሆነው ከሶስት ሚሊዮን ያላነሱት ደግሞ በተለያዩ ዓለም አገራት እንደሚኖሩ መረጃዎች ያመለክታሉ።በአሜሪካ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ፣ በአውስትራሊያ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ፣ በካናዳ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ፣ በጣሊያን ፣ በእንግሊዝ፣ በዴንማርክ እና በኖርዌ እንዲሁም በዓለማችን በተለያዩ አገራት የኢትዮጵያ ዲያስፖራዎች እየኖሩ ነው።
እነዚህ በተለያየ አገራት የሚኖሩ የኢትዮጵያ ዲያስፖራዎች በብሔር እና በቋንቋ የሚለያዩበት ሁኔታ ቢኖርም፤ የማንነታቸው መገለጫ ያው አገራቸው ኢትዮጵያ ናት። ኢትዮጵያውያን በውጭ ሀገራት ይኑሩ እንጂ ሁሌም ልባቸው ከሀገራቸው ጋር ነውና ከሀገራቸው እና ከወገናቸው ጎን የሚቆሙ የሀገር አለኝታ ሆነዋል።በዚህም በተለያዩ ጊዜያት ከሀገራቸውና ከወገናቸው ጎን በመቆም ከእነሱ የሚጠበቀውን ሁሉ በማድረግ ምስክር የማይሻው ተግባር እያከናወኑ ይገኛሉ ።ከዚህ አንፃር ለአገራቸው ትርጉም ያለው ለውጥ እንዲያስገኙ በተለያየ መልኩ ሥራዎች ይሰራሉ። የኢትዮጵያ ዲያስፖራዎች በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ መተባበር አንድነታቸውን ለማጠናከር የሚያስችል እንቅስቃሴ መጀመራቸው እየተገለፀ ነው።
በተለይም በዋናነት በአሜሪካ በመተባበር የተለያዩ ሥራዎች በመከናወን ላይ የሚገኙ ሲሆን፤ 13 የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶችን በማቀፍ ሥራው መጀመሩ ተጠቅሷል። ተፈናቅለው በመጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ለመደገፍ ጥረት እየተደረገ ሲሆን፤ ከኢትዮጵያ ጀርባ የቆሙ ኢትዮጵያውያንን ግፊት ለመመከትም ተጨባጭ ሥራ እየተከናወነ ነው።ኢትዮጵያውያን አንድ ነን የሚል ዘመቻ በማካሄድ ለሠራዊቱ ገንዘብ የማሰባሰብ ሥራ በመከናወን ላይ እንደሚገኝ መረጃዎች ያመለክታሉ።
ዲያስፖራው ውጪ ሆኖ ለአገሩ የሚሰራውን ሥራ በአገር ወዳድ ዳያስፖራዎች እና በኤምባሲዎች አስተባባሪነት የሚከናወን ሲሆን፤ በአገር ውስጥ መጥተው ለሚሰሩት ሥራ ደግሞ ከኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲ ጀምሮ በተለያዩ ክልሎች የተቋቋሙ የዳያስፖራ ፅህፈት ቤቶችም ለዲያስፖራው አስፈላጊውን መረጃ በመስጠት ላይ ይገኛሉ።ከዚህ በተጨማሪ ዲያስፖራው ወደ ሀገሩ መጥቶ ኢንቨስት ለማድረግ የሚችልበት ምቹ ሁኔታዎች የማመቻቸት ሥራ ይሰራሉ።
መረጃ ከመስጠት ጀምሮ የማስተባበር ሥራን የሚሰሩ ማህበራት እና ተቋማት መኖራቸውን ሲጠቀስ፤ ከእነዚህ መካከል የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የዲያስፖራ ፅሕፈት ቤት የዲያስፖራ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ዳይሬክቶሬት ይጠቀሳል። በዳይሬክቶሬቱ በከፍተኛ ባለሙያነት የሚያገለግሉት አቶ አወቀ ምንውዬለት እንደሚናገሩት፤ ለዲያስፖራው የተለያየ አገልግሎት በመስጠት ላይ ናቸው።
እንደአቶ አወቀ ገለፃ፤ ዲያስፖራው በዋናነት የሚፈልገውን መረጃ በመስጠት በኩል ከፍተኛ አስተዋፅኦ በማበርከት ላይ ናቸው።ዲያስፖራው ለዘመናት ውጪ የኖረ በመሆኑ በማንኛውም ጉዳይ ላይ በቂ መረጃ ላይኖረው የሚችልበት አጋጣሚ ሰፊ ነው።ይህንን መረጃ ለማግኘት ደግሞ በቀጥታ የሚመጣው የተሻለ መረጃ ይሰጠኛል ብሎ ወደ ሚያምንባቸው የዳያስፖራ ተቋማት ነው።ከእነዚህ ተቋማት መካከል አንዱ የዲያስፖራ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ዳይሬክቶሬት በመሆኑ በአማራ ክልል የሚመጡ ብዛት ያለው መረጃዎችን ለዳይሮክቶሬቱ ጥያቄ ያቀርባሉ።
ዳይሬክቶሬቱ ለዲያስፖራው መረጃ የሚሰጥ ሲሆን፤ ለምሳሌ የማህበር ቤት ጥያቄ ሲያቀርብ በመኖሪያ ቤት ዙሪያ የተዘጋጀውን መመሪያ በማሳወቅ ግልፅ ሆኖለት በክልሉ ቤት የሚሰራበትን አማራጭ እንዲያውቅ ይሰራል ይላሉ።
አቶ አወቀ እንደገለፁት፤ ዳይሬክቶሬቱ በተጨማሪ ከኢንቨስትመንት ጋር ተያይዞ ለሚቀርብ ጥያቄም ምላሽ ይሰጣል።ከኢንዱስትሪ እና ከኢንቨስትመንት ኮሚሽን የተዘጋጀ የኢንቨስትመንት አማራጮች አሉ።ይህ በክልሉ ጥናት ተደርጎ ዲያስፖራው ኢንቨስት ለማድረግ ሲመጣ አማራጮቹን ተመልክቶ መነሻ እንዲሆነው ለዲያስፖራው የተዘጋጀውን ሰነድ በመስጠት፤ ራሱ ‹‹ በዚህ ዘርፍ ብሰማራ የበለጠ ጥሩ ነው።ምክንያቱም አቅሜ እዚህ ድረስ ነው ፍላጎቴም ይህ ነው›› የሚልበት ዕድል ይመቻችለታል።ስለዚህ የኢንቨስትመንት መረጃዎች በዝርዝር የሚያገኙበት ሁኔታ መኖሩን ይናገራሉ።ከዚያም በመረጡት መልክ ወደ ሥራ የሚገቡ መሆኑንም ገልፀዋል።
ዲያስፖራው ሥራ ላይ ተሰማርቶም ዕክል ሊገጥመው እንደሚችል የሚናገሩት አቶ አወቀ፤ ከአቅማቸው በላይ እንቅፋት የሚሆንባቸው ነገር ሲያጋጥማቸው ወደ እነርሱ የሚመጡ ሁኔታ መኖሩን ይገልፃሉ።ይህ በሚሆንበት ጊዜ እንቅፋት የሆነውን አካል በስልክ ወይም በአካል ቀርቦ በማነጋገር የችግሩን ምንጭ ለማወቅ ጥረት በማድረግ መፍትሔ የሚገኝበት ሁኔታንም ዳይሬክቶሬቱ ያመቻቻል ይላሉ።በተጨማሪ በቀላሉ ካልሆነም ደብዳቤ በመፃፍም ጭምር ችግሩ እንዲቃለል እንደሚጠይቁ እና ደብዳቤያቸውም ተፅዕኖ በመፍጠር ችግሩን እንደሚያቃልል አመላክተዋል።
ዲያስፖራው በአገር ውስጥ በኢንቨስትመንት መሰማራቱ ለሥራ ዕድል ፈጠራ የሚኖረው አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑን አስታውሰው፤ ዳይሬክቶሬቱ ዲያስፖራው ከየት አገር መጣ? ምን ያህል ይዞ መጣ? በምን ዘርፍ ላይ ተሰማራ? አጠቃላይ ካፒታሉ ምን ያህል ነው? ግንባታ የሚያከናውን ከሆነም ግንባታው ያለበትን ሁኔታ እንዲሁም የፈጠረውን የሥራ ዕድል አጠቃላይ አገልግሎት እየሰጠም ከሆነ በዚህ ዘርፍ ላይ አገልግሎት እየሰጠ ነው የሚል መረጃ የሚያዝ መሆኑንም ይናገራሉ።
በሌላ በኩል ዲያስፖራውን የተመለከቱ የተዘጋጁ አዋጆች፣ መመሪያዎች እና ደንቦችን በመያዝ ዲያስፖራው እንዲያውቃቸው ይደረጋል ይላሉ።
ዲያስፖራው ለገፅታ ግንባታ የሚኖረው አስተዋፅኦም ከፍተኛ መሆኑን አስታውሰው፤ ምንም እንኳን በእነርሱ በኩል የሰው ሃይል እጥረት በመኖሩ በተለይ ከወቅቱ ጋር ተያይዞ ሰልፎችን እና ድጋፎችን ለማስተባበር በራሳቸው በኩል አቅሙ ባይኖርም በቅርብ የደም ልገሳ እና የደመወዝ ድጋፍ እየሰጡ መሆኑን ተናግረዋል። በአጠቃላይ ለሚጠየቀው ጥያቄ ምላሽ የሚሰጡ መሆኑን አስታውሰው፤ በዋናነት ውጪ ያለውን ዲያስፖራ ከማስተባበር አንፃር አዲስ አበባ የሚገኘው የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲ የሚሰራው መሆኑንም ተናግረዋል።
ምህረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 19/2013