ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን የአንድነት መሠረት ያጸና ነው። ምንም እንኳን ኢትዮጵያውያን መካከል የተለያየ አመላካከትና እሳቤ ቢኖርም የግደቡ ግንባታ አንድ ሆነው ለአንድ ዓላማ እንዲሰለፉ ያስገደደ ፕሮጀክት ነው። ግድቡን የኢትዮጵያውያን የህልውና መሠረት ነውና በሁሉም ዘንድ እንደ አይን ብሌን የሚታይና በጉጉት የሚጠብቅ ሆኗል። ለዚህም ነው፤ የግድብ ግንባታ ከተጠነሰሰበት ጊዜ ጀምሮ የህዝብ ድጋፍና ሞራል ተለይቶት የማያወቀው።
ግድቡ ለኢትዮጵያ እጅግ አስፈላጊ በመሆኑ ኢትዮጵያውያን ግድቡን በራሳቸው አቅም ለመገንባት ቆርጠው መነሳታቸው ዓለምን ያስገረመ እና ትኩረት የሳበ ጉዳይ ሆኖ ነበር። የዓለም ሀገራት ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? ብለው በመገረም ሲመለከቱ ኢትዮጵያውያን ለግደቡ ያላቸውን ሁሉ ድጋፍ በማድረጋቸው የግድቡ ግንባታ አሃዱ ተብሎ እንዲጀመረ አድርገዋል።
በውጭም ሆነ በአገር ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሁሉም የበኩላቸውን የቻሉት፤ ካላቸው ላይ እየቀነሱ ለነገ ሳይሉ ለግድቡ ድጋፍ አድርገዋል። ግድቡ ለኢትዮጵያውያን የተስፋ ብርሃን ያሳየ፤ የወደፊት የእድገት መሠረት በመሆኑ ተስፋ ተሰንቆበታል። ነገ ብሩህ ለማድረግ ዛሬ መስዋዕትነት በመክፈል በራስ አቅም ከመገንባት ባሻገር እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ አሻራ ያረፈበት የአንድነት መሠረት መሆን ችሏል።
አሁንም ኢትዮጵያውያን ለግድብ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እያደርጉ የራሳቸውን አሻራ እያኖሩ ይገኛሉ። በቦንድ ግዥ፣ በገንዘብ ልገሳ እና የተለያዩ መንገዶች በመጠቀም የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው ቀጥለዋል። በሌላ በኩል በተለያዩ የዓለም አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልድ ኢትዮጵያውያን ደግሞ ለግድቡ የእውቀት እና የገንዘብ ድጋፍ ከማድረግ ባሻገር በዲፕሎማሲ ዘርፍ ከሀገራቸው ጎን ቆመው እያገለገሉ ይገኛሉ።
በተመሳሳይ የዲያስፖራው ማህበረሰብ በተለያዩ ጊዜያት በህዳሴ ግደብ ዙሪያ የሚነሱ የተዛቡ አመለካከቶች በማርገብ፤ እውነታው ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማሳወቅ ጥረት እያደረገ ይገኛል። የህዳሴ ግድብ ላይ የሚደረገውን ድርድር የግብጽና የሱዳን ፍላጎት ዓለም አቀፍ አደራዳሪዎች እንዲታይ ያቀረቡት ሀሳብ ወደ አፍሪካ አደራዳሪነት እንዲመለስ በማድረግ ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ሥራ መስራታቸው ይታወቃል። አሁን በግድቡም ሆነ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በማሳውቅ የዲፕሎማሲ ሥራዎችን አጠናክረው ቀጥለዋል።
በውጭ የሚኖሩት ኢትዮጵያውያን፣ ትውልድ ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች ግደብ ከተጀመረበት ቀን አንስቶ ድጋፍ ሲያደርጉ ነበር። ለግድቡ እስካሁን ድረስ ከ15 ቢሊየን ብር በላይ በቦንድ ግዥና በልገሳ ድጋፍ ማድረጋቸውን የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት የተገኘ መረጃ ያመላክታል።
ሆኖም ግን እስካሁን ዲያስፖራው ለግድብ ድጋፍ ለማድረግ ፍላጎት ቢኖረውም ድጋፍ የሚያደርግበት ምቹ ሁኔታ ባለመዘርጋቱ በሚፈለገው ልክ ለግድቡ የሚያደርገው ድጋፍ ለማሰባሰብ እንዳልተቻለ በተደጋጋሚ ተጠቁሟል። ይሁን እና በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም የኢትዮጵያ ወዳጆች ለግድቡ የሚያደርጉት ድጋፍ ባሉበት ቦታ ሆነው አጠናክሮ እንዲቀጥሉ ለማድረግ የሚያስችል ድጋፍ መሰብሰቢያ ምቹ ሁኔታን መፍጠር ያስፈልጋል።
ቀደም ሲል በሀገር ውስጥ ላሉ ኢትዮጵያውያን በ8100 በኩል ድጋፍ ማድረግ የሚችሉበት አሠራር የተዘረጋ መሆኑ ይታወቃል። በዚህ በኩል በተደረገ ድጋፍ በ3 የተለያዩ ዙሮች ከ252 ሚሊየን ብር በላይ መሰብሰብ መቻሉ ተጠቁሟል። ልክ እንደዚህ ሁሉ በውጭ ለሚኖሩት የዲያስፖራው ማህበረሰብ ባሉበት ሆነው ለግድብ ድጋፍ የሚያደርጉበት ሁኔታ እየተመቻቸ ይገኛል።
በዚህም መሠረት አሁን ላይ ዲያስፖራው ባለበት ቦታ ሆኖ በሚፈልገው ልክ ለግድብ የሚያደርገው ድጋፍ እንዲቀጥል ለማድረግ ድረ-ገፅን መሠረት ያደረገ መደላድል (ፕላት ፎርም) ተዘጋጅቶ ለአገልግሎት ዝግጁ መሆኑ ይፋ ተደርጓል። ድረ-ገጹ ቀላልና አስተማማኝ ከመሆኑ ባሻገር ኢትዮጵያውያኑ ባሉበት አካባቢ ሆነው ለግድቡ ድጋፍ በማድረግ አሻራቸውን ማሳረፍ ለሚፈልጉ የተሻለ መንገድ እንደሚሆን የታመነበት ነው።
አዲስ የተከፈተው ድረ-ገጹ www.mygerd.com የሚል ሲሆን፤ ድረ-ገጽ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች የሚሳተፉበት ነው። ለግድብ ድጋፍ ማድረግ የሚፈልጉ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች በድረ ገጹ የፈለጉትን ያህል የዶላር መጠን ማስገባት እንዲችሉ ክፍት ሆኖ የተዘጋጀ ነው።
አሁን ላይ የተዘጋጀው ይህ መደላድል (ፕላት ፎርም) ሥራ መጀመሩን አስመልክቶ፤ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እንዳስታወቀው ዲያስፖራው በፕላት ፎርሙ በመጠቀም በድረ-ገጽ አማካኝነት ለግድብ የሰጠው ምላሽ አስገራሚ ነው። ድረ-ገጹ ይፋ በሆነ በ48 ሰዓታት ውስጥ ከ583 ለጋሾች ለህዳሴ ግድቡ 70 ሺህ ዶላር በላይ ድጋፍ መደረጉን እንዲሁ ተገልጿል። በድረ-ገጽ የተደረገው ድጋፍ በአማካኝ በሰዓት ሲታይ 1 ሺህ 510 ዶላር መሆኑ ዲያስፖራው በቁጭት ግድቡ እየደገፈ መሆኑን የሚያመላክት ነው።
ዲያስፖራው በድረ-ገጹ አማካኝነት ለግድቡ እያደረገ ያለው ድጋፍ በእጅጉ የሚያበረታታ ነው። ከዚህም ባሻገር በዲፕሎማሲው ረገድ እያደረገ ያለው ድጋፍ አጠናክሮ መቀጠል የሚገባው ነው።
በተባባሩት መንግሥታት የዓለም አቀፍ ሰብሰባ ላይ የውሃና መስኖ ኢነርጂ ሚኒስቴር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ እንደተናገሩት፤ “እዚህ ምክር ቤት ተገኝቶ ያስረዳ የመጀመሪያው የውሃ ሚንስትር ሳልሆን አልቀርም፤ ጉዳዩ ወደ እዚህ ምክር ቤት መምጣቱ በራሱ አግባብ አይደለም። ምክንያቱም እየገነባን ያለነው የውሃ ግድብ እንጂ የኒውክሊየር ማብላያ አይደለም” ብለው ነበር። በተመሳሳይ ዲያስፖራው በየመድረኩ ስለግድብ በማስረዳት ያደረገው ጥረት የሚረሳ አይደለም።
ግድቡ ከተጀመረ አሥር ዓመታት ተቆጥረዋል። በእነዚህ ዓመታትም በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል። ባለፉት 10 ዓመታት የግድቡን ግንባታ በ5 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ወጪ ግንባታውን መከናወኑን ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በሁለተኛ የግድቡ ውሃ ሙሌት ወቅት ተናግረው ነበር።
በአሁኑ ወቅት በግድቡ ውስጥ ሁለት የኃይል ማመንጫ ተርባይኖችን ለማንቀሳቀስ የሚያስችል ውሃ መያዝ የተቻለ ሲሆን፤ ግድቡ ሲጠናቀቅ ከፍተኛ ቁጥር ላለው ሕዝብ የኤሌክትሪክ ብርሃን ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል። በዚህም ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሊት ከተጠናቀቀ በኋላ በከፊል የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት እንደሚጀምር ይጠበቃል።
የህዳሴው ግደብ ግንባታ ሲጠናቀቅ ከአፍሪካ ቀዳሚ በመሆን ከአምስት ሺህ በላይ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት ከኢትዮጵያ ህዝብ ባሻገር ለጎረቤት አገራት ሳይቀር እንደሚተርፍ ተስፋ የተጣለበት ነው። አሁንም ግድብ እስከሚጠናቀቅ ድረስ የሁሉም ሰው ርብርብ በእጅጉ የሚፈልግ ነው።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ነሐሴ 5/2013