ልጆች እንደምን ናችሁ? የባለፈው የትምህርት ዘመን ተጠናቆ ውጤት ተቀበላችሁ አይደል? እንዴት ነበር? መቼም የኔ ልጆች ጎበዞች ስለሆናችሁ አንዳችሁም ዝቅተኛ ውጤት እንደማታመጡ እርግጠኛ ነኝ። ልጆቼ በክረምት የእረፍት ወራት ንባብን ተቀዳሚ ስራ ማድረግ በነገሮች ላይ ያላችሁን ግንዛቤ ያሰፋላችኋል። ለዛሬ የኢትዮጵያ አባቶች አንድ ላይ ከሰበሰቧቸው ተረቶች መካከል በመጋቢ እንየው ገሠሠ የተተረከውን በዚህ መልኩ አቅርቤላችኋል መልካም ንባብ።
አንድ የነብር ግልገልና የፍየል ግልገል ሳይተዋወቁ አብረው ይጫወቱ ነበር። የነብሩም ግልገል ማታ ወደቤቷ ስትመለስ ለእናቷ እንዲህ ስትል አጫወተቻት “ዛሬ ከቆንጆ ፍጡር ጋር ስጫወት ዋልኩ። ተወዳጅ፣ ቆንጆና ተጫዋች ፍጡር። ደስ የሚል ጊዜ ከእሷ ጋር አሳለፍኩ።”
እናትየውም ልጇ ከሰጠቻት ማብራሪያ በመነሣት ከማን ጋር ስትጫወት እንደዋለች አወቀች።
“ታዲያ እሷ ከጥንት ጀምሮ ተወዳጅ ምግባችን አይደለችም እንዴ? ለምን ይዘሽ አላመጣሻትም ነበር?” አለቻት።
የነብሯም ግልገል “አሃ! ታዲያ ነገ እኮ ቀጠሮ አለን።
አመጣታለሁ።” አለች።
የፍየሏም ግልገል ለእናቷ እንዲህ ብላ ነገረቻት “ዛሬ በጣም ቆንጆና ቆዳዋ ላይ ነጠብጣብ ካላት እንስሳ ጋር ስጫወት ዋልኩ፤ የሚያምር መልክ አላት።”
እናትየዋም ፍየል “አንቺ ጅል! እነዚህ እንስሳት ከተፈጠርን ጊዜ ጀምሮ ጠላቶቻችን እንደሆኑ አታውቂም? ሁልጊዜ ስታያት መሮጥና ማምለጥ አለብሽ።” ብላ መከረቻት።
በማግስቱም የነብሯና የፍየሏ ግልገሎች ተገናኙ።
የፍየሏ ግልገል የነብሯን ግልገል ባየቻትም ጊዜ የነብሯ ግልገል ተንኮለኛ በመምሰልና በሃሰት በሚጣፍጥ ድምፅ “እንደምንድነሽ?” ስትላት ሰማች። የነብሯም ግልገል ተንኮል በተሞላበት እርምጃ ወደ ፍየሏ ግልገል ተጠጋች።
የፍየሏም ግልገል በማፈግፈግ እንዳትይዛት ሰግታ ወደ ኋላ፣ ወደ ኋላ፣ ወደ ኋላ እያለች ሄደች።
የነብሯ ግልገል “ነይ! እንደትናትናው እንጫወት። ዛሬም እንደምንጫወት ቃል ገብተሽ ነበር።” አለቻት።
“አይ ይህንን አላደርግም። በእናንተ ቤት የተሸረበው ሴራ በእኛም ቤት ተሴሯል። እናትሽ የነገረችሽን ለእኔም እናቴ ነግራኛለች።” አለቻት። ይህንንም ብላ ሮጣ አመለጠች።
ልጆች የመጡ ችግሮችን በጥበብ ማለፍን ከዚህ ተረት እንማራለን።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ነሐሴ 2/2013