ባለፈው ሳምንት ዓርብ ምሽት ለመከላከያ ሠራዊቱ የድጋፍ የኪነ ጥበብ መርሐ ግብር በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቴአትር ተከናውኖ ነበር። ድጋፍ ለተደረገለት መከላከያ ሠራዊት የሚመጥን የኪነ ጥበብ ቡፌ በብሔራዊ ቴአትር መድረክ ተዘርግቶ ታዳሚው ሲቋደስ አምሽቷል። መድረኩ ከቀረቡበት ጠንካራ የኪነ ጥበብ ሥራዎች አኳያ ሲታይ ታሪካዊውን የህዝብ ለህዝብ የኪነ ጥበብ ዘመቻ ያስታውሳል ሲሉም በደርግ ወቅት የኪነጥበብ ባለሙያዎች በመላ ዓለም እየተዘዋወሩ ያቀረቡትን የህዝብ ለህዝብ ኪነጥበብ ዝግጅት የሚያውቁ ተናግረዋል። እስኪ መድረኩን እንዳስሰው…
የመድረኩ ታዳሚዎች ከመርሐ ግብሩ መጀመር ቀደም ብለው ደርሰዋል፤ የተቀበላቸው ደግሞ የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የማርች ባንድ ነበር። ባንዱ ለእንግዶች የእንኳን ደህና መጣችሁ በሚል ሲያቀርባቸው የነበሩ ተወዳጅ የዘመቻ ሙዚቃዎች የታዳሚዎቹን ብቻ ሳይሆን በብሄራዊ ቴአትር ደጅ የሚያልፉ የሚያገድሙትን ቀልብ ጭምር በእጅጉ ስቧል። ብዙዎች ጆሯቸውን ዓይናቸውን በአጠቃላይ ቀልባቸውን እንዲሰጡት ያስገደደ ነበር።
ከቀኑ 11 ሰዓት ሲሆን፤ ድግሱ በኢትዮጵያ ህዝብ ብሄራዊ መዝሙር ተጀመረ። ታዳሚዎች ከመቀመጫቸው ተነስተው በማርሽ ባንዱ እየተመሩ ደመቅ አድርገው ዘመሩ። ከዚያም የመድረኩ አጋፋሪ ቀጣዩ መርሐ ግብር የሰርከስ ትርዒት መሆኑን አስታወቀ። አቅራቢዎቹም ሰርከስ ኢትዮጵያ እና አዲስ አበባ ሰርከስ ቡድን ነበሩ።
ወትሮውንም ቢሆን የተመልካችን ልብ ሰቅዞ የሚይዘው የሰርከስ ትርዒት የኢትዮጵያዊነት መልዕክት ተጨምሮበት ተመልካቹን ከፍ ያለ ስሜት ውስጥ ከተተው። በተለይም የሰርከስ ቡድኑ አባላት እርስ በርስ ተደራርበው በሠሩት ከፍታ ላይ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ አርገው ሲያውለበልቡ ተመልካቹ ሞቅ ያለ ጭብጨባ ከመለገስ በቀር አማራጭ አልነበረውም።
የዕለቱን መርሐ ግብር በማስመልከት ንግግር ያሰሙት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማህበራዊ ጉዳይ አማካሪ እና የመርሐ ግብሩ አስተባባሪ ረዳት ፕሮፌሰር ነቢዩ ባዬ ባሰሙት ንግግር ኢትዮጵያዊነትን ‹‹ይሞታል ሲሉት የሚያብብ” ሲሉ ገልጸውታል። በእንዲህ ዓይነቶቹ አስቸጋሪ ጊዜያት ኢትዮጵያውያን ማንነታቸውን እንደሚያስታውሱም ተናግረዋል።
ወቅቱ ከጥበብ አኳያ ታላላቅ የኪነ ጥበብ ሥራዎች የሚሠሩበት እንደነበር የጠቀሱት ረዳት ፕሮፌሰሩ፣ ለዚህም ተወዳጆቹን የእነ ጥላሁን ገሰሰ “እናት ሀገር ኢትዮጵያ” እና የመሀሙድ አህመድ “ተከብረሽ የኖርሽው” ሙዚቃዎችን አስታውሰዋል። አሁንም ሀገር አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ መሆኗን በመጥቀስ፣ ማንኛውም የኪነ ጥበብ ባለሙያ በሚችለው መልኩ ሙያዊ አገልግሎቱን በመስጠት የሕለውና ዘመቻውን እንዲደግፍ ጥሪ አቅርበዋል።
የኦሮሚያ ባህል ማዕከል እና የኦሮሚያ አርቲስቶች ማህበርም በኦሮምኛ ቋንቋ ህብረ ዝማሬ አቅርበዋል። ከዚያም በአማርኛ ቋንቋ እሳት የላሰች አንዲት ፍሬ ልጅ “እውን አባትህ አንተን ወለደ?” የሚል ቃለ ተውኔት አቀረበች። በዕንባ የታጀበው የወጣቷ አቀራረብ የድግሱን ታዳሚዎች ወደ መድረክ እየወጡ እንዲሸልሟት አስገደዳቸው።
በኦሮምኛ ቋንቋም ተውኔት የቀረበ ሲሆን፣ የተውኔቱ መልዕክት ኦሮምኛ ቋንቋን ለማይሰሙት ሁሉ ግልጽ ነበር። በነገራችን ላይ የኦሮሞ አርቲስቶች ማህበር ከሁሉም የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ቀድሞ ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ ለመከላከያ ሠራዊቱ ድጋፍ የኪነ ጥበብ ድግስ በኦሮሚያ ባህል ማዕከል አዘጋጅቶ አቅርቧል።
ወትድርናን እና የጥበብ ሰውነትን አስተባብረው የያዙት የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ጌትነት አዳነም በመድረኩ ላይ ንግግር አደረገዋል። በንግግራቸው መግቢያ በቆሙበት የብሄራዊ ቴአትር መድረክ ላይ ‹‹ሀገር ማለት ሰው ነው እና አፋጀሽኝ›› የሚሉ ተውኔቶች መተወናቸውን ጠቅሰው፣ የንግግራቸው ዋነኛ መልዕክትም “መባባት አያስፈልግም” የሚል ነበር። ‹‹ኢትዮጵያን ማሸነፍ አይቻልም›› ያሉት ኮሎኔል ጌትነት፣ ኢትዮጵያውያን በሚሰሙት ወሬ መረበሽ እንደሌለባቸውም አስገንዝበዋል።
የብሄራዊ ቴአትር የሙዚቃ ቡድን ዝማሬም ሌላው የመድረኩ ጌጥ ሆኖ አምሽቷል። መድረኩን የያዘው ታዋቂው ገጣሚ ኤፍሬም ስዩም “እመሰክራለሁ፤ እናገራለሁ ሀቅ” በሚል ርዕስ በብእሩ የኢትዮጵያን ልእልና አውጇል። ከእርሱም በመቀጠል አርቲስት የማታወርቅ ደስታ የታላቁን የጥበብ ሰው ገብረክርስቶስ ደስታ ግጥም በግሩም አቀራረብ በአዳራሹ እየተንጎማለለ አቅርቧል።
ቀጣይ ተረኞች ደግሞ የኢትዮጵያዊነት ውዝዋዜ ቡድን ነበር። ኢትዮጵዊነቶች ኢትዮጵያ ለሚለው ስም የሚመጥን ሥራ በማቅረብ ይታወቃሉ። የዚያን ቀንም መድረኩን ብቻ ሳይሆን የተመልካችንም ቀልብ ለመውሰድ የፈጀባቸው ጥቂት ደቂቃ ነበር።
ስሜትን የሚኮረኩር ውዝዋዜ አቅርበው እነሱ ከመድረክ ሲወርዱ ተመልካቹ ግን እነሱን ለማድነቅ ከመቀመጫው ተነስቶ እያጨበጨበ ነበር። ከኢትዮጵነት የውዝዋዜ ቡድን በኋላ በኢትዮጵያም ሆነ በአፍሪካ ብርቅዬ የሆነው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቴአትር ቫራይቲ ኦርኬስትራ ስለ ሀገር የተዘፈኑ ሙዚቃዎችን በሦስት ድምፃውያን አቅርቧል።
ወደ መርሐ ግብሩ ማገባደጃ ላይ ኮሜዲ ሥራቸውን ይዘው ወደመድረክ ብቅ ያሉት የኮሜድያን ማህበር አባላት በሳቅ እያዋዙ በውጭ ሀገራት የሚገኙ የጁንታው ደጋፊዎችን ሸንቆጥ አድርገዋል። ከነጮቹ ይልቅ እኛ ወንድሞቻችሁ ኢትዮጵያውያን እንሻላችኋለን የሚል መልዕክትም ለጁንታው ደጋፊዎች አስተላልፈዋል።
የዕለቱ ድግስ የመጨረሻ ተናጋሪ በቀድሞው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የአየር ወለድ አዛዥ ሆነው ብዙ ጀብድ የፈጸሙት እና ብዙ ጀብደኞችን የመሩት ብርጋዴር ጄነራል ተስፋዬ ሀብተማርያም ነበሩ። ብርጋዴር ጄነራሉ እርጅና እየዳበሳቸው ቢሆንም ኢትዮጵያዊ ስሜታቸው ግን ገና የወጣት ነው። በመለዩአቸው ተውበው መድረኩን ከተቆጣጠሩ በኋላ ይህን መለዮ የለበሱት ከሦስት አስርት ዓመታት በኋላ መሆኑን እና ይህም ለዘመቻ ዝግጁ መሆናቸውን ለማሳየት እንደሆነ ገልጸዋል። በጃንሆይ ፤ በደርግ እና በኢትዮ ኤርትራ ዘመቻ ሀገራቸውን ያገለገሉት ሰው አሁንም ከታዘዙ ለሀገራቸው ለመሞት ዝግጁ መሆናቸውን ሲናገሩ በታዳሚው ዘንድ ግሩም ስሜት ፈጥረዋል።
መርሐ ግብሩ ውብ ነበር። በመድረኩ የቀረቡት ሥራዎች በሙሉ እንከን የማይወጣላቸው ሥራዎች ነበሩ። አሁን የሚፈለገው ነገር ይህን መርሐ ግብር ይዞ በየክልሉ መጓዝ እና ህዝብን ማንቃት ነው።
አዘጋጆቹ ልብ ሊሉት የሚገባ እንዲህ ዓይነት ሥራዎችን ማቅረብ በቴአትር ቤት ውስጥ የሚገኙ ባለሙያዎች ግዴታ ብቻ እንዳልሆኑ ነው። ልክ እንደነ ገጣሚ ኤፍሬም ስዩም ሁሉ ፤ ልክ እንደ ኢትዮጵዊነት የውዝዋዜ ቡድን ሁሉ ሌሎችም በግል የሚንቀሳቀሱ አርቲስቶች ይህን እንቅስቃሴ ማገዝ አለባቸው። ይህ ወቅት መሽኮርመም እና መጋበዝ የሚቻልበት ጊዜ ሳይሆን እኔ ልቅደም ተብሎ ለመስዋእትነት የሚሻሙበት ነው። በዚህ ጊዜ የሚደበቅ አርቲስት ነገ በታሪክ መዝገብ ከሚጎድሉት መሀከል ይሆናል።
አቤል ገ/ኪዳን
አዲስ ዘመን ነሐሴ 9/2013