
የዛምቢያ ዜጎች ፕሬዚዳንታቸው እና ተፎካካሪ ያቸው በደቡብ አፍሪካዊቷ ሀገር የተረጋጋ ዴሞክራሲን ለማስፈን ውጥረት በተሞላበት ሁኔታ 3ኛውን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ሀሙስ ዕለት አካሂዳለች።
የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ኤድጋር ሉንጉ ለ3ተኛ ጊዜ በፕሬዚዳንትነት ለመመረጥ በዕጩነት የቀረቡ ሲሆን፤ ዋነኛ ተፎካካሪያቸው የሆኑት አንጋፋ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ኪንዳይቺ ሊማ ጋር ከፍተኛ ፉክክር የተደረገበት ነው።
በሬውተርስ ዘገባ መሰረት ዛምቢያ በከፍተኛ እዳ እና እየተንገዳገደ በሚገኘው ኢኮኖሚ ውስጥ ባለችበት ወቅት በምታደርገው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫው የተፎካካሪዎቹ ውጤት የተቀራረበ ሆኖ ይገኛል።
ወደ ፖለቲካው ከመግባታቸው በፊት የሕግ ባለሙያ የነበሩት የ64 ዓመቱ ኤድጋር ሉንጉ እ.ኤ.አ ከ2005 ጀምሮ በስልጣን ላይ ይገኛሉ። ጥቁር ሌዘር ቆዳ ለብሰው እና ነጭ ማስክ አድርገው በማለዳ ድምፅ ከሰጡ ከቀዳሚዎቹ መራጮች መካከል አንዱ ናቸው።
ዛምቢያውያን በተጨናነቀው የምርጫ ጣቢያዎች ተገኝተው ድምፃቸውን የሰጡ ሲሆን፤ የምርጫ ጣቢያዎች ምሽት 12 ሰዓት በይፋ ያበቃ ቢሆንም በርካታ ጣቢያዎች ላይ ምርጫ ሲደረግ እንደነበርም ተዘግቧል።
በዛምቢያ ቀደም ተብሎ ከተዘጋው ዋትስአፕ በተጨማሪ የማህበራዊ ብዙሃን መገናኛዎች እና ትዊተር፣ ኢንስታግራም እና ሚሴንጀርን ጨምሮ ሌሎች የመልዕክት መላላኪያ አውታሮች በምርጫው ዕለት ተዘግተው መቆየታቸውም ኔትብሎክስ ትዊተር ላይ አስፍሯል።
የዛምቢያ የምርጫ ኮሚሽን እንደገለጸው ከሰባት ሚሊዮን በላይ ሰዎች ወይም ከ83 በመቶ በላይ ብቁ ከሆኑ መራጮች ድምፅ ለመስጠት ተመዝግበዋል።
ፕሬዚዳንት ኤድጋር ሉንጉ በመሰረተ ልማት ግንባታዎች በተለይም በቻይና የገንዘብ ድጋፍ እና እንደ ዘር እና ማዳበሪያ ያሉ የግብርና ግብዓቶች በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ አርሶ አደሮች በማሰራጨታቸው አሸናፊ የሚሆኑበት ድምፆችን አስቀድመው ሲያሰሉ ነበር።
የ59 ዓመቱ ተቀናቃኛቸው ኪንዳይቺ ሊማ በ18 ሚሊዮን ህዝብ ሀገር ውስጥ በፕሬዚዳንትነት በተወዳደሩበት ምርጫው አሸናፊ ከሆኑ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ፣ በመንገዳገድ ላይ ያለውን የዛምቢያ ኢኮኖሚ በተሻለ ሁኔታ ለማስተዳደር እና የተንሰራፋውን ሙስና ለማጥፋት እችላለሁ በማለት ነጋዴ እንደነበረ በማንሳት የኋላ ታሪካቸውን ገልጸዋል።
በምርጫው ዋዜማ ለጋዜጠኞች እንደገለጹት “ምርጫው የመንግሥት ለውጥን ሊያስከትል ይገባል” ብለዋል። በአንድ ወቅት በማደግ ላይ ባለው የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በከፍተኛ ሁኔታ ማሽቆልቆል ያመጣቸው ችግሮች ዛምቢያውያን ለለውጥ እንዲመርጡ ይገፋፋቸዋል የሚል ተስፋ አላቸው።
የፕሬዚዳንት ሉንጉን ተቺዎች ከወዲሁ “አንዳንድ የመገናኛ ብዙሃን አውታሮችን በመዝጋት፣ ተቃዋሚዎችን በማሰርና የሚተቿቸውን ሰዎች በማሳደድ ዴሞክራሲያዊ መብቶችን እያፈኑ ነው” ብለዋል።
ሂዩማን ራይትስ ባለፈው ሰኔ ባወጣው ሪፖርቱ ሉንጉ ዛምቢያን ወደ ሰብዓዊ መብት ቀውስ አፋፍ እየወሰዷት መሆናቸውን በመንቀፍ ተችቶ ነበር።
ኤድጋር ሉንጉ በመሰረተ ልማት ኢንቨስትመንትና በመአድን ዙርያ ዘመቻ በማካሄድ ላይ ሲሆኑ፤ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ የ70 በመቶ ድርሻ ያለውን ኮፐር ለፖለቲካ መሳርያ መጠቀማቸው ተገቢ አለመሆኑንም በርካቶች በማንሳት ላይ ናቸው። የሀገሪቱ ባለሀብቶች በኮፐር አምራቿ ሀገር የሚካሄደውን ምርጫ በቅርበት እየተመለከቱት ይገኛል።
የዓለም አቀፉ ገንዘብ ድርጅት /አይአምኤፍ/ በበኩሉ ለደሃ ሀገራት እንደሚያደርገው ድጋፍ ሁሉ ለዛምቢያ የሚያደርገው ድጋፍ ምርጫው አስኪያልፍ ገታ ለማድረግ መስማማቱን አስታውቋል።
በኃይሉ አበራ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 8/2013