በአዲስ አበባ ከተማ መሠረታዊ የምግብ ፍጆታ እቃዎች አቅርቦት እጥረት በየጊዜው የሚስተዋል እና እስካሁን ያልተቀረፈ ችግር ነው። የመዲናዋ ነዋሪዎች በዕለት ተዕለት ኑሯቸው አስፈላጊ የሆኑ መሠረታዊ የምግብ ፍጆታ እቃዎች በሚፈልጉት መጠን እና ልክ ለማግኘት በእጅጉ እንደሚቸገሩ ይናገራሉ። ለእዚህም እንደምክንያት ከሚጠቀሱት ውስጥ አንዱ ከአቅርቦት እጥረት ጋር ተያይዞ የሚነሳው ችግር ነው።
ህብረተሰቡ የሚፈልገው የፍጆታ ዕቃን ለማግኘት ተግዳሮት እየሆነበት ይገኛል። ይህም በህብረተሰቡ ምሬት ውስጥ የሚከት እና ከፍተኛ ቅሬታ እያሳደረ የሚገኝ ነው። ይሁን እና የከተማ አስተዳዳር መሠረታዊ የፍጆታ እቃዎች አቅርቦት ያሳልጡልኛል ያላቸውን የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም ወደ ህብረተሰቡ ለመድረስ በርካታ ተግባራት እያከናወነ ይገኛል።
በዚህም መሠረት ነዋሪውን ከሸማች ማህበራትና ከችርቻሮ ሱቆች ጋር በማገናኘት መሠረታዊ የምግብ ፍጆታ እቃዎችን በቅርበት የሚያገኝበትን መንገድ የማመቻቸት ሥራ ተጠቃሽ ነው። ሆኖም ነዋሪው ህብረተሰብ እነዚህ መሠረታዊ የምግብ ፍጆታ እቃዎች በሚፈለገው ልክና መጠን ለማግኘት በአቅርቦት እጥረትና በተለያዩ ችግሮች ምክንያት መቸገሩን በተለያዩ አጋጣሚዎች ያነሳል።
አሁን ላይ ደግሞ ይባስ ብሎ እንደ አዲስ በተደራጀው ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ የሚገኙ አንዳንድ ነዋሪዎች እንደሚሉት፤ እነዚህን መሠረታዊ የምግብ ፍጆታ እቃዎች ለማግኘት ተቸግረዋል። እነዚህ ነዋሪዎች ቀደም ሲል በወረዳቸው ካለው ሸማች ማህበር እና ከችርቻሮ ሱቆች መሠረታዊ የምግብ ፍጆታ እቃዎች እንደሚያገኙ ጠቅሰው፤ አሁን ግን ወደ አዲሱ ክፍለ ከተማ ከመጡ በኋላ ለማግኘት መቸገራቸውን ይናገራሉ። ይህ ችግር ለአላስፈላጊና ተጨማሪ ወጪ እየዳረገ ይገኛል ይላሉ። ይህንን ችግር አስመልክቶ ለዝግጅት ክፍላችን ጥቆማ ያደረሱን የአዲሱ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሁለት ነዋሪ ወይዘሮ ትግስት ሹምዬ እና አበራሽ ዳዊት ናቸው።
ቀደም ባሉት ጊዜያት በቂ ባይሆንም በወር አንድ ጊዜ ስኳር እና ዘይት ያገኙ እንደነበር አስታውሰው፤ ከአራት ወራት ወዲህ ደግሞ ከነአካቴው ምንም አይነት ነገር ማግኘት እንዳልቻሉ ይናገራሉ። ወደ ወረዳ ሁለት ጽህፈት ቤት ሄደው ሲጠይቁም ወረዳው አዲስ በመሆኑ ገና የሸማች ህብረት ሥራ ማህበራትን እያደራጀ እንደሆነ የተነገራቸው መሆኑን ገልጸው፤ ይህ ለምን ሆነ መሠረታዊ የምግብ ፍጆታ እቃዎች ዕለታዊ ተፈላጊ ነገሮች በመሆናቸው ለምን በፍጥነት እንዲመጣ አይደረግም ሲሉ ጠይቁልኝ ብለዋል ።
ለዝግጅት ክፍላችን ጥያቄውን ያደረሱትን ነዋሪዎች በቅድሚያ እያመሰገንን ጥያቄዎቹን ይዘን የሚመለከተው የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሁለት ጽህፈት ቤት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ እዮብ እሸቱ አነጋግረን የሚከተለውን ይዘን ቀርበናል።
አቶ እዮብ፤ በመሠረታዊ የምግብ ፍጆታ እቃዎች ላይ እጥረት መኖሩን አምነው፤ የችግሩ መንስኤ ግን የለሚኩራ ክፍለ ከተማ አዲስ ከመሆኑ እና ከሰው ኃይል እጥረት ጋር ተያይዞ የተፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል። ወረዳው አዲስ እንደመሆኑ መጠን የወረዳ ነዋሪ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን በአዲስ መልኩ ማደራጀት አስፈላጊ ሆኗል ብለዋል። ለዚህም የህብረት ሥራ ማህበራትን በአዲስ መልኩ ለማደራጀት ስለሚያስፈልግ ከወረዳው ነዋሪዎች ጋር በጉዳዩ ዙሪያ ውይይት ከተደረገ በኋላ ከነዋሪው በተመረጡ የኮሚቴ አባላት አማካይነት የሸማች ህብረት ሥራ ማህበራትን የማደራጀት ሥራ እየሰራ ይገኛል።
የሸማች ህብረት ሥራ ማህበራቱ በአዲስ መልኩ ሲያደራጅ የወረዳ ነዋሪዎችን በመመዝገብ የህብረት ሥራው ማህበሩ አባል በማድረግ መሠረታዊ የምግብ ፍጆታ እቃዎችን እንዲደርሳቸው ተደርጓል ። የሸማች ማህበራትን ለማደራጀት አባላትን ማፍራት ስለሚያስፈልግ የወረዳው ነዋሪዎች መቶ ብር ከፍለው ከተመዘገቡ በኋላ የሸማች ማህበሩ አባል እንዲሆኑ ተደርጓል። በዚህ መልኩ የወረዳው ነዋሪ ህብረተሰብን በመመዝገብ እና የህብረት ሥራ ማህበራትን በማደራጀት ለነዋሪው እንደ ዘይት፣ ስኳር እና ዱቄት አይነቶቹን መሠረታዊ የምግብ ፍጆታ አቅርቦቶች የሚገኙበት ሁኔታ ይፈጠራል።
እንደ አቶ እዮብ ገለጻ፤ አሁን ላይ ወረዳው መሠረታዊ የምግብ ፍጆታ እቃዎች ለነዋሪዎቹ በተቻለ መጠን ለማድረስ ጥረት እያደረገ ነው። ምናልባት ቅሬታ የሚያቀርቡ ሰዎች የሸማች ማህበራት ለማደራጀት ነዋሪው የሚከፈለውን መቶ ብር ላለመክፈል የፈለጉ ሰዎች ወይም ደግሞ ወረዳ የሸማች ማህበራት እያደራጀ መሆኑ ግንዛቤው የሌላቸው ሰዎች ሊሆኑ እንደሚችሉ ጠቁመዋል። እነዚህ ነዋሪዎች ግን ግንዛቤ የላቸውም ለማለት አያስደፍርም ይላሉ። ምክንያቱም የሸማች ማህበራቱ ኮሚቴዎች ከነዋሪው ህብረተሰብ የተወጣጡ በመሆናቸው ጉዳዩ በደንብ ያውቁታል ብለዋል።
አሁን ላይ ወረዳው ማህበራትን በማደራጀት መሠረታዊ የምግብ ፍጆታ እቃዎች አቅርቦት ለነዋሪው እንዲደርስ እያደረገ ይገኛል። በተመሳሳይ ደግሞ ነዋሪዎችን እየመዘገበ ሌላ አዲስ የሸማች ማህበራት እያደራጀ የማህበራቱን ቁጥር በማብዛት አባላት በሚከፍሉት ብር መሠረታዊ የምግብ ፍጆታ እቃዎች ለህብረተሰቡ በማድረስ ላይ ነው። ሆኖም ግን አሁን ላይ እነዚህን መሠረታዊ የምግብ ፍጆታ እቃዎችን ለማምጣት የተፈቀደውን ያህል እንኳን ለማምጣት የሚሆን ብር ባለመኖሩ ምክንያት ሳይገባ የቀረበት ሁኔታ መኖሩን አስረድተዋል።
በቀጣይ የሸማች ማህበራት እያደራጁ ለህብረተሰቡ ተደራሽ የማድረጉ ሥራ ይቀጥላል ያሉት አቶ እዮብ፤ የሸማች ህብረት ሥራ ማህበር ለማቋቋም የሚያስፈልገው ነዋሪዎች ወረዳው ጽህፈት ቤት ዘንድ በመምጣት ተመዝግበው መቶ ብር በመክፈል አባል ሲሆን እንደሆነ ጠቁመዋል።
የሸማች ማህበራት ከማደራጀት በተጨማሪ ወደ ታች ነዋሪው ዘንድ ለመድረስ የሚያስችል ምን እየተሰራ ነው? ብለን ላቀረብንላቸው ጥያቄ አቶ እዮብ ሲመልሱ ወረዳው እስከታች ድረስ በመውረድ የሸማች ማህበሩን ከነጋዴዎች ጋር በማስተሳሳር ሥራ ይሰራል። በዚህም የሱቅ ነጋዴዎች አቅራቢያው ከሚገኘው ነዋሪ ህብረተሰብ ጋር የማስተሳሰር ሥራ ይሰራል። ለሱቁ በተመደበው ነዋሪ ልክና መጠን የሚያስፈልገው መሠረታዊ የምግብ ፍጆታ አቅርቦት በመሰጠት ለህብረተሰብ በቅርበት እንዲደርስ ይደረጋል። ለዚህም ነጋዴዎቹ መሠረታዊ የምግብ ፍጆታ እቃውን የሚያመጡበትን ገንዘብ ቀድመው ከራሳቸው በመክፈል በሱቁ በተመደበው ነዋሪ ቁጥር የሚሰጣቸውን መሠረታዊ የምግብ ፍጆታ እቃዎች በማምጣት ለነዋሪ የሚያከፋፍልበት ሁኔታ ለማመቻቸት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በመጨረሻም የለሚኩራ ክፍለ ከተማ የወረዳ ሁለት ነዋሪ ሆነው በወረዳ ጽህፈት ቤት መጥተው ያልተመዘገቡ የህብረተሰብ ክፍሎች ካሉ ወደ ወረዳው ጽህፈት ቤት ሁለተኛ ፎቅ በመሔድ መመዝገብ የሚችሉ መሆኑን አቶ እዮብ ጠቁመዋል።
በዚህ ገፅ ላይ አንባቢያን በሚፈልጉት ጉዳይ ላይ ጥያቄ የሚያቀርቡበት እና እኛም የሚመለከተውን አካል መልስ ጠይቀን የምናስነ ብብበት ሲሆን፤ ማንኛውም ሰው በስልክ ቁጥር 0111264326 በመደወል ጥያቄ እና አስተያየት ማቅረብ ይቻላል።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ነሐሴ 7/2013