ከአዲስ እስከ አንኮበር / ክፍል ሁለት የመስክ ስራና መስከኛው/
ለኢትዮጵያ አንድነት ምስረታና ለአድዋ ጦርነት ድል መገኘት የሚጠቀሱትና በታሪክ ትልቅ ስፍራ ያላቸው አፄ ሚኒሊክ በዚህ ሳምንት ነው ወደ ዚህች ምድር የመጡት፤ የተወለዱት። የንጉሱ የትውልድ አካባቢና ቤተ መንግስታቸው የሚገኝበት አንኮበር ደግሞ የዚህ ፅሁፍ መዳረሻ ነው። ባለፈው ሳምንት በጋዜጠኛው ቅኝት አምዳችን ከአዲስ አበባ እሰከ አንኮበር የተመለከትነውንና የታዘብነውን እያነሳን አውግተናችኋል። ዛሬ ደግሞ በአንኮበር ቆይታችን የተመለከትነውን አሰናድተን አቅርበናል።
ወደ አካባቢው የተጓዝንበት ዋንኛ ምክንያት አንኮበር ከሚገኘው የንጉስ ሚኒሊክ ቤተ መንግስት ጥቂት ኪሎ ሜትሮችን አልፎ በሚገኝ ቦታ ላይ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ባሰናዳው የችግኝ ተከላ መርሀ ግብር ላይ ለመካፈል መሆኑን ባለፈው ገልጬ ነበር። እናም ጉዞ ወደ ችግኝ መትከያ ስፍራ ተጀምሯል፤ ይሁንና የምንጓዝበት መኪና ችግኙ ወደሚተከልበት ስፍራ የሚወስደው መንገድ አቃታት፤ ሹፌሩ ይህ መሆኑን እንደ እንደወረድን፤ እናም ቁልቁል ወደ እግር መጓዝ ቀጠልን። በእርግጥ ከተማ ሰልችቶት ለቆየና የአካባቢውን የተለየ መልካም ምድር እየተመለከተ መጓዝ ለፈለገ ለኔ ቢጤ ከመኪናው መውረዱ እንደ እድል ይቆጥራል።
በዚያው አጋጣሚ ከተዋወኳቸው የመገናኛ ብዙኋን ባለሙያዎች ጋር እያወራን ቁልቁለቱን ተያያዝነው። ቁልቁለቱ ግን ፈታኝ ነበር። ቁልቁለት ነው ምን ችግር አለው አንዳትሉኝ፤ አንዳንድ ቁልቁለት የዳገት ያህል ይከብዳልና ይህም የዋዛ አልነበረም።
ወደ ቁልቁለቱ እየዘለቅን ሄድን፤ ወደ ኃላ መለስ ብዬ ስመለከት ከጀርባችን ትልቅ ተራራ ታየኝ። ተራራውን ጭምሮ የአካባቢው መልካ ምድር አቀማመጥና የቀኑ መልካምና ነፋሻማ የአየር ንብረት ጉዟችን አሰልቺ እንዳይሆን አድርጎታል።
በየመንገዱ መሀል እያስቆሙ የቅርብ ወዳጅ አይነት ሞቅ ያለ ሰላምታ የሚሰጡንና ሳያውቁን ወደየት እንደምንሄድ የሚጠይቁን የአካባቢው ነዋሪዎች ትህትና አስገረመኝ። ጎበዝ መሀል አገር ላይ ሰው ስያገኝህ ገርምሞህ እንጂ መች ሰላምታ ሰጥቶህ ያልፋል። ለማናውቀው መንገደኛ ሰላምታ ብንሰጥ ለነገር ነው የምንባል ይመስለኛል። አንኮበር ላይ በተሰጠን ሞቅ ያለ ሰላምታ መደነቄም ለዚሁ ነው።
እኛ ወደምንሄድበት አቅጣጫ የሚጓዝ አንድ የአካባቢው ወጣት አገኘሁና ከእርሱ ጋር እያወጋሁ መሄድ ጀመርኩ። ስለ አካባቢው እንዲነግረኝ ጥያቄዎችን እያከታተልኩ አቀረብኩለት። በእርግጥ የጠየኩትን ያህል ምላሽ የሚሰጠኝ እልነበረም። እጅግ በጣም ቁጥብ ነው። አቶ በላይ ምናዬ ይባላል። ከቤቱ ወደ እርሻ ስራ እየሄደ መሆኑን ነገረኝ። የመኖሪያው አካባቢውና የእርሻ ቦታው 3 ኪሎ ሜትር ያህል ይራራቃሉ።
ስንዴ ገብስና በቆሎ አልፎ እልፎም ባቄላ አካባቢው ላይ ይመረታል። የመሬቱ ተዳፋት መሆን ለእርሻ ብዙም አመቺ እንዳይሆን አድርታል። በመሬቱ አቀማመጥ የተነሳ የአካባቢው አርሶ አደሮች ብዙ እንደሚደክሙ ይገልጻል።
መብራትና ውሀ የማህበረሰቡ ዋንኛ ጥያቄዎች መሆናቸውን ተናግሮ፣ በቅርቡ የቦኖ ውሃ ለማስገባትና በከተማና ውጪ አገር በሚኖሩ በአካባቢው ተወላጆች ርብርብ እየተደረገ መሆኑን አቶ በላይ ጠቁሞኛል።
በመንገድ ግንባታውም የደብረብርሃን አንኮበር ጠጠር መንገድ ወደ አስፋልት እየተቀየረ ነው። የመንገድ ፕሮጀክቱ ከአንድ ነጥብ አንድ ቢሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ እየተገነባ ሲሆን፣ ግንባታውም የሚካሄደው በሀገር በቀሉ ሰንሻይን ኮንስትራክሽን ኃ/የተ/የግ/ማ ነው።
መስመሩ ከሚያሰተናገደው የተሸከርካሪ ብዛት፣ ማህበራዊና ኢኮኖማዊ ፋይዳ አኳያ እንዲሁም ከከተማው ቀጣይ አድገት ጋር ተስቦ በአስፋልት ደረጃ እንዲገነባ እየተደረገ ነው። ግንባታው ከደብረ ብርሃን አንኮበር ብቻ የሚዘልቅ አይደለም፤ በምዕራፍ በምዕራፍ ተከፋፍሎ እየተገነባ ሲሆን፣ ከአፋር ክልሏ አዋሽ ከተማ ድረስ ይዘልቃል። የደብረ ብርሃን አንኮበር መንገድ ግንባታ ሲጠናቀቅ በአካባቢው እየተካሄዱ ለሚገኙ ተስፋ ሰጪ የልማት ስራዎች የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ ነው።
ከ20 ደቂቃ የማያንስ የእግር ጉዞ እንዳደረግን አብረውን ካሉት የመገናኛ ብዙኋን ባለሙያዎች ጋር መራራቅ መከሰት ጀመረ፤ አንዳንዶቹም በድካም ምክንያት ወደ ኋላ ቀሩ። እኔም በእግሬ ረጅም ርቀት ከተጓዝኩ ቆይቼ ነበርና ድካም ቢጤ ተሰማኝ።
በጉዞው አስተባባሪዎች ግማሽ ያህል መንገድ እንደቀረ ሲነገረን በድካማችን ላይ መርዶ የተነገረን ያህል በረጅሙ ተነፈስን። ይሁንና መድረስ አለብን ብለን ጉዞውን ቀጠልን። ይሄኔ ከእኛ ጋር ብዙም ሳይራራቅ ከፊት ይጓዝ የነበረው አስተባባሪ ቀድመው ቦታው ላይ በሌላ መኪና ደርሰው ከነበሩት የስልክ መልዕክት ደረሰውና አስቁሞን ይነግረን ጀመር።
ቀድመው በሌሎች መኪኖች የችግኝ መትከያ ቦታው ላይ የደረሱት የተቋሙ ከፍተኛ አመራሮች ችግኙን ተክለው እየተመለሱ መሆኑን አሳወቀን። እዚያ የተገኘነው ለዘገባ መሆኑንና የተሰራውን ስራ ለማየት የግድ ቦታው ላይ መድረስ አንዳለብን ሀሳብ አቀረብን። ምን ይዤ ልመለስ ነው? ያለው ድምጻዊው።
የቀረው መንገድ እጅግ አድካሚ መሆኑንና እዚያ ብንደርስ አንኳን ሀላፊዎቹ ጨርሰው እየተመለሱ ስለሆነ እንደማናገኛቸው አስተባባሪው ሲነግረን ተስፋ ቆረጥን። የጉዟችን ዋንኛ ግብ በዚህ መልክ መቋጨቱ ሁላችንንም አሳዘነን።
ከአዲስ አበባ አንኮበር ድረስ ለዚያውም አድካሚ የእግር ጉዞ የታከለበት ሁነት ዋንኛ ጉዳዩን ሳያሳካ ወደ ኋላ መመለስ ግድ ሆነበት። ስንለስ መጀመሪያ የሄድንበት መንገድ በድካምና ያሰብነው ባለመሳካቱ ሳቢያ እጅጉን ረዘመብን። እያለከለክን ዳገቱን ወጥተን በመጨረስ መኪናው ጋ የደረስነው በጣም ጥቂት ነበርን፤ አብዛኞቹ ገና ታች ነበሩ። ሰዎች እስኪደርሱ አጋጣሚውን ለመጠቀም አሰብን። ከቦታው በቅርብ ርቀት ላይ ያለውን የአጼ ሚኒሊክ ቤተ መንግስት ለመጎብኘት ከአንድ ባልደረባዬ ጋር አመራን።
ከዋንኛው የመኪና መንገድ ፈንጠር ብሎ ካለው የቤተመንግስቱ መግቢያ በር እስከ ቤተመንግስቱ የተሰራው መወጣጫ ደረጃ እጅጉን ፈታኝ ነው። ቀጥ ያለ ዳገት የመውጣት ያህል ጉልበትን ያርዳል። በስፍራው የአንኮበር ቤተመንግስት በሚል እየተጎበኘ የሚገኘው ቤተመንግስቱን ተመሳስሎ የተሰራ ህንጻ ነው። በአካባቢው ግን የቤተመንግስቱ ፍርስራሽ ይታያል።
በ18ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ አካባቢ በንጉስ ሳህለ ስላሴ የተገነባው ቤተ መንግስት አፄ ይኩኑ አምላክና ሌሎች ነገስታት በቤተመንግስትነት ነግሰው ተቀምጠውበታል። ከ4 በላይ ነገስታትም መቀመጫ ሆኖ አገልግሏል።
የአፄ ሚኒሊክ ቤተመንግስት በሚል እየተጎበኘ ያለው ህንጻ ልክ ቤተመንግስቱን እንዲመስል ተደርጎ እጅግ ጥበብ በተሞላበትና ዙሪያውን በሚገባ ለመቃኘት በሚያስችል ከፍታ ላይ የተገነባ ነው። ደረጃዎቹን እያለከለክን ወጥተን ጨርሰን ቤተመንግስቱ ጋ ደርሰን ጥቂት እረፍት ወሰድን።
ቤተ መንግስቱ ጥንታዊነቱን በጠበቀ መልኩ በ1998 ዓ.ም በኢንጅነር ተረፈ ተመሳስሎ እንደተገነባ መረጃዎች ያመለክታሉ። ቤተመንግስቱ ባለ አንድ ወለል ነው፤ ባህላዊ ገፅታን እንዲለበስ ተደርጎ ነው የተገነባው። በውስጡም አፄ ሚኒሊክ በወቅቱ ይገለገሉባቸው የነበሩ የቤት ውስጥ መገልገያ ቁሳቁስን፣ የመጀመሪያ ስልኮችን፣ መመገበያና መቀመጫዎችን፣ ታሪካዊ ሁነቶችን በሚያስታውሱ ፎቶዎች ተሞልቷል። ሰፊ በሆነው ክፍል ውስጥ በተለያዩ የህንፃው ግድግዳዎች የተሰቀሉ ታሪካዊ ፅሁፎችና የንጉስ ሚኒሊክ መልዕክቶች አዋጆችና ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች በብራናና በሌሎች ቁሶች ተከትበው ተሰቅለዋል።
ቤተ መንግስቱ በውስጥ የምግብና መጠጥ መስተንግዶም ይሰጥበታል። በእርግጥ በዚህ ታሪካዊ ህንፃ ላይ የሚሰጡ አገልግሎቶች በቅርሱ ምን ያህል አሉታዊ ተፅዕኖ ሊያሳድሩ እንደሚችሉ የታሰበበት አልመሰለንምና በዚሁ መጠቆም ፈለግን። አበቃን ቸር ያሰማን።
የቤተ መንግስቱ አስጎብኚ እንደነገረን፤ በክፍሉ ውስጥ ስለሚገኙት መገልገያ ቁሳቁስና ታሪካዊ ፎቶች ማብራሪያ ሰጠን፤ ይህ ስፍራ በአመት ከ30 እስከ 40 ሺ በሚደርሱ የአገር ውስጥና የውጪ እንግዶች ይጎበኛል። አሁን ላይ ኮቪድ የጎብኚዎች ቁጥር በእጅጉ እንደቀነሰው ከስፍራው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 15/2013