ባለፉት 9 ወራት አሸባሪው ህወሓት በሀገር ላይ በፈጸመው ክህደት ሳቢያ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ከባድ ፈተና ውስጥ ቆይተዋል። የፈተና ዘመን ከምንም ጊዜ በላይ ያጠነክራል እንደሚባለውም ኢትዮጵያውያን ከየትኛውም ጊዜ በተሻለ መልኩ አንድነታቸውንና ወንድማማችነታቸውን አጠንክረው ከሀዲዎችንና ባንዳዎችን አይቀጡ ቀጥተዋቸዋል፡፡
በሀገራችን ክህደት የፈጸመው አሸባሪው ህውሓት በእነዚህ ጊዜያት ነው በህግ ማስከበር ዘመቻው እንዳይጠገን ተደርጎ የተሰባበረው፡፡ ከማዘዣው መቀሌ ወደ ተፈጠረበት ጉድጓድ እንዲገባ የተደረገው፡፡ ትህነግ ዛሬ አካኪ ዘርፍ ሲል ቢሰማም በአልሞት ባይ ተጋዳይነት መፍጨር ውስጥ ነው የሚገኘው፡፡ የእሱ ጉዳይ አሁንም እዳው ገብስ ነው፡፡
በእነዚህ ጊዜያት አገራችን በእጅጉ የለየችው ወዳጅና ጠላቷን ነው። ለዘመናት ወዳጆቻችን ያልናቸው አንዳንድ ሀገሮች ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ለሚሰራው አሸባሪው ህወሓት ድጋፍ ሲያደርጉ ኖረዋል፤ እያረጉም ናቸው፡፡ እነዚህ ሀገሮች ቡድኑ በኢትዮጵያውያንና በኢትዮጵያ ላይ በፈጸመው የክህደት ተግባር በሃይል ተወግዶም እንዲያንሰራራ ላይ ታች ሲሉ ይታያሉ፡፡
እነዚህ የውጭ ሀይሎች በሴራ ጠልፈው ሊጥሉን ከጀርባ ሆነው ብቻ አይደለም የሚሰሩት፡፡ ጥርሳቸውን አግጠው አይናቸውን አፍጥጠው ሀገሩን ከከዳ የእናት ጡት ነካሽ ባንዳ ጋር አብረው ሊበታትኑን ሌት ተቀን እየሰሩ ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያን ከመበታተን ውጪ ሌላ አጀንዳ የላቸውም። አንዳንዶቹ በማእቀብ ሊያንበረክኩን፣ አንዳንዶቹ በእርዳታ ሰበብ ወደ ሀገራችን በመግባት አሸባሪውን ቡድን ሲደግፉ እየታዩ ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ተላላኪ ሆነው እየሰሩ ናቸው፡፡
ከእነዚህ ሀገሮች መካከል አንዷ ጎረቤታችን ሱዳን ነች። ሱዳን ፊትም ለአሸባሪው ህወሓት እስትንፋስ ነበረች፡፡ ህወሓት የትግል ወቅቴ ለሚለው ዘመን ሁሉ ነገሩ ሆና ሰርታለች፤ ኢትዮጵያን በእጅጉ ካደማችባቸው ወቅቶች አንዱም ያ ወቅት ነው፡፡ ቡድኑ ጓዙን ጠቅልሎ የመጣውስ ከዚችው ከሱዳን አይደል፡፡
ይህች ሀገር አሸባሪው ህወሓት መልሶ ወደ በረሃ ሲገባም ወደ ቀድሞ እኩይ ተግባሯ ተመልሳለች፡፡ ይህም ጉዳይዋ ከኢትዮጵያ ጋር ሳይሆን ከአሸባሪው ቡድን ጋር መሆኑን በግልጽ ያመለክታል፡፡ የአሸባሪው ህወሓት ተጣቂዎች በማይካድራ ያን ዘግናኝ ጭፍጨፋ ፈጽመው የገቡት ወደዚችው ሀገር ነው፡፡ ለአቀባባል ቀይ ምንጣፍ ሳይደረግላቸውስ ይቀራል፡፡
ይህን ጉዳይ የኢትዮጵያ መንግስት በተደጋጋሚ ለራስዋ ለሱዳን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጭምር አስታውቋል፡፡ ሀገሪቱ እነዚህን ወንጀለኛ ታጣቂዎች አሳልፋ መስጠት ሲገባት ከዚህ በተቃራኒው እየሰራች ነው፡፡ ለእነዚህ ስደተኛ መሰል ታጣቂዎች ወታደራዊ ስልጠና በመስጠት መልሰው ኢትዮጵያን እንዲወጉ እየሰራች ትገኛለች፡፡ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ በኩል ያን ሁሉ ቀውስ ያስከተለ ጥቃት ሲፈጸም ያቀናበረው በሱዳን ስልጠና እየተከታተሉ ወደ ኢትዮጵያ በሚገቡ ሃይሎች ነው፡፡
የአሸባሪው የህወሓት ቡድን ሰሜን እዝን በካደበት ወቅት መልካም አጋጣሚ አገኘሁ ብላ የኢትዮጵያን መሬት አሁንም ድረስ በወረራ ይዛለች፡፡ አጋሯ ህወሓት አኩርፎ መቀሌ ከገባ አንስቶ ከግብጽ ጋር በመሆን በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ያልሸረበችው ሴራ የለም፡፡ አሸባሪው ህወሓትና ምእራባውያኑ ሌላ የእርዳታ ማስተላለፊያ ኮሪደር ጥያቄ ሲያቀርቡ አሸባሪው ቡድን ወደ ሱዳን እንደልብ እንዲመላለስ ለማስቻል ብቻ ሳይሆን ሱዳንን ለስውር ሴራቸው ፈልገዋት እሷም ፈልጋ ጭምር ነው፡፡
መፅሃፍ ቅዱስ ላይ እየሱስ ክርስቶስ ጴጥሮስን ዶሮ እስከሚጮህ ድረስ ሶስት ጊዜ ትክደኛለህ እንዳለውና ይህም እንደተፈጸመ ሁሉ ሱዳንም በኢትዮጵያ ላይ ከዚህም በላይ ክህደት ፈጽማለች፡፡ አዎን የጉዳዩ አሳሳቢነት ነገሮችን ወደ ኋዋላ መለስ ብሎ መመልከትን ይጠይቃል፡፡ በመሃዲስቶቹ ዘመን፣ በአባይ ጉዳይ ላይ ከግብፅ ጋር በማበር፣ ቀን ጠብቃ ድንበር ጥሳ ሉአላዊነታችንን በመዳፈር እንዲሁም የእናታቸውን ጡት የነከሱ የኢትዮጵያ ባንዳዎችን በጉያዋ ስር ወሽቃ የጭቃ ውስጥ እሾክ በመሆን ኢትዮጵያን ‹‹ሶስት ጊዜ›› ከድታለች።
ከጉርብትናና ህዝብ ለህዝብ ካለው የረጅም ዘመን ወዳጅነት አንፃር ኢትዮጵያውያን አሁንም ቢሆን ለሰላምና ለወዳጅነት በራችን ዝግ ባይሆንም፤ ይህችን ሀገር ግን በሴራ መጥለፍ እንደማንፈልግ በግልፅ ቋንቋ እያስገነዘብናት ነው።
ይህች በኢትዮጵያ ጉዳይ እየፈተፈተች ያለች ጉደኛ አገር በቅርቡ ደግሞ አዲስ የመቆመሪያ ካርድ መዛለች፡፡ አይኗን በጨው አጥባ የኢትዮጵያ መንግስትን ከአሸባሪው ህወሓት ለማደራደር እንደምትፈልግ አስታውቃለች፡፡ ሽምግልና መሆኑ ነው፡፡ ለዚህ አስቂኝ ጥያቄዋ የኢትዮጵያ መንግስት በቂ መልስ የሰጣት ቢሆንም፣ ሃሳቡን ምን ስትል አሰበችው ፤ሽምግልናውንስ ይዞ ለመምጣት ድፍረቱንስ ከየት አገኘችው ያሰኛል።
ይህ ዜና ሱዳን ሽምግልና ጠፍቷት ይሆን እንዴ ሊያሰኝ ይችል ይሆናል፤ እንደ እኔ በኢትዮጵያ ላይ የማትሸርበው ሴራ እንደሌለ እያወቀች ለሽምግልና የምትነሳ አይመስለኝም፤ ሊሆን የሚችለው የሆነ እየጋለባት ያለ አካል መኖሩ ነው፡፡ ይህን አረግልሻለሁ ኢትዮጵያን አሸማግዪ ሳትባል አትቀርም፡፡
ጎበዝ ስለ ሽምግልና ትንሽ ማለት የሚያስፈልግ መሰለኝ፡፡ ሽምግልና በማህበራዊ ፋይዳው ስንመለከተው እድሜን ብቻ የሚጠይቅ አይደለም፡፡ ከምንም በላይ ንጽህናን ይፈልጋል፡፡ ተሰሚነትን ይጠይቃል፡፡ እንደ ሀገርም ቢታይ የቆየ ወዳጅነት፣ ከሌለች ሀገሮች ጋር ያለ ቅርበትን ይጠይቃል፤ በአሁኑ ወቅት እንደ ሀገር፣ እንደ ጎረቤት ሀገር፣ ክፍለ አህጉር ፣ አህጉር፣ ዓለም አቀፍ ያለን ተጽእኖ ፈጣሪነትን ይፈልጋል፡፡
በአንድ ሀገር ለዚያም በጎረቤት ሀገር ጉዳይ ውስጥ እየፈተፈቱ፣ ሉአላዊነትን እየደፈሩ፣ የአንድን ሀገር ታጣቂ እያስጠለሉ እያሰለጠኑ፣ እየደገፉ፣ ወዘተ ሽማግሌ ለመሆን ማሰብ የጤናም አይመስለኝም፡፡ ሱዳን ኢትዮጵያን የማሸማገሉን ሀሳብ አውጥታው አውርዳው ያደረገችው ነው ብዬ አላስብም፡፡
ይሁን ሌላ አካል ልኳት ሳይሆን እንዳልቀረ ነው የምጠረጥረው፡፡ የሌላ ቡድን አጀንዳ ይዛ የመጣች ይመስለኛል፡፡ ይህም ቢሆን ሌላ ግዙፍ ስህተት ነው፡፡ የተላኩትን አንጠልጥሎ መሄድ አደጋ እንዳለው ያለመረዳትም ያለ ይመስለኛል፡፡ ለማናቸውም ሽምግልናውን ወድቃለች። በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ሽምግልናዋ ተቀባይነት እንደሌለው በጨዋ ቋንቋ ተነግሯታል፡፡ እስቲ እናጢነው እንኳ አልተባለችም፡፡
ኢትዮጵያውያን በየትኛውም ግጭት ወቅት መሃል ገብቶ “አንተም ተው እናንተም ተው” የሚልና ለችግሩ የመፍትሄ ሃሳብ የሚያመጣ የሽምግልና ባህል አላቸው፡፡ ይህን ባህል ያከብራሉ። በዚያው ልክ ለሽምግልና የማይበቃ ማንነት ያለው ግለሰብም ሆነ ቡድንን ይጸየፋሉ፡፡
በባህላችን መሰረት ክፉና ደጉን ያዩ ሽማግሌዎች የበዳይንም ሆነ የተበዳይን እሮሮ በማድመጥ ሰላምና እርቅን የሚያመጡ ሃሳቦችን በማፍለቅ ያስታርቃሉ። በተቃራኒው እድሜያቸው ለሽምግልና የበቁ ሆኖ ለማሸማገል አቅሙ ተሰሚነቱ የሌላቸው ደግሞ “የአሸማጋይነት” ክብር እንደማያገኙ ባህላዊ ማንነታችን በሚገባ ያሳያል። ለዚህ ነው አገረ ሱዳንን እየመሩ ያሉ ባለስልጣናት “እናሸማግላችሁ” ሲሉ ከቁም ነገሩ ይልቅ ቧልቱ ያመዘነብን።
ሱዳን አይደለም ለማሸማገል አሁን በኢትዮጵያ ውስጥ ስላለው አጠቃላይ ሁኔታ ትንፍሽ ለማለትም የሚያበቃቸው ነገር የለም፡፡ የግጭቱ ደጋፊ አንዳንዴም ጠንሳሽና ጠማቂ ሆኖ የሽማግሌ ሚና ይዞ ብቅ ማለት አይነት ጨዋታን እኛ ኢትዮጵያውያን “ቧልት” እንለዋለን። በዚህ ላይ ሱዳን በኢትዮጵያ ጉዳይ እጇ ክፉኛ ያደፈ እንደመሆኑ ለሽምግልና ሳይሆን የምትፈለገው በወንጀለኛነት ነው፡፡
ሱዳን ሆይ የአሁኑ ሽምግልና አልሰራም፡፡ ለከርሞ ለመሞከር የምታስቢ ከሆነ በቅድሚያ በሃይል ከያዝሽው የኢትዮጵያ ግዛት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ልቀቂ፡፡ አሸባሪው ህወሓትን መደገፍሽን አቁሚ፤ የምእራባውያኑ የጋሪ ፈረስ፣ የግብጽ መጫወቻ ከመሆን ውጪ፡፡
ይህን ይህን መፈጸም ስትችይ ሽምግልናው ትክክለኛ ቦታ ላይ ሲገኝ ይደርሳል። የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት አሁን “ሽምግልና” በሚያስፈልገው ግጭት ውስጥ አይደሉም። የአሸባሪውን ትህነግ ቀብር ለመፈጸም ርብርብ ላይ ናቸው፡፡ የሚበጀው በዚህ ቀብር ላይ ብትገኚ ነው፡፡
የኢትዮጵያ መንግስትም የሱዳን ባለስልጣናትን ሴራ እንደተረዳ ብንገነዘብም አሁን የያዘውን ቁርጠኛ አቋም አጠናክሮ ቀጥሎ ለጎረቤታችን ሱዳን “ሽምግልናም ወግ አለው” የሚል ተደጋጋሚ ምላሽ እንዲሰጥልን እንጠይቃለን። ሰላም!
የዮቶር ክንድ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 11/2013