አሸባሪው ህወሓት ጫካ ከገባበት ጀምሮ ኢትዮጵያን ለማጎሳቆል ያልገባበት ጉድጓድ አልነበረም:: ጫካ በነበረበት እና በስልጣን ዘመኑም በሀገራችን ላይ ያልፈጸመው የለም:: ይህ የጥፋት መፈልፈያ ቡድን በፈጸመው እኩይ ተግባር መጸጸት ሲገባው ይባሱኑ ብሎ መከላከያን ወጋ:: መከላከያም በተፈጸመበት ግፍ ህገ ወጥ ተግባር ህግ ለማስከበር ተንቀሳቀሰ:: በህገ ወጥ ተግባሩ የተሳተፉትን አካላት ለህግ ለማቅረብ መከላከያ ባካሄደው ዘመቻ እጃቸውን ለመስጠት ፈቃደኛ ያልሆኑትን ሲደመመስ እጃቸውን የሰጡትን ደግሞ ለፍርድ ማቅረብ የቻለ ሲሆን የተወሰኑት ደግሞ በየጥሻው በመደበቅ ጠፉ::
ይህ በእንዲህ እንዳለ የትግራይ ገበሬዎች የእርሻ ወቅቱ ሳያልፋቸው እንዲያርሱ ለማድረግ እና አጠቃላይ ህዝቡም ደግሞ በጥሞና አስቦ ህገወጦችን በራሱ ይዞ እንዲያቀርብ በማሰብ መንግስት ለትግራይ ህዝብ የጥሞና እንዲያገኙ ለማድረግ የተናጥል ተኩስ አቁም አውጆ ክልሉን ጥሎ ወጣ:: ይሁን እና ሽብርተኛው ቡድን ይህን የተናጥል ተኩስ አዋጅ ተጠቅሞ ከስህተቱ ምንም የማይማረው እና የማይጸጸተው ትህነግ አሁንም በአማራ ህዝብ ላይ የማወራርደው ሂሳብ አለኝ፤ ኢትየጵያንም ለማተራመስ እና ለማፍረስ ሲኦል ድረስ እወርዳለሁ ሲል በአፈቀላጤዎቹ ተናገረ:: ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ይረዱኛል ያላቸውን የጥፋት ዘዴዎች በሙሉ ተጠቀመ::
በዚህ ሰዓት ሁሉም ኢትዮጵያዊ ማንም ኢትዮጵያን ሲፈርስ ቆመን ማየት ከአባቶቻችን አልወረስነውም ብለው በወኔ እና በልህ በአንድ ላይ ከጫፍ ጫፍ ተሰባሰቡ:: በዚህ መካከል በሃገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚገኙ የጁንታው ደጋፊዎች እና አንዳንድ ከሆዳቸው ውጭ ነገ የተሻለች ኢትዮጵን ማየት የማይፈልጉ እንዲሁም የጁንታውን ሴራ ያልተረዱ አካላት በተለያዩ መስኮች ጁንታውን ሲደግፉ ታዩ::
ጁንታው ሀገርን ለማፍረስ ከተጠቀመባቸው መንገዶች አንዱ የኢኮኖሚ አሻጥር በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ ነው:: በኢኮኖሚ አሻጥር ውስጥ ደግሞ ህገወጥ የዶላር ዝውውር ፣ ቤትን በባንክ በማሲያዝ እና በመሸጥ ገንዘብ ከሀገር ማሸሽ፣ በአዲስ አበባ ያሉ ቤቶችን በመሸጥ ለጁንታው እኩይ ተግባር ማስፈፀሚያነት ማዋል ወዘተ ይገኙበታል ::
በዚህ ጊዜ የጁንታውን የኩይ ተግባር መንገዶች ቀድሞ የተረዳው መንግስት ህገወጥ የዶላር ዝውውር እንዳኖር ፣ ቤትን በባንክ በመሲያዝ ገንዘብ ከሀገር ማሸሽ እንዳይፈጸም ፣ በአዲስ አበባ ያሉ ቤቶችን በመሸጥ ገንዘብን ለገህወጥ ተግባራት እንዳይውሉ ለማድረግ ዘዴዎችን መዘየዱ አልቀረም:: ከእነዚህ ጋር ተያዞ ከሰሞኑ የአዲስ አበባ አስተዳደር ካቢኔ የመሬትና መሬት ነክ አገልግሎቶችን ላልተወሰነ ጊዜ እንዲታገዱ ውሳኔ አስተላለፈ:: የአዲስ አበባ ካቢኔ ውሳኔ ወቅቱን የጠበቀ ነው:: ምክንያቱም አገር ለማፍረስ እየተንቀሳቀሰ ያለው ጁንታ ግንባር ላይ ከሚደረጉ ጦርነቶች በተጨማሪ ሀገርን ወደ ማትወጣው ችግር ውስጥ ለመክተት የኢኮኖሚ ጦርነት ጀምሯልና ነው::
ከዚህ ውሳኔ ጋር ተያይዞ በአዲስ አባባ በድለላ ስራ የሚኖሩ ሰዎች የዕለት ገቢያቸው የቆመባቸው በመሆኑ ለአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል ለሚመለከተው አካል ጠይቁልን ሲሉ አቤት አሉ:: የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍልም ስለጉዳዩ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኮሙኒኬሽን ቢሮ የተሰጠውን ምላሽ ከከተማ አስተዳደሩ የኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት ድህረ ገጽ ያገኘውን መረጃ በማጣቀስ በአዲስ አበባ ከተማ የድለላ ስራ ለሚተዳደሩ አካላት የሚከተለውን መልስ ይዘን መጥተናል::
ሀገር ችግር ውስጥ ስትሆን ሀገርን እና ህዝብን ከጉዳት እና ከጥፋት ለመከላከል ብዙ ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲየዊ መብቶች በገደብ ውስጥ እንዲያልፉ ይገደዳሉ:: ለምሳሌ የመንቀሳቀስ መብቶች ፣ የሰዓት እላፊ ፣ ወዘተ መብቶች በገደብ ውስጥ ይሆናሉ::
ከዚህ በጋር ተያዞ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ከአርብ ነሐሴ 7 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ለመሬት አስተዳደር ተቋማት፣ ለመሠረተ ልማት ቅንጅት እና ግንባታ ፈቃድ ባለስልጣን እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ ለሚገኙ ለአስራአንዱ ክፍለ ከተሞች ባስተላለፈው ሰርኩላር ፣ የመሬት እና የመሬት ነክ ጉዳዮች ጋር ተያይዞ የሚሰጡ አገልግሎቶችን ሙሉ በሙሉ እንዳይሰጡ ላልተወሰነ ጊዜ ውሳኔ ማስተላለፉን አሳውቋል ።
እንደ የከተማ አስተዳደሩ ኮሙኑኬሽን ገለጻ ካቢኔው እግዱን ያስተላለፈው በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች ትኩረታቸውን በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ባደረጉበት ወቅት አንዳንድ ስግብግብ ግለሰቦች ወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታውን እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም በአቋራጭ ለመክበር በመሬትና መሬት ነክ አገልግሎቶች ላይ ትኩረት በማድረግ በመንቀሳቀስ ላይ መሆናቸውን የከተማ አስተዳደሩ በመገንዘቡ ነው።
በዚህም ምክንያት ማንኛውም መሬትና መሬት ነክ አገልግሎት ላልተወሰነ ጊዜ የታገደ ሲሆን በስድስቱም የመሬት ነክ ተቋማት ፣ በአስራ አንዱም ክፍለ ከተሞች እና የመሠረተ ልማት ቅንጅት እና ግንባታ ፈቃድ ባለስልጣን የመሬት አገልግሎቶችን እንዳይሰጡ ውሳኔ ተላልፏል። ስለዚህም ውሳኔው ወቅታዊና የሴረኞችንም ተግባር መግታት ስለሚያስችል የሚበረታታ ነው::
በተለይም ሀገር ግጭት ውስጥ በሆነችበት ወቅት ከሀገርና ከወገን ጥቅም ይልቅ የራሳቸውን የማይጠረቃ ፍላጎት ለማሳካት የሚጥሩ ግለሰቦች ስለማይጠፉ ለጊዜው የመሬት እግዱ ተገቢነት ላይ ብዙዎች የሚስማሙበት ነው:: በተለይም እንደ አሸባሪው ህወሓት ያሉ መሬት በሸጥና በመለወጥ የካበተ ልምድ ያላቸው ግለሰቦችና ተላላኪዎች ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም የተለመደ ህገወጥ ተግባራትን ለመፈጸም ማኮብኮባቸው የሚቀር አይደለም:: ስለዚህም የአዲስ አበባ አስተዳደር የወሰደው እርምጃ ኃላፊነት የተሞላበትና ለሀገርና ለወገኝ ጥቅም ሲባል የተወሰ ውሳኔ መሆኑን መረዳት ይገባል::
ሙሉቀን ታደገ
አዲስ ዘመን ነሃሴ 14/2013