
አፍጋኒስታንን ሲያስስተዳድሩ የነበሩት ታሊባኖች እንደ ጎርጎሮሲያዊያኑ በ2001 ሥልጣናቸውን ቢያጡም፤ ለ20 ዓመታት ተዋግተው መልሰው ሥልጣን በእጃቸው ማስገባት ችለዋል፡፡ ታሊባኖች ከአሜሪካ ጋር ለሁለት አሥርት ዓመታት ጦርነት ላይ እንጂ ድርድር ውስጥ አልነበሩም።
ከሦስት ዓመት በፊት ነው ለመጀመርያ ጊዜ ፊት ለፊት ድርድር የተቀመጡት። ይህም በኳታር ዶሃ የተደረገ ነበር። ድርድሩ አሜሪካ ወታደሮቿን ከአፍጋኒስታን ሙሉ በሙሉ ለማውጣት መወሰኗን ተከትሎ የተጀመረ ይመስላል።
በታሊባንና በአሜሪካ መካከል የተደረገው ድርድር ዘለግ ያለ ጊዜን ከወሰደ በኋላ በፈረንጆች 2020 የካቲት ወር ላይ ስምምነት ላይ ደረሱ ተባለ።
ስምምነቱ አሜሪካ አፍጋኒስታንን ሙሉ በሙሉ ለቃ እንድትወጣ፣ በአንጻሩ ታሊባን በአሜሪካ ኃይል ላይ ምንም ዓይነት ጥቃት እንዳይፈጽም፣ አል-ቃኢዳ ወይም ሌሎች አሸባሪዎች ጋር ታሊባን እንዳይተባበር አልያም ታሊባን ተቆጣጥሮ በያዛቸው ስፍራዎች ቡድኖቹ እንዳይንቀሳቀሱ የሚሉ ናቸው።
ታሊባን ማለት በፓሽቶ ቋንቋ “ተማሪዎቹ” ማለት ነው። ፓሽቶ በፓኪስታን፣ አፍጋኒስታንና ኢራን ውስጥ የሚነገር ቋንቋ ነው። ታሊባን በጎርጎሮሲያዊያኑ 1990ዎቹ መጀመርያ በሰሜን ፓኪስታን ብቅ ያለ መደበኛ ያልነበረ እንቅስቃሴ ሲሆን፤ ይህም የያኔዋ ሶቭየት ኅብረት ከአፍጋኒስታን ጦሯን ማስወጣቷን ተከትሎ የተጀመረ ነበር። ይህ የፓሽቱን እንቅስቃሴ ሲጀምር መንፈሳዊ ቅርጽ የነበረው ይመስላል።
ከሳኡዲ አረቢያ ጥብቅ እስልምናን በሚሰብኩ ሰዎች የተማረኩ ወጣቶች አማካኝነት ስብስቡ እየተጠናከረ መጣ። መንፈሳዊ እንቅስቃሴው ፖለቲካዊ መልክን እየያዘ መጣ። ከኢመደበኛ እንቅስቃሴ ወደ ቡድን ከፍ አለ።
ይህ ቡድን በፓኪስታንና አፍጋኒስታን መሀል የሚገኘውን ፓሽቱን አውራጃን ቀስ በቀስ በመያዝ ጽኑ የሸሪዓ አስተዳደርን በመትከል ሰለምና ደኅንነት ለማረጋገጥ ቃል ገባ። እንዲህ እንዲህ እያሉ ከደቡብ ምዕራብ አፍጋኒስታን ተነስተው ወጣቶቹ ታሊባኖች ተጽእኗቸውን ማስፋት ያዙ። በመስከረም 1995 ደግሞ ኢራንን የምትዋሰነውን ሔራት የምትባለውን አውራጃ መያዝ ቻሉ። ይህን ካሳኩ ከዓመት በኋላ ደግሞ ካቡልን ተቆጣጠሩ። ያን ጊዜ ፕሬዚዳንት የነበሩት ቡርሃንዱኒ ራባኒ ነበሩ።
ቡርሃንዱኒ ራባኒ ከአፍጋኒስታን የነፃነት አባቶች አንዱ ተደርገው የሚወሰዱና የሶቭየት ኅብረትን ታግሎ ያስወጣው የሙጃሂዲን (አርበኞቹ) ቡድን መሥራች ነበሩ። እንደ ጎርጎሮሶዊያኑ 1998 ታሊባን የአፍጋኒስታንን 90 ከመቶ ይቆጣጠር ነበር። በዚያን ጊዜ ሕዝብ ዘንድ ሰፊ ተቀባይነትን ማግኘት ችሎ ነበር።
ይህም የሆነው ምናልባት አፍጋኒስታዊያን በሙጃሂዲኖች የርስበርስ ሽኩቻ ተሰላችተው ስለነበር ይሆናል።
ታሊባኖች በተለይም ሙስናን በማጥፋትና ሥርዓት አልበኝነትን በመቀልበስ ስማቸው ይወደሳል። በአፍጋኒስታን ዋና ዋና መንገዶችን በመቆጣጠርና የእንቅስቃሴ ደኅንነትን በማረጋገጥ ንግድ እንዲስፋፋ በማድረጋቸው በአጭር ጊዜ ሰፊ ተቀባይነትን ማግኘት ችለው ነበር።
ጥብቅ የሸሪዓ ሕግጋት
ታሊባን ጥብቅ የሸሪዓ ሕግጋት ተግባር ላይ እንዲውሉ ይደግፋል ተግባራዊም ያደርጋል። ለምሳሌ ሴቶች ቡርቃ የሚባለውንና ከራስ ጸጉር እስከ እግር ጥፍር ሙሉ የሴት ሰውነትን የሚሸፍን ልብስ እንዲለብሱ ማስገደድ እንዲሁም ወንዶች ፂማቸውን እንዲያሳድጉ ማድረግ ይገኝበታል። ዝሙት ፈጻሚዎች በአደባባይ እንዲሰቀሉና የሰረቁ እጆችም እንዲቆረጥ አድርገዋል።
ታሊባኖች ቴሌቪዥንን፣ ሙዚቃን እና ሲኒማን ሙሉ በሙሉ ያገዱ ሲሆን፤ ዕድሜያቸው ከ10 ዓመት በላይ የሆኑ ሴቶች ትምህርት እንዳይማሩ መከልከላቸውም ለውግዘት ዳርጓቸው ነበር። ታሊባኖች በከፍተኛ የሰብዊና ቁሳዊ ጥሰት የሚከሰሱ ሲሆን፤ ከዚህም መሀል በ2001 ዓ.ም በማዕከላዊ አፍጋኒስታን ይገኝ የነበረውን እጅግ ዝነኛውን የባሚያ ቡድሃን ሐውልት ማፍረሳቸው ይጠቀሳል። ይህ ድርጊታቸው ዓለም አቀፍ ቁጣን ቀስቅሶ ነበር።
ታሊባንን ማን ፈጠረው?
የታሊባን ቡድን በፓኪስታን መንግሥት ስለመፈጠሩ የሚከራከሩ በርካቶች ናቸው። ታሊባንን የፈጠረችው ፓኪስታን ናት የሚባልባቸው አንድ ሁለት ምክንያቶችን እንጥቀስ። ምንም እንኳ ፓኪስታን ይህን የማትቀበል ቢሆንም ብዙዎቹ የታሊባን አባላት ግን በፓኪስታን ሃይማኖታዊ ትምህርት ቤቶች (መድረሳ) የተማሩ ናቸው።
እንቅስቃሴያቸውን ያፋፋሙትም በፓኪስታን ሳሉ እንደሆነ ይነገራል። ታሊባን ወደ ሥልጣን ሲመጣ ዕውቅና ከሰጡ ሦስት አገራት የመጀመርያዋ ፓኪስታን ነበረች። ሁለቱ ቀሪ አገራት ደግሞ ሳኡዲ አረቢያና የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ነበሩ። ፓኪስታን የታሊባን ፈጣሪ ሳትሆን አትቀርም ካስባሏት ሌሎች ምክንያቶች አንዱ ለታሊባኖች ቀድማ እውቅና መስጠቷ ብቻ ሳይሆን ነገሮች ከፍተው ታሊባን ቅቡልነትን እያጣ ሲመጣም ከታሊባን ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን ለማቆም የመጨረሻዋ አገር መሆኗን ጭምር ነው።
አሜሪካና ታሊባን
የአፍጋኒስታን ጦርነት አሜሪካን ከፍተኛ ዋጋ አስከፍሏል፡፡
አሜሪካ ለአፍጋኒስታን በገንዘብ 2 ትሪሊየን የአሜሪካ ዶላር በብድር መልክ ያወጣች ሲሆን፤ የብድር ወለዱ በአውሮፓውያኑ 2050 6 ነጥብ 5 ትሪሊየን ዶላር ይደርሳል ይላል ከሲ.ጂ.ቲ.ኤን የተገኘው መረጃ።
አሜሪካ በአፍጋኒስታን ለ20 ዓመታት በነበራት ቆይታ 2 ሺ 448 ወታደሮቿን አጥታለች፡፡
አሁን ታሊባን የአፍጋኒስታንን ዋና ከተማ ካቡልን መቆጣጠሩን ተከትሎ አሜሪካን ጨምሮ የበርካታ ሀገራት ዜጎችና ዲፕሎማቶች ከሀገሪቱ እየወጡ ነው፡፡
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ነሐሴ 11/2013