ልጆች እንደምን ሰነበታችሁ? እረፍት እንዴት ነው? እንደመከርኳችሁ በደንብ እያነበባችሁ ነው አይደል? ሰሞኑን ኤልቤቴል የተባለ ትምህርት ቤት የኬጂ ተማሪዎች ምረቃ መርሐ ግብር ላይ ተገኝቼ ነበር። በዛ ወቅት ያገኘኋቸው ህፃናት በጣም ማንበብ የሚወዱ ሲያድጉ መሆን ለሚፈልጉት ነገር በትምህርት መጎበዝ እንዳለባቸው የሚያወቁ ልጆች ናቸው።
ልጆቹ በምርቃ ዝግጅታቸው ላይ የተለያዩ ግጥሞችን እንቆቅልሾችንና የተማሯቸውን ነገሮች በሙሉ ለወላጆችና ለተጋባዥ እንግዶች አቅርበው ነበር።
በምረቃ ሥነሥርዓቱ ላይ መድረክ መሪ የነበረችው ተመራቂ ተማሪ የማሪያም ረድኤት በጣም ጎበዝ የማትፈራ፤ አዳራሽ ሙሉ ሰው ፊት ፕሮግራሙን እያስተዋወቀች የነበርች ልጅ ናት። ተማሪ የማሪያም ሰባት ዓመቷ ሲሆን የኬጂ ትምህርቷን አጠናቃ አንደኛ ክፍል የሚያስገባት ጊዜ ላይ ደርሳለች። የማሪያም በትምህርት ቤታቸው ካሉ የመጨረሻ ዓመት የኬጂ ተማሪዎች ባጠቃላይ አንድም ኤክስ ያላገኘች ተብላ ተሸልማለች። የማሪያም ስታድግ አውሮፕላን አብራሪ መሆን ነው የምትፈልገው።
ይሄም እንዲሳካላት የፃፈችውን በድንብ እያነበበችና የቤት ሥራዋን በደንብ እየሰራች ለዚህ ደረጃ መብቃቷን ትናገራለች። ልጆች እናንተም እንደ የማሪያም ትልቅ ቦታ ለመድረስ ታልማላችሁ? የማሪያም አውሮፕላን አብራሪ ለመሆን ጎብዝ ተማሪ መሆን ስለሚያስፈልግ ጎበዝ ተማሪ ለመሆን በርትታ ትሰራለች።
ከየማሪያም ጋር መድረክ ሲመራ የነበረው ተማሪ ጂሰን ተሻለም ከሚማርበት ክፍል አንደኛ እንደሚወጣ ነግሮናል። ተማሪ ጂሰን ከአማርኛም በተጨማሪ የእንግሊዘኛ መፅሐፍትን በማንበብ ጠቅላላ እውቀቱን አሳድጓል። ጂሰን ዶክተር የመሆን ህልም አለው። ህልሙንም ለማሳካት ሁልጊዜ የሚያነብ መሆኑን ነግሮናል።
በምርቃ ፕሮግራሙ ላይ እንቆቅልሽ ያቀረበው ተማሪ ሚካኤል ፍቅረማሪያምም ከክፍሉ ሶስተኛ የወጣ ሲሆን ሲያድግ አውሮፕላን አብራሪ መሆን የሚፈልግ መሆኑን ይገልፃል። አውሮፕላን አብራሪ ለመሆን ሁልጊዜ እንደሚያጠና የነገረን ሚካኤል እንድትኖረው የሚፈልጋትን አይነት አውሮፕላን ከእህቶቹ ጋር በመሆን በካርቶን ለመስራት እየሞከረ እንደሆነ ይገልፃል።
አውሮፕላን አብራሪ ለመሆን ለምን ፈለግህ ስንል ላቀረብንለት ጥያቄ እናቱን ከጎን አስቀምጦ ለመብረር እንደሚፈልግ ነግሮናል። ህልሙ እንዲሳካለት ተመኝተን ሚካኤል በምረቃ መድረኩ ላይ ካቀረበው እንቆቅልሾች ሁለቱን እነሆ ብለናል ።
እንቆቅልሽ
ምን አውቅልህ
ዞራ ዞራ እራቷ ጥፊ
ወንፊት
እንቆቅልህ
ምን አውቅልህ
የምትበላው ሰርቃ የመትኖረው ተደብቃ
አይጥ
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ነሐሴ 9/2013