ኢትዮጵያውያን የእልፍ ቋንቋ ተናጋሪ ፣ሺህ ባህልና ወግ አክባሪ፣ አንድ ቃል ተናጋሪ ናቸው:: ይሁንና ጠላቶቻቸው ከዚህ በተቃራኒው እንዲሆኑ ሲሰሩ ኖረዋል:: ጠላቶቻቸው እንደ አንድ ልብ መካሪ እንዳይሆኑ በየዘመናቱ ቢፈታተኗቸውም ሁሉንም በማሳፈር በአንድነታቸው ጸንተው የሀገራቸውን ሉአላዊነት እያስከበሩ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲያስተላልፉ ኖረዋል::
ዛሬም አሸባሪው ህወሓትና እድገቷን የማይፈልጉ ምእራባውያን መንግስታት እየተፈታተኗት ይገኛሉ:: አሸባሪው ህወሓት የምእራባውያኑ ተላላኪ በመሆን የውክልና ጦርነት እንዲከፍቱብን አድርጓል:: ይህ ከሀዲ ቡድን የስልጣን ጥመኝነቱን በመላላክ በኩል አገኛለሁ ብሎ ኢትዮጵያውያን በግፍ እየጨፈጨፈ ይገኛል:: የጭካኔው ጥግ ያንገፈገፋቸው፣ በሚያካሂደው የውክልና ጦርነት የሀገር ሉአላዊነት መደፈሩ ያንገበገባቸው ኢትዮጵያውያን ግን ቡድንና የአይዞህ ባዮቹን ተግባር ለመፋለም ዛሬም አንደ ጀግኖች አባቶቻቸውና እናቶቻቸው ተቆጥተው ተነስተዋል::
የምስራቁ የሰሜኑ የደቡብ እና ምዕራብ የአብራኳ ክፋይ የወገቧ ፍልቃቂ አለሁልሽ ባይ ውብ ፍሬዎቿ ደርሰውላታል:: ለዘመናት የወዲሁ የወዲያውን፤ የወዲያኛው የወዲሁን ባህል አክብሮ፣ የራሱን ባህል አክበሮ ከኖረበት ቀዬው ነቅሎ ወጥቶ በአንድነት አደባባይ አንድ ሆኖ በጠላቶቿ ላይ ሊዘምት ድሉንም ሊዘክር ከያለበት እየተመመ ጠላትን ለመፋለም ሆ ብሎ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ገብቷል::
እነዚህን የሀገር ፍቅር ስሜት ያንገበገባቸውን ኢትዮጵያውያን የተመለከቱት ጀግኖች የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችና የባህል ከዋክብትም “ ኢትዮጵያያን ለማዳን እዘምታለሁ፤ የትም፣ መቼም፣ በምንም” እያሉ ጦላይ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ደረሰዋል:: ከእነዚህ መካከልም ደግሞ ልዩ ታሪክ የላት አንዲት እንስት ትገኛለች::
ነገሩ እንዲህ ነው፤ ጊዜው 1981 ዓ.ም ሲሆን፤ የብሔራዊ ቴአትር አርቲስቶች በኤርትራ ለሚገኘው ሰራዊት /ምስራቅ እዝ/ የሞራል ስንቅ ለመስጠት ወደ አስመራ ሊያቀኑ ተዘጋጅተዋል:: ሁሉም ነገር ተሰናድቶ ካለቀ በኋላ የቡድኑ አባል የነበረችው አርቲስት መሰሉ ተሰማ ባጋጠማት የግል ጉዳይ ከቡድኑ ጋር መሄድ ሳትችል ትቀራለች::
17 የቡድኑ አባላት ግን በማለዳ ጉዞአቸውን ይጀምራሉ:: ኢርትራ ደርሰውም ዝግጅታቸውን ወደሚያሳዩበት ስፍራ እየተጓዙ ባለበት ወቅት አሳዛኝ ክስተት ደረሰ፤ ለጀግናው ሠራዊት አባላትም ያሰቡትን የሞራል ድጋፍ ሳያደርጉ፤ በወቅቱ ለኤርትራ ነጻነት ይታገል በነበረው ሻእቢያ በተፈጸመባቸው ጥቃት ወሬ ነጋሪም ሳይተርፍ ሁሉም የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ተገደሉ::
ትረፊ ያላት የአርቲስት መሰሉ ተሰማ ነፍስም በህይወት ኖራ ዛሬ ላይ ታሪክ ነጋሪ ሆናለች:: ታሪክ መንገር ብቻ ሳይሆን የዛኔ ያተረፋት ለአንዳች ምክንያት እንደሆነ በማመን ዛሬ ላይ ሠራዊቱን በአካል ተገኝታ በሙያዋ ለማበረታታት እድሉን አግኝታለች::
በደርግ ሥርዓት ወደ ጦር ግምባር የሚሄዱትን የሠራዊት አባላት በማነቃቃት ድጋፍ ትሰጥ የነበረችው የብሔራዊ ቴአትር የባህል ሙዚቃ ተጨዋች አርቲስት መሰሉ ተሰማ፤ በአሁኑ ወቅትም እድሉን አገኝታ በጦላይ ማሰልጠኛ ማዕከል በመገኘት በሙያዋ ሠልጣኞችን አነቃቅታለች::
ከመከላከያ ሠራዊት ጎን ለመቆም ያነሳሳት የአገር ሉዓላዊነት ጉዳይ እንደሆነና አሸባሪው የህወሓት ቡድን በሀገሪቱና በዜጎች ላይ በፈጠረው ችግር ኢትዮጵያውያን ይበልጥ ወደ አንድነት መጥተዋል ስትልም ትገልጻለች::
አርቲስቷ፤ “ከልጅነቴ ጀምሮ ኢትዮጵያ በአንድነቷ ተክብራ እንደምትኖር ነው አባቶች ያስተማሩኝ:: የህወሓት ሥርዓት ከመጣ በኋላ ግን ኢትዮጵያዊነት የጠፋበትና የደበዘዘበት ሁኔታ መታየቱን ትጥሳለች:: በዚህም እጅግ በጣም አዝኛለሁ የሚትለው አርቲስቷ፣ ዛሬ ራሳቸው በፈጠሩት ችግር ኢትዮጵያዊያን ወደ አንድ መሆን ችለናል፤ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለአገሩ ዘብ ቆሟል ብላለች::
እንደ አርቲስት መሰሉ ማብራሪያ፤ ኪነ ጥበብ በአገር ጉዳይ ላይ ሲነሳ ጥንት በጣሊያን ወረራ ጊዜ የጥበብ ሰዎች ማሲንቆ፣ ዋሽንት፣ ከበሮና ሌሎች አገር በቀል የሙዚቃ መሳሪያዎችን ይዘው ኢትዮጵያውያንን እያነቃቁ አባቶች ድል እንዲያደርጉ ከፍተኛ ሚና ነበራቸው:: ይህ ዘርፍ ወኔን ቀስቃሽና ማጀገኛ ጭምር ነበር:: በዚህ መስክ ከማነቃቃት ባሻገር በርካታ አርቲስቶችም መስዋእትነትም የከፈሉበት ሁኔታ ታይቷል::
አሁን ላይ ደግሞ ኪነ ጥበብ ሠራዊቱን በመቀስቀስ፣ ወጣቱን በማነቃቃትና በማነሳሳት ጦር ግንባር በመሄድ ለኢትዮጵያ አንድነት እንዴት መስዋእት መክፈልና ድል ማድረግ እንደሚችል ሞራል በመስጠት ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው:: ይህም በመሆኑ ነው በርካታ ከያኒያን ወደ ማሰልጠኛው በመሄድ ወጣቶች ለአገራቸው በብርቱ እንዲቆሙ ለማድረግ የበኩላቸውን ያደረጉት::
ሌሎች የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችም ለመከላከያ ሠራዊቱ የማያቋርጥ ድጋፋቸውን እንዲያደርጉና ግንባር ድረስ በመቅረብ ሠራዊቱን በመቅስቀስ የሞራል ስንቅ እንዲሰጡ አርቲስቷ ጥሪዋን አስተላልፋለች::
ለምልምል ወታደሮች በጦላይ ማሰልጠኛ ማዕከል የማነቃቂያ ፕሮግራም ያቀረበው ኮሜዲያን ምትኩ ፈንቴ ከሙያ አጋሮቹ ጋር በመድረኩ ያቀረባቸው ሥራዎች ወጣቶቹን በእጅጉ አዝናንቷቸዋል::
ኮሜዲያኒ በአሁኑ ወቅት አገሪቷ የሠላም አየር እንድትተነፍስ ኢትዮጵያውያን በጋራ እየሰሩ ናቸው ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል:: ያለን አንድ አገር በመሆኑ ሁሉም በየፊናው የራሱን ድርሻ በመወጣት ለሠላሙ አስተዋጽኦ ማበርከት ይኖርበታል ሲልም አሳስቧል:: በአሁኑ ወቅት እየታየ ያለውን ኢትዮጵያዊ አንድነት አጠናክሮ ለማስቀጠል የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ሚናም የጎላ እንደሆነ ተናግሯል::
“አርቲስት ልክ እንደ ክብሪት ነው” የሚለው በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር የባህልና ዘመናዊ ዳንስ ኬሮግራፈር ደጀን ሀይሉ (ዲጄ)፤ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ለሠራዊቱ የሚያቀርቡት የማነቀቃቂያ ፕሮግራምም የሀገር ፍቅር ስሜት እንደ መጫር አይነት መሆኑን ጠቅሷል:: አርቲስቱ ያለውን ትልቅ አቅም ተጠቅሞ እየሰራ እንደሆነና የኢትዮጵያ ህዝብም ወንድማዊ ፍቅሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል መልእክቱት አስተላልፏል::
በወቅቱ አርቲስቶቹ በመድረክ ላይ ባቀረቧቸው ጥበባዊ ትዕይንቶች በጦላይ ማስልጠኛ ያሉ ምልምል ወታደሮች ማህጸን ውስጥ ያለ ጽንስ እንደሚዘል ነው የሆኑት:: በዝማሬያቸው፣ በሚያወጡት መፈክር፤ ሰንደቅ ዓላማውን ከፍ አደርገው በሚያደርጉት ወታደራዊ እንቅስቃሴ ልብ የሚነካ ትውስታን አኑረዋል:: በሥፍራው የነበሩት አርቲስቶችም በዚህ አጋጣሚ መንግስት አገሪቷ ተተኪ ትውልድ እንዳላት አስቦ ወጣቶች ላይ በደንብ ሊሰራ ይገባል ብለዋል ::
አርቲስቶቹ ባቀረቡት ሙዚቃ፣ ውዝዋዜ፣ ግጥም፣ ሰርከስና በመሰሰሉ የጥበብ ትእይንቶች በስፍራው የነበሩት ጣቶች እጅጉን ተደስተዋል:: ኪነ ጥበቡን እንደ መንፈስ ወጌሻ ተጠቅመውበታልም:: መድረኩም ወጣቱ በአገር ጉዳይ ላይ የሚያሳየውን ትልቅ ስሜት ያመላከተ ነበር::
አዲሱ ገረመው
አዲስ ዘመን ነሃሴ 16/2013