ኪነ ጥበብ እና ወታደራዊ ዘመቻ የኖረ ወዳጅነት አላቸው። ወታደራዊ ዘመቻ ካለ ዘማቹን የሚያበረታቱ፣ ጀግኖችን የሚያወድሱ ፣ ፈሪን የሚያንኳስሱ አዝማሪዎች የዘመቻው አንድ አካል ሆነው ይላካሉ። ይህ ጥንታዊ ኢትዮጵያዊ ባህል ነው።
ታሪክ የመዘገበውን ብናስታውስ እንኳ ከአድዋ ድል አንስቶ እስከ ዛሬ ድረስ በጦር አውድማው ላይ ጀግኖችን ተከትለው የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች አብረው የዘመቱ ሲሆን፣ ከነዚህ መካከል አንዷ እና ታዋቂዋ ደግሞ አዝማሪ ጣዲቄ ናት። አዝማሪ ጣዲቄ በአድዋ ዘመቻ ላይ ከነበራት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አኳያ በስሟ ጎዳና ሁሉ ተሰይሞላት እንደነበር በእውቀቱ ስዩም የታሪክ መዛግብትን አገላብጦ መርምሮ ጽፏል። አዝማሪ ጣዲቄ ከሌሎቹ በተለየ ስሟ ታውቆ ገነነች እንጂ ከጦርነቱ በኋላ ታሪካቸው እንደሚገባው ያልተተረከላቸው ብዙ አዝማሪዎችም እንደነበሩ ይነገራል።
ከነዚህም መካከል አንደኛው ወለዬው ሀሰን አማኑ ናቸው። አይነስውሩ ሀሰን አማኑ የወሎው ራስ ሚካኤል አዝማሪ ቢሆኑም እንኳ በአጼ ዮሀንስም ሆነ በአጼ ምኒልክ ቤተ መንግስት ተወዳጅነት ነበራቸው። በብላቴን ጌታ ማህተመ ስላሴ ወልደ መስቀል መጽሀፍ ላይ እንደሰፈረው ከሆነ እኚህ አዝማሪ ለአድዋ ዘመቻ ብዙ ዜማዎችን አበርክተዋል። ለምሳሌ ስለ አለቃቸው ንጉስ ሚካኤል የጦር ሜዳ ውሎ የሚከተለውን ብለዋል።
ማን በነገረው ለጣሊያን ደርሶ፤
ሚካኤል መጣ ረመጥ ለብሶ።
ስለ ጀግናው ፊታውራሪ ገበየሁ የተገጠመውን
ታዋቂ ግጥም የገጠሙትም እኚሁ ሰው ናቸው።
ስንኙ እንዲህ ይላል፤-
ታጭዶ ሲወቃ፣ ዐድዋ ላይ ገብስ፤
አናፋው ዘልቆ፣ (ጎራው) በመትረየስ።
ዐድዋ ሥላሴን፣ ጣሊያን አረከሰው፤
ገበየሁ በሞቴ፣ ግባና ቀድሰው።
ከአዝማሪዎቹ ባለፈ ባለቅኔዎችም እንዲሁ በጦርነቱ ላይ ጀግኖችን የሚያወድስ ብዙ ቅኔ ተቀኝተው እንደነበርም እንዲሁ ይነገራል። ለምሳሌ ያህል ከደራሲ በእውቀቱ ጽሁፍ አንዱን ወስደን እንመልከት። አንድ ሰሙ የማይታወቅ ባለቅኔ ለአጼ ሚኒሊክ ከዘመቻ በኋላ እንዲህ ብሎ ተቀኝቶ ነበር፤-
ሰላም ለአፉከ ለፈጣሪ ዘየአኩቶ
ዘኢይትናገር ስላቀ ወኢይነበብ ከንቶ
ንጉሠ ነገሥት ምኒልክ ለኢትዮጵያ ማህቶቶ
ኀልቀ ማንጀር ወስእነ ፍኖቶ
ዤኔራል ባራቴሪይ ሶበ ገባ ደንገጸ ኡምበርቶ
ትርጉሙ እንደሚከተለው ግድም ነው።
ሰላም ላንደበትህ፤ ለሚያቀርብ ለእግዜር ምስጋና
ዘበት፤ ስላቅ ፤ ከንቱ ወሬ፤
መናገርን መች ያውቅና
ንጉሠ ነገሥት ምኒልክ፤ የኢትዮጵያ መብራት ፋና
ተጨነቀ ማጆር፤ እግሩ ዛለ በጎዳና
ደነገጠ ኡምበርቶ፤ በባራቴሪ ምርኮ ዜና ።
ከዚህም ባለፈ ግን በህዝባዊ ሙዚቃዎች እና ስነቃሎች ውስጥ ለሀገር መሞትን የሚያበረታቱ ብዙ ዜማዎች እና ስንኞች ተገጥመዋል።ለምሳሌ ያህል
እናት አባት ቢሞት በሀገር ይለቀሳል
እህት ወንድም ቢሞት በሀገር ይለቀሳል
ሀገር የሞተ እንደው ወዴት ይደረሳል
የሚለው ታዋቂ እንጉርጉሮ ተጠቃሽ ነው።
ከመጀመሪያው የጣልያን ወረራ በኋላ በሁለተኛውም ወረራ ወቅት እንደሁ ኪነ ጥበብ ብዙ አስተዋጽኦ የነበራት ሲሆን፣ በተለይም የሀገር ፍቅር ማህበር አባላት የሚያቀርቧቸው የኪነ ጥበብ ስራዎች ህዝቡ ሞራሉ እንዳይወድቅ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ድርሻ ነበራቸው። በዚህም የተነሳ ፋሽስት የኪነ ጥበብ ባለሙዎችን ማሳደድ ጀምሮ ነበር።
በዘመነ ደርግ የሶማሊያው የዚያድባሬ ወራሪ ድንበር ጥሶ ሲገባም እንዲሁ በዜማ ወታደሩን እና ህዝቡ አነቃቅቷል። ለምሳሌ ያህል ታዋቂውን ዜማ ብንሰማ
አጥንቴም ይከስከስ ደሜም ይፍሰስላት
እንጂ ሀገሬን በጭራሽ አይደፍራትም ጠላት
የተሰኘው ዜማ ስንኞች በወቅቱ ታዋቂ ነበሩ። በዘመነ ኢህአዴግ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ በድንበር ጉዳይ ጦርነት ገጥመው በነበር ጊዜም ቢሆን ኪነ ጥበብ በስፋት ጥቅም ላይ ውላለች። ለእዚህም የአንድ ሁለቱን ሙዚቃዎች ስንኞች እንመልከት።
በል በለው በል በለው ጀግናዬ በለው፣
ትእግስትም ራሱ በቃ ልክ አለው።
…….
ተከብረሽ የኖርሽው በአባቶቻችን ደም፣
እናት ኢትዮጵያ የደፈረሽ ይውደም››
….
እነሆ አሁን ደግሞ ኢትዮጵያ ሌላ ጦርነት ውስጥ በገባችበት በአሁኑ ወቅት የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች የተለመደ ድርሻቸውን ለመወጣት ባለፈው ሳምንት ተሰባስበው እቅድ ነድፈው ፤ አመራር መርጠው ፤ስራም ተከፋፍለዋል።በምክክሩ ወቅት ያነጋገርናቸው የኪነ ጥበብ ባለሙዎች ኪነ ጥበብ በዚህ ሀገርን የማዳን ዘመቻ ላይ ምን ድርሻ ሊኖራት እንደሚገባ ገልጸውልናል።
የመጀመሪያውን ሀሳብ የሰጡን የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ማህበር ሰብሳቢ አንጋፋው የሙዚቃ ሰው ዳዊት ይፍሩ ነበሩ። ”ሀገራችን ችግር ላይ ወድቃለች። ይህን ችግር ለመፍታት ደግሞ ወታደሩ በግንባር ዘምቷል። ስለዚህ የኪነ ጥበብ ባለሙያውም በሙያው መዝመት አለበት። ሙያው ደግሞ ግንባር ላይ ያለው ወጣት አሸናፊ እንዲሆን መርዳት አለበት።”ይላሉ።
ጋሽ ዳዊት እንደሚሉት፤ የኪነ ጥበብ ባለሙያው ለዚህ ዘመቻ የሚመጥን አዲስ ስራ ማዘጋጀት አለበት። ላለፉት ሰላሳ እና አርባ አመታት የተሰሩ ስራዎችን ማቅረብ ሳይሆን፣ ለቀጣይ ሰላሳ እና አርባ አመት የሚቆዩ ስራዎችን መስረት ይኖርበታል። ከዚህም ባለፈ የኪነ ጥበብ ባለሙያው ከዘመቻ በኋላም ህዝቡን ለልማት በማነሳሳት በኩል የሚጠቅሙ ስራዎችን ማዘጋጀትም ይኖርበታል።
የኮሜዲ አርቲስቷ ቤቲ ዋኖስ በበኩሏ ሙያዋ ከዚህ ቀደም ሀገር ችግር ውስጥ በነበረችበት ጊዜ ሁሉ ነገሮችን አለዝቦ ለማቅረብ ትልቅ ፋይዳ እንደነበረው ታስታውሳለች። ለምሳሌነትም በኮሮና እና በህዳሴ ግድብ ዙሪያ የሰሩትን ስራዎች ትጠቅሳለች። ”ጦሩ ወደ ግንባር ከመሄዱ በፊት ተፍታቶ እንዲሄድ ኪነ ጥበብ በተለይም ኬሜዲ ትልቅ ድርሻ አላት” የምትለው ቤቲ፣ አሁን ያንን ለማከናወን እሷም ሆነ ሌሎች የኮሜዲ ባለሙያዎች ዝግጁ መሆናቸውን ነግራናለች። ዝግጁነታቸው ጦሩ ሀይል ካነሰው እስከ መዝመት እንደሚሆንም ነው ያረጋገንጠችው።
ተዋናይት አስቴር አለማየሁ ለዚህ ሀገራዊ ጥሪ በመጠራቴ በጣም ደስተኛ ነኝ ትላለች። ሰራዊቱን በሙያዋ ማገዝ ደግሞ ሀገራዊ ግዴታዋ እንደሆነ ጠቅሳ፣ ከአምስት አመት በፊት ዛሬ ጦርነት በሚካሄድባቸው ስፍራዎች በመገኘት የኪነ ጥበብ ስራዎችን ለመከላከያ ሰራዊቱ ማቅረቧን ትገልጻለች። ሰሜን እዝን እንደምታውቀው እና በሰራዊቱ ላይ የደረሰው ነገር ስሜቷን እንደነካውም ትናገራለች። በተለይ የጥቅምት 24ቱን ጥቃት በኪነ ጥበባዊ መልኩ በትወና ለህዝብ ለማሳየት አቅም እንዳለ የምትናገረው ተዋናይዋ፣ የኪነ ጥበብ ባለሙያው በህብረት ለዚህ ዘመቻ ስኬት መስራት እንዳለበት ተናግራለች።
ኤፍሬም ስዩም በዚህ ዘመን ከሚጠቀሱ ገጣምያን መካከል አንዱ ነው። ”በዚህ ወቅት ዋናውን ቦታ የሚይዘው ስነ ግጥም ነው” ይላል። ”ግጥም መሀል ላይ መቆም እንዲሁም ስንጥቆችን መድፈን ይችላል የሚለው ገጣሚው፣ ጥግ ሳይዝ ጠላትን በመምከር የወገንን መንፈስ ከፍ በማድረግ ረገድ ብዙ አቅም በስነ ግጥም ውስጥ መኖሩን ገጣሚ ኤፍሬም ያብራራል። ጦርነት ከተፈጠረ ግን ቢቻል ጠላትን ማለዘብ አልሆነ ካለ ግን ወገንን በማበረታት ድርሻውን እንደሚወጣ ይገልጻል። ስለዚህም ይህን ጥበብ ለመጠቀም ጊዜው አሁን መሆኑን ይገልጻል።
በጥቅሉ በእለቱ የነበረው የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ስሜት ኪነ ጥበብ ከአድዋ አንስቶ ፤ በሁለተኛው የፋሽስት ወረራ ፤ የሶማሊያ ወረራ እንዲሁም በኤርትራ ጦርነት ወቅት ጠላቶቻችንን በማሳፈር የተጫወተውን ከዋጋ በላይ የሆነ ድርሻ ለመወጣት እና ሀገርን ከአደጋ ለማዳን መዘጋጀቱን የሚያመለክት ነበር። ይሁን ብለናል
አቤል ገ/ኪዳን
አዲስ ዘመን ነሐሴ 2/2013