ሕይወት በብዙ ውጣ ውረዶች የተሞላች በመሆኗ ብዙዎች ሲወጡ ሲወርዱ፤ ሲወድቁና ሲነሱ፤ መመልከት የተለመደ ነው፡፡ ታዲያ ይነስም ይብዛ ሰው ሁሉ በህይወት ሲኖር የህይወትን ውጣ ውረድ ሳያጣጥምና ሳይፈተን ያለፈ አይኖርም ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡
ቁም ነገሩ ሰዎች የገጠማቸውን የሕይወት መሰናክል የሚቀበሉበትና መፍትሔ የሚያበጁበት መንገድ ነው፡፡ በሕይወት እሽክርክሪት ውስጥም ብዙዎች የገጠሟቸውን መሰናክሎች አልፈው ከወደቁበት የተነሱ እንዳሉ ሁሉ በተቃራኒው ደግሞ ለገጠማቸው መሰናክልና የሕይወት ውጣ ውረድ እጅ ሰጥተው ወድቀው የቀሩም ብዙዎች ናቸው፡፡
ዛሬ በስኬት እንግዳችን ይዘን የቀረብነው ባለታሪክም ወድቆ መነሳትን ማስተማር የሚችል፤ የነበረን ነገር ሁሉ በቅጽበት እንዳልነበር ቢሆንም በሕይወት ሌላኛው መንገድ ብዙ መውጫ በሮች እንዳሉና፤ የሚገጥሙ ችግሮችን ሁሉ እንደ ዕድል በመጠቀም ወደ ቀጣይ የሕይወት ምዕራፍ መሸጋገር እንደሚቻል ያስተምራል፡፡
ወጣት ዳግማዊ አሰፋ ይባላል፡፡ ትውልዱ በአሰላ ከተማ ይሁን እንጂ ዳግማዊ ገና በለጋነት እድሜው ወደ ሀዋሳ ከተማ በመምጣት የአንደኛ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ተከታትሏል፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በጥሩ ውጤት ያጠናቀቀው ዳግማዊ በዲላ ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት መከታተል እንዲችል በር ከፍቶለታል፡፡ በዲላ ዩኒቨርሲቲ አንድ ዓመት የህግ ትምህርቱን ተከታትሎ በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ሀዋሳ ተመልሷል፡፡ በሀዋሳ ከተማም ቀሪውን የህግ ትምህርት ለአራት ዓመታት ተከታትሎ በማዕረግ ተመርቆ አጠናቅቋል፡፡
በሙያው ማህበረሰቡን እና ሀገሩን የማገልገል እውነተኛ ፍላጎት ያደረበት ገና ተማሪ እያለ ጀምሮ ነው፡፡ በመሆኑም ከህግ ጋር በተያያዘ ያሉ ጉዳዮችን በማስረዳት ለተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ያለውን እውቀት አጋርቷል፡፡ በዚህም ጥቂት የማይባሉ ሰዎች ከእስር እንዲፈቱና ጉዳያቸው በፍጥነት ታይቶ የህግ ውሳኔ እንዲያገኙ ምክንያት ሆኗል፡፡
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የሶስተኛ ዓመት የህግ ተማሪ እያለ የጀመረው የነጻ አገልግሎት ተጠናክሮ በመቀጠል በዩኒቨርሲቲው በተቋቋመ ነጻ የህግ አገልግሎት መስጫ ማዕከል ውስጥ በመሆን አቅም ለሌላቸው ሰዎች በነጻ ሲያገለግል ቆይቷል፡፡ በዚህ ያላበቃው ዳግማዊ፤ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በከፈተው የነጻ የህግ ማዕቀፍ ውስጥ ተካትቶም አገልግሏል፡፡
በዚህ ወቅት ታዲያ ማረሚያ ቤት በመሄድ ነጻ የህግ አገልግሎት ይሰጥ ነበር፡፡ በዚህም ከጓደኞቹ ጋር በመተባበር ከ30 እስከ 40 የሚደርሱ ታራሚዎችን በነጻ ማስለቀቅ ችሏል፡፡ የእስር ጊዜያቸው እንዲቀንስ አድርጓል፡፡ ሳይከሰሱ በሰዎች ቸልተኝነት ማረሚያ ቤት የተቀመጡ ሰዎች እንዲከሰሱ አልያም እንዲለቀቁ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡
በዚህ ልክ ለህዝብና ለሀገሩ የሚሰራው፣ ለፍትህ የሚቆም እና የሚታትረው ዳግማዊ፣ በአንዲት ቅጽበት ያሰበው ሁሉ እንዳላሰበው የነበረው ሁሉ እንዳልነበር ሆነበት፡፡ ምክንያቱም ደግሞ በሥራ ላይ እንዳለ በተተኮሰበት ጥይት በደረሰበት ከፍተኛ አደጋ ነው። በመሳሪያ አንገቱን የተመታው ዳግማዊ በመተንፈሻ ቱቦው፤ በምግብ ማስተላለፊያውና በጀርባ አጥንቱ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበት ከፍተኛ ስቃይና ብዙ መከራ አሳልፏል፡፡
ጥይቱ የጀርባ አጥንቱን ሰንጥቆ ወጥቷል፡፡ አደጋው አከርካሪ አጥንቱ ላይ በመድረሱ ከነርቭ ጋር ተያይዞ አደጋውን የከፋ አድርጎታል፡፡ አደጋው የከፋ በመሆኑም በቀላሉ ከአደጋው መላቀቅ አልቻለምና ውሎ አዳሩ ዊልቸር ላይ እንዲሆን የግድ ሆነ፡፡
ረዥም ጊዜ በዊልቸር ላይ መቆየቱን እና ብዙ ነገሮችን በራሱ ማድረግ አለመቻሉን የተረዳው ዳግማዊ ነገሮች ሁሉ እጅግ በጣም ተስፋ አስቆራጭና የማይሆን ሆኖበት ነበር፡፡ ይሁንና በርካታ ሥራዎችን ይሰራ የነበረውና ብዙ ለመስራትም እየተጋ ባለበት አፍላ ጊዜው የደረሰበትን አደጋ ተቋቁሞ እንዴት ማለፍ እንዳለበት ሲያወጣና ሲያወርድ ቆይቶ መጽናኛዎችን ፈልጓል አፈላልጓል፡፡
የጉዳቱ ውጤት በዚህ ልክ የከፋ ይሆናል ብሎ ያላሰበው የ25 ዓመት ወጣት ሁሉም ነገር ጨለማ በሆነበት ጊዜ የሚያጽናናውና ወደ ተሻለ ሕይወት የሚወስደውን ጎዳና በሚፈልግበት ወቅት አንድ ነገር ታዝቧል፡፡ እንደ እርሱ ትዝብትም ውጭ ሀገር ሰዎች ታሪካቸውን ያለፉበትን ውጣ ውረድ አስታማሪ በሆነ መንገድ ጽፈው ለንባብ ያበቃሉ፡፡ ኢትዮጵያውያን በአንፃሩ ያለፉበትን ማንኛውም የሕይወት ውጣ ውረድ ለሌሎች አስተማሪ በሚሆን መንገድ ቀምረው አይጽፉም፡፡
ወጣቱ አደጋውን ተከትሎ ማንን አይቼ ልበርታ ምን አንብቤ ልጽናና የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ባደረገው ጥረት የራሱን መጽሀፍት ለመጻፍ አንድ መንገድ አገኘ፡፡ እሱ የደረሰበትን የጉዳት መጠንና ከጉዳቱ አገግሞ በጥንካሬ ተጉዞ ዛሬ ላይ የደረሰበትን የሕይወት ውጣ ውረድ ለሌሎች አስተማሪ በሆነ መንገድ ለመጻፍ ተነሳሳ፡፡
በደረሰበት አደጋ እጅ ሳይሰጥ መፍትሄ ላይ ትኩረቱን ያደረገው ዳግማዊ፣ ሌሎች ሰዎች እርሱ የተጓዘውን ያህል ርቀት ሳይጓዙ የሚገጥማቸው ችግር ተቋቁመው በቀላሉ ማለፍ ባይችል እንኳን ሊያበረታ ይችላል፣ ስንቅ ይሆናል፣ በማለት አዲስ ሕይወት በሚል ርዕስ የተጻፈ የመጀመሪያ መጽሀፉን ለንባብ አበቃ፡፡ አዲስ ህይወት ያለበት ምክንያትም የህይወት መስመሩ ከነበረበት መስመር ወጥቶ ባልታሰበ አቅጣጫ መታጠፉን ለማሳየት ነበር፡፡
መጽሀፉ በአምስት ምዕራፎች ተከፋፍሏል። መልዕክቱም ምንም አይነት መከራ በሕይወታችን ቢገጥመን በርትተን ማለፍ ከቻልን የማንሻገረው ድልድይ እንደሌለ የሚያስተምር ነው፡፡ መጽሀፍም ከጠበቀው በላይ ተሸጦ በብዙዎች እጅ ገብቷል፡፡ በዚህም ስኬታማ እንደሆነ ይናገራል፡፡
ዳግማዊ የሰው ልጅ ባደረሰበት አደጋ ምክንያት ብዙ ስቃይና መከራ ያሳለፈና የሕይወትን አስከፊ ገጽታ ቢጋፈጥም ይህን ባደረገው የሰው ልጅ ላይ ቂም ሳይዝ ይቅርታን አድርጓል፡፡ ለዚህም ሁለተኛ መጽሀፉን ይቅርታ በሚል ርዕስ አሳትሟል፡፡ ጭብጡም በይቅርታ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ‹‹ጥላቻ ማለት ለራስ መርዝ እየጠጡ ሌላኛው ሰው ይገድለዋል ብሎ እንደማሰብ ነው›› የሚለው ዳግማዊ ጥላቻ ከግለሰብ አልፎ ሀገርን የሚያጠፋ ክፉ መርዝ እንደሆነም ይናገራል፡፡
ጥላቻ እኛኑ ምልሶ እየገደለን ያለ መርዝ በመሆኑ ከጥላቻና ከቂም መውጣት እንዳለብንም ይመክራል፡፡ ዛሬ የሆኑ አካላት ጉልበተኛ ሆነው በጥላቻ መንፈስና በቂም በቀል ጉዳት ማድረስ ቢችሉ ነገ ደግሞ ሌላ በቀል ይፈጠራል፡፡ ስለዚህ ከጥላቻና ከበቀል እራሳችንን ልናጸዳ ይገባል፡፡ ምክንያቱም ምንጊዜም ቢሆን የምንለኩሰው የጥላቻ እሳት ወደ ወረወርንበት ብቻ ሄዶ አያበቃም ወደ እራሳችንም ተመልሶ ይመጣል፡፡
የሀገራችን አሁን ከገባችበት ውጥንቅጥ ውስጥ ለመውጠትም የሚያስፈልገን ይቅርታ እንደሆነ በጽኑ የሚያምነው ዳግማዊ፤ የኋላ ታሪኮችን ብናነሳ አብዛኞቹ የመገዳደል ታሪክ ያላቸው እንደነበሩ ያነሳል። ስለዚህ ይህን የመገዳደል ታሪክ ለመቀየር ይቅርታን በሕይወታችን፣ በትምህርታችንና በእያንዳንዱ የህይወት እንቅስቃሴያችን ልንለምደው የሚገባን ብርቱ ጉዳይ እንደሆነና ሊሰራበት የሚገባ ነው ይላል፡፡
የህግ ትምህርቱን ሲከታተል በፍትህ እጦት ምክንያት የተቸገሩ ሰዎችን ለማገዝና እራሱን ለመርዳት ዓላማ አድርጎ እንደነበር የሚናገረው ዳግማዊ፤ እራሱን ከደረሰበት ከፍተኛ አደጋ በላይ አድርጎ በማሰብ ተስፋ ሳይቆርጥ ችግሮቹን ተቋቁሞ ማለፍ ችሏል፡፡
የሕይወት ውጣ ውረዱን ለማለፍ ባደረገው ከፍተኛ ጥረትም ዛሬ ላይ በራሱ መቆም ችሏል። ከራሱም አልፎ በቤት ውስጥ በህግ የማማከር ስራ ለመስራት በከፈተው ቢሮ ለሶስት ሰዎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል፡፡ በጻፋቸው ሁለት መጽሀፍቶችም ሰዎችን ለማስተማር ሞክሯል፡፡ ይህም ወድቆ በመነሳት ሂደት ውስጥ መማር እንደሚቻልና ለሌሎች የሚተርፍ ሥራን መስራት እንደሚቻል ያሳያል፡፡
አደጋው ተስፋ አስቆራጭ ከመሆኑም ባለፈ በሕይወት ቆሜ እዚህ እደርሳለው የሚል እምነት ያልነበረው ዳግማዊ፣ ዛሬ ላይ የደረሰበትን አደጋ ተቋቁሞ የሕይወት ውጣውረዶችን ሁሉ አልፎ በሕይወት ሌላኛው ምዕራፍ ላይ ተገኝቷል፡፡ የሕይወት መስመሩ በተናጋበት አንድ ጥይት ምክንያት ዛሬ እንደወትሮው በእግሮቹ ባይሮጥም ካሰበበት ሁሉ በእግሮቹ ባደርስም በዊልቸር ላይ ሆኖ ግን ‹‹ሕይት ትቀጥላለች›› ይላል፡፡
‹‹የደረሰብኝን ጉዳት ተቋቁሜ በማለፌ ዓላማዬን አሳክቻለሁ›› የሚለው ዳግማዊ፤ ከስድስትና ከሰባት ጊዜ በላይ ከባድ የሚባሉ የቀዶ ጥገና ህክምናዎችን አድርጓል፡፡ ይህን ሁሉ ተቋቁሞ ሰርቶ ማደር ችሏል፡፡ በመሆኑም በቤቱ ውስጥ በከፈተው የህግ ቢሮ በርካታ ሰዎችን አገልግሏል፡፡ እያገለገለም ይገኛል፡፡
‹‹ከወደቅንበት መነሳት መቻል ስኬት ነው›› የሚለው ዳግማዊ፤ እርሱም ከወደቀበት ለመነሳት ባደረገው ትግል ውጤታማ ከመሆን ባለፈም ለሌሎች አስተማሪ መሆን ችሏል፡፡ ስኬት መንገድ ነው መንገዱም ብዙ አይነት እንደመሆኑ ሁልጊዜ ዓላማ አድርገን የያዝነውን ነገር ማሳካት ከቻልን እርሱ ስኬት ነው፡፡ ስኬት አይቆምም ማደግ መቻል አለበት የስኬት ፍሬው ደግሞ ለሰውዬው ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም መትረፍ እንደሚገባ ያምናል፡፡
እኛም የትኛውም ችግር መፍትሔ አለውና ለመፍትሔው እንትጋ በማለት አበቃን፡፡
ፍሬህይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 11/2013