ዶክተር ጉቱ ቴሶ የምጣኔ ሀብት ባለሙያ ናቸው፡፡ ምዕራብ ወለጋ አይራ ወረዳ አይራ ከተማ ነው የተወለዱት፡፡ ከመጀመሪያ እስከ ሁለተኛ ደረጃ በዚያው አካባቢ ተምረዋል፡፡ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ ነው በምጣኔ ሃብት ትምህርት ዘርፍ ተመርቀዋል፡፡ በሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ እና ሌሎች ዩኒቨርሲቲ በቅንጅት የሚሰጡ ሦስተኛ ዲግሪያቸውንም አጠናቀዋል፡፡ ከሙያቸው ጋር በተያያዘ 16 የጥናት ውጤቶች በዓለም አቀፍ ጆርናሎች ላይ አሳትመዋል፡፡
በአየር ንብረት ለውጥና በምጣኔ ሃብት ላይ የሚፈጥረው ተፅዕኖ፣ በምግብ ዋስትና፣ በገንዘብ ሴክተር፣ ምጣኔ ሀብትና ሥርዓተ ፆታ፣ የገንዘብ ለውጥና ምጣኔ ሀብት፣ የበሽታዎች መከሰትና ምጣኔ ሀብት እና የፖለቲካል ኢኮኖሚ ላይ ጥናት አድርገዋል፡፡ በሥራ ልምዳቸውም በተለያዩ ተቋማት ሠርተዋል፡፡ ወርልድ ቪዥን፣ ሴቭ ዘችልድረን፣ ችልድረን ቢሊቭ በተሰኙ ግብረሰናይ ድርጅቶች ውስጥ አገልግለዋል፡፡ ከኢትዮጵያ ውጭ ደግሞ በኬንያ ወርልድ ቪዥን በተባለ ድርጅት ውስጥ ለስድስት ዓመታት ሠርተዋል። በአሁኑ ወቅት ደግሞ በአውሮፓ ህብረት በኦሮሚያ የአደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን አማካሪ ሆነው በመሥራት ላይ ናቸው።በዛሬው እትም በወቅታዊና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ሃሳባቸውን እንዲሰጡ እንግዳ አድርገናቸዋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በእርስዎ ጥናት ፤ኢትዮጵያ አሳሳቢ ተብለው የተለዩ አደጋዎችና ስጋቶች ምንድን ናቸው?
ዶክተር ጉቱ፡- በኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ የአደጋ ስጋቶች አሉ፡፡ ከክፍለ ዘመን በላይ የዘለቁና አሁንም ድረስ መቋቋም የተሳናት ችግር የመጀመሪያው ድርቅ ነው፡፡ ድርቅ በኢትዮጵያ ውስጥ ከክርስቶስ ልደት በፊት የነበረና እስካሁንም የሚስተዋል ነው፡፡ ሰፋ ያለና ኢትዮጵያን እየጎዳ ነው፡፡ ድርቅ ምስራቅ ኢትዮጵያ፣ ሰሜን ምሥራቅ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ኢትዮጵያ ትልቅ ጉዳት እያደረሰ ነው፡፡ ከድርቅ ቀጥሎ በትልቁ የሚነሳው ሰው ሰራሽ ሲሆን ይህም ችግር ግጭት ነው፡፡ ጦርነት ያልተለያት ሀገር ናት፡፡ ከኤርትራ፣ ሶማሊያ ጋር ጦርነት ላይ ነበርን፡፡ በተለያየ ጊዜ መጠነ ሰፊ ጦርነቶችና መፈናቀሎችን ያስከተሉ ጦርነቶችና ግጭቶች ነበሩ፡፡
በቅርብ ጊዜ እየተለመደ የመጣው ደግሞ ጎርፍ ነው፡፡ ጎርፍ የማያጠቃቸው የነበሩ አካባቢዎች በጣም እየተጠቁ ነው፡፡ ከዚህም በመቀጠል ደግሞ ወረርሽኝ በስፋት እየተከተለ ነው፡፡ በቅርብ ጊዜ ደግሞ የበረሃ አንበጣ አስቸጋሪ ሆኗል፡፡ በተለይ ከአምስት ዓመት ወዲህ ሁኔታዎች ተባብሰዋል፡፡ ባለፈው ዓመት ብቻ ስድስት ክልሎች በአንበጣ መንጋ ተጠቅተዋል፤ ከፍተኛ ምርት ወድሟል፡፡ ከእነዚህ በተጨማሪ የመሬት መንሸራተት፣ መሬት መንቀጥቀጥ አደጋ እያደረሰ ነው፡፡ ሀገሪቱ ከዓመት ወደ ዓመት የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አደጋዎች እየተበራከቱባት መጥተዋል፡፡ ይህ ደግሞ በሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት ላይ የራሱን አሉታዊ ሚና እያሳደረ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከአደጋዎች አንዱ ጦርነት ነው። ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ጦርነት የሚገጥማት ለምንድን ነው?
ዶክተር ጉቱ፡- በየዘመናት የተለያዩ መንስዔዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ እንደ ሀገር የገጠምናቸው ከኢጣሊያን፣ ሶማሊያ እና ኤርትራ ጋር ያደረግናቸው ጦርነቶች ከግዛት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ብዙ መስዕዋት እና ጊዜም አስከፍሎናል፡፡ ይህ የሉዓላዊነት ጉዳይ ስለነበር ብዙ ጦርነት አካሂደናል፡፡ ግን በእነዚህ ጦርነቶች የሚሠራው ሰው ኃይል ያጣንበትና ከፍተኛ ንብረት የወደመበት እና ሀገሪቱን ምጣኔ ሀብት ጉዳቱ ከፍ ያለበት መሆኑ ይታወቃል፡፡ ከዚህ በመቀጠል ደግሞ አልሽባብን ለመዋጋት ወደ ሶማሊያ ለመዝመት ተገደናል፡፡ የኢትዮጵያ ሠራዊትም በእዚህ ሀገር ብዙ ጊዜ እንዲቆይ አስገድዷል፡፡ ከዚህ በመለስ ላለፉት 30 ዓመታት በክልሎች በአስተዳደራዊ ወሠን የተነሳ በርካታ ግጭቶች ሲስተዋሉ ነበር፡፡ በተለይም አርብቶ አደሮች ባሉበት አካባቢ በግጦሽ መሬትና በውሃ ሲጋጩ ነበር፡፡ በዚህም ሀገሪቱ ግጭት የማይለያት ሀገር ተደርጋ እንድትሳል አድርጓታል፡፡ ግጭቶች እንዲበራከቱ ያደረገው ደግሞ በኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ በጣም ባለመበልፀጉ፣ የአብዛኛውና ዋነኛው የኑሮ መሰረቱ የተመሰረተው መሬትና መሬት ነክ ስለሆነ እና አርብቶ አደርነት ስለሆነ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅትም በትግራይ ክልል ጦርነት አለ፡፡ ይህ ምጣኔ ሀብት ላይ የሚኖረው ተጽዕኖ ምንድን ነው?
ዶክተር ጉቱ፡- ኢትዮጵያ ብዙ ጦርነት አካሂዳለች፡፡ በታሪክ ውስጥ በጣም አውዳሚ የሚባለው ጦርነት ግን በሰሜን ኢትዮጵያ የተካሄደው ነው፡፡ ይህን በብዙ መልኩ መግለፅ ይቻላል፡፡ ያለፉት ጦርነቶች ከሌሎች ሀገራት ጋር ያደረግነው ነው። አሁን የሚካሄደው ጦርነት የምንጠቀመው የጦር መሳሪያ በሙሉ የኢትዮጵያ፣ የሚሞተው ኢትዮጵያዊ፣ የሚወድመው የጦር መሣሪያ ሁሉ የኢትዮጵያ ነው። አሸባሪው ህወሓትም ሆነ የሀገር መከላከያ ሰራዊት የሚጠቀሙት መሣሪያ በኢትዮጵያ አንጡራ ሀብት የተገዙና የዘመኑ ቴክኖሎጂ የወለዳቸው ናቸው፡፡ ሌሎች ጦርነቶች ድንበር ላይ የተካሄዱ ሲሆን በአሁኑ ወቅት የሚካሄደው ግን በሀገሪቱ ግዛት ውስጥ ነው፡፡ በዚህም ፋብሪካዎች፣ መሠረተ ልማቶች፣ አገልግሎት መስጫ መስመሮች እና ተቋማት ወድመዋል፡፡
ትግራይን ከጦርነቱ በፊት ወደነበረችበት ቦታ ለመመለስ በእርግጠኝት 15 ዓመታት ይወስዳል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እንደገለጹት ትግራይ ክልልን ለመደጎም 100 ቢሊዮን ብር ወጪ ተደርጓል፡፡ ግን የወደመው የጦር መሳሪያ እና ሌሎች ሲደማመሩ እጅግ ከፍተኛ ሀብት ነው፡፡ ከእርሻ ውጭ የሆነው የእርሻ መሬት፣ መጠጥ ውሃ፣ ድልድዮች፣ የአየርና የየብስ ጉዞ፣ የተዘረፉ ንብረቶች፣ የተጎዱ ተሽከርካሪዎች የተቋረጡ አገልግሎቶችና የመሳሰሉት ላይ የደረሰው ውድመት በትንሹ የኢትዮጵያ 10 ዓመት በጀት ወድሟል፡፡
በነገራችን ላይ ኢትዮጵያ ላይ ለዘመናት ኢንቨትመንት ሲካሄድ የነበረው ትግራይ አካባቢ ነው። የኢትዮጵያ የንግድ ሥርዓትና ድርሻ ትልቁን ድርሻ የያዙት አሸባሪው ህወሓት እና ከእነርሱ ጋር ተያያዥ የሆኑ ድርጅቶች ናቸው፡፡ በፋብሪካ፣ አስመጪና ላኪ ሲታይ እንኳን የሀገሪቱን እስከ 60 በላይ ከመቶ የያዙ ነበሩ፡፡ ለምሳሌ ኤፈርትን ብንመለከት እ.ኤ.አ እስከ በ2017 ብቻ ካፒታል ኢንዶውመንታቸው አራት ቢሊዮን ዶላር ነበር፡፡ ግዙፍና የአንበሳውን ድርሻ የያዙት ኢንዱስትሪዎችም ከአሸባሪው ህወሓት ወይንም ለሥርዓቱ የቀረበ ቁርኝት ካላቸው ባለሀብቶች ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ይህን ያክል ሃብት በአንድ ክልልና ቡድን እጅ ከተከማቸ በሀገሪቱ ውስጥ ግዙፍ የኢኮኖሚ አሻጥር ሲሠራ ነበር ማለት ነው?
ዶክተር ጉቱ፡- የኢኮኖሚ አሻጥር ሁሉም ቦታ አለ፤ አሁንም አለ፡፡ የኢኮኖሚ አሻጥር ያልነበረበት ሥርዓት የለም፡፡ ሙስና እና ኪራይ ሰብሳቢነት አለ።በአጼ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግስት ከባድ የኢኮኖሚ አሻጥር ነበር፡፡ በንጉሱ ዙሪያ ብቻ የሚኖሩት ብቻ ተጠቃሚ ነበሩ፡፡ በደርግ ዘመንም ኢኮኖሚ አሻጥር ነበር፡፡ በዘመነ ሕወሓትም በጣም ትልቅ ነበር፡፡ በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ሀብት ከዚህ ሀገር አሸሽተዋል፡፡ በኢትዮጵያ ሥም የመጡ ብድሮች ኢትዮጵያን ምድር ሳይረግጥ ወደ ውጭ ሄዷል፡፡ ዛሬ በዓለም ዙሪያ ያሉና የአሸባሪው ህወሓት አቀንቃኞችና ደጋፊዎች የሚንቀሳቀሱት ሲሠራ በነበረው አሻጥር ነው፡፡ በጥቅም እና በዝምድና የተሳሰሩ ባለሀብቶችም አሉ፡፡
የሀገራችን ትልቅ አስመጪና ላኪዎች ከእነዚህ ድርጅቶች ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ ዘይት፣ ብረት፣ ሲሚንቶ፣ የኢንዱስትሪ ግብዓቶችን አስመጪዎች እነርሱ ነበሩ፡፡ በ30 ዓመት ብዙ ነገር ሠርተዋል። ከሁሉም በላይ ደግሞ ከፍተኛ የሆነ ሰብዓዊ ቀውስ ተከስቷል፡፡ በጦርነቱ የመጣው ቀውስ በኢትዮጵያ ታሪክ ተከስቶ አያውቅም፡፡ አሁን ሀገሪቱ የመሸከም አቅም ስለፈጠረች እንጂ በጣም ከባድ የምጣኔ ሀብት ቀውስ ተከስቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ቢዝነስና ኢንቨስትመንት ለመስራት አስቸጋሪ ሆኗል፡፡ በሀገሪቱ ያለው ሁኔታና ኢኮኖሚ የተሳሰረ ነው፡፡ በአንድ ቦታ የሚመረተው ሌላ ቦታ ነው የሚሸጠው፡፡ የእነዚህ ሰዎች ኢንቨስትመንት በአንድ ቦታ ብቻ የተመሰረተ አይደለም፡፡ በመሆኑም ተፅዕኖው በዚያው ልክ ነው፡፡ ቢዝነስ ለመስራትም ሠላም ያስፈልጋል። በጦርነቱ የተነሳ ኢንቨስትመንት ተቀዛቅዟል፡፡ የውጭ ባለሀብቶችን ለመሳብም አስቸጋሪ ነው፡፡ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎችም ስለ ኢትዮጵያ እያራገቡ ያሉት ባለሀብቱን የሚያርበቀው ነው፡፡ በብዙ መንገድ ኢኮኖሚ እንዲቀዛቀዝ አድርጓል፡፡
አዲስ ዘመን፡- አሸባሪው ህወሓት ሀገር ሲመራ ስለነበር ይህ ሁሉ ችግር እንደሚከሠት ይገነዛባል ብዬ አስባለሁ፡፡ ታዲያ ጦርነትን እንደ ቀዳሚ መፍትሄ አንግቦ የተነሳው ለምንድን ነው?
ዶክተር ጉቱ፡- ጦርነትን ለምን ብቸኛ አማራጭ አደረገ ለሚለው ‹‹በኢትዮጵያ ውስጥ ያለጦርነት አማራጭ የለም የሚል አስተሳሳብ ነግሷል፤ ይህንን በመርህ ደረጃ መቀበል አለብን›› አጼ ኃይለስላሴና ደርግ ከስልጣን የወረዱት በአመፅና እልቂት ነው፡፡ ኢህአዴግም በአመጽ ነው፡፡ ስለዚህ በጦርነት የመጣ ሁሉ በጦርነት ነው የሚያስበው፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ በጦርነት ስልጣን ይዞ በሠላም የወረደ መንግስት የለም፡፡ በአፍሪካም የለም፡፡ ውስን የሆኑ ሀገራት ብቻ ለዴሞክራሲ መስዕዋትነት ከፍለዋል፡፡ አሸባሪው ህወሓት በጦርነት መጥቶ በጦርነት ነው የወረደው። ወደ ስልጣን ለመመለስም ጦርነት ነው የመረጠው። 30 ዓመት ሙሉ ሠላም አልለመደም፡፡ አሸባሪው ህወሓት እና የትግራይን ሕዝብ ለይቶ ማየት ይገባል። አሸባሪውን ህወሓት የመሰለ 17 ዓመት ሙሉ ጫካ የነበረ ቡድን አማራጩ ጦርነት ነው፡፡ ከጦርነት ውጭ ማሰብ አያውቅም፡፡ ቢሆን ኖሮ ኢትዮጵያ የምታሸንፍበት ዕድል ነበር፡፡ በሰጥቶ መቀበል መርህ ኢትዮጵያን ወደ ጥሩ ሁኔታ ማሸጋገር ይችሉ ነበር፡፡ ነገር ግን ተወልደው ያደጉትና የተጠመቁት፣ ልምዳቸው፣ የተማሩትና የተመረቁበት፤ የሚበሉትም ሆነ የሚጠጡት ጦርነትና ግጭት ብቻ ስለሆነ ከዚህ ውጭ ማሰብ የሚችል አዕምሮ የላቸውም፡፡ በኢትዮጵያ ደረጃ ግን ይቻል ነበር፡፡
የህዝብ አመጽ መጥቶ በቃኝ ሲል ህዝብ የሚፈልገው ነገር አለ ማለት ነው፡፡ አንድ ቡድን 27 ዓመት ስልጣን ላይ ከቆየ በቂ ነው፡፡ ያን ሁሉ ለታገሰ ህዝብ ወደ ትግራይ የሄዱትም ሆኑ እዚህ ያሉትን ጨምሮ ቢወያዩ ለኢትዮጵያ ይበጅ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ወደ ዴሞክራሲ ለማሸጋገርና የተስፋ ጮራ ወጥቶ የነበረው ባለፉት ሦስት ዓመታት የምትሸጋገርበትን ዕድል አጨልመዋል፡፡ ህዝቡም ዕድሉን ሰጥቶ ነበር። ወደ ጦርነቱ የገቡት ህወሓት በጣም የገዘፈ ምስል ለራሱ ሰጥቶ ነው፡፡ በዚህም በኩል ችግር ነበር፡፡ ህወሓት ከጦርነት ውጭ ሌላ ማሠብ አይችልም፡፡
አዲስ ዘመን፡- አሁን ባለው ጦርነት የኢትዮጵያ ውስጣዊ ጉዳይ ሆኖ ኃያላን ሀገራት
ጭምር ትልቅ ትኩረት የሰጡት ለምንድን ነው ?
ዶክተር ጉቱ፡- ኢትዮጵውያ ማሰብ ያለብን አንድ መሰረታዊ ነገር አለ፡፡ ውስጣዊ ነገሮቻችንን ውስጣዊ ብቻ አድርጎ ማሰብ አይገባም፡፡ ዓለም አቀፋዊ ይሆናል፡፡ ጋና ውስጥ የሚከሰት ዓለም አቀፋዊ መሆኑ ቀርቶ ቀጣናዊ ላይሆን ይችላል። በአሁኑ ወቅት በጦርነት ውስጥ ያሉ ሀገራት አሉ፡፡ ኮንጎ ሠላም አግኝታ አታውቅም፡፡ ናይጄሪያ ችግር አለ። በምዕራብ አፍሪካ ብዙ ችግሮች አሉ፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያ በጂኦ ፖለቲክሱ ስትራቴጂክ ሀገር ናት፡፡ ጎረቤት ካሉ ሀገራት ጋር ይያያዛል፡፡ ለሰሜኑና ለደቡብ ወሳኝ ቦታ ላይ ነች፡፡
ኢትዮጵያ መገኛዋ ለአሜሪካ፣ አውስትራሊያ፣ አውሮፓ፣ ለምስራቁ ዓለም፣ ለዓረቡ ዓለም ሆነ ለአፍሪካ በጣም ወሳኝ ናት፡፡ የብዙ ፍላጎቶች ትኩረታቸው ኢትዮጵያ ናት፡፡ በአህጉሩ በህዝብ ብዛት ሁለተኛ ናት፡፡ ኦሮሞ ኬንያ አለ፣ አፋር ጅቡቲ አለ፤ ጋምቤላው ደቡብ ሱዳን ውስጥ አለ፤ ሶማሌው ሞቃዲሾ አለ፤ ትግሬው ኤርትራ አለ፡፡ በዚህ ቀጣናዊ ትርጉሙ ከፍ ያለ ነው፡፡ እዚህ የሚከሰተው ነገር የቀጣናው ሀገራት በሙሉ ይነካል፡፡
ሱዳን እና ግብጽ ኢትዮጵያ ላይ ጥገኛ ናቸው፡፡ ኬንያ ተፈጥሮ ሀብት ማልማት ስትፈልግ ከኢትዮጵያ የሚመነጭ ሀብት ነው የምትጠቀመው፡፡ የምዕራብ እና ምስራቁ ዓለም የፍላጎት ማቋረጫ መስመር ናት። ወደ አፍሪካ ለመግባት መግቢያ በር ኢትዮጵያ ናት። ኃያላን ሀገራት ትኩረታቸው ኢትዮጵያ የሆነው ለዚህ ነው፡፡ ይህ ጦርነት እንኳ ትልልቅ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ዋንኛ ሥራ አድርገው ነው ያራገቡት። በመሆኑም የኢትዮጵያ ነገር ዓለም አቀፋዊ ቅርጽ እንደሚይዝ ኢትዮጵያውያን መገንዘብ አለባቸው። የትኛውም ወደ ፖለቲካው ሜዳ የሚገባ አካል ይህን ከግምት ውስጥ አስገብቶ መሆን አለበት፡፡ በዚህም የተነሳ ጫና መፍጠር የሚፈልጉ አሉ፡፡ ይህን የሚያደርጉት ደግሞ ትግራይ ውስጥ በተከሰተው ነገር ኢትዮጵያን ማጣት ስለማይፈልጉ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከጦርነቱ በተጨማሪ የኑሮ ጫና እየበዛ ነው፤ የኑሮ ውድነቱ ኢኮኖሚያዊ ምክንያት አለው?
ዶክተር ጉቱ፡- መሠረታዊ የሆነ የምጣኔ ሀብት ምክንያት አለው፡፡ በሳይንሱ መሠረት የገበያ ዋጋን የሚወስነው ፍላጎትና አቅርቦት ነው፡፡ ፍላጎት ከአቅርቦት እየገዘፈ ከሄደ ዋጋ ይጨምራል፡፡ ለአንድ ሰው የሚቀርበው ለአንድ ሺህ ሰው ለማቅረብ ስታስብ ዋጋ ይጨምራል፡፡ ባለፈው ዓመት የነበረው ምርታችን በበረሃ አንበጣ ተጎድቷል፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች ፋብሪካዎች ተዘግተዋል፡፡
በኢትዮጵያ ትርፍ አምራች የነበሩ አካባቢዎች ግጭቶች ስለነበሩ ግብርና በሥርዓት አልተመረተም። ምርት ከነክምሩ በእሳት ሲቃጠል ነበር፡፡ የእንስሳት ምርትም በብዛት በሚገኝበት አካባቢ ግጭቶች ነበሩ። ሠላምና መረጋጋት ባለመኖሩ ገበያው ላይ ችግር ፈጥሯል፡፡ ለከተሞች የፍጆታ ዕቃ ይመጣ የነበረው ከውጭ ነበር፡፡ የዶላር ምንዛሪ በጣም እየጨመረ ነው። የዶላር ከፍተኛ አቅራቢ ደግሞ ጥቁር ገበያ እየሆነ ነው። ለዚህ ባንኮችም ተባባሪ ናቸው፡፡ ነዳጅ፣ መድሃኒት፣ ዘይት ሁሉን ነገር ወደ ሀገር የምናስገባው በዶላር ነው፡፡ የኢንዱስትሪ ግብዓቶች በብዛት የምናስገባው በዶላር ነው፡፡ ነዳጅ የማይነካካው የምጣኔ ሀብት መስመር የለም፡፡ በዓለም አቀፍ ገበያው ላይ ነዳጅ ዋጋ እየጨመረ ነው፡፡ በመሆኑም የኑሮ ውድነቱ ምጣኔ ሀብታዊ ምክንያት አለው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ምጣኔ ሀብታዊ ምክንያት ቢኖረው እንኳን የንግዱ ማህበረሰብ ጤናማ ንግድ ውስጥ ነው ማለት ይቻላል?
ዶክተር ጉቱ፡- ‹‹የዚህ ሀገር ነጋዴ እኮ አብዛኛው ሌባ ነው›› አጋጣሚውን ፈልጎ ሚሊየነር የሚሆን ነጋዴ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ ከተወሰነ የሠራተኛ ጉልበትና ትራንስፖርት ዋጋ ውጪ ጨው የሚመረተው በኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኝ ግብዓት ነው፡፡ እ.ኤ.አ 2018 አንድ ኪሎ ጨው ሦስት ብር ነበር፡፡ አሁን 500 በመቶ ጨምሯል፡፡ አብዛኞቹ ነጋዴዎች በአቋራጭ ለመክበር ስለሚፈልጉ እነርሱ እጃቸው የለበትም ማለት አይቻልም፡፡ ጤናማ የሆነ የዋጋ ጭማሪ አይደለም፡፡ አቅርቦት እያለ ማንም ማስረዳት በማይችልበት ሁኔታ ዋጋ ይጨምራሉ፡፡ አንዳንዱን ነገር ለመግለጽም አስቸጋሪ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ምርት እያለ ነጋዴ ዋጋ ከጨመረ የኢኮኖሚ አሻጥር እየተከናወነ ስለመሆኑ ማሳያ አይደል?
ዶክተር ጉቱ፡- እያልን ያለነው ምጣኔ ሀብታዊ ምክንያት የለውም የሚባለው ነገር ውሸት ነው፡፡ ለአንድ ነጋዴ በአቋራጭ መበልፀግ ምጣኔ ሀብት ነው እኮ፤ ሸፍጥ ቢሆንም፡፡ ትርፋማነትን ከሚፈለገው በላይ ማሰብ ምጣኔ ሀብታዊ ነው፡፡ ግን አስተሳሰቡና አካሄዱ ጤናማ አይደለም፡፡ አንዳንዶቹ ነገሮች ፖለቲካዊ እና ማህበራዊም ናቸው፡፡ አንዳንድ ነገሮች ለማስረዳት አስቸጋሪ ናቸው፡፡ ግን የምጣኔ ሀብታዊ ምክንያት የለውም ማለት ጤናማነት አይደለም፡፡ ጥቅማቸውና ፖለቲካዊ ስልጣናቸው ስለተነካ የሚረብሹትም እኮ ተከትሎ የሚመጣ ነው፡፡ የአንበሳውን ድርሻ የሚይዘው ምጣኔ ሀብታዊ ምክንያት ነው፡፡ ምጣኔ ሀብታዊ ምክንያት አይደለም ስንል ለኢንቨስተር፣ አምራች፣ ባለሀብቱንና ነጋዴውን የምናስተላልፈውን መልዕክት ማሰብ አለብን፡፡ ከጤናማ አስተሳሰብና አሰራር ዘዴ ወጥቶ እንዲያስብ ነው የምናደርገው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በጦርነት ወቅት ከሚከሰት የኢኮኖሚ መላሸቅ ለመውጣት ምን መደረግ አለበት?
ዶክተር ጉቱ፡- አሁን ለገባንበት መልከ ብዙ ችግር ዋነኛው ምክንያት ግጭት ውስጥ መግባታችንና ሰላምና መረጋጋት መጥፋቱ ነው፡፡ ብዙ የሀገሪቱ አካባቢ ችግሮች ይስተዋላሉ፡፡ ስለዚህ ይህ ጤናማ ካልሆነ አንዱ የቢዝነስ እንቅስቃሴ ማድረግ አስቸጋሪ ነው፡፡ የኢንቨስትመንት አንዱ አመላካችና አስቻይ መንገድ ሠላምና መረጋጋት ነው፡፡ በመሆኑም ከተቻለ የተከፈለው ዋጋ ተከፍሎ ሀገሪቱ ወደ መረጋጋት መመለስ አለባት፡፡ ከዚህ ውጪ የትኛውም የኢኮኖሚ ቲዎሪ አይሠራም፡፡ መንግስት ትልቁን ድርሻ መውሰድ አለበት፡፡ በዚህ ላይ የተሳተፉ አካላትም እንዴት ወደ ሠላም መምጣት አለባቸው የሚለው ላይ ማሠብ አለባቸው፡፡ አንዱ አካል ብቻ ሠላም ስለፈለገ አይሆንም ፤ሁሉም ተዋናይ መስማማት አለባቸው፡፡
ሌላው ባለሀብቶች ሀገር እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ስትገባ ምን ዓይነት ቢዝነስ እና እንዴት መስራት እንዳለባቸው ማሰብ አለባቸው፡፡ ነገር ግን ሀገሪቱ ስትረጋጋ እሠራለሁ የሚሉ ከሆነ ሀገሪቱ መቼ እንደምትረጋጋ መተንበይ አስቸጋሪ ነው፡፡ በእንዲህ ዓይነት አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንዴት ሰርቼ ምጣኔ ሀብቱን ማረጋጋት እችላለሁ ብሎ ማሰብ አለበት። በአሁኑ ወቅት እኮ ሰው ጋዛ፣ ኮንጎ፣ ሶሪያ ላይ ቢዝነስ ይሰራል፡፡ ቀውሱ እንዳይመጣ የበኩሉን ድርሻ መወጣት አለበት፡፡ ነጋዴ፣ ባለሀብቶችና አርሶ አደሮች ምጣኔ ሀብቱ ላይ መሥራት አለባቸው፡፡ በተለያ ዘርፎች ላይ የሚሠሩ ዓለም አቀፍ እውቀትና ልምድ ያላቸው ምሁራን አሉ፡፡ እነርሱም ምጣኔ ሀብቱ እንዴት መያዝ አለበት በሚለው ላይ በትጋት ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል፡፡
ባለሙያ ቴሌቪዥን ላይ የሚያወራ ብቻ ሳይሆን ጦር ሜዳ እንደገባ ሰው አስቦ ወደ ተግባር ገብቶ መሥራት አለበት፡፡ እውቀት፣ ትምህርት፣ ክህሎትና ቴክኖሎጂን ማጣመር ይገባል፡፡ የተማርነው ትምህርት እንዴት በጦርነት ወቅት ኢኮኖሚን መታደግ ይቻላል የሚለው ላይ መሥራት አለባቸው፡፡ የድርሻዬን እንዴት ተወጥቼ ሀገሬን መታደግ እችላለሁ ብሎ ደጋግሞ ማጤንና ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ የኢኮኖሚ ቀውስ እንዳይከሰት ምን መደረግ አለበት በሚለው ላይ በትጋት መሥራት አስፈላጊ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ ስትከተለው የነበረው የምጣኔ ሀብት ፖሊሲ በሀገራችን እድገትና አሁናዊ ችግር ሚና አልነበረውም?
ዶክተር ጉቱ፡- ምጣኔ ሀብቱን ከሚጎዱት አንዱ ጦርነት ነው፡፡ ሌላው የተፈጥሮ አደጋዎችንም አንስተናል፡፡ ለአብነት አንበጣ፣ ጎርፍ የመሳሰሉትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ምጣኔ ሀብቱን ፈተና ውስጥ ካስገቡት ሌላኛው የመጣንበት የምጣኔ ሀብት ፖሊሲና ስትራቴጂ ነው፡፡ በእያንዳንዱ ሥርዓት ውስጥ ያለው ንግድ ሲታሰብ መንግስታዊ ጥገኝነት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ በአጼ ኃይለስሴ ዘመን የነበረው የመንግስት እርሻ እና ባለሀብት የደርግ ሥርዓት ሲመጣ ሙሉ ለሙሉ ነው የቆመው፡፡ በደርግ ዘመን የነበረው ደግሞ በተመሳሳይ ዕጣ ፋንታ ገጥሞታል፡፡ በዚህ ዘመን የነበሩ ባለሀብቶችም ኢህአዴግ ሲገባ ተመሳሳይ እጣ ገጠማቸው፡፡
እዚህ ሀገር ያለው ባለሀብት፣ የንግድ ሥርዓትና ኢንቨስትመንት የፖለቲካ ጥገኛ ነው፡፡ የባለሀብት ሚና እና ፖለቲካ መለያየት አለበት፡፡ ምጣኔ ሀብቱን የሚመራውና የፓርቲ የንግድ ተቋማት የተባሉት ሁሉ ፓርቲ ሲጠፋ አብረው ነው የሚጠፉት፡፡ በዚህ ላይ መስራት ይገባል፡፡ ከፖለቲካ ጥገኝነት ወጥተው በምጣኔ ሀብት ፖሊሲ መመራት አለባቸው፡፡ በተለየ ሁኔታ ለእነዚህ ብቻ ዶላርና ድጎማ እየቀረበና አመቺ ሁኔታ እየፈጠሩ መሄድ አደገኛ ነው፡፡ ወንዙ ውስጥ ገብተው መከራውን ሁሉ ቢለማመዱና ፈተናውን ሁሉ መቋቋም ቢማሩ የትኛውም ሥርዓት ቢመጣ በጥንካሬ ተቋቁመው ማለፍ ያስችላቸዋል፡፡
ልማታዊ መንግስት ሃሳቡ መጥፎ አልነበረም። ግን ልማታዊ መንግስት ማለት መንግስት ባለሀብት ይሆናል ማለት አልነበረም፡፡ ሆኖም ሥራ ላይ ሲውል ዋናው ባለስልጣን፣ ዋናው ኤታማዦር ሹሙ እና ከፍተኛ አመራር ነው ባለፋብሪካ እና ነጋዴ የሆነው። ልማታዊ ባለሀብት አስተሳሰቡ ይህ አልነበረም፡፡ ቢሮ ውስጥ ቁጭ ብሎ ነፃ ገበያ ብሎ ፖሊሲ የነደፈው ራሱ ነጋዴ ሆነ፡፡ በመሆኑም የንግድና ቢዝነስ ተቋማት ገለልተኛ መሆን አለባቸው፡፡ ባለሀብቱ የፖሊሲና ስትራቴጂ ጥገኛ እንጂ የፖለቲካ ወይንም የአንድ ፓርቲ ጥገኛ መሆን የለበትም፡፡ ለዚህ ነው የዳበረ የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ በውድድር ላይ የተመሰረተ ሜዳ ስለሌለ ፖለቲካ በተረበሸ ቁጥር ምጣኔ ሀብቱ የሚረበሸው፡፡ ምጣኔ ሀብት በራሱ ርዕዮተ ዓለም መመራት አለበት፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ምጣኔ ሀብት ዋና አጀንዳ ሆኖ አያውቅም፡፡ በንጉሱ ዘመን፣ በደርግም ሆነ በኢህአዴግ ዘመን ምጣኔ ሀብት ዋና አጀንዳ ሆኖ አያውቅም፡፡ ያለፉት ሥርዓቶች ዋና አጀንዳና ግባቸው ፖለቲካና ስልጣን የማመቻቸት ነው፡፡ እንዴት ስልጣን ላይ እንደሚቆዩ ነው ሲያስቡ የነበሩት፡፡ ፖለቲካው ያለ ምጣኔ ሀብት አይሳካም፡፡ አሜሪካ እና አውሮፓም ኢኮኖሚ ቀዳሚ አጀንዳ ነው፡፡ በኢትዮጵያም የኢኮኖሚ ጎል ቀዳሚ መሆን አለበት፡፡
አዲስ ዘመን፡- የተፈጥሮ አደጋዎች ለሀገሪቱ ምን ያህል ፈተና ሆኗል?
ዶክተር ጉቱ፡- ድርቅ ኢትዮጵያ ውስጥ መከሠት የጀመረው ከክርስቶስ ልደት በፊት ነው፡፡ እስካሁን ድርቅ የምናሸንፍበት መንገድ አልተማርንም፡፡ ድርቅ ግብጽና ሱዳን አለ፡፡ ግን ግብጽ በርሃብ የእርዳታ እህል ሲሠራጭ አናስተውልም፡፡ በተለይ መካከለኛው ምሥራቅ ዝናብ የማይዘንብባቸው ሀገራት አሉ። ድርቅ ችግር አይደለም፡፡ ድርቅ የምንቋቋምበት አቅም አለማጎልበትና በዚህ ዋና ዓላማ አድርገን አለመስራታችን ነው፡፡ ተፈጥሮ ክስተቶችን እንዴት እናሸንፍ የሚለው ዋና አጀንዳ ሆኖ አያውቅም፡፡ ጎርፍም ችግር አይደለም፡፡ ጎርፍ ከመምውጣቱ በፊት ቀድሞ ዝግጅት ከተደረገ መፍትሄው በጣም ቀላል ነው፡፡ ጎርፍ ተፈጥሯዊ ነው፡፡ እነዚህ በራሳቸው ችግር አይደሉም፡፡ የአንበጣ መንጋም ችግር አይደለም፡፡ አንበጣው ሲፈለፈል ገና በጅምሩ ማጥፋት ይቻላል። ለሁሉም ነገር ቀድሞ መዘጋጀት አለመቻል ነው፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ የሚስተዋሉ የተፈጥሮ አደጋዎች ከሌሎች ሀገራት አኳያ ሲታዩ ችግር የሚያደርሱ አይደሉም፡፡ በጣም አነስተኛ ናቸው፡፡ ኤዥያ ፓስፊክ፣ ፍሊፒንስ ብንመለከት በጣም ፈተና ውስጥ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ጎርፍ ቴክኖሎጂ ሳንጠቀም በባህላዊ መንገድ ማስቆም ይቻላል፡፡ ይህን አደጋ መከላከል፣ ከአቅም በላይ ከሆነ ደግሞ ተፅዕኖን መቋቋም፤ ይህም ካልሆነ ደግሞ መላመድ ይቻላል። ከችግሩ ጋር የተዛመደ አኗኗርና ንግድና ሥርዓት መዘርጋት ይገባል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የመጠጥ ውሃ ተደራሽነት አለ፡፡ ይህን ጎርፍ በመገደብ ወደ ጥሩ አጋጣሚ መቀየር ይቻላል፡፡ በመሆኑም እነዚህን ወደ መልካም አጋጣሚ በመቀየር መጠቀም ይቻላል፡፡ ይህን ግን ዋና አጀንዳ አድርጎ መንቀሳቀስ ይቻላል፡፡ ከፍተኛ የሆነ ሙቀትን ደግሞ ወደ ኤሌክትሪክ ሃይል መቀየር እንችላለን፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ አመሠግናለሁ። ተጨማሪ ሃሳብ ካለ ማከል ይችላሉ፡፡
ዶክተር ጉቱ፡- እኔም አመሠግናለሁ፡፡ ለመላው ኢትዮጵያ ህዝብ የምንናገረው ኢትዮጵያ ትልቅ ሀገር፤ ትልቅ ሀብት ያላት መሆኑን መዘንጋት የለብንም፡፡ አሁን ካለው ህዝብ በሦስት እጥፍ ቢጨምር እንኳን በቂ ሀብት አለን፡፡ የምንጣላው በትንሽ ነገር ነው፡፡ በመሬት ውስጥ ያለን ሀብት ኢትዮጵያን ወደ ስልጣኔ ማማ የሚወስድ ነው፡፡ ይህን እንዴት አድርገን እንጠቀም የሚለው ላይ ማሰብና መስራት ይገባል። ስልጣን ላይ ያለው ፖለቲከኛ ስልጣን ላይ መሞት ይፈልጋል፡፡ ግን ስልጣኔን እንዴት አድርጌ ለሀገሪቱ የዳበረ ፖለቲካና የምጣኔ ሀብት እድገት ላውል ብሎ ማሰብ ይጠበቅባቸዋል፡፡ አሁን ያለው ጦርነት በአጭር ጊዜ ተደምድሞ የተራበውን የምናበላበት፤ ሥራ አጥ ወደ ሥራ የሚመለስበት ላይ ብናተኩር የተሻለ ነው። እያንዳንዱ ዜጋ ከራሱ አልፎ እዚህ ሀገር ላለው 110 ሚሊዮን ህዝብ ማሠብ አለበት፡፡ የሰው ልጅ ዕድሜ አጭር ነው፡፡ ለዚህች አጭር እድሜ ብሎ የመጪው ትውልድ ተስፋ ማጨለም የለበትም፡፡ ምሁራን፣ ፖለቲከኞች እና የሃይማኖት አባቶችም በዚህ ላይ ትኩረት ማድረግ አለባቸው፡፡
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ነሐሴ 13 ቀን 2013 ዓ.ም