ትህነግ ኢትዮጵያን ለማፈራረስና የጥቂት ቡድኖችን ጥቅም ለማስከበር ሲያካሂዳቸው ከነበሩ መጠነ ሰፊ ትግሎች መካከል አንዱ በህዝቡ ዘንድ የሀሰት የስነ ልቦና ጦርነትን ማካሄድ ነው። ይህንንም ከትጥቅ ትግል አንስቶ መንግስት በሆኑበት ጊዜና ዛሬም በሽብር ስራ ተጠምደው በስፋት እየከወኑት ይገኛል። ለመሆኑ ይህ የትህነግ የስነ-ልቦና ጦርነት እንዴት ተጀምሮ ዛሬ ላለበት ደረጃ ደረሰ ስንል በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የስነልቦና ትምህርት ክፍል ሃላፊና መምህር የሆኑትን ረዳት ፕሮፌሰር ነጻነት ባይለየኝን አነጋግረን የሚከተለውን ይዘን ቀርበናል።
ረዳት ፕሮፌሰር ነጻነት እንደሚያብራሩት ትህነግ ወደ ስልጣን ከመምጣቱም በፊት የሀሰት የስነልቦና ጦርነትና ፕሮፖጋንዳ በማካሄድ የሚታወቅ ነበር። በዚህ አካሄዱም ቀድሞ በትጥቅ ትግል በነበረበትም ጊዜ ሆነ እንደ መንግስት ሀገር ሲገዛ አሁንም በሽብር ስራ ውስጥ ሆኖ በርካታ ጥፋቶችን ፈጽሟል። በተለይም በትጥቅ ትግሉ ወቅት ከፍተኛ የደርግ ባለስልጣናትን ባህሪ በማስጠናትና ያላቸውን ደካማ ጎን በመውሰድ የተለያዩ ሴራዎችን በመስራት አላማውን ሲያሳካ ቆይቷል። ይህ የስነልቦና ጦርነት ለደርግ ሰራዊት መውደቅም አንዱ ምክንያት ነበር።
ትህነጎች አራት ኪሎ ገብተው ስልጣን ከተቆናጠጡም በኋላ የተለያዩ የሀሰት ወሬዎችን በመንዛት የስልጣን ዘመናቸውን ለማራዘም ሲጠቀሙበት ኖረዋል። የዚህ ሴራቸው መወጫ የሚያደርጉት ደግሞ የራሳቸውን በመንግስት ሃላፊነት ያሉ አባሎቻቸውን ሳይቀር ነበር። በተለይ ግምገማ በሚባለው መድረክ የራሳቸውን የድርጅት አባላት ሳይቀር በተለያዩ የሀሰት ወሬዎች ስነልቦናውን በማዳከም ተገዢ እንዲሆን በማድረግ የሚፈልጉትን ሲያሰሯቸው ነበር።
በሀገሪቱ የተከሰተውን ለውጥ ተከትሎም ወደ መቀሌ በመሸሽ የሽብር ስራቸውን እስከጀመሩበት ጊዜ ድረስ
ይህንኑ የሃሰት የሥነልቦና ጦርነት እየተጠቀሙበት ይገኛል። ለዚህም በዋናነት ዲጅታል ወያኔ የተባለ ይህንን ስራ ብቻ የሚከውን ተቋም በመመስረትና ሌሎች ከግለሰብ እስከ ድርጅት ያሉ ሰዎችን በመጠቀም አሁንም ድረስ እየሰሩበት ይገኛል። ይህ አካሄዳቸው ደግሞ እነሱ እንደሚያስቡት አይሳካላቸውም እንጂ ኢትዮጵያ እስከምትፈረስ ድረስ የሚቀጥሉበት ነው።
በስልጣን በነበሩበት ጊዜ ያሰራጯቸው ከነበሩ የሃሰት የሥነልቦና ጦርነቶችና ፕሮፖጋንዳዎች በህዝቦች መካከል ሲነዙት የነበረው የመከፋፋል ሴራ መቀጠሉ የማይቀር ነው። በእነዚህ ጊዜያት የግዛት እድሚያቸውን ለማራዘም በተለይ የአማራ ህዝብ ጨቋኝ ገፊ እንደነበር በማስመሰል የዘሩት የሀሰት ወሬ ብዙ አስከፍሏል። ይህ አካሄድም በህዝቦች መካከል መተማመን እንዳይኖር በማድረግ ሀገሪቱ ልታገኝ የሚገባትን ሰላም ሳታገኝ ልትደርስበት የሚገባትን እድገት ሳትጎናጸፍ እንድትቆይ አድርጓታል።
ዛሬም በጦርነት ውስጥ ሆነው አማራ የራሱን ግዛት ለማስፋፋትና ስልጣን ለመያዝ ሌሎችን ለመጫን እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ ለማስመሰል ይጥራሉ። ነገር ግን እነሱ የራሳቸውን አላማ ብቻ ለማሳካት የሚንቀሳቀሱ መሆናቸውን በቅርቡ በአፋር ህዝብ ንጹሀን ዜጎች ላይ ያደረሱት ጭፍጨፋና ወረራ ምስክር ነው። ይህ የሚያሳየን በአንድ ወገን ወያኔ የስነ ልቦና ጦርነቱ ያዋጣኛል ብሎ የያዘውና በቀጣይም አጠናክሮ የሚቀጥልበት መሆኑን ሲሆን በሌላ በኩል ከመንግስትና ከሌላው ህዝብ ብዙ ያልተሰራ የቤት ስራ መኖሩን ነው።
ወያኔ ይህን የስነ ልቦና ጦርነት በዚህ ደረጃ እንድትጠቀምበት ያደረጓት የተለያዩ ምቹ ሁኔታዎች ያሉ ሲሆን ከእነዚህም መካከል የማህበራዊ ሚዲያው ምቹ መሆን። የማህበረሰቡ የስነ ልቦና ስሪትና አስተዳደግ ይጠቀሳሉ፤ በኢትዮጵያ ባህል ያደገ ሰውን የማመንና የተነገረውን ሁሉ በጥልቀት ከማጣራትና ከመመርመር ባለበት እውነት ነው ብሎ የመቀበል አካሄድ አለ። ከሁሉም በላይ ደግሞ የኢትዮጵያን እንደ ሀገር መቀጠል የማመይፈልጉ የውጪ አካላት የሚያራግቡላቸው ወሬ ለሀሰት የስነልቦና ጦርነቱ ውጤታማናት ትልቅ መሰረት ነበር። እነዚህ አካላት የሚፈልጉትን ለማሳካት በተላላኪነት ትህነግን ሲጠቀሙ ስለነበርና ከዚህ በኋላ የእነሱን አላማ ለማሳካት የሚረዳን የለም ብለው ስለሚያስቡ በተመቻቸው አጋጣሚ ሁሉ መቀጠላቸው አይቀርም።
በመሆኑም የትህነግን እኩይ ዓላማ በመረዳትና የመጡበትን አጥፊ መንገድ በመመርመር ተገቢውን መስራት ይጠበቃል። ይህንንም ለማድረግ ማህበረሰቡ ትህነግ ባለፈው ሰላሳ ዓመት ሲሰራ የነበረው እርስ በእርስ የማጋጨት የማቃቃር ስራ ተመልሶ በመገምገም መረዳት አለበት። በመረጃ ማግኘት ረገድም ተአማኒነት ተጠያቂነት ካላቸው ሚዲያዎች መውሰድ ይጠበቅብታል። ጦርነት በመሳሪያ ብቻ የሚደረግ ባለመሆኑ የሚባለውን ሁሉ እየተቀበለ ራሱን በሽብር ውስጥና ባለመረጋጋት ወስጥ እንዳይቆይ ማድረግ አለበት። በመንግስትም በኩል በመጀመሪያ ወቅቱን የጠበቀ መረጃ ህብረተሰቡ እንዲያገኝ ማድረግ። በተጨማሪ ለመግስት ሃላፊዎች በተለይ በጦርነቱ ለሚሳተፉት ጠንካራ ስነልቦና እንዲኖራቸው ማድረግና በየወቅቱ ለሚደርሱ ሀሰተኛ መረጃዎች በመከታተል እውነታውን ማድረስ ይጠበቅበታል።
ለውጡ ሲመጣ መንግስት ያካሄደው አብዮት ሳይሆን ሪፎም ነው በመሆኑም በመንግስት የስልጣን ተዋረድ ወስጥ የነበሩት በሙሉ አልተነሱም። ከእነዚህም መካከል በትህነግ ፍልስፍና የተጠመቁና ያደጉ ዛሬም ድረስ ያንን የሚያቀነቅኑ መኖራቸው አይቀርም። እነዚህ አካላት ትህነግ ትክክለኛ ነው ብለው የሚያምኑና ትልቅ ሊደፈር የማይችል አካል አድርገው የሚያዩም ስላሉ፤ የእነዚህን አመለካካት መቀየር ካልሆነም ቁርጠኝነት ወስዶ ካሉበት ማንሳት ይጠበቃል። ካለው አካሄድና ከሚፈጠረው ችግር እንዲሁም ከሚያስከትለው ጥፋትና ጉዳት አንጻር የኢትዮጵያን ህልውና የሚነካ ሆኖ ሲገኝም ሪፎርሙን ወደ አብዮታዊ መቀየር ይገባል። በሚዲያውም ጥሩ ጅማሮ ቢኖርም በርካታ ስራዎች ስለሚቀሩ ተአማኒ መረጃ በማድረስና የጥበብ ስራዎችን በማከል መስራት እንደሚጠበቅ አሳስበዋል።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 11/2013