ክፍል አንድ (የመስክ ስራና መስከኛው)
ምሽት ላይ ከቢሮ ልወጣ በመሰናዳት ላይ እያለሁ፤ አለቃዬ አንድ ደብዳቤ ይዞ ወደኔ ቀረበ። “ነገ አንድ ጉዞ አለ” ብሎ በነጋታው ለስራ ከከተማ የሚያስወጣ የመስክ ስራ እንዳለ ነገረኝ። ያው ጋዜጠኛና ሀኪም የራሱ የሆነ መርሀ ግብር የለውምና ሳይነገረኝ ሳልዘጋጅ ሂድ ለምን ተባልኩ? ሳልል እንደ ተለመደው ትዕዛዙን ተቀበልኩ። ከቢሮ ወጥቼ እቤት እስክደርስ ስለመስክ ስራው ጉዞና ስራ ብዙ አሰብኩ። ከዚህ በፊት በስራ አጋጣሚ ወይም በሌላ የሄድኩበት ስላልሆነ አዲስ አካባቢ ለማየት የሚያስችለኝ በመሆኑ መሄዴን አልጠላሁትም።
እቤት ገብቼ በነጋታው ለጉዞ የሚሆነኝን የድምፅ መቅረጫና ለምሄድበት አካባቢ የአየር ሁኔታ የሚሆኑ አልባሳት አዘጋጅቼ ቶሎ መንቃት እንድችል አላርም ሞልቼ በጊዜ ተኛሁ።
እንዲቀሰቅሰኝ ራስጌዬ ያደረኩት ሰዓት ቀጠሮውን አክብሮ ባልኩት ሰዓት እሪታውን ሲያቀልጠው ተነስቼ ለቅለቅ ብዬ ለጉዞና ለስራዬ የሚሆነኝን አንግቤ ሳይረፍድ ለመድረስ ከቤት ወጣሁ። ሰፈሬ ለታክሲ ብዙም ስለማይመች የመኖሪያ ቤቴ ህንፃ ደረጃዎች ቁልቁል እየወረድኩ ካሰብኩበት የሚያደርሰኝ ታክሲ(ራይድ) አዘዝኩ። ከህንፃው ወርጄ 3 ደቂቃ ሳልቆም ባለ ራይዱ ከተፍ ብሎ ይዞኝ ወደሳብኩበት ቦታ ይከንፍ ጀመር።
እጅግ መሮጡ አልወደድኩትም እንጂ መፍጠኑ ደስ ብሎኛል። ቀን ላይ በትራፊክ የሚጨናነቁት የአዲስ አበባ መንገዶች ለካስ እንዲህ ንጋት ላይ ክፍትና ለመንዳት ምጩ ናቸው? ከሹፌሩ ጋር ቀን ስለሚታየው የትራፊክ መጨናነቅና የምሽትና ንጋት የመንገድ ባዶ መሆንና ምቹነት እያወራን ከጉዞው መነሻ ቦታ ደረስኩ።
መነሻ ከኢፌዲሪ ባህልና ቱሪዚም ሚኒስቴር። ጉዞ ወደ አፄ ሚኒሊክ አገር አንኮበር። ጉዳዩ የተቋሙ ሰራተኞች በአንኮበር የሚያካሂዱት የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ነው። የሚዲያ ባለሙያዎችም ተከትለዋቸዋል። በሚኒስቴሩ መልዕክት ወይም ደብዳቤ ላይ ሁሉም ተጓዥ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በር ላይ ከጠዋቱ 12 ሰዓት መገኘት እንዳለበት ያስገነዝባል። እኔም ይህን ተረድቼ ነው ሳላረፍድ መድረስ አለብን ብዬ በመወሰኔ ማልጄ መገኘቴ።
አካባቢው ላይ ስደርስ ያገኘሁት አንድ ኮስትር መኪና ብቻ ነው። ጠጋ ብዬ ሳናግረው ለሚዲያዎች ጉዞ የተዘጋጀ መሆኑን ነገረኝና ወደመኪናው ሆድ ጠለኩ። ከሹፌሩ ሌላ አንድ ሰው ብቻ ነበር መኪና ውስጥ ያገኘሁት። መኪናውና ይህ ሰው ብቻ ናቸው የቀደሙኝ።
ባየሁት ነገር ግራ በመጋባት “ምነው ገና ነው ማለት ነው?” ብዬ ጠየኩ። “አዬ የሀበሻ ነገር ታውቅ የለ፤ መች ቀጠሮ ይከበርና ሲል አሽከርካሪው መለሰለኝ። መርጬ ቦታ ይዤ አብረውኝ የሚጓዙ የሚዲያ ባለሙያዎች እስኪመጡ መጠበቅ ጀመርን።
ቀስ በቀስ ለጉዞ ከተለያዩ ተቋማት የተመደቡ ጋዜጠኞች መሰባሰብ ጀመሩ። እኔ የተጓዦቹ ሰዓት አክብሮ ቦታው ላይ አለመገኘትና የሌሎች ተጓዦች አጠቃላይ ሁኔታ ማየቴን ቀጠልኩ። ከጠዋቱ 12፡50 መኪናው ገና አልሞላም። የሚገርመው ሚዲያውን እንዲያስተባብር በተቋሙ የተመደበው ባለሙያ በሰዓቱ አልደረሰም። ለጉዞ የተመደቡ የመገናኛ ብዙኋን ባለሙያዎች እየደወለ የት እንደደረሱ መጠየቁን አስተባባሪው ቀጥሏል። 1፡ከ10 ከቦታው ተንቀሳቀስን።
ያልመጡ ባለሙያዎች ስለመኖራቸውና መንገድ ላይ እየሰበሰብን እንደምንሄድ የጉዞው አመቻች ወይም አስተባባሪ አሳወቀን። በቦታው ላይ ያልደረሱ ጋዜጠኞችን እየተደዋወሉ መንገድ ላይ እየጫኑ መሄዱ ግድ አለንና መንገድ ላይ አስሬ እየቆሙ መጠበቁ ቀጠለ፤ ስልክ እየተደዋወሉ አድራሻ መጠያየቅ ሆነ።
ከከተማ ሳንወጣ አዲስ አበባ ነቅታ ልጆችዋን በተለያየ አቅጣጫ ለስራ ታራውጣለች። ከወደ ምስራቅ አቅጣጫዋ ብቅ ያለችው ፀሀይ ከተማዋን ልዩ ውበት አላብሷት “እኔንማ ትታችሁ አትሂዱ” የምትል ነው የሚመስለው። በአጭር ጊዜ ውስጥ ለውጥዋ የእድገት ፍጥነትዋ ያስደንቃል።
የጉዟችን ማሳረጊያ የአፄ ሚኒሊክ አገር አንኮበር ነውና እኔ ተቻኩያለሁ። አካባቢውን ከዚያ በፊት አላውቀውም ነበርና መድረሱን ናፍቄያለሁ። ነገር ግን አሁንም አዲስ ላይ የተጓደሉ ሰዎች በመልቀም ላይ ነን። በዚህ ሂደት የአዲስ አበባን ግዛት ለቀን ለመውጣት የ3፡30 ሰዓት ጊዜ ወስዶብን ከጠዋቱ 4፡30 ላይ ከተማዋ ጫፍ ላይ ደረስን። የጋዜጠኞች ቀጠሮ አክብረው በሰዓቱ አለመገኘት የአስተባባሪዎቹ መርሀ ግብሩን በስርዓት ለመምራት አለመሞከር ለሰዓት አለመከበር ምክንያት ሆኖ ታይቶኛል።
የመኪናው ሹፌር መኪናዋን በስርዓት የማሽከርከር ክህሎቱ ደስ ያሰኛል። እዚያ መስመር ላይ በተደጋጋሚ የሚሰማው የትራፊክ አደጋ መንስዔው የአሽከርካሪዎች ሞገደኛነት መሆኑን ስለምሰማ ምነው ይህንን አሽከርካሪ ለሁሉ አርዓያ ነህ ተብሎ የመኪና አነዳድ ክህሎቱንና እርጋታውም ምን እንደሆነ ከጎኑ ቁጭ አድርጎ ባሳያቸው ብዬ ተመኘሁ። ምሳ ሰዓት ላይ ደብረ ብርሀን ደረስን። ከ5 ዓመታት በፊት የማውቃት ከተማዋ እጅጉን ተለየችብኝና ተደነቅሁ። እድገትና ለውጧ የሚገርም ነው።
ደብረ ብርሀን ከተማ እጅግ በፍጥነት እያደገች ያለች ከተማ እንደሆነች በተለያዩ መረጃዎች ብሰማም በአይኔ አይቼ ገራሚ ለውጧን ተመለከትኩ። በከተማዋ ዋናው መንገድ ግራና ቀኝ ረጃጅም ህንፃዎች ይታያሉ፤ ህንጻዎቹ ከተማዋን ውበት አላብሰዋታል። የንግድ እንቅስቃሴዋ ጦፏል። በኢንቨስትመንት የላቀ እምርታ እያሰመዘገበች ያለች ከተማ ናትና በአሁኑ ወቅት የኢንቨስትመንት አብዮት ማሳያ የለውጥ ሞዴል ብትሰኝ የሚገባትና የሚገልፃት ሆና አገኘዋት።
ምሳ የበላንበት ሆቴል የምግብ አዳራሹ ታሪካዊና ባህላዊ ስምን ተላብሶ በዘመናዊ መልክ ታንጾ እንግዶቹን ሲቀበል በመመልከቴ የከተማዋ የወደፊት እድገትና የእንግዶች ምቹ ማረፊያነትን ተረዳሁ። ሰዓት ኖሮኝ ከተማዋን ዞር ዞር ብዬ ባያት በወደድኩ ነበር። ነገር ግን አስተባባሪዎቹ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሀላፊዎች ከፊት መሆናቸውና እኛን እንደሚጠብቁ ነግረው አቻኩለው ወደታሰበበት አንኮበር ጉዞ ሆነ። መንገዱ ብዙም አስቸጋሪ አይደለም። ቀድሞ የነበረው ጠጠር መንገድ ወደ አስፓልት ንጣፍ በመቀየር ላይ በመሆኑ በተወሰነ ርቀት ያለቀለት የአስፓልት መንገድና በመሀል መሀል የቀረ የፒስታ መንገድ በጉዟችን አንዴ በገጭ ገጭ ሌላው ጊዜ ደግሞ ሽው ማለት ሆነ።
በመስኮት አሻግሬ የአካባቢውን መልካም ምድር ስመለከት የገጠሪቱ ኢትዮጵያን ውበት የመልካም ምድሩ መስህብነት አስገረመኝ። ይህ ደግሞ አንዳንዴ ጫጫታና ሁካታ የሚበዛበትን፣ በጪስ ታፍነን የምንውልበትን ከተማ ትተን ለወጣነው ትልቅ ለውጥ ነው። እዚህ ኑር እዚህ መስክ ላይ ተሯሯጥ የሚያሰኝ ስሜትን ያጭራል። እጅግ የገዘፉ ተራሮች፣ አልፎ ደግሞ ለጥ ብሎ አድማስ የሚጋረድ ሜዳ ይታያል። አርሶ አደሮች በተለያዩ የእርሻ ስራዎች ተጠምደው ይታያሉ፤ የሚያርሱ፣ የሚጎለጉሉ፣ ወዘተ። ሜዳው ላይ የሚጫወቱ ህፃናትና ወጣቶች የውብ ትዕይንቱ ድምቀቶች ናቸው።
አንኮበር መድረሳችን የተነገረን በምመለከተው መልካምድራዊ አቀማመጥ ስደነቅና ስገረም ነበር። አሽከርካሪው መኪናው ከዚያ በላይ መሄድ እንደማይችልና መንገዱ አስቸጋሪ መሆኑን ነግሮን በእግር ለመሄድ ከመኪናው ወረድን። የችግኝ መትከያ ቦታው መኪናው ከቆመበት ቦታ ያለውን ርቀት ስንጠይቅ ከ6 ኪሎ ሜትር እንደማያንስ ቢነገረንም የአካባቢው ገፅታ ማራኪና ለእግር ጉዞም የማያስቸግር ነበረና ለእግር ጉዞው የሚጠቅሙ ቁሳቁስን ሸክፈን መጓዝ ጀመርን።
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 8/2013