በአገራችን ብዙ ጊዜ ሲዋከቡና ሲንገላቱ ከሚስተዋሉት (ልክ እንደ “አርቲስት”፣ “ዴሞክራሲ” ወዘተ) “ቃላት” (ጽንሰ-ሃሳቦች/አሃዞች) አንዱ ፍልስፍና ነው። ለዚህ ሁሉ ቃል ስቃይ ዋናው ምክንያት ደግሞ፤ “ሁላችንም” እንደምናውቀው ድፍረት ነው። ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም ደጋግመው “በሰለጠነው ዓለም ስልጣን ከእውቀት ይመነጫል፤ እኛ አገር ግን እውቀት ከስልጣን ይመነጫል።” እንዳሉትም ሆነ ሌሎች በዚህ ጽሑፍ የምንጠቅሳቸው እንደሚነግሩን ትልቁ ችግር የአመክኖ ትጥቅ መላላት ነው።
እጅጉን ከሚያስፈልገን እንጀምር – እዚህና እዛ እየረገጥንም ቢሆን ሃሳብ እንለዋወጥ። በተለይም የሰው ልጅ አስቀድሞ ከነበረው ሶስትነት (Negroid፣ Caucasoid እና Mongoloid) ተነስቶ ዛሬ ተቆጥሮ ወደ እማያልቅበት የብሄር ብዛት ላይ ስለመድረሱና ይህም እርስ በእርሱ ይተላለቅ ዘንድ ምክንያት አልባ ምክንያት መሆኑን በስሱ ተንተርሰን አንዳንድ ጉዳዮችን እናንሳ። ርእሳችንን “ሰውን ያለፍልስፍና–ፍልስፍናን ያለሰው” ማለታችንን በልባችን ይዘን እንዘለቅ።
ከሁሉ አስቀድሞ “የ”ሥነምግባር” ጽንሰ ሃሳቦች በሁሉም ማህበረሰብ ውስጥ ወጥ ትርጉም ያላቸው ናቸው ከሚለው የሁሉን አቀፎች (universalists) አቋምና፤ ሥነምግባር ከሰው ሰው፣ ከማህበረሰብ ማህበረሰብ ይለያያል ከሚለው የአንጻራውያን (subjectivist) እይታ አንጻር አመክኗዊ ማብራሪያ ይሰጣል” ተብሎ የተመሰከረለትን፤ በአጥኚዎቹም የፀደቀለትን የፍልስፍና ዘውግ (Ethicism) በእኛ አገር ምን ያህል ታውቋል፤ ተግባራዊስ ተደርጓል? ጉዳዩን ደራሲና ተርጓሚ አማረ ማሞ በ”የቀለም ጠብታ”ቸው ጠብ እንዳደረጉት – ያወያያል፤ ያነጋግራል፤ ያመራምራል። የ”አመክህኖ” ጉዳይም እንደዛው።
ከእደጥበብ ስራዎቻችን ጀምሮ፣ ከዘርዓያዕቆብ ቀዳሚ ፍልስፍናዎች ጀምሮ ምን እንደሆኑ በህዝባዊ ቋንቋ ሳንናገር፤ “ፍልስፍና ማለት” ምን ማለት ነው? ብለን ሳንጠይቅም ሆነ ሳንመልስ፣ ሰውን ከፍልስፍና፣ ፍልስፍናንም ከሰው ሳናገናኝ እንዴት አድርጎ በጉዳዩ ላይ መግባባት ይቻላል? አይቻልም። ዘርዓያዕቆብ “የእግዚአብሔር ህላዌነት፣ ሥነ ምግባር፣ እውነት፣ በዓለም ላይ ስላሉ ሃይማኖቶች እሰጣ’ገባ፣ ፍትህ፣ ስለመለኮታዊውና ሰዋዊ ሕግ፣ ማህበራዊ ኑሮና ዘመናዊነት” ላይ ከማንም ቀድሞና እርቆ ለእኛ፣ ለእራሳችን ካልጠቀመ ፋይዳው ምንድን ነው? “የሌለውን ፈላስፋ ፍለጋ” ጸሐፍትም ቢሆኑ በማይረባው ላይ ከማተኮር በሚበጀው ላይ፣ ሰውን ከፍልስፍና፤ ፍልስፍናንም ከሰው ማገናኘቱ ላይ ለምን አልተጉም? ያወያያል፤ ያነጋግራል፤ ያመራምራል።
“ዘርዓያዕቆብን የመካከለኛው ዘመን ፖስት ሞደርኒዝም አቀንቃኝ” መሆኑን፤ እንዲሁም “ዘርዓያዕቆብ የመካከለኛው ዘመን የዓለም ፍልስፍና ፈር ቀዳጅ” እንደሆነ በእነሰምነር በሚገባ ተነግሯል። ታዲያ የታል? ነው ወይስ ይዞት ወደ መቃብር ወረደ? ወይስ ድንጋይ ላይ ነበር ፍልስፍናውን ሲዘራው የነበረው? ካልሆነ ለምን የፍልስፍና ድርቅ ተከሰተ? ለምንስ የአመክህኖ ትጥቅ እጅጉን ላላ? ያወያያል፤ ያነጋግራል፤ ያመራምራል።
“ቋንቋ ያጣላል እንዴ?” በእኛ አገር ገና ያልተመለሰ ጥያቄ ነው። “ብሔር ምንድነው፣ ብሔረሰብስ?” ማንም ከማንም በሚባል ደረጃ ሁሉም አልገባውም ማስባል እሚቻልበት ደረጃ ላይ ነው ያለነው። የጋራ “ባህል፣ እሴት፣ ታሪክ ወዘተርፈ አለን/የለንም” የሚለው ገና መሳ ለመሳ ነው። ቶሎ ካልተጣረ፣ ወደ አንድ ለመምጣት መንገዱ ቀና ነው ጠመዝማዛ፣ ዳገት ነው ቁልቁለት ለማለት አይደለም ገና መንገድ መኖሩም ሆነ አለመኖሩ አልታወቀምና አማረ ማሞ እንዳሉት ሁሉ ገና ብዙ ስራ አለብን። (ከዚህ፣ በተለይም ከ”ብሄርተኝነት”/ናሽናሊዝም ጋር በተያያዘ በዘርፉ ጠልቆ መሄዱ የታመነለት የኧርነስት (Ernest André Gellner FRAI (1925 –1995))ን ስራዎች መመልከት ጠቃሚ ነው።)
እንደ አማረ ማሞ (ያወያያል፤ ያነጋግራል፤ ያመራምራል) ሁሉ ጥላሁን ገሠሠም “ኧረ ምን ያህል ነው … አሃሃሃ” እንዳለው ምን ያህሎቻችን ነን “ሽማግሌዎቿን፣ ጥበቦቿን፣ ታሪኮቿን፣ ቅርሶቿን የምትጥል ሐገር” የምንለው/የማንለው? ስለ ኢትዮጵያ ብለንም ይሁን/አይሁን፤ “ትፍረስ/አትፍረስ” የዘመኑን ነጠላ ዜማ የምናቀነቅን/የምናንቆረቁርስ በቁጥር ምን ያህል ነን?” ይህ ቁጥራችንስ እየጨመረ ነው እየቀነሰ? (ከላይ የጠቀስነው ኧርነስት ለእንደዚህ አይነት ጥያቄዎች መልስ የሚሰጡ ስራዎች አሉት።)
ስለዘርዓያዕቆብ “የሌለውን ፈላስፋ ፍለጋ” ተባለ እንጅ መች ፍልስፍናውንና ሰዋዊ ፋይዳውን ፍለጋ ተደከመ? ማርክስ እንዳለው፣ ሮሶ እንደ ፃፈው፣ ኒቸ እንደቀባጠረው፣ ለወሲብ የወገነው ፍሮይድ እንዳቆለጳጰሰው ወዘተርፈ ከማለት ውጪ “በአገርህ ላይ ክፉ አትይ፣ ክፉ አትስራ፣ ክፉ አትናገር” ያለውን አበሻ ማን አስታውሶት ያውቃል? ሎሬቱ ጨረቃ ላይ ያወጣትን ሰንደቅ ዓላማ እኛ ምን እያደረግናት ነው ብሎስ ቆም ብሎ ያሰበ አለ? ያስተዛዝባል፤ ያነጋግራልም።
“ሞክሼ የአማርኛ ቋንቋ ፊደላት ይቀጥሉ/ይነቀሉ” የሚለው የማይረባ አተካሮ ከተጀመረ ስንት ዓመቱ ነው? እንጃ። ግን አንድ ትውልድ ላይ መቆም አቅቶት እየተንከባለለ እዚህ መድረሱን መካካድ አይቻልምና በዚህ ትውልድ ችግሩ ይፈታ፣ ጥያቄው ይመለስ፣ በቋንቋው ውስጥ ያለው እምቅ የፍልስፍና ሀብትና ማንነት ተገቢውን ቦታ ያገኝ ዘንድ ይገባልና ጉዳዩ ፋታ የሚሰጥ ሳይሆን የሚያወያይ፣ የሚያነጋግርና የሚያመራምር መሆኑ ላይ ተስማምቶ አንዳች መደምደሚያ ላይ መድረስ ያስፈልጋልና ጉዳዩ አማረ እንዳሉት ነው።
ባለፈው አንዱን “የኢትዮጵያ የጀግንነት ፍልስፍና ምንድን ነው?” ብለው፤ “ደሞ ከመቼ ወዲህ ነው …” በሎኝ ጥሎኝ እብስ (አይፈረድበትም፤ “ፍልስፍና ማለት መጠየቅ ማለት ነው” ብቻ ተብሎ ሲነገረው ስለኖረ)። “እውነት የጀግንነት ፍልስፍና የለንም?” (ለነገሩ የጋራ ድል ባለበት አገር “የጋራ ጀግና የለንም” የሚሉም አሉ አይደል እንዴ)፣ የዘራፍ ዋጓው ስንት ነው፤ የቀረርቶ ትርጉሙ ምንድን ነው፣ የሽለላስ ፋይዳው ምን ይሆን?? እራስ አስይዘው የሚያስጮሁ ብዙ ጉዳዮች አሉ። መፍትሄው ግን ራስ ይዞ መጮህ፣ ጮሆም ማጮህና ማጯጯህ ሳይሆን አማረ “ያወያያል፤ ያነጋግራል፤ ያመራምራል” እንዳሉት ስለሆነ እዳው ገብስ ነው።
ቆይ ቆይ፣ ለመሆኑ በአገራችን ጤና አለ? የለም። ካለ በፌዴራሊዝሙ ለምን መግባባት አቃተን? ጦርነትን ምን አመጣው? በቋንቋ፣ ተረተር፣ ወንዝ፣ ጋራና ሸንተረር? የቱ (mode of government) ነው ለእኛ የሚበጀው? የሚናገር የለም። “ጉራ ብቻ!!!” – “ምላስና ሰንበር” እንደተባለው ሁሉም በያለበት ለየብቻው ያወራል እንጂ ወደ መሀል መምጣትን እንደጦር የሚፈራ ነው ስብስቡ ሁላ። ባለፈው ሳምንት ጽሁፋችን እንደተመለከትነው ኢትዮጵያን እንደአገሩ በማየት የሚለፋ እንዳለ ሁሉ ኢትዮጵያን እንደፕሮጀክቱ የያዘ ሁሉ አለና መሀሉ ባዶ ቢሆን አይገርምም።
እዚህ አገር ስነምግባር ቢኖር ኖሮ፣ አመክኗዊነት ቢኖር ኖሮ፣ ጤና ቢኖር ኖሮ …. ኖሮ …. ኖሮ ….፤ የእነ ጆን ሎክ ፍልስፍና በአሜሪካኖቹ፣ የእነጋንዲ በህንዶቹ፣ የኮንፊሺየስ በቻይናዎቹ ወዘተርፈ እንደሰረጸው ሁሉ የእነዘርዓያዕቆብ ፍልስፍና በእኛ ውስጥ ሰርፆ ቢሆን ኖሮ፣ የእነፀጋዬ መንፈስ በእኛ አድሮ ቢሆን ኖሮ፣ የአፈወርቅ “በአገርህ ላይ ክፉ …” ገብቶንና አድርገነው ቢሆን ኖሮ “ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦል መግባት ካለብን እንገባን” ይባል ነበር? አይባልም። ግን ተባለ፤ ለምን ብሎ የጠየቀ አለ? ይህ ጸሐፊ አንድ ሰው ያውቃል፤ “ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦል ድረስ ለምን?” በማለት የጠየቀውን የአዲስ አድማሱን ኤሊያስ።
“ፍልስፍና ማለት መጠየቅ ማለት ነው” የሚለው ሁሉ አልጠየቀም። ተናጋሪውን በቀቀን በሚገባው ቋንቋ “ምክንያትህን ዱብ አድርግ፤ አለበለዚያ ውርድ ከራሴ” ያለው አለ? እስካሁን የለም። “ኢትዮጵያን እንዳትፈርስ ሲኦል መግባት ካለብን እንገባን” በማለት እኩያ መልስ ከሰጠው አንድ ለእናቱ በስተቀርስ ማን ነው ይህን የ21ኛውን ክ/ዘ ደንቆሮ ኧረ በሕግ ያለው? እሚያነጋግር፣ እሚያወያይ ካለ ብዙ ጥያቄዎች ነበሩን፤ አሉንም።
የሰሞኑን “የዘር ፖለቲካን የሚያቀነቅኑ አክራሪ የብሔር ፓርቲዎችም ዋነኛ መሳሪያቸው ሃሰተኛ ትርክትና የጥላቻ ፕሮፓጋንዳ ነው። ደጋፊዎቻቸውን የሚያሰባስቡትና የሚያበዙት … “ተበድለሃል …”፣ “ተፈልጠሃል”፣ “ተቆርጠሃል” … “ተገርፈሃል”፣ “ተጨቁነሃል” ወዘተ…. የሚሉ የሃሰት ትርክቶችን ፈጥረው ነው፡፡ ያለዚያ ለደጋፊው የሚሰጡት ነገር የላቸውም (ያሳዝናል-ጥላቻ ዘርቶ ደጋፊ ማሰባሰብ!)፡፡” የሚለውን ያነበበ እንደ ጸሐፊው እሱም ማዘኑን የነገረን ማንም የለምና ጉዳዩ ያሳዝናል። እርግጥ ነው ሰሞኑን ድምፃዊ ቴዲ አፍሮ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክተሬት ዲግሪውን ሲቀበል ባደረጋት እጭር (እንደ’ሱ) ንግግር “ዘረኝነት እንደማንኛውም ፍልስፍና ተወልዶ፣ አድጎ […] የተፈጥሮ ሞቱን ሞቷል።” ማለቱን አንዘነጋም። (ከቴዲ አፍሮ የምናገኘው መጽናኛ ቢኖር “ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦል መግባት ካለብን እንገባለን” ያለው ተፈጥሯዊ ሞቱን መሞቱ የማይቀር መሆኑን ነውና ደስ ይላል።)
ሰሞኑን ባንከሩ ወዳጄ አብረሀም ማርቆስ በአንድ ጭውውታችን “ምንድነው እንደዚህ የትውልድ ክፍተት እንዲፈጠር ያደረገው? ‘የእኔ ብቻ ነው ትክክል’ የሚሉ አመለካከቶች (Racist attitudes) አልበዙም?” ሲል ደጋግሞ ያነሳውን ጥያቄ ይህ ጸሐፊም መጋራትና እንደገና መጠየቅ ይፈልጋል (“ባለፉት 27 ዓመታት…” የሚለው በቂ መልስ ነው ካልተባለ)።
ለዚህ የሰዎችን የግል የፖለቲካ ምርጫ (personal political choice)ና መብት (political rights)ን ሳይቀር የሚገድበው፣ በፖለቲካ ኢኮኖሚው ለማያባራ ውዝግብ፣ በአንድ አገር ውስጥ ለከፋ የእርስ በእርስ ጦርነት መንስኤ የሆነው የዘር ፖለቲካ (ቃሉ (Ethnicity) በኦክስፎርድ እንግሊዝኛ መዝገበ ቃላት ላይ ለመጀመሪያ የገባው በ1972 ነው) ላመጣው ችግር ብቸኛው መፍትሄ የዜግነት ፖለቲካ፣ (civic nationalism) የዜጋዊ ብሄርተኝነት የጋራ ቱባ እሴቶችን ማክበር ነው የሚሉ ወገኖች እየበዙ ነውና ተስፋ አለ ማለት ይሆን?
እንደእውነቱ ከሆነ ዛሬ አንዳንድ ሰዎች ዘረኝነትን እንደ አንድ ተቀባይነት እንዳለው የጥናት መስክ አድርገው ሲወስዱ፤ ሲነግሩንም ይታያል። ይህ ግን ስህተት ነው። ዘር፣ ጎሳ… እያሉ የሚቀጥሉ ቃላትም ሆነ የተሸከሙት ኮተት የፖለቲካ ፍልስፍና (political philosophy) ጉዳይ ወይም በዘርፉ ተቀባይነትን አግኝተው የተካተቱ አይደሉም። ዘርፉ እጅግ ይጠየፋቸዋል። በተለይም ከEthics ጋር ጭራሽ ፍቅር የላቸውም። እነዚህ ቃላት ከፍ ያለ ትኩረትን እንዲያገኙ ያደረጋቸው ሰው ተኮር መሆናቸውና ከሁሉም የጥናት ወይም እውቀት መስክ (ዲሲፕሊን) ጋር መገናኘታቸው ነው። ምን እያልነን ነው? በፖለቲካ ፍልስፍና ትኩረት የተቸራቸው ቃላት አይደሉም ነው። የዚህ ደግሞ መሰረቱ ፍልስፍና ሰው ሁሉ (ሁለንታዊ/ዩኒቨርሳል) መሆኑ ነው። ልዩ ትኩረት አላቸው ወይም ያገኛሉ ከተባለም በፖለቲከ ኢኮኖሚ (political economic)ው ዘርፍ ነው። (እዚህ ላይ ሬሲስት ፈላስፎች የሉም እያልን እንዳልሆነ ግን ሊታወቅልን ይገባል።)
አሁን ጥያቄው እኛ አገር የስነምግባር፣ የሞራል፣ የፖለቲካ ወዘተ ፍልስፍና አቀንቃኝ ነው ያለው ወይስ በተቃራኒው የሬሲዝም አፈቀላጤ? አማረ ባይሉትም ጉዳዩ ያነጋግራል፣ ያነጫንጫል፣ ያበሳጫል።
አሁን ወደ ከፊል ርዕሳችን፣ ፍልስፍና ምንም አይነት የውስብስብነት ባህርይ የለውም፤ ግልጽ ነው። ግልጽነቱ ደግሞ ከአንባቢው ወይም ጸሐፊው የመረዳት /በመደነቅ/ መገረም አቅም የሚመነጭ ነው። በመሆኑም የጥናት መስኩን በመሳሪያነት በመጠቀም ወደ ምክንያታዊነት መምጣት ይገባል። የችግሮቻችን መፍቻ ቁልፍም አድርገን ልንጠቀምበት ግድ ነው። “ዘርዓያዕቆብ የፍልስፍና ት/ቤት /ZaraYacob School of Philosophy”ን የመሳሰሉ ተቋማትም ከማህበራዊ ሚዲያው በተጨማሪ በምድርም ይበዙልን ዘንድ ምኞታችን ነው። በየተቋማቱም፣ በሁሉም ስፍራ ምክንያታዊ፣ አመክኗዊ … ባለሙያዎች ይኖሩ ዘንድ “institutionalized philosophy” እንደሚሉት የተጠናከሩ የፍልስፍና አስተምህሮዎች የሚሰጡበት ሁኔታ እንዲፈጠር እንጸልያለን። የሰው ልጅ ጭራሹን ከመተላለቁ በፊት እንዳይተላለቅ የሚያደርገው ዋናው መድሃኒት ምክንያታዊ፣ አመክኗዊ መሆን ነውና እሱን ለመሆን እንጣር የሚለው ከቅድመ ሶቅራጥስ ፈላስፎች ጀምሮ እስከ 20ኛው ክ/ዘ ድንቅ ፈላስፋ ሉድቪግ ቪትገንስታይን (Ludwig Wittgenstein፣ 1889–1951) ድረስ እየተጮኸበት ያለ ቁልፍ ሰዋዊ-ፍልስፍናዊ ጉዳይ ነው።
ኢማኑኤል ኦላሌካንና ኡቼ ሳሙኤል በPhilosophy and National Development ጥናታቸው የሚሉን ይህንኑ ነው – በተለይ በአፍሪካ። እስከዛሬ እንደታየው ሌሎች የሙያ ዘርፎች (ሕግ፣ ህክምና፣ ኢኮኖሚክስ ወዘተ) የአህጉሪቱን ችግሮች ሊፈቱ አልቻሉምና የያዙትን ስፍራ ለፍልስፍና ሊሰጡ ይገባል ነው የሚሉት አፍሪካውያኑ የፍልስፍና ምሁራንና ተመራማሪዎች።
አገራችን ልክ እንደነፓፑዋ (Papua New Guinea፣ በኦሺኒያ በኒው ጊኒ ደሴት ላይ የምትገኝና በ1975 ሉአላዊነቷን የመሰረተች ሀገር ነች) አይነት ችግሮችን ለማስተናገዷ ምክንያቱ የዚህ አይነቱ የእውቀት ክፍተት ሲሆን፤ ከኢማኑኤልና ኡቼ ጥናትም የምንረዳው ይህንኑ ነው። (አዲሱ የአገራችን “የትምህርት ፍኖተ ካርታ”ም እንደ አንድ ቁልፍ ጉዳይ አስተናግዶታልና ስለ ተግባራዊነቱ ወደፊት የምናየው ይሆናል።)
ዛሬ በሺዎች የሚቆጠሩ የተለያዩ ቋንቋዎችን የሚናገሩ ሰዎች (ethnic groups) ያሉባቸው አገራት በሰላም እየኖሩ፤ ከ800 በላይ ቋንቋዎች የሚነገሩባት ኒው ዮርክ ከተማ በሰላም ውላ እያደረች፤ እኛ በአገር ደረጃ 80 ቋንቋዎችን ብቻ ይዘን እንዲህ ለመሆናችን ምክንያቱ ምንድነው? የጤና ጉድለት፣ የእውቀት እጥረት፣ የአመክኖ ትጥቅ መላላት?” አያነጋግርም፣ አያወያይም??
ከትንሿ የመንደር ቤተመጻሕፍት እስከ ትልቁ አየር መንገድ ድረስ ባሉት ተቋማቱ በዜግነት (national identity) ላይ አጥብቆ የሚሰራ፣ እንደ ጃፓን አይነት መንግሥት ያስፈልገናል/አያስፈልገንም? ብሎ የሚጠይቅና የሚጨነቅ ቢኖርስ? ጉዳዩ ከፍላጎት፣ ነፃ ፍቃድ ወዘተ አኳያ ብቻ ሳይሆን ከፖለቲካ መብት አንፃር፤ ከአገር ማፍረስና መፍረስ ተግባር ወዘተ አኳያ እንዴት ይታያል? የፕሌቶን (Republic) “ቁንጮ መሪ” (philosopher king)ስ ማንሳት ይቻላል ወይስ አይቻልም? ይቻላል። ካልተቻለ ችግር አለ ማለት ነውና አሁንም አማረ እንዳሉት ነው ማለት ነው። ከፖለቲካው ወደ ሌሎች ዘርፎች እንሂድ።
ከበርካታ የጥናት ውጤቶች አንዱ እንደሚነግረን የንግዱ ዓለም እንዲህ ቅጡን ያጣው ከቢዝነስ አስተዳደር (MBA) ተመርቀው የሚወጡ የቢዝነስ ተቋማት ሃላፊዎች ከሙያ ትምህርቱ ጎን ለጎን የፍልስፍና ትምህርትን አለመውሰዳቸውና ችግሮቻቸውን ሊፈቱበት የሚያስችላቸውን እውቀት አለመታጠቃቸው መሆኑን Philosopher Versus MBA How Academic Pursuits Impact Entrepreneurship በሚል ጥናታቸው ደርሰንበታል ብለዋል። እንደአጥኚው (REID HOFFMAN) አስተያየት በየትኛውም የጥናት መስክ የሚሰማሩና አጠናቅቀው የሚወጡ ምሩቃን ዘርፈ ብዙ እውቀት ይዘው የተለያዩ አቀራረቦችን (multidisciplinary approach) በመጠቀም ውጤታማ ይሆኑ፣ ለሰው ልጅ ምቹ የሆኑ አገልግሎቶችን ያቀርቡ/ይሰጡ ዘንድ በ“እና” የተጣመረ የፍልስፍና ትምህርትን መውሰድ ይገባቸዋል፤ ለምሳሌም Philosophy and Politics, Philosophy and Economics, Philosophy and Physics ወዘተ። ይህ ካልተደረገ ሁሉም ነገር የተዋጣለት፣ ሰውን ማእከል ያደረገና ስለ ሰው ልጅ ግድ የሚለው አመራር (compassionate management and leadership ይሉታል) ይኖራል ብሎ መጠበቅ መጃጃል ነው። “ሰውን ያለፍልስፍና–ፍልስፍናን ያለሰው” ብለን ስንነሳም (የላዩ እታች ሆኖብን እንጂ) መሰረታችን ይኸው ነበር።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 11/2013